>

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ሲታወሱ...!!! (ዳንኤል ገዛህኝ)

ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ሲታወሱ…!!!

ዳንኤል ገዛህኝ

* …..ባለቅኔ፣ መምህር ፣ ጸሐፌ ተውኔት ፣ ዲፕሎማት፣ አርበኛ፣ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ፣ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር ግጥም ደራሲ የነበሩት ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ ሰኔ 30 ቀን 1939 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። በማግስቱም ቀብራቸው በቅዱስ በዓለወልድ ቤተክርስቲያን ተፈጸመ።
የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ አጽም በልማት ምክንያት ከተቀበረበት ቦታ ተነስቶ በትንሽ ሳጥን ተቀምጦ ለሰባት ዓመታት ከቆይ በኋላ ሐምሌ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ወደ ትውልድ ቦታቸው ተወሰዶ አጽማቸው ዳግም በደብረ ገነት ኤልያስ ቤተክርስቲያን እንዲያርፍ ተደርጓል። ይህም ማለት ከሞቱ ከሰባ ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው።
***
የአማርኛን ስነ ጽሁፍ ካሳደጉት ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን መካከል ባለቅኔው ዮፍታሄ ንጉሴ ይጠቀሳሉ፡፡ ዮፍታሄ ንጉሴ የተወለዱት በጎጃም ክፍለ ሀገር በደብረ ኤልያስ በ1885 ዓ.ም ሲሆን በደብረ ኤልያስ ደብር የጥንቱን የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ትምህርት በሚገባ ተምረዋል፡፡ ደብረ ኤልያስ ደብር የ”ፍቅር እስከ መቃብር” ደራሲ ሃዲስ አለማየው የተማሩበት ደብር ነው፡፡
ለዛሬ ከተለያዮ ምንጮች ያገኘናቸውን የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ ስራወች ልናስነብባችሁ ወደናል።
የቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ግጥሞች ትንቢታዊ ሲሆኑ በአንድ ስንኝ የሚጽፉት ግጥም ተሰጦአቸው የላቀ መሆኑን ያሳየናል። ለአብነት ያክል የሚከተሉትም ምጡቅ ስንኞቻቸውን እንመልከት፤
የሰማይ አሞራ ልጠይቅሽ ወሬ፣
ተቃጥሏል መሰለኝ ሸተተኝ አገሬ፡፡
ማሽላና ስንዴ በአንድ አብረን ስንቆላ፤
እያረረ ሳቀ የባህር ማሽላ፡፡
ከሰል የሚሆኑ ብዙ እንጨቶች ሳሉ፤
ዝግባ ለምን ይሆን ይቆረጥ የሚሉ፡፡
“ሰውን ሰው ቢወደው አይሆንም እንደራስ፣
ታመህ ሳልጠይቅህ መቅረቴን አትውቀስ፣
ባውቀው ነው የመጣሁ እንደማልመለስ፣
ይማርህ መሀሪው እስመጣ ድረስ።
በጣሊያን ወረራ ወቅት ለፋሺስት ያገለገሉ ባንዳዎችን በማስመልከት የገጠሙት ምፀታዊ ግጥም እንዲህ ይላል፡-
“ለጌሾ ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ
ለመጠጡ ጊዜ ከየጐሬው ወጣ፡፡”
ሌላኛው የቀኝ ጌታ እምቅ ቅኔ ደግሞ “አጥንቱን ልልቀመው” የሚለው ግጥም ሲሆን አርበኞቹን የዶጋሊውን አሉላ አባ ነጋ እና ራስ ጎበናን በማነፃፀር የገጠሙት ግጥም ነው፤
አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣
ጎበናናን ከሽዋ አሉላን ተትግሬ፣
ስመኝ አድሬያለሁ ትላንትና ዛሬ፣
አሉላን ለጥይት ጎበናን ለጭሬ፣
ጎበና ሴት ልጁን ሊያስተምር ፈረስ፣
አሉላ ሴት ልጁን ጥይት ሲያስተኩስ፣
ሀገሬ ተባብራ ካልረገጠች እርካብ፣
ነገራችን ሁሉ የዕምቧይ ካብ፣ የዕምቧይ ካብ።” ይላል።
ቀኝ ጌታ ድንግል ሀገሬ ሆይ የተሰኘውን ድርሰት የፃፉት በስደት ኢሊባቡር ሆነው በ1929 ዓ.ም ነበር፡፡ ይሄ ግጥም ዮፍታሄ ንጉሴ ህዝቡ በፋሺስት ወረራ የደረሰበትን ስደት የገለፁበት ስንኝ ነው፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ከእስራኤል ወደ ግብጽ ያደረገችውን ስደት እና በኤሮድስ ህፃናት መቀላታቸውን ከኢትዮጵያ ስደት ጋር ያነፃፀሩበት ግጥምም ደሞ እንዲህ ይነበባል።
“ጥንተ ተደንግሎ ጥንተ ተደንግሎ
ህፃናቱ ታርደው ያንቺም ልብ ቆስሎ
ልጅሽ ተሰደደ አንቺን ተከትሎ
የህፃናቱ ደም አዘክሪ ኩሎ፡፡
አዝማች፤ አስጨነቀኝ ስደትሽ
እመቤቴ ተመለሺ እመቤቴ ተመለሺ።”
***
እኒህ ታላቅ ደራሲ በርካታ ድርሰቶችን የጻፉ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች አብዛኛዎቹ ሥራዎቻቸው ለኅትመት አልበቁም።
Filed in: Amharic