>

 "በሕወሓት አመራሮች ላይ አልመስክርም!”  ኬሪያ ኢብራሂም

 “በሕወሓት አመራሮች ላይ አልመስክርም!” 

ኬሪያ ኢብራሂም
ዋዜማ ራዲዮ

 

* ….መንግስት ስርዞት የነበረውን ክስ በድጋሚ ሊመሰርትባቸው ነው!!!
የሕወሓት ስራ አስፈፃሚና የቀድሞው የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም በሕወሓት ሌሎች መሪዎች ላይ ምስክር ለመሆን “ተስማምተው” ከተከሳሽነት ቢሰናበቱም አሁን በድጋሚ ሃሳባቸውን ቀይረው ምስክር እንደማይሆኑ ተናግረዋል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በስምምነት ትቶት የነበረውን ክስ በወ/ሮ ኬሪያ ላይ በድጋሚ ሊያቀርብ እየተዘጋጀ መሆኑን  ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከመቀሌ መያዝ ተከትሎ በሕዳር ወር ለመንግስት እጃቸውን የሰጡት ወ/ሮ ኬሪያ የሕወሓትን የጦርነት ዕቅድ እንዲሁም ድርጅቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲፈፅማቸው ነበሩ ለተባሉ የተደራጁ ጥቃቶች ብሎም ከጦርነቱ ሽንፈት በኋላ ወደ በረሃ የተደረገውን ሽሽት የተመለከቱ “ቁልፍ መረጃዎችን” ለመንግስት በፈቃደኝነት ስጥተዋል።
መንግስት ወ/ሮ ኬሪያ ስጡኝ ያለው መረጃ እጅግ ጠቃሚና ዋና ዋና የሕወሓት አመራሮችን ለመያዝና ሌሎቹንም ለመግደል እንዳስቻለው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ይገልፃሉ።
ወ/ሮ ኬሪያ ለመንግስት በሰጡት “ጠቃሚ መረጃ” ና ባሳዩት ከፍተኛ የትብብር መንፈስ የሕወሓት መሪ በመሆናቸው ቀርቦባቸው የነበረውን ክስ በማንሳት የኢትዮጵያ መንግስት ሕግ በሚፈቅደው መሰረት በሕወሓት መሪዎች ላይ ምስክር ለመሆን “ስምምነት” ላይ ደረሱ። ወ/ሮ ኬሪያም መንግስት ጥበቃ ሊያደርግላቸው እሳቸው ደግሞ የጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው ለመቅረብ “ተስማሙ”። ከእስርም ተለቀቁ።
በእስካሁኑ ሂደት በቪዲዮ በተቀረፀ የምርመራ ቃላቸው ሕወሓት በተለያየ ጊዜ በምስጢር ያደረጋቸውን ውይይቶች፣ የተደረሰባቸውን ስምምነቶች እንዲሁም የጦር መሳሪያ ክምችትን፣ የገንዘብ ዝውውርን፣ ስውር የንግድ እንቅስቃሴዎችን የሚመለከቱ መረጃዎችን ለፌደራል ፖሊስ መርማሪዎች በዝርዝር መናገራቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የሕወሓት ስራ አስፈፃሚ እና ማእከላዊ ኮሚቴ መቀሌ ከተማን ለቆ ወደ በረሃ ለመሸሽ በወሰነበት ጊዜ አመራሮቹ የት መደበቅ እንዳለባቸዉ የተወሰነዉን ዉሳኔ በዝርዝር የገለፁበት መረጃና ምስክርነት ከሌሎች መረጃዎች ጋር ተጣምረው መንግስት ሲወስዳቸው ለነበሩ ወታደራዊ እርምጃዎች እጅግ ጠቃሚ እንደነበሩና ይህ ትብብር መንግስት ከወ/ሮ ኬሪያ ጋር “ስምምነት” እንዲደርስ መተማመኛ ሆኖት እንደነበረ ስምተናል።
ይሁንና ወ/ሮ ኬሪያ ከትናንት ግንቦት 17 ቀን ዓ.ም የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት የምስክርነት ቃል ለመስጠት ቀርበዉ እያለ ምስክር ለመሆን ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ለፍርድ ቤት ገልፀዋል፡፡
ይህን የወ/ሮ ኬሪያ ውሳኔ ተከትሎ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከወ/ሮ ኬሪያ ጋር የገባውን “ስምምነት” በማጠፍ ሲያደርግላቸው የነበረውን የምስክር ልዩ ጥበቃ በማንሳት እንዲሁም ቀድሞ እንዲቋረጥ ተደርጎ የነበረው ክስ እንዲቀጥል ከውሳኔ መድረሱን ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ስምተናል።
ለሀገርና ሕዝብ ጥቅም ሲባል ይህ አይነቱ ከተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ ጋር የሚደረግ ስምምነት በተለያዩ ሀገሮች የሚሰራበት የሕግ ፍልስፍና መሆኑን የሚያስረዱት በሰሜን አሜሪካ ሀገር ነዋሪ የሆኑ የህግ ባለሙያ በኢትዮጵያም ይህን አስራር የሚደግፍ የህግ አግባብ መኖሩን ያስታውሳሉ።
የጠቋሚዎች እና ምስክሮች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 699/2003 አንቀፅ 4/1/ረ ስር አንድ ምስክር ጥቆማ በሰጠበት ጉዳይ እንዳይከሰስ ጥበቃ እንዲደረግለት ጠይቆ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጥበቃዉን ለመወሰን እንደሚችል ባለሙያው ይጠቅሳሉ።
Filed in: Amharic