>

ሰበር ሰሚ ችሎት ለባልደራስ የወሰነውን ውሳኔ ምርጫ ቦርድ ለምን ተፈጻሚ እንዳላደረገ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትእዛዝ ሰጠ...!!! (ታምሩ ጽጌ)

ሰበር ሰሚ ችሎት ለባልደራስ የወሰነውን ውሳኔ ምርጫ ቦርድ ለምን ተፈጻሚ እንዳላደረገ ቀርቦ እንዲያስረዳ ትእዛዝ ሰጠ…!!!
ታምሩ ጽጌ

 

*…ፓርቲው ምርጫ እንዳይካሄድ ዕግድ ጠይቋል

 *… ቦርዱ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሰበር እንዲያስረዱ ጠይቋል

 *… ምርጫ የማይደረግባቸው ቦታዎችና አካባቢዎች ይፋ ተደረጉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እነ አቶ እስክንድር ነጋ (3 አባላት) በዕጩነት እንዲመዘገቡ የሰጠውን ውሳኔ ለምን መፈጸም እንዳልቻለ ሐሙስ ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ ለቦርዱ ትዕዛዙን ያስተላለፈው ሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ ለትዕዛዙ መነሻ የሆነው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)፣ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ፣ ቦርዱ ‹‹አልፈጽምም›› ማለቱን ገልፆ፣ እስከሚፈጽም ድረስ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲካሄድ የተወሰነው አገራዊ ምርጫ እንዲታገድለት አቤቱታ በማቅረቡ መሆኑን ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ፓርቲው ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ባቀረበው አቤቱታ፣ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ቦርዱ ለመፈጸም እምቢተኛ መሆኑን ጠቁሞ፣ ዕጩዎቹ በተወዳዳሪነት ሳይመዘገቡ ድምፅ ቢሰጥ፣ መብቱን በእጅጉ ከመንካቱም በላይ፣ ፍርድ ቤቶች በምርጫ ጉዳይ የሚሰጡት ውሳኔ ‹‹ተፈጻሚነት አይኖረውም›› የሚል ጥርጣሬ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ እንደሚያሳድር በማስረዳት፣ ምርጫው እንዲታገድለት አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን ውሳኔ ትክክል እንደሆነና ‹‹መፈጸም አለብህ›› የተባለውን ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበለው በመግለጽ፣ ነገር ግን አግባብነት ካላቸው የአገሪቱ የምርጫ ሕግ ማዕቀፍ አንፃር ውሳኔውን ተፈጻሚ ለማድረግ ፍጹም አዳጋች እንደሚሆንበት በመጠቆም፣ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለችሎቱ ቀርበው እንዲያስረዱ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

አንድን ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ከሚያደርጉና ለዜጎች የተረጋገጠውን የመምረጥና የመመርጥ መብት ሙሉ በሙሉ ዕውን ለማድረግ ቁልፍ ጉዳዮች መካከል፣ በሕግ አግባብና ከአድልኦ ነፃ በሆነ ሁኔታ የሚደረግ የዕጩዎች ምዝገባ አንዱ መሆኑን ያብራራው ቦርዱ፣ ነገር ግን የተጠቀሱት ነገሮች የሚከናወኑበትን ሥርዓት የመደንገግ አስፈላጊነት እንደሚገኝበት አስረድቷል፡፡ ዕጩ ለመሆን አስፈላጊ የሆኑ መሥፈርቶችን ዘርዝሮ፣ ይህንን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ የምርጫ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 ከአንቀጽ 30 እስከ 42 ተደንጎ እንደሚገኝም አክሏል፡፡

ከተጠቀሰው አዋጅ አንቀጽ 39(3) ሥር ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ የፖለቲካ ዕጩን መለወጥ ወይም መተካት የሚቻለው የዕጩ የምዝገባን በተመለከተ የተዘጋጀው የጊዜ ሰሌዳ ካበቃ በኋላ፣ ከድምፅ መስጫው ቀን አንድ ወር በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑንም ቦርዱ አስታውሷል፡፡ የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ፣ የድጋፍ ፊርማ አሰባሰብና መለያ ምልክት አመራረጥ መመርያ ቁጥር 7/2013 አንቀጽ 29(5) ድንጋጌ መሠረት፣ እነ አቶ እስክንድር በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት እንደማይከለከሉ ጠቁሞ፣ ነገር ግን በወቅቱ መሥፈርት አያሟሉም ተብሎ ውድቅ መደረጉን ገልጿል፡፡ ነገር ግን የሚያሟሉትን መዝግቦ የዕጩነት የምስክር ወረቀት እንዲወስዱ ማድረጉን ተናግሯል፡፡ ፓርቲውም በሚወዳደርባቸው የምርጫ ክልሎች የመረጠውን የመወዳደሪያ ምልክት በመጠቀም የ‹‹ምረጡኝ›› ቅስቀሳውን ሊያበቃ የቀረው ጥቂት ቀናት ብቻ መሆናቸውንም አስታውቆ፣ የተወከሉትና መሥፈርቱን የሚያሟሉት ዕጩዎችን ያካተተ የድምፅ መስጫ ወረቀት ህትመት መጠናቀቁን ገልፆ፣ እነ አቶ እስክንድርን እንዲመዘግብ የታዘዘውን ለመፈጸም ቦርዱ እንደሚያዳግተው አብራርቷል፡፡

ቦርዱ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ቀርበው እንዲያስረዱ ጠይቋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ላይ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከዚህ በፊት የተጠቀሱት አራቱም (መተከል፣ ሺናሻ ልዩ፣ ካማሽ እና ዳለቲ) የምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ የመስጠት ተግባር አይከናወንባቸውም፣ ቦርዱ ተጨማሪ የአፈጻጸም ሁኔታዎችን ለወደፊት የሚያሳውቅ ይሆናል።

በሶማሌ ክልል 14 ምርጫ ክልሎች ላይ (11ዱ ምርጫ ክልሎች ምርመራ ላይ ያሉ) ሰኔ 14 ቀን 2013 ድምፅ የመስጠት ሒደት ለማካሄድ አስቸጋሪ ይሆናሉ የተባሉ ሲሆን፣ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ላይ የታየ መጠነ ሰፊ የአሠራር ችግር አለ በሚል የቀረበውን አቤቱታ ተከትሎ የአጣሪ ቡድን አሰማርቶ የማጣራት ተግባሩን አጠናቋል፡፡ በዚህም መሠረት የአጣሪ ቡድኑን ግኝት መሠረት አድርጎ ድምፅ መስጠት ሊከናወንባቸው የሚችል ምርጫ ክልሎች ካሉ ለይቶ የሚያሳውቅ ይሆናል። በኦሮሚያ ክልል ከዚህ በፊት እንደተጠቀሰው ሰባት ምርጫ ክልሎች (ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣ አያና፣ ገሊላ፣ አሊቦ፣ ጊዳሚ፣ ኮምቦልቻ) ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ የመስጠት ተግባር አይከናወንባቸውም።

በአማራ ክልል ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት ስምንት ምርጫ ክልሎች መካከል ድልይብዛ ምርጫ ክልል ላይ ቦርዱ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ድምፅ መስጠት ሒደት አንዲከናወን ወስኗል። ይህም ከክልሉ መንግሥት በተሰጠ ማረጋገጫ መሠረት የመራጮች ምዝገባ በተስተጓጎለባቸው አምስት ምርጫ ጣቢያዎች አካባቢ ያሉ ዜጎች ሌሎች ጣቢያዎች ላይ መመዝገባቸው በመረጋገጡ ነው።

በሌላ በኩል ግን በአማራ ክልል አንኮበር የምርጫ ክልል ሰኔ 14 ድምፅ መስጫ እንደማይካሄድም ቦርዱ ወስኗል፡፡ ቦርዱ ይህንን የወሰነው የአርጎባ ልዩ ምርጫ ክልል ላይ ድምፅ የሚሰጡ ዜጎች ለክልል ምክር ቤት በዚህ ምርጫ ክልል ድምፅ የሚሰጡ በመሆኑና በአካባቢው ባለ የፀጥታ ችግር ምክንያት ባለመመዝገባቸው ነው። በዚህም መሠረት በአማራ ክልል በስምንት ምርጫ ክልሎች ሰኔ 14 ቀን ድምፅ መስጠት ሒደቱ አይከናወንም።

በደቡብ ክልል ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት አራት የምርጫ ክልሎች በተጨማሪ ማጀት መደበኛ የምርጫ ክልል ሰኔ 14 ቀን ድምፅ አይሰጥበትም፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት በሱርማ፣ በዲዚ፣ በሜኢኔት ልዩ የሚኖሩ ከብሔሩ ውጪ ያሉ ዜጐች ለተወካዮች ምክር ቤት በማጀት መደበኛ ላይ ድምፅ ስለሚሰጡና በተጠቀሱት ቦታዎች ምዝገባ ስላልተከናወነ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጉራፈርዳ ላይ ባለው የፀጥታ ችግር እንዲሁም ሸኮ ልዩ የምርጫ ክልልና ቴፒ ምርጫ ክልል ሰኔ 14 ቀን ድምፅ መስጠት አይከናወንም። በዚህም ምክንያት ደቡብ ክልል ሰባት ምርጫ ክልሎች ላይ በዕለቱ ድምፅ አይሰጥም።

Filed in: Amharic