>

"ጊዜያዊ አስተዳደሩ  ከህወሓት  ጋር ግንኙነት ስለነበረው ነው በትግራይ ለውጥ ያልመጣው....!!!" ( አቶ መኮንን ዘለሌ (የትዴፓ መስራች)

“ጊዜያዊ አስተዳደሩ  ከህወሓት  ጋር ግንኙነት ስለነበረው ነው በትግራይ ለውጥ ያልመጣው….!!!” 
           
            አቶ መኮንን ዘለሌ (የትዴፓ መስራች)

መከላከያው ትግራይ ክልል ከገባ ጀምሮ የነበረው ትልቁ ድክመት ህወሓትን ደመሰስኩኝ ይበል እንጂ የህወሓት ኔት ወርክ(መዋቅር) ፍጹም አልተነካም ነበር፡፡ ህወሓት በትግራይ ከታች እስከላይ ድረስ ጠንካራ ኔትዎርክ በተቋም ደረጃ እና በህዝቡ ውስጥ ፈጥሯል፡፡ ድርጀቱ በጣም ተፈሪነቱ ከባድ ነው፡፡ ይሄንን የሚያውቁ እንደ ትዴፖ አይነት የፖለቲካ ድርጅቶችን ሳያካትት መንግስት ብቻዬን እወጣዋለሁ ብሎ ነው የገባው፡፡ በአንድ በኩል ወታደራዊ ሚሽኑን አሳክቷል፤ ነገር ግን ወታደራዊ ሚሽንን ማሳካት ብቻውን በትግራይ ክልል ዘላቂ መፍትሔ አላመጣም፤ የህወሃት ስር አልተነቀለም፡፡
ህዝቡ ከብልጽግና ውጪ ሌሎች አማራጭ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንዲመለከት ዕድሉ አለተሰጠውም፡፡ ለትግራይ ህዝብ ለ30 እና ለ40 ዓመት የታገሉ፣ ያለቀሱ፣ ህዝቡ የሚወዳቸው ግለሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ትግራይን ከህወሃት ነጻ በማውጣት ዘመቻ ላይ አልተካፈሉም፤ ዝም ብሎ ወታደራዊ ሚሽን ላይ ብቻ ነው ትኩረት የተሰጠው፤ አባራሪና ተባራሪ ነው የሆኑት፡፡
ህዝብ ላይ ትኩረት አልተሰጠም፡፡ የህወሃት ኔት ዎርክ አልተበጣጠሰም፡፡ ወደ ትግራይ የሄደው ዕርዳታ ሁሉ  ህወሃት ነው የወሰደው፡፡ እርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ራሳቸው በህወሃት ተገድለዋል፤ ሌሎችም ታፍነው ተወስደዋል፡፡ ለህዝቡ የሚያስብ ድርጀት ቢሆን ለህዝብ የሚመጣውን እርዳታ ለራሱ መጠቀሚያ አያደርግም ነበር፡፡ ነገር ግን ህወሃት ከመጀመሪያው ጀምሮ ጸረ ህዝብ በመሆኑ ይሄንን መፈጸሙ አዲስ አይደለም፡፡ እኛ ደጋግመን አስጠንቅቀን ነበር፡፡ መንግስት ባስቀመጣቸው የትግራይ ብልጽግና አመራሮች ውስጥ ህወሃት ኔትዎርክ ነበረው፤ አዳዲስ የተሾሙ የፖሊስ ሰራዊት አባላት ውስጥም ኔትዎርክ ስለነበረው እንደልቡ ያሽከረክራቸው ነበር፡፡ መንግስት በክልሉ ያለውን የህወሃት ጠንካራ ኔትዎርክ ካለማወቅ ነው ይሄ ሁሉ ችግር የመጣው እላለለሁ፡፡
አመራሩ ቀድሞ ባይገባም፤ ካቢኔው፣ካድሬው እና የህወሃት ወታደሮች ጥይት እየተኮሱ ነው መቀሌ የገቡት፡፡ ስለዚህ መጀመሪውኑ ያለተበጣጠሰው የህወሃት ኔትዎርክ ስለነበረ ነው ተመለሶ የተደራጀው፡፡ ህወሓት ኔትዎርክ በመዘርጋት በጣም የተካነ ነው፡፡ እንኳን አሁንና ድሮ ጫካ እያለም የደርግ አመራሮችን ሳይቀር ኔትዎርክ ውስጥ አስገብቶ ነበር ደርግን ሲሰልል እና መረጃ ሲዘርፍ የነበረው፡፡ በደርግ ጊዜ  ትግራይ ክልልን ያስተዳድሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች አመራሮችን ሁሉ በራሱ የስለላ መረብ ውስጥ አስገብቶ የደርግን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሚስጢር እንዳሻው ሲጠቀም ነበር፡፡ ደርግ የተሽመደመደው ህወሃት በውስጥ ሰርጎ በመግባት ባደረሰበት ወታደራዊ የመረጃ ዘረፋ ነበር፡፡ አሁንም በትግራይ ክልል የተመሰረተውን ብልጽግና በተመሳሳይ መረጃ መረባቸው ጠልፈው ቀን ከሌት ቁም ስቅል ሲያሳዩት መከላከያው የጥቃት ሰለባ ለመሆን ቻለ፤ በዚህን ጊዜ መንግስት በትግራይ ክልል ተጨማሪ ጊዜ ቢቆይ ከዚህ በላይ በመከላከያው ላይ ጉዳት ማስከተል መሆኑን ስለተገነዘበ ለቆ መውጣቱ አግባብ ነው፡፡
ህወሃት በወታደራዊ መንገድ ከተሸነፈ በኋላ በትግራይ ያለው ሁሉም የብልጽግና አመራር መገምገም ነበረበት፡፡ የፖሊስ ሰራዊቱም፣ የደህንነት ቢሮውም እና ሌሎች የአስተዳደር አካላት እንደየደረጃቸው ከህወሃት ኔትዎርክ ነጻ ስለመሆናቸወ መገምገም ነበረባቸው፡፡ አስር ሺህ የሚጠጉ ሰራዊቶችን አሰልጥነናል ብለው አስታጠቀው ነበር፤ ነገር ግን ትጥቁን እንደያዘ ነው ወደ ህወሃት የተቀላቀሉት፡፡
   ስለዚህ ችግሩ የትግራይ ህዝብ ጋር ሳይሆን፣ ህወሃት ከተወገደ በኋላ ያልተበጣጠሰው የህወሃት ኔትዎርክ ስለነበረ ነው ተመልሶ የተቋቋመው፡፡ ስለዚህ ቀድሞውንም ህወሃትን ይደግፉ የነበሩ ሀይሎች በተለያየ የመንግስት አመራር ውስጥ ስለነበሩ ለመግስት በጣም እንቅፋት ሆነዋል፡፡
የትግራይ ህዝብ እኮ ህወሃት እንዲታተቁ የሰጣቸውን መሳሪያ የመንግስት ጦር ትግራይን ከተቆጣጠረ በኋላ የተሰጣቸውን መሳሪያ ለመንግስት አስረክበው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን በትግራይ ዘላቂ ሰላም መፈጠር ያለመቻሉ እና የህወሃት ኔትዎርክ አለመበጣጠሱ የተጠበቀውን ሰላም ሊያስገንኝ አልቻለም፡፡ አዲስ የተሾሙትን ፖሊሶች መልሶ ለራሱ ዓላማ ይጠቀማቸው ነበር፡፡ የአስተዳደር ሃላፊ የነበሩትን ሳይቀር በመረባቸው ውስጥ አስገብተዋቸዋል፡፡ መንግስት ከትግራይ ክልል ከተቆጣጠራቸው ቦታዎች ውስጥ በአንድ ወረዳ ላይ እንኳን ከህወሃት የተሻለ መሆኑን የሚያመላክት አስተዳደር ማሳየት አልቻለም፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ከማላውቀው መልአክ የማውቀው ሰይጣን ይሻለኛል ብሎ በሰይጣኑ ህወሃት መመራትን መረጠ፡፡ ይህም ወዶ ሳይሆን ተገዶ ነው፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ብልጽግና ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ቀውስ መባባስ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ያለመረጋጋትና ሌሎች ተደራራቢ ቀውሶች በመበራከታቸው ህዝቡ ህወሃትን መናቀፉ አያስገርምም፡፡ ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩም በፖለቲካና በዲፕሎማሲ መሸነፋቸውን ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚደረገውን የመብራት፣ የኔትዎርክና  እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች መቋረጣቸውን ተገቢ ነው አልልም፤ ምክምያቱም ህወሃት የአብይ መንግስት ነው ይሄንን  ያደረገብህ ዕያለ ህዋሀት ራሱን ተወዳጅ በማድረግ  መንግስትን የትግራይ ጠላት እንደሆነ  እንዲረዳ ዕድል እየሰጠ ነው፡፡  ህወሃት ብዙ ነገር ሊያደናግር ይችላል፤ በትግራይ ክልል የደረሰውን ችግር ሁሉ ለዓለም አሳስቶ እያቀረበው ነው፡፡ ድርጅቱ በውሸት የተካነ ድረጅት ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግስት ህወሃት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያቀርባቸውን ቅሬታዎችና ክሶች አንድ በአንድ እየተከታተለ እውነታውን ለዓለም ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡
 ከዚህ ሌላ በህወሃት ጦስ ህዝቡ መጎዳት ስለሌለበት ህዝቡ በሰበዓዊ ድጋፍና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን የሚያጣበት ሁኔታ መኖር የለበትም እላላሁ፡፡ የትግራይ ህዝብና ህወሃት አንድ ስላልሆነ መንግስት ቆም ብሎ በማሰብ ህዝቡ ድጋፍ የሚያገኝበትን መንገድ መፍጠር አለበት እላለሁ፡፡ በተለይም የህወሃት ቀንደኛ ጠላት ከሆነውና የህወሃትን ባህሪ ከማንም በላይ ከሚያውቀው ከትዴፓ ጋር መንግስት በጋራ በመስራት በክልሉ ያለው ችግር በዘላቂነት መፍታት ይቻላል፡
Filed in: Amharic