ያ በእናት ሀገር ፍቅር የነደደው የዋህ ትውልድ…!!!
አሰፋ ሀይሉ
ዘመኑ የብልጠት ነው! ብልጥነት ሳይገባቸው ቤተሰባቸውን አጉድለው፣ ራሳቸውን ለሀገራቸውና ለወገናቸው ክብር አሳልፈው ለሰጡ ለህዝባዊት ወታደራዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች እንደወጡ ያለአስታዋሽ ቀርተዋል፡፡ ታሪካቸው አኩሪ የሀገር ተጋድሎ ታሪክ ሆኖ ሳለ፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች እስካሁን ሀገሪቱን በቁጥጥራቸው ሥር አውለው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የጠላቱን ታሪክ ታሪኬ ብሎ ያቀነቅነዋል! እውነተኛ ለሀገራቸውና ለባንዲራቸው የቆሙ ጀግኖች ተረስተው፣ ኢትዮጵያን ያደሙና ባንዲራዋን ያዋረዱት ባለታሪክ ጀግኖች ሆነዋል!
እነዚያ እውነተኛ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሚያሳዝነው ነገራቸው አንድዬ የማትተካ ውድ ህይወታቸውን ለሀገራቸው አሳልፈው መስጠታቸው ብቻ አይደለም! ከሁሉም ነገር በላይ እጅግ የሚያሳዝነው ያለ ስም፣ ያለ ዕውቅና፣ ያለ ምስጋና፣ ያለ ታሪክ መቅረታቸው ነው!
ታሪካችን ያለ እነርሱ ጎዶሎ ነው! ታሪካችን የቆርጦ ቀጥሎች ታሪክ ነው! እነዚያ ጀግኖች ደማቸውን ለእናት ሀገራቸው አፍስሰው ቤተሰባቸውን አጉድለዋል! ለወገን እንዳልተዋጉ፣ ለሀገር እንዳልወደቁ – በየጣራው ሥር መከራውን የቆጠረ ቤተሰባቸውን ዞር ብሎ ያየ ወገን፣ የደገፈ ሀገር የለም!
በዓለም ላይ የፈለገውን ሀገር ብናይ.. ተሸንፈው በወጡባቸው የጦር ቀጣናዎች ሳይቀር የሀገራቸውን ባንዲራ ይዘው የወደቁ ጀግኖቻቸው ስንት ክብር ይቸራቸዋል! ቤተሰቦቻቸው ስንት ክብርና ድጋፍ ይቸራቸዋል! እኛ ሀገር እያለን፣ ለሀገሩ ለቆመ ጀግና ክብር የማይገኝበት፣ ሀገሩን የተቀማ ሀገር እንደሌለው የሆነበት፣ ልክ ሀገሩ ጠፍቶ በሌላ ጠላት በቅኝ የተወሰደበት፣ በቅኝ የሚገዛ ህዝቦች መስለንና ሆነን እየኖርን ነው!
አንዳንዴ ሳስበው ኢትዮጵያውያን ማንም ላይ ሳንደርስ ሀገራችንንና ነጻነታችንን ክብራችንን ባንዲራችንን ስንል በገዛ ሀገራችን በጀግንነት ለቆምነው፣ በምን ሀጢያታችን ነው ልክ እንደ ናዚዎችና ፋሺስቶች የተቆጠርነው? እያልኩ ሁልጊዜ እገረማለሁ፡፡
ዘረኝነትና ክፋትም ታክሎበት፣ አባት ሀገራቸው ጀርመንን የዓለም ገዢ፣ ህዝባቸውን ደሞ የዓለም የበላይ ዘር እናደርጋለን ብለው ከተነሱት የናዚ ጀርመን ወታደሮች መካከል፣ ስለሀገራቸው ሲሉ ታላላቅ ተጋድሎ የፈጸሙና፣ ለሀገራቸው ሲሉ ተነግሮ የማያልቅ መስዋዕትነት የከፈሉ ታላላቅ ጀግኖች እንዳሏቸው ምንም ጥርጥር የለውም፣ ግን ተሸንፈዋልና፣ ዓለም ናዚዝምን ለዝንተዓለም መቃብር ሊከትተው ወስኗልና የዚያ ዘመን ጀርመኖች ያለታሪክ፣ ያለጀግና፣ ያለምንም ‹‹ቫኪዩም ተሸናፊዎች›› ብቻ ሆነው ቀርተዋል!
ያ ሁሉ ያለ ወላጅ የቀረ ጀርመናዊ ትውልድ ስለ ናዚ አባቶቹ ትንፍሽ ማለት እንዳይችል ሆኖ ይኸው ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ኖረዋል፡፡ ይሄ በራሱ ብዙ ዝርዝር ነገሮች አሉት፡፡ ሁሉም ህዝብና ሀገር የየራሱ ጀግና አለውና ይሄን የታሪክ ፍቀት ሙሉ በሙሉ ፍትሃዊ ነው ማለት የሚቻል አይመስለኝም፡፡
የሆነ ሆኖ የሚገርመኝ ትልቁ ነገር – የእኛ ሀገር ጀግኖችና ታሪካቸው ጉዳይ ነው! በምን ተዓምርና በምን ዓይነት ምድራዊም ሰማያዊም ሎጂክ ነው የእኛ ለሀገራቸው ትልቁንና ውዱን መስዋዕትነት የከፈሉ እነዚያ የኢትዮጵያችን እውነተኛ ጀግኖች ታሪክ ከታሪክ መዝገብ እንዲፋቅ፣ ቤተሰቦቻቸው ታሪክ እንደሌላቸው፣ ሀገራችን ታሪክ እንደሌላት፣ የኢትዮጵያ ጠላቶች ታሪክ የኢትዮጵያ ታሪክ ሆኖ እንዲቀጥል የተደረገው?
ዓለምን እናስገብራለን ብለው ከተነሱ ናዚዎችና ፋሺስቶች እኩል እንዴት ሀገራችንን አናስደፍርም ብለው ቤት ንብረታቸውን ጥለው፣ ዘመድ አዝማዶቻቸውን ተሰናብተው፣ ድሎትና ምቾታቸውን ተስፋቸውን ሁሉ ትተው ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያኖች ክብር ዘብ የቆሙ ጀግኖቻችን ያለ ታሪክ፣ ያለ ሀገር፣ ያለ ምስጋና፣ ያለ ምንም ነገር የሚቀሩት? በምን ሀጢያታቸው? ሀገርን አሳልፈን አንሰጥም፣ እኛ እያለን ሀገራችን በባንዳዎች፣ በገንጣዮች፣ አስገንጣዮች እጅ ተላልፋ አትሰጥም፣ ብለው ሀገራቸውን ስለጠበቁ፣ ለባንዲራቸው ስለቆሙ፣ ይህ ነው ታሪካቸውን ከታሪክ መዝገብ ላይ ያሰረዘባቸው ምክንያት? በእርግጥ የዓለም ታሪክ ሁሉ ፍርደ-ገምድል እንደሆነ የሚታወቅ ነው፣ ታሪክ የአሸናፊዎች ነውና!
ነገር ግን እንዲህ የሀገር ታሪክ ያው ትውልድ በህይወት እያለ – እውነት ሞታ ስትቀበር፣ ጀግና ሞቶ ሲቀበር፣ ታሪኩም እና የቆመለት ሀቅም አብሮ በቁሙ ሞቶ ሲቀበር ሲታይ – አጥንት ድረስ ገብቶ ያንገበግባል! ዜግነትን ያስረግማል! ሰውነትን ያስጠላል! በምን አፋችንና በምን ዓይናችን ነው ቤተሰቦቻቸውን የምናየው? ብዙዎች አንብተው ወጥቶላቸዋል! ለዚህች ሀገር የቆሙ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች አጥንታቸውን አሞራ ሲጫወትበት፣ ከሞት የተረፉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ከነክብር ልብሳቸው መንገድ ዳር ቆመው ሲለምኑ፣ በአካልና በመንፈስ ሲታመሙ፣ በችግር ሲማቅቁ – ያኔ ወጥቶላቸዋል ሀዘኑ! ቁጭቱ ግን መቼም አይለቅም! ሞተውም ነፍሳቸው እኛን የቆምነውን ብልጥ ትውልዶች የሚከሰን ይመስለኛል!
ቤተሰቡን አጉድሎ፣ ልጆቹን ሜዳ ላይ በትኖ ለሀገሩና ለወገኑ፣ ለባንዲራውና ለነጻነቱ የወደቀ ጀግና በማይከበርበት፣ ከሁሉ ነገር ርቆ፣ ከማንኛውም መስዋዕትነት ከሚያስከትል ሥፍራ ጠፍቶ፣ ልጅን በፍቅር እያሳደጉ የሚስትና የባልን ጭን እያሞቁ በሠላም በልጽጎ መኖር የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ተደርጎ በተቆጠረበት ሀገር ላይ፣ ሞኝ ጀግና መቼውኑም ሊበቅል አይችልም! ቤታቸውን ያጎደሉ፣ አካላቸውን ያጎደሉ፣ ልጆቻቸውን ያጎደሉ፣ ቤተሰባቸውን ያጎደሉ፣ እና በመጨረሻም ሀገራቸውን ያጎደሉ ጀግኖች ደም እንዲህ እንደ ውሻ ደም ደመ-ከልብ ሆኖ መቅረቱ የማያንገበግበው ‹‹ብልጥ›› (ማለትም ‹‹ድንዙዝ››) ትውልድ ለመፍጠር የተሠራው የግማሽ ክፍለዘመን ሥራ ውጤቱ እየታየ ነው!
ብዙ ጊዜ በግል ሩጫችን (በብልጠታችን) ላይ አተኩረን ልብ አንለውም እንጂ፣ የጀግና ደም እንደ ውሻ ደም በሚታይበት በየትኛውም ሀገር፣ ጀግና ዳግመኛ ሊበቅል አይችልም! ለሀገር የተገለጠ ጅልነት በሚዘበትበት ሀገር፣ ዳግመኛ የሚገለጥ ጅልነት ሊኖር አይችልም! ለሀገር ጅል መሆን ፈጽሞ አይታሰብም! በብልጠት ብዛት ሰማይ የነካ ትውልድ፣ ሀገር ጭንቅ ውስጥ የገባች ዕለት የሚቆምለት ጅል ጀግና አይኖረውም!
ለሀገራቸው የተዋደቁት እነዚያ ጀግኖች የቆሙለት ዘር፣ ጎጥ፣ ብሔር፣ ቡድንና ዘርማንዘር አልነበረም! ንጹህ የሀገር ፍቅር የፈነቀላቸው፣ ንጹህ የባንዲራ ፍቅር ያገነፈላቸው፣ ንጹህ የወገን አለኝታነት ያጀገናቸው ንጹሃን ጅል ጀግኖች ነበሩ! ይህቺ ምድር – ዳግመኛ እነዚያን የመሰሉ ጅል ጀግኖች ለማየት የምትታደል አይመስለኝም! ሁሉም ከሁሉ የበለጠ ብልጥ ሆኖ ለመሞት በሚጋደልበት ሀገር ላይ፣ የብልጠታችን መጨረሻ የት እንደሚያደርሰን ማየት ይናፍቃል!
ለኢትዮጰያ አንድነትና ለባንዲራቸው ክብር ለተሰዉት ለእነዚያ የጅል ዘመን እውነተኛ ጀግኖች ትልቅ ክብርና ፍቅር አለኝ! ጅልነታቸው ተወዳዳሪ የሌለው እጅግ ውዱ ሥጦታ ነበር! ያንን የሚያውቀው ትውልድ እስኪገኝ የሚተርፍ ሀገር አይኖርም! አጉድለዋቸው የቀሩት ቤተሰቦቻቸው በዚህች ሀገር ላይ እንደምን ያለ እምነት ሊኖራቸው እንደሚችል፣ እንደምን ያለ ትምህርት እንደሚወስዱ ማሰብ ያቅታል! የኢትዮጵያ አምላክ ይካሳቸው! ፈጣሪ ባረፉበት የክብር ሥፍራ ሁሉ ለነፍሳቸው ዘለዓለማዊ እረፍትን ይስጣት!
አንድ ቀን ጅል ትውልዶቹን የሚያነሳና ጅልነትን የሚናፍቅ ጅልነት የጠማው ትውልድ እንደሚመጣ አስባለሁ፣ እንዲመጣም እመኛለሁ! ይህ የጮሌዎችና የሀገር ጠዪዎች፣ የኢትዮጵያ ጠላቶችን የዘመን ቀንዲል ተሸካሚ ጎሰኞችና ዘረኞች ዘመን ከምንም ነገር በፊት ፈጥኖ እንዲያበቃ አጥብቄ እመኛለሁ! የታሪክ ጉድፋችን ጠርቶ፣ እውነተኛ ጀግኖቻችንንና ታሪካችንን ማየት እስከምንችልበት፣ እስከምንናፍቅበት እስከዚያው ዘመን ድረስ፣ ፈጣሪ የቃልኪዳኑን ምድር ኢትዮጵያችንን በኪነጥበቡ ይጠብቅልን ዘንድ ከልብ እመኛለሁ!
ለእነዚያ ስለ ሀገራቸው ሲሉ ጅል መሆንን ለመረጡ፣ እና ጅል ሆነው የሞቀ ቤታቸውን ጥለው ወጥተው የአሞራ ሲሳይ ሆነው ለቀሩ፣ በአካል ተርፈው ለመንፈስ ስብራት ለተዳረጉ፣ ሀገርን ቤትን ትውልድን ላጎደሉ፣ ታላቅ ታሪክ ሠሪዎች ሆነው ሳለ ያለታሪክ ለቀሩት፣ ለእነዚያ ታላላቅ ጅል ጀግኖቻችን ዘለዓለማዊ ፍቅርና ክብር ይድረሳቸው! የጅልነትን ጥበብ ይስጠን! ከታሪካችን ያስታርቀን! አበቃሁ!