መንግሥት የባልደራስ ወኪል ታዛቢዎችን እያደነ ነው…!!!
ጌጥዬ ያለው
ባለፈው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ወኪል የነበሩ ታዛቢዎችን የአብይ አሕመድ መንግሥትና ገዥው ፓርቲ እያሳደዷቸው ይገኛል። ከወኪሎች መካከል የአንደኛው መኖሪያ ቤት ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ረፋድ ላይ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተበርብሯል። ብርበራውን አቶ ሙሉዓለም ዋዋዬ የተባሉ የኦሮሞ ብልፅግና ካድሬ የመሩት ሲሆን ራሳቸውን ‘ቄሮ’ በማለት የሚጠሩ ሰባት የኦሮሞ ወጣቶች ተሳትፈውበታል።
በተመሳሳይ ሌሎች ወኪሎች ሊገደሉ፣ ሊታሰሩ ወይም ንብታቸውን ሊነጠቁ እንደሚችሉ በቀበሌ ካድሬዎች እየተዛተባቸው መሆኑን ተናግረዋል። “ሊያፍሱን ተዘጋጅተዋል። በዱላ እንዲደበድቡን። በተለይ እኔን ደግሞ በተገኘሁበት እንዲገድሉኝ ፖሊሶች ከቀበሌ አመራሮች ትዕዛዝ ተቀብለዋል። ከሥራ ሊያፈናቅሉን ተዘጋጅተዋል” ብለዋል አቶ አሰፋ ነጋሽ የተባሉ የባልደራስ ወኪል። እየጠቆሙ የሚያሳስሯቸው መርጋ የተባሉ በምርጫው የብልፅግና ወኪል የነበሩ ካድሬ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በተያያዘ ዜና በምርጫው ዋዜማ ማለትም ባለፈው አርብ ሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ሦስት ሰዓት ላይ የታሠሩ 3 የአዲስ አበባ ኗሪዎች የደረሱበት ጠፍቷል። አሰፋ ሻረው እና ለማ ሻረው የተባሉ ወንድማማቾች እንዲሁም ተክለ አረጋይ ገብረ ዮሃንስ የተባሉ ዜጎች ‘የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የባልደራስ ደጋፊዎች ናችሁ’ በሚል የታሠሩ ሲሆን ሌሎች ስድስት የአማራ ተወላጅ የከተማዋ ኗሪዎች እየታደኑ ነው።