>

ግለሰቡን አፍኖ ወስዶ ያሉበትን መሰወር ትልቅ የመብት ጥሰት ነው....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ግለሰቡን አፍኖ ወስዶ ያሉበትን መሰወር ትልቅ የመብት ጥሰት ነው….!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

     ጋዜጠኛ እና ታሪክ አጥኝው ታዲዮስ ታንቱ በሌሊት በመንግስት የጸጥታ ጏይሎች ከመኖሪያ ቤታቸው በድጋሚ ተይዘው ከተወሰዱ ስምንት ቀን ቢሆናቸውም እስካሁን ታስረው የሚገኙበትን ስፍራ ቤተሰቦቻቸው ማወቅ አልቻሉም።
ግለሰቡ በሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል ፈጽመው እንኳ ቢሆን በሕግ አግባፍ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ፣ በቤተሰቦቻቸው ሊጎበኙና የሕግ ምክር አገልግሎት ማግኘት መብታቸውን በሚገፍ መልኩ ግለሰቡን ያሉበትን መሰወር ትልቅ የመብት ጥሰት ነው።
ህገ-መንግስቱንም የጣሰ ተግባር ነው። መንግስት አቶ ታዲዎስ ታንቱ ያሉበትን ሁኔታ ለቤተሰብ ሊያሳውቅ ይገባል።
 ከመኖሪያ ቤታቸው ታፍነው ወዳልታወቀ ስፍራ ከተወሰዱ አንድ ሳምንት እንደሆናቸው ለሚድያ የገለፁት ባለቤታቸው ወ/ሮ ጸጋ ሞገስ መላ ቤተሰቡ በጭንቀት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በውድቅት ሌሊት ጦር መሳሪያ በደገኑ የሲቪልና የፖሊስ አባላት ታፍነው ሲወሰዱ ያዩ ልጆቻቸው ለቀናት አድራሻቸው የት እንደሆነ በትክክል የሚነግር የመንግስት አካል ከመጥፋቱ ጋር ተያይዞ ወደ ትምህርት ገብታቸው አንሄድም እያሉኝ ተቸግሬያለሁ ብለዋል።
ወ/ሮ ጸጋ በመልዕክታቸው የሚዲያ ተቋማት በሙሉ የጋዜጠኛ ታዲዮስ ታንቱ አድራሻ አለመታወቅ ሊያሳስባቸውና የዘገባ ሽፋንም ሊሰጡ እንደሚገባ አመላክተዋል።
እየተደረገ ያለው ነገር የመንግስት ስራ ከሆነ እጅ ያሳዝናል ሲሉ ያማረሩት ወ/ሮ ጸጋ መቀየሪያ ልብስ እንኳ ሳይዝ አፍነው በመውሰድ አድራሻ በማጥፋት ቤተሰብን ለጭንቀት በመዳረጉ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ብለዋል።
ፍትህ ለጋዜጠኛ ታዲዎስ ታንቱ!
Filed in: Amharic