>

እስክንድር ነጋ ከታሰረ 11 ዓመት ሞላው!!! ( ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል )

እስክንድር ነጋ ከታሰረ 11 ዓመት ሞላው!!!

( ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል )

ዛሬ ሰኔ 24 እስክንድር ነጋ፤ ስንታየኹ ቸኮል
አስቴር ስዩምና አስካል ደምሴ በሀሰት ክስ ከታሰሩ ድፍን አንድ ዓመት ይሞላቸዋል። 
በተያያዘ:-
 እስክንድር ነጋ በኢህአዴግ ቁጥር 1-
 10 ዓመት
በኢህአዴግ(ብልፅግና) ቁጥር 2-
1 ዓመት 
በአጠቃላይ  ድፍን 11  ዓመት  ወይም 4,015 ሌሊት በእስር ላይ አሳልፋል።
….እነዚህ ከወርቃማ የጉርምስናም የጉልምስናም ዕድሜው ላይ የተቀነሱ ዓመታቶች  ለሀገር  የተከፈሉ ድንቅ መስዋዕትነቶች እንደሆኑ ታሪክና የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀው ሀቅ ነው። እንደዛሬ  የድል አጥቢያ አርበኛ ባልበዛበት፣ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የተገኘ ሻማ ለራሱ እየቀለጠ ለሌላው ብርሃንን ካጎናፀፉት ግንባር ቀደምቶች ውስጥ  እስክንድር ነጋ በዋናነት ይጠቀሳል።
  የእስክንድርን 11 ዓመታት በእስር ማሳለፍ  አስመልክቼ አምና   ዳግም የመታስሩን ዜና እንዴት እንደሰማኹ ላካፍላችኹ:-
 23/2012 ምሽት
ስልኬ በጣም ተጨናንቁዋል። በተደጋጋሚ ይጠራል።  በማውቀው እና በማላውቀው ቁጥር። ‘ምን ተፈጠረ ? ላንሳው ወይስ ልተወው ?’ የሚደወሉ ቁጥሮች ላይ ዐይኔን አፍጥጬ ከራሴ ጋር አወራለኹ።  ስልክ ተለዋውጠን ፣ ነገር ግን ተደዋውለን የማናውቅ ሰዎች ኹሉ  መደወል ይዘዋል። (በነገራች ላይ፣ ስልክ መመለስ ላይ ከፍተኛ ድክመት አለብኝ)
 የጥሪው መብዛት ስላሳሰበኝ  ማናገር ጀመርኩ።  መጀመሪያ ያወራኹት ታማኝ በየነን ነበር። ሰላምታ ከተለዋወጥን በኅላ:-
‘እስኬው እንዴት ነው? ‘ ሲል ጠየቀኝ።
 ጠዋት  ማግኘቴን ሰላም መሆኑን ገለፅኩለት።
‘ እየደወልኩለት ስላላነሳው ነው ወደአንቺ የደወልኩት’  አለኝ።
‘አሁን  እነሱ ጋር ለሊት ነው …ምናልባት ስልኩን ሳይለንት አድርጎት ይኾናል።  በሰላም ነው ግን ታማኛችን?’ በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት።
አይ…’ራስህን ጠብቅ ለማለት ነበር። አንዳንድ የሚሰሙ ነገሮች ደስ አይሉም’ ሲል  የተረበሸ በሚመስል ድምፅ ገለፀልኝ።
‘ምን  እየተሰማ ነው?’ ግራ ገባኝ…
ያው ‘እስቄ ….ነገሮች እስኪበርዱ ብዙም ባይንቀሳቀስ…’  ታማኝ መጨነቁን ድምፁ እና በቀጭኑ ሽቦ የሚሰማው ረጅም ትንፋሽ ያሳብቅበታል።(ብዙ ግዜ  ታማኝ እስክንድርን ‘እስቄ’ ሲል በራሱ ቁልምጫ  ይጠራዋል።)
‘በቃ እደውልለታለኹ። ቴክስትም አደርግለታለኹ። አመሰግናለኹ ታማኛችን’ አልኩት።
‘አዲስ አበባ   አሁን  እደውላለኹ።  በጥዋት እንዲያገኙትና እንዲነግሩት’ ብሎኝ  ስልኩን ዘጋው።
 የልብ ትርታዬ ጨመረ። ከማህበራዊ ሚድያ ከራቅኹ ሰንበትበት ብያለኹ።  ዳግም ላልመለስ ለራሴ ቃል ገብቼ ነበር። በፌስቡክ ሀገራዊ መረጃና  ዜና ለማየት በገባኹ ቁጥር ጩኸቶች፣ ለቅሶዎች፣ ‘ታከለ ከንቲባችን እስክንድር ጠላታችን’የሚሉ ድምፆች  እመለከት ነበር።  ስሙን ያለመታከት እንደዳዊት ሲደግሙ የሚውሉ፣ ሱስ የሆነባቸው ነበሩ ብል ማጋነን አይኾንም።  በደቦ  ዘመቱበት።  እግዚኦ የተሳዳቢ ብዛት። እግዚኦ የተራጋሚ ብዛት። እግዚኦ የአልቃሽና አስለቃሽ ብዛት። የአንዳንዶቹን አሁንም ድረስ ማመን ያቅተኛል።  በዚህ ልክ ይወርዳሉ  ብዬ የማልገምታቸው ፣ እስክንድር የሚያራምደውን ሃሳብ ሳይሆን እሱነቱ ላይ ተንጠልጥለው  ለማሳጣት የሄዱበት ርቀት  አጃኢብ የሚያሰኝ ነው።  ዓለማዊ ኅጢያቱን ሳያጥቡለት አልቀሩም።  እግዜር ይባርካቸው።
  እኔ ግን እመሰክራለኹ። እስክንድር ፣ እጅግ  ክብሩን የጠበቀ ጨዋ፣ አንደበቱ የተገራ፣ ፈሪሃ እግዚያብሄር ያለው ፣ ጮክ ብሎ  የማይናገር ለስላሳ፣ የተቆጣን ስቆ የሚያበርድ፣  ለራሱ ግዜ የማይሰጥ እረፍት-አልባ  ባተሌ…ዓለምን የናቀ የከተማ መናኝ፣   ቁሳቁስ የማያስደነግጠው፣ ከምንም ዓይነት ሱስ   የፀዳ ንፁህ ፣ቀና አስተሳሰብ የተላበሰ  ትሁት፣   ሰው ላይ የማይደርስ  የመልካም ስብዕና ባለቤት እንጂ …የሴራና ተንኮል ሰው አይደለም ።  ማንንም  የቤት ስራው አድርጎ ለማሳዘን የሚንቀሳቀስ  እንዳልሆነ አውቃለኹ። እስክንድር  ከአምባገነን ሥርዓት እንጅ ከግለሰብ ጋር ሲጋጭ ሰምቼም አይቼም አላውቅ።  ክብር ለቸሩ መድሃኒያለም። ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም።  ለማንኛውም፣ ጠዋትና ማታ እስክንድርን ላይ የሚዝረከረኩትን  ላለማየት ስል ማህበራዊ ሚዲያው  መሰናበት ግድ ብሎኝ ነበር።  አደረኩት። ለ4 ወር አካባቢ ከስፍራው ጠፋኹ። ሲቀር ይቀራል አይደል የሚባለው።
የተነሳኹበትን ሳልዘነጋ ፣ በአጋጣሚ ሳልጠቅሰው የማላልፈው ፌስ ቡክ በዘጋኹበት ሰሞን ‘ጠፋሽ’ ሲል ገጣሚና ደራሲ  ዮሃንስ ሞላ(ጆ) ደውሎልኝ ነበር።
“ሰዬ በሰላም ነው የጠፋሽው?”
” ጆ አሜሪካ ገብቼ ነው”
 መልሴ ግራ ሳያጋባው አልቀረም.. አሜሪካ ተቀምጬ፣ አሜሪካ ገባኹ ማለት። …ዝምታ ሲያበዛ ሳይጠይቀኝ መመለስ ጀመርኩ። ‘ይኸውልህ ጆ ወደ ስራ ስሄድና ከስራ ስመጣ ባስ ውስጥ ፌስቡክ እያየኹ አንዳንዴ መውረጃዬን ኹሉ አልፈዋለኹ። አንጎብሼ ስልኬን መመልከት ስለማበዛ መንገዱን አላስተውለውም።  ፌስቡክ ከዘጋኹ በኅላ፣ ዓመት የተመላለስኩበት መንገድ  አዲስ መስሎ ታየኝ።  የሚያምሩ ፎቆች፣  የተለያዩ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶች  የልጆች መጫወቻ ስፍራዎች፣ ትያትር ቤት እረ ምኑ.. (አለኹ ማለት ከንቱ  አልኹ በውስጤ  )  ዘረዘርኩለት። በሌላ ርዕስም ብዙ አወጋን። እናም … ለዚህ ነው አሜሪካ  ገባኹ ያልኩህ።
ጆ በመጥፋቴ አሳስቦት  እንጂ ምክንያቴና ውሳኔዬ  መልካም መሆኑን ገለፀልኝ።
እዚህ ላይ በስም የማልጠቅሳቸው መወለድ ቁንቁዋ ነው የሚለውን ብሂል በተግባር ያሳዩኝ ወንድሞችም አሉ ተባረኩልኝ።
የታማኝን ስልክ እንደዘጋኹ ሌላው ደዋይ ጌታነህ ካሳሁን ነበር። ጌታነህ  የሀገሩን ጉዳይ በንቃት የሚከታተል፣ በተለያየ መንገድ   አስተዋፅኦ የሚያበረክት ፣በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ ቃለ-ምልልስና ትንተና  ሲሰጥ ይታወቃል።
ከሰላምታ ለጥቆ ‘በማህበራዊ ሚዲያ እስክንድር ላይ መጥፎ ቅስቀሳ እየተደረገ ነውና እባክህ ራስህን ጠብቅ’ በይው ሲል ቀደም ብዬ ከታማኝ የሰማኹትን ባዘነ ስሜት ውስጥ ሆኖ ደገመልኝ።
 “እሺ እነግረዋለኹ። አመሰግናለኹ’ ብዬ ስልኩን ዘጋኹ።
ሌላም ስልክ መጮህ ጀመረ። ኅይለገብርኤል አያሌው ነበር። ኅይለገብርኤል የእስክንድር የቅርብ ጎደኛ ነው። ይቅርታ ጎደኛ የሚለውን ሰንሰለት በጣጥሰን ቤተሰብ ከሆንን ዓመታት አልፈዋል። ለእኔና ለልጄ ከነባለቤቱ ኹሉ ነገራችን ናቸው። ቤታችንን ዘግተን፣ ውሎና አዳራችን በእነሱ ቤት የሚሆንበት ግዜ ተደጋጋሚ ነው። ተባረኩልኝ። እሱም እንደሌሎቹ ተመሳሳይ መልዕክት ‘እስክንድር እንደው ለትንሽ ግዜ ወዲህ ወዲያ ባይል’ የሚለውን  ሐሳብ ቴክስት እንዳደረገለት ነገረኝ። ሰኔ 23/2012 ምሽት ስልኬ ፋታ አልነበረውም።  ሲጠራ  ያላነሳኹትና አናግሬ ስማቸውን ያልጠቀስኩዋቸው በርካቶች  ስለ ደህንነቱ ተጨንቀዋል።
//
ሰዓት ተመለከትኹ። ኢትዮጵያ ሌሊት 8 ሰዓት ይላል። ወደ እስክንድር መደወል ጀመርኩ። መልስ የለም። የመጨረሻው መልዕክቴ  ከንዴት ጋር የተፃፈ ነው
” እስክንድር ብዙ ሰው ስላንተ እያሰበ ይገኛል። ለምን ሰው እንዲጨነቅ ታደርጋለህ?  ራሱን ይ ጠብቅ የሚል ስልክ በዝትዋል” ላኩለት።  አላየውም። ሰዎች ጋር ደወልኩ።  ሰላም መሆኑን መብራት ጠፍቶ አድሮ ስልኩ ቻርጅ ማድረግ እንዳልቻለ ገለፁልኝ።
24/2012
ምስቅልቅል ያለ ቀን። በስልክ የማገኛቸው ሰዎች ከወደ ሃገር ቤት የሚሰሙትን  እያነቡ ይነግሩኝ ነበር። እጅግ የሚያም። ልብ የሚሰብር። መፈጠር የሚያስጠላ። ህፃናት፣ አዛውንት፣ ሽማግሌ፣  በዘራቸው እየተመረጡ  በገጀራና በካራ ሲጨፈጨፉ ማደራቸውን ። እግዚኦ ጭካኔ ህፃናት ምን ስላደረጉ ይገደላሉ? ለህፃናት ፖለቲካ ምንድነው?  ብይ? ቆርኪ? ብስኩት?..ህፃናት እሳት እንደሚያቃጥል እንኩዋ አያውቁም። መጫወቻ ነው የሚመስላቸው። ሊጨብጡትና ሊነኩት ይታገላሉ።  በማንኛውም ምክንያት የእነሱን አሰቃቂ ግድያ መስማት ያሳዝናል። ፈጣሪ ይዘገያል እንጂ ፍርድ ይኖረዋል።
በዚህ ቀን በእስክንድር ዙሪያ አዲስ ነገር ሳይሰማ መሸ።ተመስገን!!
 ሰኔ 25/2012
  በዲሲ አቆጣጠር ጥዋት 10:15 አካባቢ ስልኬ ጠራ።  የተደወለው ከካናዳ ነበር። ጋዜጠኛ ነው። ወዳጃችን።
ሰላምታ ከተለዋወጥን በኅላ፣
‘እስክንድር እንዴት ነው ዛሬ አግኝተሽው ነበር? ” ሲል ጠየቀኝ። ገና መነሳቴ እንደሆነ፣  ትንሽ ቆይቶ እንደሚደውልልኝ  (በእኛ ምሳ ሰዓት ላይ ነው  ሁልግዜ የሚደውለው)  ነገር ግን ትላንት ሰዎች ጋር ደውዬ ሰላም መሆኑን እንደነገሩኝ ገለፅኩለት። ድምፁን ቀነስ አድርጎ ‘ ዛሬ ምንም የሰማሽው ነገር የለም? አለኝ።
‘እረ ምንም አልሰማኹም። ምን ተፈጠረ?”
‘እ..እ..ያው የፌስቡክ ወሬ ሊሆን ይችላል.. ‘
አላጨረስኹትም። ‘እባክህ፣ ፌስቡክ ስለዘጋኹ  ያየኹት የለም። የሰማኸውን እንደወረደ ንገረኝ አልኩት።  ከትንሽ ዝምታ በኅላ፣ ‘እስክንድር ታሰረ አኹን ከቢሮ ወሰዱት እየተባለ ነው’ አለኝ። ዕውነት መኾኑን አጣርቼ መልሼ እንደምደውልለት ገልጬ ስልኩን ዘጋኹት።
ከቢሮ ወሰዱት ስለተባለ  ገለታው ጋር ደወልኹ።  ፖሊሶች እየገፈታተሩ እንደወሰዱት ነገረኝ። ገራሚ ነው።  በዚህ ግዜ እስክንድር የሚታሰርበት  ምክንያት አልነበረም። እንቅስቃሴው ሰላማዊና ህጋዊ ነው። ለአንዲትም ሰከንድ ከህግ ማዕቀፍ ወጥቶ አያውቅም። ስለሰላም የቆረበ እስኪመስል የአመፅን  መንገድ አጥብቆ ያወግዛል።  በምን ምክንያት ሊታሰር ይችላል??  ንግግሩ ሁሉ በ’ምርጫ እንገናኝ’ ነበር። ግራ ገባኝ። ቀደም ሲል፣   በሀሰት ክስ ‘አሸባሪ’ ተብሎ  7 ዓመታት ታስሮ  በወቅቱ ጠ/ሚር ኅይለማርያም ደሳለኝ ትዕዛዝ ከተፈታ ሁለት ዓመት አላለፈውም። ( በነገራች ላይ ለእስክንድርና ለአንዱዓለም መፈታት ኅይለማርያም ደሳለኝ  የነበራቸው ሚና ወደፊት የሚገልፅ ይኾናል።) ዳግም ወደነበረበት ቦታ የሚመለስበት አሳማኝ ነገር የለም። እስክንድር ከጋዜጠኝነት ሙያው ባሻገር  ወደ ፖለቲካ እንቅስቃሴ መግባቱ ወንጀል አይደለም። ጤናማ ነው። ያፈለገውን የመሆን መብት አለው።  መስመር እናስምርልህ፣   በዚህ ውስጥ ብቻ ተንቀሳቀስ፣ ይህንን አትንካ፣ ያንን አታንሳ ሊባል አይገባውም።  አንዳንድ ሰዎች ወደ ፖለቲካው ባይገባ የሚሉ አሉ።  ከቅን አስተሳሰብ በመነሳት  ከሆነ እሰየው። ከዚያ ባለፈ በ”እኛ እናውቅልሃልን” እሳቤ ግን ድካም ይኾናል። እስክንድር ነፃነቱን ማንም በመስፈሪያ ቆንጥሮ እንዲሰጠው  የሚፈቅድ ስብዕና የለውም።  ያለመተዋወቅ ካልኾነ።
አንዳንዶች ፣ ‘መንግሥታቸው’ የተነካ እስክንድር ለ’ፖለቲካ አይሆንም’ ሲሉ ይደመጣሉ። ፖለቲከኛ ለመኾን  መስፈርቱ ምንድነው? የትምህርት ደረጃ? ዕድሜ? ቁመት?የሰውነት ክብደት  …ይመቻችኹ!!!
እንግዲህ ፣ የእስክንድር መታሰር ዕውን ሆንዋል። እኔም የተውኩትን ፌስቡክ  መመልከት ግድ ኾኖብኛል።
አምና በዛሬዋ ዕለት ሰኔ24/2013 ትልቁ ዜና ጁዋር መሃመድ ጋሽ በቄ፣  እስክንድር ነጋና ስንታየኹ ቸኮል መታሰራቸውን የሚገልፅ   ነበር። ካልተሳሳትኩ፣ አስቴር ስዩምና አስካል እነእስክንድር ከተያዙ ከሁለትና ሶስት ቀን በኅላ ይመስለኛል የታሰሩት።
ምራቂ
 በእስር ዜና  የድብርት ድባብ ውስጥ እያለን  ዲሲ  ጠ/ሚር አብይ “ወንጀለኞችን በማሰርዎት  ተደስተናል” የሚል የድጋፍ  ሰልፍ  ተጠራ።
ነገር ግን …..
 እስክንድርም ሆነ ጃዋር  ከታሰሩ አንድ  ዓመት ሞልቶቸዋል። ፍ/ቤት እስካሁን በማናቸውም ላይ ‘ወንጀለኞች’ ናችኹ ብሎ  አልፈረደባቸውም  ሃ.ሌ.ሉ. ያ!!!
አንዳንዶች   ደግሞ በ “ህቡዕ” መንቀሳቀስ ሲሉ ለዐቃቤ ህግ ክስ ተጨማሪ ግብዓት ለመሆን ሞከሩ።  ከመተዛዘብ ውጭ ያተረፍነው የለም።
የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ!!!
የአምና የሁለት ቀናት ትዝታዬ በአጭሩ ይህንን ይመስላል።
ወዳጆች ….ለአቶ እስክንድር የ11 ዓመት 4,015 የእስር ሌሊት 
11 ግዜ ርችት በስሙ ይለቀቅ
እስክንድር ነጋ እስክንድር ነጋ 
እስክንድር ነጋ እስክንድር ነጋ
እስክንድር ነጋ  እስክንድር ነጋ
እስክንድር ነጋ.   እስክንድር ነጋ
እስክንድር ነጋ
እስክንድር ነጋ
እስክንድር ነጋ
Filed in: Amharic