>

ለሰሞኑ እንዲሆን ተደርጎ remix  የተደረገ የከረመ ወግ  (በእውቀቱ ስዩም)

ለሰሞኑ እንዲሆን ተደርጎ remix  የተደረገ የከረመ ወግ 

በእውቀቱ ስዩም

ጎረቤቴ ቺስታ ግብፃዊ ነው፤ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ከገነባች እንግዲህ ተስፋ የለንም ብሎ አሜሪካ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቆ በመኖር ላይ ይገኛል ! እኔ  ከወራት በፊት “ግድቡ ተሽጧል” እሚለውን  ቀደዳ  አምኜ ጥገኝነት መጠየቄን የሰማ አይመስለኝም፡:
ኑሮየ ለክፉ እሚሰጥ አይደለም፤ አውቶብስ  እነዳለሁ፤  በተረፈው ጊዜየ ዲሽ አጥባለሁ፤ የናሳውን ሳተላይት ዲሽ ማለቴ ነው፤ ግብጡ ግን መና-እጢ ደሃ ነው፤(by the way “ መናጢ ድሃ”  ማለት  በጣም ከማጣቱ የተነሳ እጢ ሳይቀር የሚቸግረው   ድሃ ማለት መሆኑን ስንቶቻቸን እናውቃለን?  )   ስላሳዘነኝ እኔ በወር ሰማንያ ዶላር እምከፍልበትን ዋይፋይ እንዲጠቀም ፓስወርዱን ሰጠሁት ፤ አንባቢ ሆይ! ለዚህ ደግነቴ ያገኘሁት ምላሽ ምን ይመስልሃል? ባለፈው መንገድ ላይ አግኝቶኝ እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ባረብኛ  “ኢንቲ አዩኒ” ብሎ ባረቀብኝ ! የዛሬ አመት  ወደ አሜሪካ ስበርር  ለትራንዚት ዱባይ አምስት ሰአት ሰለተቀመጥሁ  አረብኛ በመጠኑ እሰማለሁ፤  ምን ማለቱ መሰላችሁ : “ ፊልም ላይ ተጥደህ እየዋልክ ኔትዎርኩን ስሎው እያደረግህብኝ ነው! “ ማለቱ ነው ! እረ ገለስ! ውፈር ተበገስ  it is my Wi-Fi ‘ ብየ ቀወጥኩት!
(በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር እንዳጫወቱኝ  ግብፆች “ ጀ“ የሚል ቃል የላቸውም፤ ገማል ይላሉ እንጂ ጀማል አይሉም! ለዛ ነው” ጀለስ “ ማለት ሲገባኝ “ገለስ “ የሚለውን ቃል የተጠቀምኩኝ ! ለምሳሌ፤ ባህር ዳርቻ አሸዋ ላይ በጀርባህ  ተንጋለህ  ተኝተህ፤   ደረትህን ለጸሀይ፥ ጉያህ ላይ ያለውን ፎጣ ደግሞ  ለነፋስ  ሰጥተህ ዘና ስትል ፤ አንዲት ግብፃዊ “ገላህ ያምራል ካለችህ” ሙገሳ አይደለም፤ ሃራስመንት ነው!
 በምነዳው አውቶብስ ውስጥ እንደ ወያላ ሆኖ የሚሰራ ፈረንጅ አለ፤  ትናንት የተቃውሞ  ሰልፈኞችን ኒውዮርክ አራግፈን ስንመለስ  ያባይ ነገር ተነሳና   “ግብጻውያን በፍቅር ዘፈን ውስጥ ሳይቀር ስለ ናይል እንደሚዘፍኑ ታቃለህ?  “ አለኝ  “  አንተ በዚህ ትገረማለህ?  የእኛ ዘፋኞችማ  ግድቡ  ከመሰራቱ ሃያ አመት አስቀድሞ  ስለግድቡ  ሲዘፍኑ ኖረዋል “ ብየ መልሰኩለት  ፤ የነገርኩትን  ሰምቶ አማትቦ  ዞር ይላል ብየ ሳስብ  “እስቲ እንዱን ዝፈንልኝ  “ ብሎ አያፋጥጠኝም? ዞር ዞር ብየ አውቶብሱ ውስጥ  አበሻ አለመኖሩን ካረጋገጥኩ በሁዋላ የንዋይ ደበበን ዘፈን  ተረርር ር አደረኩለት ፤
“ገዳም የፍቅር ገ-Dam 
ልቤ አንቺን አይከ-dam”
 በነገራችን ላይ ፤ ግድቡን ትተን ስለባልቦላው ማውራት የምንጀምርበትን ጊዜ አልናፈቃችሁም?! እንደኔ እንደኔ፤ ግድቡ ስራ ሲጀምር ለአንድ አመት ያህል ህዝቡ ለመብራት መክፈል የለበትም! እንዲያውም በጊዜ መብራት አጥፍቶ የተኛ ሰው በወንጀል ቢጠየቅ ደስ ይለኛል !
የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና ግድቡ ተርባይኑን ማንቀሳቀስ ቢያቀተው ወይም ተርባይኑን ለጥቂት ቢስተውስ ? ወይ ደግሞ የግልገል ጊቤን አርአያ ተከትሎ ቢገግምስ? እኔ ጣጣ ያለው አይመስለኝም ፤  ሌላው ቢቀር ሳልመን   እናረባበታለን፤  በነገራቸን ላይ ሳለመን  የፈረንጅ ሞጃ እሚበላው  ምርጥ ያሳ አይነት ነው  ፤ በአሳ በሎች ግምገማ  እንደሀረር ሰንጋ ይቆጠራል፤   ሳልመን የበላ ትውልድ ጭንቅላቱ ይሰራል ፤  ጭንቅላቱ ከሰራ  አጥብቆ ይመራመራል፤ ኤሌክትሪክ የሚያመነጭ ኒውክልየር ይፈጥራል ፤
ይህ በአንዲህ እያለ፤  አባይ በተነሳ ቁጥር “ አባይ ማደርያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል “ የሚለው እጅ እጅ እሚል ተረት መጠቀሱ የማይቀር ነው ፤ የሆነው ሆኖ ፤ከግድቡ ሙሌት በሁዋላ ግንዱ ለማን  ይደርሳል ? ዶክተር አቢይ;-ሶስት ቦታ ተቆርጦ እንደ ቅርጫ እንካፈለው እንደማይል ተስፋ አለኝ! እዛው ግብፅ ፈልጣ ሩዝ ትቀቅልበት!
ከአበዛሁት አትፍረዱብኝ ! የአገር ፍቅር ሲበዛ  ካቲካላ ነው! አናት ላይ ይወጣል!
Filed in: Amharic