>

የሀይል ሚዛን - የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይል...!!! (ኦሉማ ወዳጆ)

የሀይል ሚዛን – የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይል…!!!

ኦሉማ ወዳጆ

የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ልዩ ሀይል ከትግራይ ክልል እንዲወጡ የሚደረገው ጫና በዋናነት ከወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎት የመነጨ ነው። የእነዚህን ሀይሎች ከክልሉ የመውጣት ጉዳይ የሚወስነው ግን የፌደራል መንግስት ፍላጎት እና ውሳኔ ብቻ ሳይሆን፤ በሰሜን ዕዝ መጠቃት እና በአፀፋው ሳቢያ የተፈጠረው ወታደራዊ እና የደህንነት ሁኔታ መቀየር ነው። ይሄ ምን ማለት ነው?
በጥቅምት 24ቱ ጥቃት የሀገሪቱ 80% ወታደራዊ አቅም በህወሐት እጅ ገብቶ እንደነበር የሚታወቅ ነው [ይሄ ከደብረፅዮን እስከ ፃድቃን ያሉ ህወሐታውያን ያመኑት ነገር ነው]። በዚህም ሳቢያ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ወታደራዊ የሀይል ሚዛኑ ወደ ህወሐት አድልቶ ነበር። ይህን አዲስ የሀይል ሚዛን reconfigure ለማድረግ በህወሐት እጅ የገባው የሀገራችን ወታደራዊ እና ስትራቴጂክ ሀብት በድሮን እና በጄት በተፈፀመ ጥቃት መውደም ነበረበት። የኤርትራ እና የአማራ ክልል ታጣቂዎችም ከመከላከያ ጎን መሰለፍ  ነበረባቸው። ይህ ባይሆን ኖሮ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ አማራ ክልል እና ኤርትራ የህወሐትን የሮኬት ጥቃት እያስተናገዱ፤ የፌደራል መንግስትም ትልቅ ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ውርደት ውስጥ ይሆኑ ነበር። መንግስት ለወሰደው ፈጣን እና realistic እርምጃ ምስጋና ይግባውና፤ ይህንን በሶስት ሳምንታት ውስጥ ብቻ መቀልበስ ተችሏል።
ይሁንና የተናጋው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም ሙሉ በሙሉ አልተመለሰም። ሀገራችን የነበራትን ወታደራዊ hardware (ህወሐት ከዘረፈው ውስጥ አጋንነን ግማሹ ተርፏል ብንል እንኳን) ከ40-50% ገደማ አጥታለች። የነበራት የሰለጠነ ተዋጊ ሀይልም (ወደ ህወሐት የኮበለሉትን፤ በህወሐት በግፍ የተገደሉትን፣ በውጊያ ወቅት የተሰዉትን እና ለራሳቸውም ለሀገርም ደህንነትም ሲባል leave እንዲወጡ የተደረጉትን ጨምሮ) እንዲሁ ከ50% ባላነሰ መጠን ቀንሷል። ይሄንን ጉድለት ማሟላት ጊዜ እና ሀብት ይጠይቃል። በአራቱም የሀገራችን አቅጣጫዎች ያለው ሁኔታ እና የኢኮኖሚ አቅም ደግሞ ጊዜ አይሰጥም። ስለዚህ መንግስት የተጓደለውን የሰው እና የቁሳቁስ ጉድለት ወደነበረበት እስኪመልስ ድረስ የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ልዩ ሀይል ባሉበት መቆየታቸው ግድ ነው። ይሄ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። በህወሐት የተፈጠረው ሁኔታ ያስከተለው አዲስ የደህንነት ሁኔታ (the new security exigency) ነው። ይሄን ከስሜት በፀዳ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መረዳት ያስፈልጋል።
የሆነው ሆኖ በህወሐት orphans፣ በአሜሪካ እና በአጋሮቿ፣ እንዲሁም በሌሎች አካላት የኤርትራ እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይሎች እንዲወጡ የሚደረገው ጫና በጥንቃቄ መታየቱ መቀጠል አለበት። የህወሐት orphans የኤርትራ እና የአማራ ክልል ሰራዊቶች እንዲወጡ የተደረገውንም ያልተደረገውንም አጋንነው የሚያቀርቡት፤ ሁለቱ ሀይሎች ቢወጡ የሚፈጠረውን የሀይል ክፍተት (power vacuum) በማስላት ነው። በእነሱ ስሌት አቅሙ significantly የቀነሰውን፣ በመልሶ መቋቋም ላይ ያለውን እና በየአቅጣጫው overstretched የሆነውን መከላከያ ለመግጠም ያለው አማራጭ ይኸው ነው። ከስሌታቸው አንፃርም በትግራይ ክልል ውጊያው የፈጠረው ጉዳት በቂ ሆኖ ስላላገኙት፤ አንድ ፀሀፊ እንዳለው they are manufacturing outrage።
በባይደን አስተዳደር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እና እንደ ጆሴፍ ቦሬል ያሉ የአውሮፓ ህብረት ሹማምንቶችም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዚህ ዘመቻ አካል ናቸው። ሁለቱ ሰራዊቶች ከትግራይ ክልል ወጥተው፤ የፌደራል መንግስቱ አቅም ካልተዳከመ በቀር በልዩ ልዑኮቻቸው አማካይነት ለማደራደር የያዙት እቅድ እንደማይሳካ ያውቃሉ። Asymmetric በሆኑ አካላት መካከል አደራደሪ መሆን እጅግ ከባድ ነው። የመሳካት ዕድሉም ጠባብ ነው። ስለዚህ በፌልትማን ወይም በሀቪስቶ በኩል ሊያደርጉት ካቀዱት ድርድር አንፃር የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ልዩ ሀይል ካልወጡ የሚሉት የሀይል ሚዛኑን ለመቀየር ነው። የሰብአዊ መብት ጉዳዮች secondary አጀንዳዎች ናቸው።
በእኔ ግምገማ እና እምነት መከላከያ ሰራዊታችን ወደ ሙሉ አቅሙ እስኪመለስ ድረስ የኤርትራ እና የአማራ ክልል ልዩ ሀይል ባሉበት መቆየታቸው ግድ ነው። ሁለቱም ላይ ከሰብአዊ መብት አንፃር የሚነሳባቸው ምሬት እና ቅሬታ ግን በአስቸኳይ መታረም አለበት። ከዲሲፕሊን እና ከወታደራዊ እና ሰብአዊ (humanitarian) ህጎች አንፃር ያሉ ክፍተቶችም መታረም አለባቸው። ሁለቱ ሀይሎች የሸፈኑትን የሀይል ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል አቅምም በአስቸኳይ መፈጠር አለበት። ከዚህ በተረፈ ሁኔታዎችን ለህወሐት ፍርራሽ ለማመቻቸት የሚደረጉ ጫናዎች ባለመቀበሉ መንግስት ሊደገፍ ይገባል።
[P.S. ለበርካታ ኢትዮጵያውያን (በተለይ ለትግራይ ክልል ተወላጆች) የኤርትራ ሰራዊት በትግራይ ክልል በሚደረጉ ዘመቻዎች መሳተፍ እንደሚጎረብጥ ይገባኛል። እነሱም ደግሞ ይህን ሁኔታ የፈጠረው ምን እንደሆነ ሊገባቸው ይገባል።]
Filed in: Amharic