>

ማሸነፍ ፤ መሸነፍ እና መበሻሸቅ...!!! (በእውቀቱ ስዩም)

ማሸነፍ ፤ መሸነፍ እና መበሻሸቅ…!!!

(በእውቀቱ ስዩም)

ከልጅነታችን ባንዱ ቀን፤  እኔ ከማ አቡኔ ቤት ጠላ ገዝቼ   ወደ ቤቴ ስመጣ ፤ ሌላው እኩያየ ደሞ ላምባ ገዝቶ ወደ ቤቱ ሲሄድ መስቀልኛ መንገድ ላይ እንገናኛለን ፤   ከዩንበርሱ በጥቂት አመት የሚበልጥ ጥንታዊ     ድንጋይ ላይ የተቀመጠ ቦዘኔ  ጎረምሳ ይጠራንና “ ትቸለዋለህ?” ይለናል፤
እኔ ወደ ባለላምባው እያየሁ  “ከነካኝ አለቀውም “ እላለሁ፤ ባለ ላምባውም ተመሳሳይ መልስ ይሰጣል፤  ‘ከነካኝ አለቀውም”  የሚለውን ሰላማዊነትን እና አይበገሬነትን እንዲሁም “ፍትሃዊነትን” አስተባበሮ የያዘ አባባል በልጅነታችን ማን   እንዳቀበለን አላውቅም   ጎረምሳው በዚህ አባባል ረክቶ አያሰናብተንም፤   ነገር ቆስቁሶ ያፋጥጠናል፤ ዘመዶቼ ሰርግ ላይ ሲሉ እንደሰማሁት” አረንዛው ዳሞቴ “ብየ እፎክርና የጠላ ማንቆርቆሪያየን አስቀምጣለሁ ፤ ባለላምባው ልጅ  ጀሪካኑን ማስቀመጥ አይጠበቅበትም፤  ከሳሎን ተነስቶ  ምኝታ ቤቱ  እሰኪደርስ ደረስ በሩም ግድግዳውም እየገጨው ያደገ  የላምባ ሰፈር ልጅ ነው ፤  በቴስታ መታኝ ማለት ጉዳቴን  ማቃለል ይሆንብኛል  ፤ ጭንቅሎውን  እንደ መርግ ደጋግሞ  ጣለብኝ ማለት ይሻላል፤
  ከሰአታት በሁዋላ  አይጠ-መጎጥ ቀምሶ የተወው  ቀይ ስር መስየ ቤት ሰመጣ  እናቴ
“ ተመተህ  ወደ ቤት መጣህ አይደል?” ትለኛለች፤
“ አይ ! ሳልሰናበትሽ መሸፈቱ ከብዶኝ ነው እንጂ በዛው ጫካ ልገባ ነበር” እንድላት ነበር የፈለገችው?
በዘንድሮው ምርጫ ማግስት በተሸናፊዎች ላይ የዘነበውን ብሽሽቅ ሳይ  አንድ ነገር አሰብኩ  ፤ ለማብሸቅ የማይመች ባህርይ ያላቸው ፍጡራን  የታደሉ ናቸው- ልክ እንደ ፈንቴ!
 ፈንቴ በጉርምስና ዘመኔ የማውቀው  የሰፈራችን ልጅ ነበር፤
  አንድ ቀን ረፋድ ላይ ፤ ከተማችን በታወቀ  ቡና ቤት በረንዳ ላይ የትምርት ቤት    ዩኒፎርም የለበሰች ቆንጆ   ኮረዳ  ልጅ ጋር ቁጭ ብሏል ፤  ከፊታቸው ሁለት ንብ የሚዞራቸው  የተጀመሩ የኮካኮላ ጠርሙሶች ይታያሉ ፤    ተግባሩ የሚባለው የሰፈራችን ነገረኛ ልጅ በዚያ ሲያልፍ   ፈንቴን ከኮረዳይቱ ጋራ ሲያየው  ተናደደ፤ እድል እንዲህ ናት ፤ ላንዱ Dateቱን ” ለሌላው ንዴቱን ትሰጠዋለች፤
“ ፈንቴ ” ብሎ ተጣራ ፤ ተግባሩ
“ አቤት”
“ ትናንት  መኩርያ፤   በቆላ ሽመል ሲያሯሯጥህ ለምን ነው  የሸሸኸው  ?  “  አለና ፈገግ ብሎ ልጂቱን አያት፤
“የቱ መኩርያ? “ አለ ፈንቴ
“መኩርያ የጋሸ ተጫነ ልጅ?”
“የትኛው ጋሸ ተጫነ? ”
“ ያልገባህ  ይመስል አታድርቀኝ
“ እ መኩርያ ተጫነ  አወቅሁት! እና እሱ የት ላይ ነው ያባረረኝ?”
“  ሙስጠፋ ጮርናቄ ቤት አጠገብ “
“ የቱ ሙስጠፋ?   “ ፈንቴ ቀጠለ፤
“  አታምታታ! መኩርያ ለምንድነው ሲያባርርህ የሮጥከው? “
“ ዥል!  ለምን ይመስልሃል?  ሙሉ አካሌን ይዥ ወደ ቤቴ ለመግባት ስለፈለግሁ ነዋ “
Filed in: Amharic