>
5:31 pm - Wednesday November 12, 1862

በጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባውን የወልቃይትና ሁመራን ወደካሽሚር አንቀይረው...!!! (ያሬድ ጥበቡ)

በጥንቃቄ ሊያዝ የሚገባውን የወልቃይትና ሁመራን ወደካሽሚር አንቀይረው…!!!

ያሬድ ጥበቡ

የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት የሆነችው ወይዘሪት ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር የተኩስ ስምምነት ለማድረግ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ስላቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ተናግራለች :: ከንግግሯ ከማስታውሳቸው ነጥቦች የሚከተሉት ይገኙበታል:
1ኛ) ከመስከረም ጀምሮ የተያዘው የክልሉ በጀት እንዲለቀቅ
2ኛ) የተቋረጡ የመብራት: ስልክ: ኢንተርኔት: ባንክ ወዘተ አገልግሎቶች ወደነበሩበት ደረጃ እንዲመለሱ
3ኛ) ከየሥራ ገበታቸው የተፈናቀሉም ሆነ የታሰሩ ተጋሩ ወደሥራቸው እንዲመለሱ
4ኛ) የተጋሩም ሆኑ ሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ
5ኛ) የትግራይ ክልል አስተዳደር ከጦርነቱ መጀመር በፊት ወደነበረባቸው ወረዳዎች ሁሉ እንዲመለስና የተፈናቀለውም ህዝብ እንዲመለስ: ከጦርነቱ ወዲህ አዲስ የሰፈሩ ሰዎችም እንዲነሱ
6ኛ) በጦርነቱ ትግራይ ላይ የደረሰውን ውድመት የሚያጠናና የሚገመግም ዓለምአቀፍ ቡድን እንዲቋቋምና ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ይገኙባቸዋል:: ያላስታወስኳቸውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል አድምጡ::
በእኔ አስተሳሰብ የትግራይ ክልል ምእራብ ትግራይ ብሎ የሚጠራው የወልቃይት ሁመራ ጉዳይን እንዲህ በቀላል ባያየውና: የሁለት ኢትዮጵያን መሥራች ህዝቦችን ደም የሚያቃባና አቢይ የጠነሰሰውን ሁለቱን ህዝቦች ደመኛ ጠላት አድርጎ የማቆላለፍ እቡይ ዓላማ የሚያሳካ በመሆኑ ጉዳዩን ከወታደራዊ አኳያ ከማየት ይልቅ በሁለቱ ህዝቦች መሃል መደረግ ያለበት ንግግር: ሰጥቶ መቀበልና  እርቅን ያካተተ አድርጎ ቢመለከተው ምኞቴ ነው:: አንድ የጦርነትና ብካይ ምእራፍ አገባደን ወደሌላ እንዳንሸጋገር የትግራይ መከላከያ ሃይሎችን አመራርም ሆነ የትግራይ ክልል መግስትን አመራር  ለህሊናቸው አቤቱታ ማቅረብ እወዳለሁ:: ወልቃይትና ሁመራን ወደካሽሚር አንቀይረው: በጥንቃቄ መያዝ የሚያስፈልገው ጉዳይ በመሆኑ የሚገባውን ስሱነት ማሳየት ይጠበቅባችኃል::እስቲ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ከራሳችሁ ጋር በጥሞና ተነጋገሩ::
Filed in: Amharic