>

ስለምን ትክዱናላችሁ...???  (ሙሉአለም ገብረመድህን)

ስለምን ትክዱናላችሁ…??? 

ሙሉአለም ገብረመድህን

መነሻዬ የዶክተር ብርሃኑ ነጋ ቃለ-መጠይቅ፣ ሰውየው ‘በኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀል አልተፈጸመም’ ሲል ከሕግ ፍሬ ነገር ትንተና የሚቃረን ምላሽ ሰጥቷል። የሕግ ባለሙያ ባልሆንም ዓለማቀፍ ብያኔዎችን መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ በተለየ ሁኔታ በአማራ ተወላጆች  ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል የሚል እምነት አለኝ።
እ.አ.አ  በ1948 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት ባወጣው ድንጋጌ (Convention on the prevention and punishment of the crime of Genocide [Article 2]) ላይ ግልጽና ዓለማቀፋዊ የሕግ ትርጉም አስቀምጧል።
Article II
In the present Convention, genocide means any of the following acts committed with intent to destroy, in whole or in part, a national, ethnical, racial or religious group, as
such:
(a) Killing members of the group;
(b) Causing serious bodily or mental
      harm to members of the group;
(c) Deliberately inflicting on the group conditions of life calculated to bring about its physical destruction in whole or in part;
(d) Imposing measures intended to prevent births within the group;
(e) Forcibly transferring children of the group to another group.
በተለጠጠ ትርጉም የዘር ማጥፋት ወንጀል ማለት አንድን የተለየ ዘውጋዊ፣ ኃይማኖታዊ ወይም ሌላ ቡድን/ቡድኖች ሆን ብሎና አቅዶ በሙሉ ወይም በከፊል ለማጥፋት፣ ህልውናውን ለማናጋት የሚደረግ አካላዊ፣ ማህበረ ፖለቲካዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት ነው። የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጠበብ ካደረግነው ደግሞ የተቀናጀና የተሰላ ጅምላ ግድያ ነው። በተለይም የጥቃቱ ሰለባዎች መሳሪያ ያልታጠቁና ወታደራዊ ፍልሚያ ውስጥ ያልገቡ፣ አቅም የሌላቸው ከሆኑ ማናቸውም የጅምላ ጭፍጨፋ የዘር ማጥፋት ይባላል።
የ Genocide Watch ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር  Gregory H. Stanton; “THE EIGHT STAGES OF GENOCIDE” በሚል ባቀረቡት ጥናት የዘር ማጥፋት ወንጀል ደረጃዎችን ለይተው አቅርበዋል። እነዚህን ደረጃዎች እያጣቀስን የአማራን ጉዳይ በወፍ በረር ቅኝት እንመልከተው
1) CLASSIFICATION (መከፋፈል) ነው። ይህ “እኛ” እና “እነሱ” የሚል ከፋፋይ መስመር  በኢትዮጵያ መዋቅራዊ ይዞታ አግንቶ ከበቂ በላይ ተራግቧል።
2) SYMBOLIZATION (አሉታዊ ስያሜ/ፍረጃ መስጠት) ነፍጠኛ፣ ሰፋሪ ወራሪ፣ ትምክህተኛ፣ እነዚህና መሰል አሉታዊ ስያሜዎች/ፍረጃዎች አማራውን ለመጨፍጨፍ መደላድል እንዲሆኑ ጥቅም ላይ ውለዋል። (ዶክተር ብርሃኑ በዛው ሰሞን ይሄን ‘Political Establishment’ ኢንዶርስ አድርጎት “ቤኒሻንጉል ያለ ሰፋሪ አማራ…” የሚል አደገኛ ቃል መጠቀሙን ያስታውሷል)
3) DEHUMANIZATION (የሰውነት ክብርን መግፈፍ) ይህ ለጭፍጨፋው ትልቁ መደላድል ነው። ይህ ሰብዓዊነትን የመካድ ደረጃ፣ ታርጌት የተደረገው ቡድን በእንስሳት ፣ በዕፅዋት ፣ በነፍሳት ወይም በበሽታዎች ሊሰየም ይችላል። በሩዋንዳ የሁቱ ኢንተርሃሞይ ሚሊሻ ቱትሲዎችን “cockroaches” (በረሮዎች) እንዳሉት ሁሉ በኢትዮጵያ ትህነግ የወልቃይት ጠገዴ አማሮችን “ሓድጊ”(አህያ) በሚል ነበር እየጠራ ሲጨፈጭፋቸው የነበር። ይህኛው ደረጃ ‘የሰው ልጅን ሳይሆን በረሮን፣ አህያን፣ …ነው እየገደልን ያለነው’ የሚል የግፉዓንን ሰብዓዊነት የመካድ የእርድ ቄራ ማመቻመቻ ደረጃ ነው። በኢትዮጵያ በግልጽ በሚዲያ  ባይለፈፍም በዝግ የአዳራሽ ስብሰባዎችና በኢ-መደበኛ ወጎች የአማራ አራጆች ይህን ሰብዓዊነትን የመካድ ተግባር ደጋግመው ፈጽመውታል።
4) ORGANIZATION (መደራጀት) የዘር ማጥፋት ወንጀል ሁሌም ቢሆን በተደራጁ አካላት (usually by the state) ነው የሚፈጸመው። አንዳንዴ መደበኛ በሆነ አደረጃጀት  (Special army and  units) ሌላ ጊዜ ደግሞ በ Paramilitary እና  ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችን በማስተባበር ወንጀሉ ሊፈጸም ይችላል። (በሩዋንዳ የኢንተርሃሞይ ሚሊሻ፣ በሱዳን ዳርፉር የጃንጃዊድ ኃይል፣ በኢትዮጵያም በጋምቤላ [አኝዋክ] አጋዚ፣ በኦሮሞ ክልል ኦነግ፣ በአማራ ወልቃይት ጠገዴ የትግሬ ታጣቂና የሳምረ ገዳይ ቡድን ‘ለማጥቃት የመደራጀት’ ተጠቃሽ  አብነቶች ናቸው)
5) POLARIZATION (በጥላቻ ቡድኖች የሚነዛ የጥፋት ፕሮፖጋንዳ) ይህ የሕግ ድንጋጌ እስከማውጣት የሚለጠጥ የጥላቻ ስብከት በዚህኛው ደረጃ ይጠቃለላል። “ከዚህ ቡድን ጋር ጋብቻ አትፈጽሙ፣ ማህበራዊ ተቋማትን አትጋሩ፣ ገበያ አትገበያዩ፣… ወዘተ” የሚሉ አደገኛ ቅስቀሳዎችን ይጨምራል። በኢትዮጵያ በሕግ ደረጃ መሰል ድንጋጌ ባይኖርም በድርጅትና በቡድኖች በተቋቋሙ ሚዲያዎችና መሰል አደረጃጀቶች አማራውን ታርጌት ያደረጉ የጥፋት ፕሮፖጋንዳዎች ተሰርተዋል (Tigray Online, Aiga Forum, TMH, OSA, OPride, OMN, … አማራን በተመለከተ ሲነዙት የኖሩትና አሁንም በርትተው እየሰሩበት ያለው የጥፋት ፕሮፖጋንዳ፣ ለአምስተኛው ደረጃ  ማሳያ ሁኖ ይቀርባል)
6) PREPARATION (ለድርጊት ፍፃሜ ዝግጅት ማድረግ) ነጥሎ ለማጥቃት ያመች ዘንድ ዒላማ የተደረጉ ቡድኖችን በብሔር አልያም በሃይማኖት መለየትን ማዕከል ያደረገ ደረጃ ነው። በዚህኛው ደረጃ የሚጨፈጨፉ ሰዎች በስም ዝርዝር ይለያሉ፣ መኖሪያ ቤታቸውን ለመለየት ምልክት ይደረጋል፣ ንብረታቸው ይወረሳል/ይወድማል፣… ይህ ደረጃ ከጭፍጨፋ በፊት በወልቃይት ጠገዴ፣ በመተከል፣ በወለጋ፣ በሻሸመኔ፣ በአርሲ፣ በባሌ፣ በጉራፈርዳ፣… በአማራ ተወላጆች ላይ ሲፈጸም ታይቷል።
7) EXTERMINATION (ማስወገድ/መፈፀም)
 በዚህኛው ደረጃ፦ የተቀናጀና የተሰላ የጅምላ ግድያ የሚፈጸምበት ነው። ጨፍጫፊዎቹ ታርጌት ያደረጉትን ቡድን ሰብዓዊነቱን ቀድሞውንም የካዱ በመሆኑ፣ በጅምላ ለሚጨፈጭፏቸው ቡድኖች ራሮት አይኖራቸውም። ይህ በማይካድራ፣ በመተከል፣ በበደኖ፣ በወተር፣ በወለጋ፣… በሚኖሩ አማሮች ላይ ተፈጽሞ ተመልክተናል።
8) DENIAL (ድርጊቱን መካድ) ይህ የድኀረ-ዘር ማጥፋት ደረጃ ሲሆን፤ ወንጀል ፈጻሚ ኃይሎችና የድርጊቱ ደጋፊዎች ትኩስ አስከሬኖችን፣ የጅምላ መቃብሮችን፣ የሟች ቤተሰቦችን የአይን ምስክርነት፣… እያዩና እየሰሙ ሽምጥጥ አድርገው የሚክዱበት ደረጃ ነው።
ከላይ የተመለከትናቸው ስምንት ደረጃዎች በአማራው ላይ አልተፈጸሙም ማለት በ Gregory H. Stanton ብያኔ ራስን ደረጃ ስምንት ላይ የማሰለፍ አቋም ተደርጎ ይወሰዳል። በድርጊቱ ባይሳተፉ እንኳ የዘር ማጥፋት ወንጀሉን “ግጭት”  ብሎ መጥራት  የድርጊቱ ደጋፊ እንደመሆን ይቆጠራል።
ማይካድራን እንደ አብነት!
በማይካድራ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓለማችን በመቶ አመት ታሪክ ውስጥ ካስተናገደቻቸው ዘግናኝ ግፎች ውስጥ እንደአንዱ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት፣ ዓለም በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ግፎችንና ጭፍጨፋዎችን አስተናግዳለች፡፡ በኦቶማኖች የተመራውና ዘግይቶ እውቅና የተሰጠው በአርመኖች ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል (እ.አ.አ.1915)፣  በብሪታንያ የቅኝ አገዛዝ ግፍ እና በደል ለዘመናት የዘለቀ ስቅየትን ያስተናገዱት ሕንዶች በ Brigadier-General Reginald Dyer የተመራው የአምሪትሳር ፍጅት (እ.ኤ.አ 1919)፣ ፋሽስት ጣሊያን ለዳግም ወረራ ወደኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ የመርዝ ጋዝ ፍጅቱን ሳንዘነጋ አዲስ አበባ ላይ በጅምላ የጨረሳቸው  የ‹የካቲት 12 ሰማዕታት› (1929)፣ የጀርመኑ ናዚ ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላ በአይሁዳዊያን ላይ ያደረሰው ዘግናኝ እልቂትና የኦሽዊት ጭፍጨፋ (እ.አ.አ 1940 ዎቹ መግቢያ)፣ በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የማያባራ ጥቃት ሲፈጸመባቸው የኖሩ አልጄርያውያን ላይ የወረደባቸው የፊሊፕቪል ዕልቂት (እ.ኤ.አ 1955)፣ በአፓርታይድ የግፍ ሥርዐት ውስጥ የነበሩት ደቡብ አፍሪካውያን ላይ የተካሄደው የስዌቶ ፍጅት (እ.ኤ.አ 1976)፣ በሩዋንዳ የቱትሲ ተወላጆች ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋት ወንጀል (እ.አ.አ 1994)፣ በቦስኒያ ከተፈጸመው የሰርበኒካ ጭፍጨፋ (#srebrenica_massacre 1995)… ጋር የሚመሳሰል የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ማይካድራ ላይ የተፈጸመው፡፡
ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ሀገራት በዜጎች ላይ የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ማንነትን (ዘርን፣ ሃይማኖትን) መሰረት ያደረጉ ጭፍጨፋዎች ናቸው፡፡
ፍጅቶቹ፣ ጭፍጨፋዎቹ፣ ግድያዎቹ፣ እና ዕልቂቶቹ ከላይ ለተጠቀሱት ሀገራትና ሕዝቦች ልዩ ትርጓሜ እና ሥፍራ እንዳላቸው ሁሉ የማይካድራ ጭፍጨፋም በኢትዮጵያ በተለይም ደግሞ በአማራ ሕዝብ ታሪክ ውስጥ ልዩ የታሪክ ምዕራፍ ይይዛል።
ለሠላሳ ዓመታት የትህነግ የጥፋት መርከብ ጉዞ … የመጨረሻ ወደቡ ያደረገው ማይካድራን ነው፡፡ ማይካድራ ላይ በትህነግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ያጣናቸው ወገኖቻችን ትህነግን ለመደምሰስ በተከፈተው ሕግ የማስከበር ዘመቻ እንደአማራ የጸጥታ ኃይል ስምሪት ከከፈልነው መስዋዕትነት አስር ከመቶ ያህል ድርሻ እንኳ የለውም፡፡ ማይካድራ ከ1500 በላይ አማራዎች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው ተጨፍጭፈዋል። ከላይ የተመለከትናቸው ስምንቱም የዘር ማጥፋት ደረጃዎች አንድ በአንድ ተፈጽመውባታል። እናም ማይካድራ የወልቃይት ጠገዴ አማራ የግፍ ጥግ ማሳያ ነች፡፡ ከማይካድራው የዘር ማጥፋት ወንጀል ቀደም ብሎ ለሰላሳ ዓመታት በወልቃይት ጠገዴ አማሮች ላይ የተፈጸሙትን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እንደመስታውት የምታመላክት የሐዘን ነጸብራቅ ብትሆንም፣ የኢዜማው መሪ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እውቅና ሊሰጣት አልፈለገም። ያን ዘግናኝ እልቂት “ግጭት” በሚል  አገላለጽ ጠቅልሎ ሊያልፈው ሞክሯል።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቁ በሽታ፣ አቅላይነት (reductionist) ስለመሆኑ ርግጥ ነው። የብዙሃን እልቂት ተደጋግሞ የታየበትን ግልጽና ተጨባጭ የዘር ማጥፋት ወንጀል ስለመፈጸሙ የአይን ምስክርም፣ የጅምላ መቃብርም፣… ሌሎችም ማስረጃዎች በቀረቡበት ሁኔታ ‘የዘር ማጥፋት ወንጀል አልተፈጸመም’ ማለት መገለጫው ከአቅላይነት በላይ ክህደት ነው።
በነገራችን ላይ ከላይ እንደአብነት ያነሳሁትን የወልቃይት ጠገዴ አማሮችን ዓለም ጀሮ የነፈገውን ግፍና በደል እና የድኀረ-ነጻነት አሁናዊ ሁኔታ በቦታው ተገኝተው የጎበኙት የ Abbay Media የጋዜጠኞች ቡድን፣ ያቀረቡት ፕሮግራም በተለይም የማይካድራውን ጭፍጨፋ የዳሰሱበት ክፍል ግሩም ምልከታ ሁኖ አግቼዋለሁ።
 ይህን 👇
ማስፈንጠሪያ በመዳበስ እንዲመለከቱ ተጋብዘዋል።
ማሳረጊያ
ለሥልጣን እውነትን የማይናገር ምሁር እርሱ አድርባይ ነው!  ብርሃኑ ፖለቲከኛ ባይሆኑ ከምመኝላቸው ሰዎች አንዱ ነበር። ባይሰበር። በሦስት ዓመቱ የሰርከስ ፖለቲካ ቆሽቴን ቢያሳርረውም፣ በዚህኛው ቃለ-መጠይቁ እጅግ አብግኖኛል። ከእንግዲህ ‘ኢትዮጵያ እንድትቀጥል አማራን መካድ’ ይሉት የኑፋቄ መስመር እንዲቀጥል የሚፈቅድ አማራ ስላለመኖሩ የማይቀበሉ ከሃዲያን እርማቸውን ሊያወጡ ይገባል።
ዶ/ር ብርሃኑ ግን መስከረም ላይ ለማያጣው አንድ የሚኒስትሪያል ፖሲሽን፣  በአማሮች ላይ ለሰላሳ ዓመታት የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል መካዱ እጅግ ያሳዝናል። ቢካድ ቢካድ ማይካድራ የማይካድ ተጨባጭ እውነታ ነበር። ሰውየው ግን ካደው!
Filed in: Amharic