>

የሥልጣን ሱስ አጓጉል መዘዞች....!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የሥልጣን ሱስ አጓጉል መዘዞች….!!!

አሰፋ ሀይሉ

 

*… ሥልጣናቸውን ያራዘሙት የሄይቲው ፕሬዚደንት ዦቨኔል ሞይስ  – በጥይት ተገደሉ – ሚስታቸው ቆሰለች!
 
*…. የእኛው መለስ ዜናዊና የመሠረተው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ  ላለፉት 30 ዓመታት ኢሳያስ አፈወርቄ እንደጠራው ‹‹የህጻናት ማታለያ ጨዋታ›› የሆነ የጨረባ ምርጫ እያካሄደ ከሥልጣኑ የማይለቅ ባለጠብመንጃ ገዢ አስታቅፎን በተፈጥሮ ሞት ተሰናብቷል! 
የምርጫ ጊዜውን በምርክርቤት ውሳኔ አራዝሞ በፕሬዚደንትነቱ የቀጠለው የሄይቲው ፕሬዚደንት ዦቨኔል ሞይስ በወታደሮች በተተኮሰበት ጥይት ተገደለ፡፡ ሚስቱም በጥይት ተመታ ክፉኛ በመቁሰሏ ወደ አሜሪካ ማያሚ ሆስፒታል ተወስዳ ህክምና እየተሰጣት ትገኛለች፡፡
ዦቨኔል ሞይስ ሀገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ሣይኖራት ከወንበሬ አልወርድም ብሎ በሥልጣን በገገመባቸው ዓመታት ሙሉ በርካታ ሄይቲያውያን ከሥልጣኑ እንዲወርድ የአደባባይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይም ከሰሞኑ ‹‹አምባገነን አንፈልግም!›› ‹‹በቃን!›› የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ሞይስ ከስልጣኑ ምስስ ብሎ እንዲወርድና ያልተበላ ህዝባዊ ምርጫ እንዲካሄድ ሲጠይቁ ነበር፡፡
አሁን ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቁና ‹‹ልዩ ኃይል›› ነን በማለት ራሳቸውን ያሳወቁ ታጣቂዎች ከሞይስ ጠባቂዎች ጋር ተኩስ በመለዋወጥ እስከወዲያኛው በሞት አሰናብተውታል፡፡ ሞይስ ፕሬዚደንት ከመሆኑ በፊት የታወቀ የሙዝ ነጋዴ ነበር፡፡
ይህን የግድያ ዜና የዓለም መሪዎች ያወገዙ ሲሆን፣ የአልጄዚራ የዜና ማሰራጫ ሄይቲ በኮሌራ ወረርሽኝ፣ በጎርፍ፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በህዝባዊ ተቃውሞ፣ በድህነትና በዘርፈ ብዙ የኑሮ ማጥ ውስጥ በመዘፈቅ – ከሣህራ በታች ካሉ ሀገራት በስተቀር (እኛን ኢትዮጵያውያንን፣ ሶማሊያውያንን፣ ኤርትራውያንን ጨምሮ) ከዓለም ከሄይቲ የማይሻል ሀገር የለም – በማለት – ይህ ዓይነቱ የመሪ ግድያ ደግሞ – በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው ሲል ኮንኖታል፡፡
/በነገራችን ላይ – ይሄ አልጄዚራ ግን የእኛን ስም በከንቱ መጥራቱ ምናባቱ ልሁን ብሎ ነው? እኛ ከሄይቲ አንሻልም ማለት ነው ግን? ወይስ ወሬ አሳመርኩ ብሎ ነው? (ስሙን ቄስ ይጥራውና!)/
በነገራችን ላይ ከሠሃራ በታች ስላሉ ሀገራት ከተነሳ አይቀር – የኤርትራው ኢሳያስ ‹‹እንደ ወያኔ ምርጫ የሚባል የህጻናት ማታለያ ጨዋታ እያካሄድን በገንዘብና በሰው ሀብት አንጫወትም!›› ብሎ በአደባባይ ምርጫ የሚባለውን ዲሞ-ፈጭስ ጨዋታ በመኮነን በመሪነት ሥልጣናቸው ላይ ከሰነበቱ ይኸው 30 ዓመት ሞላቸው!
የእኛው መለስ ዜናዊና የመሠረተው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ  ላለፉት 30 ዓመታት ኢሳያስ አፈወርቄ እንደጠራው ‹‹የህጻናት ማታለያ ጨዋታ›› የሆነ የጨረባ ምርጫ እያካሄደ ከሥልጣኑ የማይለቅ ባለጠብመንጃ ገዢ አስታቅፎን በተፈጥሮ ሞት ተሰናብቷል!
የመለስን ወንበር (ከኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ) የተረከበው አብይ አህመድም የሥልጣን ጊዜውን በምክርቤቱ በማራዘምና ሥልጣኑን አንቀበልም ያሉትን ተቀናቃኞች ጦርሠራዊቱን አዝምቶ በማዳፈን በጨዋታው ምርጫ በመሪነት ወንበሩ ተደላድሎ ቀጥሏል!
የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜም በበኩሉ የሀገሪቱን ህገመንግሥት ቀይሮ የመሪነት ሥልጣኑን ሲያራዝም የተነሱበትን ተቀናቃኞችና ሠላማዊ ሠልፈኞች በጥይት ገላግሎ ይኸው በሥልጣኑ ላይ ቀጥሏል!
በግብጽ ምድር ደግሞ ጄ/ል አብደልፈታህ አልሲሲ የሀገሪቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አድርጎ የሾመውን በህዝብ የተመረጠውን ሞሃመድ ሞርሲን በመፈንቅለ መንግሥት አስወግዶ (እና ሞርሲን በእስርቤት አስገድሎ) በመሪነት ሥልጣን ላይ ከሰነበተ እነሆ ሰባት ዓመት አለፈ፡፡
በሱዳን እንደ እነ ኢሳያስ አፈወርቄ ለ30 ዓመታት በስልጣን የከረመው ኦማር ሀሰን አልበሺር ወደ ሥልጣን በወጣበት ተመሳሳይ መንገድ (ማለትም በመፈንቅለ መንግሥት) ከመሪነት መንበሩ ተፈንግሎ በዘር ማጥፋት ወንጀል በሀገሩ ፍርድቤት አሳሩን እየበላ ሲሆን፣ ወደፊት ለዓለማቀፉ የወንጀል ችሎት አልበሽርን አሳልፈው እንደሚሰጡት ለአሜሪካ ቃል የገቡት የራሱ የአልበሽር የቀድሞ ሹመኞች ጄ/ል አህመድ አዉፍና አል ቡርሃን የመሪነቱን ወንበር አሙቀው ለአብደላ ሀምዶክ አስረክበውታል፡፡
በአጠቃላይ ከሰሃራ በታችም ሆነ ከሰሃራ በላይ – ወይም ከሰሃራ ወደጎን የሚባል ካለ ወደጎንም ቢሆን – ያሉ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች – አንዴ ወደ መንበረ ሥልጣናቸው ከወጡ በኋላ – ወይ ከፍተኛ ቁጣ በተቀጣጠለበት ህዝባዊ አብዮት አሊያም በወታደራዊ ባለሥልጣኖቻቸው በተቀናበረ መፈንቅለ መንግሥት ከወንበራቸው ተፈንግለው እንዲወርዱ ካልተደረጉ በስተቀር ከሥልጣን ንቅንቅ ማለት አይታሰብም!
ወይም ደግሞ በጥይትና በሚሳኤል (እንደ ሩዋንዳና ቡሩንዲ መሪዎች) በደም አፋሳሽ መንገድ የሥልጣን የዕድሜ-ዘመን ሃጃቸው እንዲገታ ካልተደረገ በስተቀር፣ አሊያም በህመምና በተፈጥሮ ሞት እግዜሩ ከሰው ቀድሞ ከሥልጣን ካላሰናበታቸው በስተቀር – አንዴ ሥልጣን ላይ ከወጡ የመውረዳቸው ነገር ‹‹የሞተ ጉዳይ›› (dead issue) መሆኑን – ዓለም ሁሉ የተስማማበት ሀቅ ከሆነ በጣም ቆየ!
የሆነ ሆኖ – ዦቨኔል ሞይስ – አርፎ ሙዙን ወደ ውጭ እየላከና የሚታማበትን ዶላር እየመነዘረ አርፎ የተዝናና የግል ኑሮውን መምራቱን ትቶ – በመሪነት ወንበር ላይ ሙጭጭ ሲል – ህይወቱን በጊዜ (በ53 ዓመቱ) ተነጥቋል! ያሳዝናል፡፡
እንዲህ ዓይነቱን አሳዛኝ የሶስተኛው ዓለም የመሪ ግድያና ከሥልጣን በውርደት የመሰናበት ዜና በሰማሁ ቁጥር – በአንድ ወቅት ባራክ ኦባማ አዲስ አበባ ላይ የአፍሪካን መሪዎች በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ሰብስቦ የነገራቸው አባባል ይመጣብኛል፡፡ ኦባማ በፊት ለፊታቸው እየተዘባበተባቸው እንዲህ ነበር ያላቸው የአፍሪካን መሪዎች፡-
‹‹እናንተ ከሥልጣን ወርዶ እንደ ተራ ሰው  የግልን ኑሮ መኖር መቻል ለምን እንደ ሞት አድርጋችሁ እንደምትቆጥሩት በበኩሌ አይገባኝም! አሁን እኔ ወጣት ነኝ! የአሜሪካ
ህገመንግሥት አይፈቅደልኝም እንጂ ለሶስተኛ የሥልጣን ጊዜ ብወዳደር ራሱ የማሸንፍ ይመስለኛል! ግን የምመኘው ትልቁ ነገር ከሥልጣኔ ወርጄ፣ ደስ የሚለኝን ነገር
እየሠራሁ፣ የቻልኩትን ግብረሰናይ ተግባራት እያከናወንኩ፣ የግሌን ኑሮ ከቤተሰቤ ጋር በነጻነት መምራት የምችልበትን ቀን ነው! ያውም እኮ እናንተ ከእኔ ትሻላላችሁ! ቢያንስ እናንተ በቂና የተትረፈረፈ ሀብት ያላችሁ ናችሁ! (እንደጉድ ስለምትዘርፉ ማለቱ ነበር)! ና ከሥልጣን በፈቃዳችሁ መልቀቅ ምን እንደሚያስፈራችሁ እኮ ነው ግራ የሚገባኝ!››
እየሳቀ ነው ልክ ልካቸውን የሚነግራቸው ኦባማ ለአፍሪካ ደናቁርት መሪዎች፡፡ ሁሉም በተቀመጡበት በሳቅ እየፈረሱ፣ በጣም አስደሳች ስታንድ አፕ ኮሜዲ እንዳቀረበላቸው ሁሉ – ሞቅ ያለ የማያቋርጥ ጭብጨባቸውን አቀለጡት፡፡ ኦባማ አብሯቸው በሳቅ ፈነዳ፡፡ አዲስ አበባ – የአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ – በሳቅ ተንበሸበሸ፡፡
የእኛ ነገር ይኸው ሆኗል፡፡ ሳቅ በሳቅ፡፡ አንድ የታወቀ ደራሲ ‹‹የምስቀው ማልቀስ ስለሌብኝ ነው፣ ይኸውም ይኸው ነው!›› እንዳለው፣ እኛም ከመሳቅ በቀር ምን አማራጭ አለን? እንሳቅ እንጂ! ‹‹አስራ ሰባት ዓመት ሙሉ ስቀን አናውቅም!›› ነበር ያሉት ቆፍጣናው መንጌ?
ወቸ ጉድ! መሳቅ ነው እንጂ! ከማልቀስ መሳቅ ሳይሻል አይቀርም! ግን መሪ በጥይት ተገድሎ መሳቅ? አይከብድም? እሺ ይሁን እናልቅስና እንሳቅ፡፡ እንባና ሳቅ እናድርገው፡፡ እያነቡ እስክስታ፡፡ የመከራና የጮቤ ሚስቶ፡፡ ይችው ነች ኑሯችን፡፡ እኛ ከሄይቲ ያነስነው የሣሃራ በታቾች፡፡
ፈጣሪ ለሞቱት የሄይቲ መሪ ዦቨኔል ሞይስ አፈሩን ያቅልልላቸው! ባለቤታቸውን ይማር!
የእኛዎቹንም ክፉ አይንካብን! ‹‹በመከራቸው ብዛት ከሄይቲ የባሱ የሠሃራ በታች አገሮች›› ተብሎ በዜና ከመጠቀስ ያውጣን ፈጣሪ! (እና ከዓለም ሁለት ሃያላን ሀገሮች አንዷ ያድርገን!)
አምላክ ኢትዮጵያችንን ከቀልደኛ የሥልጣን ሱሰኞች ገላግሎ፣ ህዝባችንን አብዝቶ ይባርክ!
Filed in: Amharic