>

በትግራይ ክልል ድጋፍ ለመስጠት የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎችን በተመለከተ መንግስት መመሪያ ማዘጋጀቱን አስታውቋል 

በትግራይ ክልል ድጋፍ ለመስጠት የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎችን በተመለከተ መንግስት መመሪያ ማዘጋጀቱን አስታውቋል 
 
የአውሮፕላን በረራዎች ወደ ትግራይ ከማቅናታቸው በፊት ቅድሚያ አዲስ አበባ ማረፍ ይጠበቅባቸዋል፤  
(ኢ ፕ ድ) 

በትግራይ ክልል ድጋፍ ለመስጠት የሚደረጉ የአውሮፕላን በረራዎችን በተመለከተ መንግስት መመሪያ ማዘጋጀቱን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ አስታውቋል።
መረጃ ማጣሪያው ዛሬ ከሰአት ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ እንደገለጸው በትግራይ ክልል የተናጠል የሰብአዊ የተኩስ አቁም ውሳኔን ካሳለፈ በኋላ በትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ጋር  አብሮ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን በሰሜን የአገሪቷ የአየር ክልል በረራ ቢዘጋም የኢትዮጵያ መንግስት ግን ከሰኞ እለት ጀምሮ በትግራይ የሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ ለሚፈልጉ አካላት በሙሉ በረራ ማድረግና እርዳታውን ማድረስ እንደሚችሉ ማስታወቁን መረጃው ገልጿል።
የዓለም የምግብ ድርጅት ትናንት ወደ ትግራይ ክልል ሰዎችን በሁለት በረራዎች ለማጓጓዝ ጥያቄ አቅርቧል ያለው መረጃው፤  መንግስት የዚህ አይነት ጥያቄዎችን ለማስተናገድና ለሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ጉዳዩን የተሳለጠ ለማድረግ ብሎም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ጉዳዩ ከሚመለከተው ሌላ ተቋም ፈቃድ በፍጥነት ለማግኘት ይቻላቸው ዘንድ መመሪያዎችን እና መረጃዎችን የያዘ ጋይድላይን አዘጋጅቷል ሲል ገልጿል።
በዚህ መሰረት ከውጭ አገራት ወይንም ከአገር ውስጥ የሚመጡ ማንኛውም የአውሮፕላን በረራዎች ወደ ትግራይ ከማቅናታቸው በፊት ቅድሚያ አዲስ አበባ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፍ ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
በመመሪያው ላይ በግልጽ እንደተመላከተውም፤ ሁሉም የአውሮፕላን ጉዞ ጠያቂዎች የበራረ ቁጥር፣ የአውሮፕላኑን አይነት፣ የበረራ ምክንያቱን፣ የተጓዦቹን ዝርዝር መረጃ፣ የጭነት አይነት የተመለከተ ዝርዝር መረጃ ማቅረብ አለባቸውም ነው ያለው።
እውነታው ይሄ ቢሆንም አንድ አንድ ሪፖርቶች የኢትዮጵያ መንግስት በረራ እንደከለከለ በማስመሰል እየወጡ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ እያሳሳቱ ይገኛሉ ያለው መረጃው፤ መንግስት ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ደብዳቤ መላኩን አስታውቋል።
በተለይም ዩኤንኦቻ የተባለው ድርጅት እያቀረበ ያለው ሪፖርት የተሳሳተና በኢትዮጵያ ፓርላማ አሸባሪ ተብሎ የተሰየመውን ህወሓት የሚያበረታታና ለችግሩም መፍትሄ የማይሆን ገንቢነት የጎደለው ሪፖርት ማውጣቱ ተገቢነት የጎደለው መሆኑን በመግለጽ ድርጅቱ ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ መንግስት ጠይቋል።
የኢትዮጵየ መንግስት ወደ ትግራይ ክልል ከሚደረግ በረራ ጋር በተያያዘ ያስቀመጠውን አሰራርና መመሪያ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ለህዝብ በፍጥነት እንደሚያሳውቅም መረጃው አስታውቋል።
የምስል መግለጫ:- ወደ ትግራይ  ለእርዳታ የተፈቀደ በረራ️ ፍተሻው በዚህ መልኩ ቢሆን።
Filed in: Amharic