>

ሽብርተኛው ቡድን በአፋር ህዝባችን ላይ....?!? (መሐመድ አሊ መሐመድ )

ሽብርተኛው ቡድን በአፋር ህዝባችን ላይ….?!?

መሐመድ አሊ መሐመድ 

የትግራዩ ሽብርተኛ ቡድን፣ ወደ አፋር ክልል፣ ፈንቲ ረሱ (ዞን) ያሎ ወረዳ ዘልቆ በመግባት፣ በከባድ መሣሪያ መደብደቡ፣ እንዲሁም የአፋር ተወላጅ የሆኑ በርካታ ንፁሃን ወገኖቻችን በግፍ መጨፍጨፋቸው ተነግሯል።
 የትግራዩ አሸባሪ ቡድን፣ ከአማራ ቀጥሎ ጥርሱን የነከሰው በአፋር ላይ መሆኑ ግልፅ ነው። ይኸ ከሽግግሩ ዘመን የጀመረ ጉዳይ ነው። የአፋሩ ሃይማኖታዊና የፖለቲካ መሪ ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፈሬ “የኢትዮጵያን ባንድራ እንኳን እኛ ግመሎቻችንም ያውቋታል” በማለታቸው፣ በነመለስ ዜናዊ ጥርስ ውስጥ የገቡ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በመሆኑም ወያኔ በሱልጣኑ ልጆች (ሀንፈሬና ሀቢብ) መካከል መከፋፈል በመፍጠር በ1987 ዓ.ም ምርጫ ከጨዋታ ውጭ እንዲሆኑ አደረጋቸው።
ህወሓት በሱልጣን አሊሚራህና ልጆቻቸው የሚመራውን የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር ከጨዋታ ውጭ ካደረገ በኋላ፣ በነኢስማኤል አሊሲሮ የሚመራ አሻንጉሊት መንግሥት በማቋቋም፣ በአፋር ህዝብና ልጆቹ ላይ የፈፀመው ግፍና በደል በቀላሉ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ሥርዓቱን የተቃወሙትን ከማሳደድ ከመግደል አንስቶ፣ የቀሩትም ሥራ አጥተው እንዲንከራተቱና በችግር እንዲቆራመዱ ፈርዶባቸዋል። በዚህም ሳቢያ፣ ህይወታቸውን ያጡ በርካቶች ናቸው። እኔም በግሌ ALFን ትደግፋለህ በሚል እጅና እግሬ በሰንሰለት እየታሰረ ለስንት ጊዜ ያህል ለአማራ ከልል ፀጥታ ኃይሎች ተላልፌ እንደተሰጠሁ የአፋር ተወላጅ ወንድሞቼ ምስክሮች ናቸው። ስለሆነም የማወራው በውስጡ ስላለፍኩበት እውነት ነው።
 በዘመነ ወያኔ፣ የአፋር ህዝብ በተማሩና ብቃት ባላቸው ልጆቹ የመመራት ዕድሉ/መብቱ የተነፈገው ሲሆን፣ ክልሉ የሚመራው አማካሪ ተብለው በተቀመጡት በነተክለብርሃን፣ በኋላም ከአዲስ አበባና ከመቀሌ፣ በሪሞት ኮንትሮል ነበር ማለት ይቻላል። በዚህ ሁኔታ፣ የአፋር ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ነበረው ቢባል አጉል ስላቅ ነው የሚሆነው። በዚያ ዘመን “አጋር ፓርቲ” እየተባለ በታዛቢነት ከመቀመጥ ባለፈ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የመወሰን ዕድል/ድምፅ አልነበረውም።
በወያኔ ዘመን፣ አፋር ከፖለቲካው ይበልጥ በኢኮኖሚ ክፉኛ ተደቁሷል፤ ወይም ከኋላቀርነት ሳይላቀቅ እንዲኖር ተፈርዶበታል። እንደሚታወቀው፣ በወያኔ ዘመን፣ በትግራይ ክልል እጅግ በርካታ ፋብሪካዎች እንደአሸን ፈልተው/ተስፋፍተው ነበር። በአንፃሩ በአፋር ክልል አንድም ፋብሪካ አልነበረም። አፋር ክልል ለባህር በር ካለው ቅርበት አንፃር፣ ትላልቅ የፋብሪካ ማሽነሪዎችንና ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባት፣ እንዲሁም የፋብሪካ ምርቶችን ወደውጭ ለመላክ አመች ነው። ይሁንና አፋር ላይ ፋብሪካዎች አልተገነቡም።
እንደሚታወቀው አብዛኛው የአፋር ህዝብ አርብቶ አደር ነው፤ ይሁንና አንድም የቆዳ ውጤቶች ወይም የሥጋ ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የለም። በጥጥ ምርትም አፋር ቀዳሚ ነው። ሆኖም ግን አንድም የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የለም። ከዚህም ሌላ አፋር ክልል ከፍተኛ የጨው፣ የፖታሽና ሌሎች ማዕድናት ክምችት ያለበት ነው። ሆኖም ግን እነዚህን ማዕድናት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሉም። ይልቁንም የአፍዴራን የጨው ምርት እነማን ሲዘርፉት እንደነበር የአደባባይ ምሥጢር ነው። የአዋሽ ወንዝን በአግባቡ ብንጠቀምበት የአፋር መሬት ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን በሙሉ ሊመግብ የሚችል ነው። እነዚህን ጉዳዮች ማሰብ ከፍተኛ ቁጭት ይፈጥራል። የትግራዩ አሸባሪ ቡድን የአፋር ልጆች ማሰብ እንደሚችሉ የሚገምት አይመስልም።
አሸባሪ ቡድኑ፣ ወደፊት ከኢትዮጵያ የመገንጠል ህልሙ ቢሳካ እንኳን፣ አፋርን በቀላሉ መልቀቅ አይፈልግም። እንዳውም ከአማራ ይበልጥ አፋርን በደንብ መደቆስና አቅመ-ቢስነት እንዲሰማው ማድረግ ይፈልጋል። ወያኔ አፋርን አቅመ-ቢስ የማድረግ ስትራቴጂው ዛሬ የተጀመረና በኢትዮጵያ ደረጃ ብቻ የተገደበ አይደለም። ከ1984-85 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት፣ አፋሮች FRUD በተባለ ድርጅት ሥር ተሰባስበው በመታገል የጅቡቲን 3/4ኛ ግዛት ከተቆጣጠሩ በኋላ፣ ወያኔ በወቅቱ ከነበረው የሀሰን ጉሌድ (የጅቡቲ) መንግሥት ጋር በመተባበር አፋሮችን ዳግም እንዳይነሱ አድርጎ ደቁሷቸዋል። እኔም በዚያ ትግል ውስጥ የተወሰነ ቆይታና ተሳትፍ ስለነበረኝ ጉዳዩን በቅርብ አውቃለሁ። በኋላም በኤርትራ የሚኖሩ አፋሮች “የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብታቸው ይከበር” በሚል፣ ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤት ለማድረግ አልሞ ሲንቀሳቀስ የነበረውን አርዶፍን፣ ወያኔ በወቅቱ ከሻዕቢያ ጋር በመቀናጀት ዓላማውን አኮላሽቶበታል። የወያኔ ሴራ የአርዶፍ መሪ የነበሩትን እነመሐሞዳ ጋኣስን በጥቅም ደልሎ በማምጣት ሥልጣን እስከመስጠት ይደርሳል።
የትግራዩ አፋኝ ቡድን አፋርን የተፅዕኖ ክልሉ አድርጎ የማቆዬት ፍላጎቱ፣ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባለፈ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ (geo-political) ምክንያትም ያለው ነው። አንደኛ ነገር፣ በኢትዮጵያ – በጅቡቲና – በኤርትራ ተበታትነው የሚኖሩ አፋሮች ተሰባስበው፣ በቀይ ባህር አካባቢ አንድ ትልቅና ተፅዕኖ ፈጣሪ ማህበረሰብ እንዲፈጠር የወያኔ ፍላጎት አይደለም። ወያኔ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ደረጃ ልዕለ-ኃያል ሆኖ ለመውጣት፣ አማራን ብቻ ሳይሆን አፋርንም ጭምር በማዳከም፣ ተገዳዳሪ ኃይል መሆን እንዳይችሉ ይፈልጋል፤ ኦሮሞንም እንዲሁ። ይኸ ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት በገሀድ የታዬ ነገር/ሐቅ ነው።
ሌላው፣ ምናልባትም በዋናነት ለወያኔ ትልቅ ራስ ምታት የሚሆንበት፣ አፋሮች በኢትዮጵያዊነታቸው የሚኮሩና የማይደራደሩ መሆናቸው ነው። ኢትዮጵያዊነታቸውን በሙሉ ልብ የማይቀበሉት የወያኔ ሰዎች፣ በአፋሮች ፊት ትንሽነት ይሰማቸዋል። አፋሮች በኢትዮጵያዊነታቸው ከመኩራት ባለፈ፣ ለሀገራቸው ዳር-ድንበርና ሉኣላዊነት ጋሻና መከታ ሆነው የመቆየታቸው ጉዳይ ረጅም ታሪካዊ ዳራ (historical background) ያለው ነው። በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች፣ የውጭ ኃይላት በአፋር በኩል ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረጓቸውን ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማክሸፍ፣ አፋሮች በቀላሉ የማይታለፍ የብረት አጥር መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለአብነትም ሙዚንገር በተሰኘ አውሮፓዊ ቅጥረኛ ጄኔራል እየተመራ የመጣውን ወራሪ ኃይል፣ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ በመጨፍጨፍ የማረኩት ዘመናዊ መድፍ ዛሬም ድረስ ጊፉ ተራራ ላይ የታሪክ ምስክርነቱን እየሰጠ ይገኛል። ይሁንና አሸባሪው ቡድን ለአፋር ህዝብ፣ በቁመናው ልክ የሚገባውን ዕውቅና እና ክብር አይሰጥም። ይልቁንም ወደመሐል አገር (ተመልሶ አራት ኪሉ ለመግባት) እንደመረማመጃ በመቁጠር፣ አፋርን በቀላሉ ረምርሞት ለማለፍ ይፈልጋል። ለዚህም ነው፣ አሁን ላይ የአፋር ህዝብ፣ በአሸባሪ ቡድኑ መጠነ-ሰፊ ውጊያ የተከፈተበት።
ወገኖቼ፣ ኑ ከአፋር ህዝባችን ጎን በፅናት እንቁም!!
አፋር የአሸባሪዎች መቀበሪያ እንጅ፣ ከቶም መረማመጃ አይሆንም!!!
Filed in: Amharic