>
5:26 pm - Thursday September 17, 3429

አይከፈልበትም! አይገበርበትም! ከፍቃደኝነት በቀር የሚጠይቀው ዋጋ የለም! (አሳፍ ሀይሉ)

አይከፈልበትም! አይገበርበትም! ከፍቃደኝነት በቀር የሚጠይቀው ዋጋ የለም! 

አሳፍ ሀይሉ

 

አሁንም ለመነጋገር አልረፈደም!
የወልቃይትና ራያ መሬቶች የትግራይ መሬቶች አይደሉም፡፡ ይህን እውነት የህወሃት ሽማግሌዎችም አሳምረው ያውቃሉ፡፡ በዚህን ያክል ደረጃ ድርቅ ብሎ የኛ መሬት ነው ብሎ የዜጋን ደም ለማፍሰስ መቁረጥ የጤንነት አይደለም፡፡ ይህ ሲባል ግን አካባቢዎቹ የትግራይም መሬት ባይሆኑ የአማራ ሀይል በጉልበት ቦታዎቹን መቆጣጠር ነበረበት ወይ? የሚለው ጥያቄም አብሮ መነሳት አለበት፡፡ እዚህ ላይ በህወሃት ይዞታ ሥር ያለን አካባቢ በሀይል ማስለቀቅ ሁከት እንደ መፍጠር ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም አግባብ ያለው አካሄድ አልነበረም፡፡
ሆኖም የአማራ ሀይል ከመሬት ተነስቶ በራሱ ተነሳሽነት አይደለም አካባቢዎቹን የያዘው፡፡ የትግራይ ሀይል ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር ጦርነት ሲገጥም፣ ‹‹ህጋዊ›› ለሆነው የማዕከላዊው መንግሥት በማገዝ ነው ወደ ጦርነቱ የገባው፡፡ የትግራይ ሀይል ወደ አማራ ክልል ገብቶ ወሮናል የሚልም ክስ አለ፡፡ እርሱ ወደፊት የሚጣራ ይሆናል፡፡
ስለሆነም አሁን የወልቃይትና ራያን ግዛቶች በተመለከተ ሁለት ነጥቦች ከፊታችን እናገኛለን፡፡ አንደኛ መሬቱ የትግራይ መሬት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ህወሃት ከሁለት አሰርት ዓመታት በፊት በጉልበት ወደ ትግራይ ያካለላቸው ግዛቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ አካባቢዎቹ የትግራይ ግዛት አይደሉም፡፡ ይህ አንድ እውነት አለ፡፡ ሁለተኛው እውነት ደግሞ (ከላይ እንደገለጽኩት) አካባቢዎቹ በህወሃት በጉልበት የተነጠቁ ቢሆኑም፣ የአማራ ሀይል አካባቢዎቹን የያዘበት መንገድ ግን ህጋዊ አካሄድን የተከተለ አይደለም፡፡ እሺ ምን ይደረግ? ነው ቀጣዩ ጥያቄ፡፡
አንደኛ ሁለቱ ወገኖች አሁን በያሉበት ቦታ ላይ ሆነው፣ ተኩስ የማቆም ስምምነት በማውረድ፣ እርስ በእርስ ይነጋገሩ፡፡ ለመስማማት ይሞክሩ፡፡ ሁለቱ ወገኖች በስምምነት ቃሎቻቸው ላይ ሙሉ እምነት እንዲኖራቸው ሶስተኛ ወገን አረጋጋጭ ዋሶች በመካከላቸው ይቀመጡ፡፡ ከማዕከላዊው መንግሥትም፣ ከክልልም ወይም ከውጭ ሀያላን ሀገራት ወይም ደግሞ ከአስማሚ ዓለማቀፍ ተቋማት (ኢጋድ፣ አፍሪካ ህብረት፣ ተመድ፣ ወይም ሌላ ለጊዜው የሚቋቋም የሠላምና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ሊሆን ይችላል)፡፡
ሁለቱ መካከል የቀጥታ ፊት ለፊት ውይይትም ሆነ ስምምነት ማድረግ ካልተቻለስ? ያለው አማራጭ ሌላ በሁለቱም የሚታመን ሶስተኛ ወገን አደራዳሪ ያስቀምጡ፡፡ በእኔ ግምት በሁለቱም ወገኖች እምነት ሊጣልባት የምትችል ሀገር ቻይና ትመስለኛለች፡፡ ቻይና ልታደራድራቸው ትችላለች፡፡
በዚህ ረገድ የአሜሪካ አቋም በሁለቱም ወገኖች እምነት ሊጣልበት የሚችል ስላልመሰለኝ፣ የአውሮፓ ህብረት በጀርመንና ፈረንሳይ አማካይነት አደራዳሪ ሆኖ መቅረብ የችላል፡፡ ሌሎችም ሀገሮች አደራዳሪ ሆነው ሁለቱን ወገኖች ወደ ስምምነት እንዲያመጡ ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ የውጪ ሀይል መጋበዝ የሚያስፈልግበት ምክንያት ማዕከላዊው መንግሥት ራሱ በአሁኑ ሰዓት ከህወሃት ሀይል ጋር በጠላትነት የቆመ ሀይል ስለሆነና ገለልተኛ አደራዳሪና አስማሚ ለመሆን በሁለቱም ወገኖች እምነት እንደማይጣልበት ግልጽ ስለሆነ ነው፡፡
እውነት ላይ ተመስርቶ ስምምነት ይደረጋል፡፡ ስምምነቱ በሁለቱም ወገኖች ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ በቀጣይ ደግሞ በፌዴራል (በማዕከላዊው) መንግሥትና በህወሃት መካከል አሸባሪና ጠላት የሚባሉ ፍረጃዎች ቀርተው – በአንድ ሀገር ጥላ ሥር – ሊሆን ስለሚችለውና አዋጭ የሆነ ሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚ ሊያደረግ የሚችል – ሌላ ተመሳሳይ የሰላምና ድርድር ሂደት ጊዜውን ጠብቆ ይጀመራል፡፡
አጠቃላይ ውጤቱ ይህን ያህል የሚያስፈራ ነው ወይ? በጭራሽ! ወልቃይት ከህወሃት አስተዳደር ስር ወጥቶ፣ በብአዴን (በአማራ ብልጽግና) ሥር ተዳደረና ምን ተዓምር ይፈጠራል? መሬቱ ተነቅሎ ወደ ማርስ ይሰወራል? ወይ ሌላ የሚፈጠር ተዓምር አለ? መቼ ነው የወልቃይት ሁመራ ፕሮጀክቶች በትግራይ ክልል ወጪ ተካሂደው የሚያውቁት? ሁሉ ልማቶች ሲከናወኑ የኖሩት በፌዴራል መንግሥቱ በጀት አይደለም ወይ? እና አማራ አስተዳደራቸው፣ ትግሬ አስተዳደራቸው፣ ምን እንዳይመጣ ተፈርቶ ነው?
በበኩሌ በእነዚህ ግዛቶች ላይ የአስተዳዳሪ ፓርቲ መቀያየርን እንደ ትልቅ የሀገርና የድንበር ጉዳይ አድርጎ – የሞት ሽረት ጉዳይ አስመስሎ – የሀገር መደፈር ጉዳይ አሳክሎ – እያጋነኑና የህልውና ጉዳይ እያደረጉ ማቅረብ ሃላፊነት የጎደለው አካሄድና ዜጋን ከዜጋ ደም የሚያፋስስ፣ የእርስ በእርስ ግጭትንም የሚቀሰቅስ ይመስለኛል፡፡
የግዛቶቹን አስተዳደር አስመልክቶ በእውነት ላይ የተመሰረተና፣ በአስማሚዎች ሙሉ በሙሉ ስለመከበሩ ማረጋገጫ ዋስትና የተገባለት የሁለትዮሽ ስምምነት ከተከናወነ በኋላ እኮ፣ እነዚህ አካባቢዎች በሌላም መልኩ ሊተዳደሩም የሚችሉበት ዕድል እንደሚኖር ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
ለመሆኑ ማነው አካባቢዎቹ ለዘለዓለም በህወሃት ወይም በብአዴን ቁጥጥር ሥር ይውላሉ ያለው? ማነው ትግራይ የምትባል ክልል ዘለዓለማዊ ናት ያለው? ትግራይ ክልል አጋመ፣ ኢሮብ፣ እንደርታ፣ ተንቤን፣ ራያ፣ ወልቃይት ተብላ የማትከፋፈልበት ምክንያት ምንድነው ወደፊት ለህዝቡ ልማት፣ ለሀገር እድገትና ለአስተዳደር አመቺና አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ? የአማራ ክልልስ አደረጃጀት ዘለዓለማዊ ነው ያለው ማነው? ለእነዚህ ሁሉ ግቦች አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ወደፊት ወልቃይት፣ ጎንደር፣ ራያ፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ፣ አዊ፣ ቅማንት እየተባለ የማይከፋፈልበት ምክንያት ምንድነው?
(በነገራችን ላይ የሌሎቹስ ክልሎች፣ የሌላውስ የኢትዮጵያ ግዛት አስተዳደራዊ አደረጃጀትና ክልላዊ መዋቅር ዘለዓለማዊ ነው፣ ወደፊት በምንም ተዓምር አይቀየርም ያለው ማነው?) – እንዲህማ ይህን ያህል ሰዎች ተስማምተው አመቺ ሆኖ ሲያገኙት በጋራ ውይይትና በመልካም ፈቃደኝነት የሚቀይሩትን ጉዳይ – በመጽሐፍ ቅዱስ ወይ በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ እንደሰፈረ ቃል ዘለዓለም እንደማይለወጥ አድርጎ ማመን የለየለት የዋህነትና ጽንፈኝነትም ነው፡፡
ስለሆነም ነገሮችን በረድ አድርጎ፣ እና ሰከን ብሎ ወደ ድርድር ሃሳብ መምጣት፣ የጦዙ ነገሮችን ማለዘብ፣ ለመግደልና ለመሞት የቆረጡ ስሜቶችን ማርገብ፣ እና እኔ ነኝ ጀግና፣ የለም እኔ ነኝ ከሚሉ የክፋት ውድድሮችና ውርርዶች መቆጠብ እጅግ የሚመከር ወቅታዊ ሰብዓዊ የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ ከማናቸውም አካል አመራሮች በእጅጉ የሚፈለግና የሚጠበቅ ስክነትና መርህም ነው፡፡
መርሃችን የእኔ የምንለውን ዜጋ በማናቸውም የኢትዮጵያ ግዛቶች የዜግነት ሰብዓዊ መብቶቹና ጥቅሞቹ፣ ስነልቦናውና ምኞቱ ተጠብቆና ተከብሮ የሚኖርበትን ሀገርና አስተዳደር መፍጠር ላይ ያነጣጠረ ሊሆን ይገባል፡፡ እንጂ ህወሃት እኔ ካላስተዳደርኩት ሞቼ እገኛለሁ፣ የለም ህወሃት ከሚያስተዳድረው ዛሬውኑ መሬት ተከፍታ ትዋጠኝ የሚሉ ግልብ ድርቅናዎች ወደጎን መባል ያለባቸው ጊዜ ከመቼውም በላይ አሁን እና አሁን ነው፡፡
በነገራችን ላይ እንደ አንድ በአንድ ሀገር ጥላና ዜግነት ሥር አብሮ እንደሚኖር ወገን፣ እና ክፉም በጎም አብሮ እንዳሳለፈ የአንድ ሀገር ልጆች – በአሁኑ ሰዓት ይሄ ሁሉ የየክልሉ ተዋጊ ሀይል (እና የማዕከላዊውን መንግሥት ጨምሮ) በአንድ በትግራይ (በህወሃት) ሀይል ላይ ለመዝመት ከያቅጣጫው ሲተም ስናይ እኮ – ሊዘገንነንና ሊያሳስበን ይገባል፡፡
አንዳንዴ ለሁሉም ነገር እኮ ልክ አለው፡፡ ትግራዮቹ በምንም አመኑ በምንም፣ ማንንም ተቀበሉ ማንንም መረጡ፣ ወገን አይደሉም ወይ? እንደ እኛው እኩል ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው እኩል ባለመብት ዜጎች አይደሉም ወይ? ግፍ የሚባል ነገርም እኮ አለ፡፡ ዝም ብሎ ባንድ ሀይል ላይ ሁሉም ሀይል ሲረባረብ፣ ተዉ፣ እስቲ በሌላ መልኩ ነገሩን ለማብረድ፣ ለማለሳለስ እንሞክር አይባልም ወይ?
በበኩሌ ይሄ ጠላት መጣ፣ ወራሪ መጣ፣ እገሌ ትስዕር፣ እገሌ ተደመሰሰ፣ እገሌ ጀግና፣ እገሌ ምናምን ከምንለው የእልህና ተያይዞ-ገደል የደም ጨዋታችን አሁኑኑ ወጥተን፣ ምራቅ ወደዋጠ፣ የፈጣሪን መንገድ ወደተከተለ፣ አብሮነታችንን ግምት ውስጥ ወዳስገባ፣ ኢትዮጵያዊነታችንን ወዳስቀደመ፣ ወገንነታችንን ወደማይሽር አስቸኳይ የውይይት፣ የንግግር፣ የድርድርና፣ እንደተባለውም ግን ከልብ የሆነ ‹‹የጽሞና›› ጊዜን በመካከላችን ማስፈን ይገባናል፡፡
ለዚህ በተለይ ህወሃት የሚያስቀምጣቸውን ቅድመሁኔታዎች ቢያስብባቸው መልካም ነው፡፡ ቅድመ-ሁኔታ አስቀመጥክ አላስቀመጥክ፣ ማንኛውም የትግሬ ልጅ ነገና ከነገ ወዲያ በመላዋ ኢትዮጵያ ተዘዋውሮ ከወገኑ ጋር በነጻነትና በፍቅር እንደሚኖር መርሳት አይገባም፡፡ በገዛ ሀገሩ፣ እና የገዛ ወገኑን እንደማይታመን ክፉ የውጪ ጠላት አድርጎ በትውልዳችን ጭንቅላት የምንቀሰቅሰውንና የምናኖረውን ነገራችንን አሁኑኑ አቁመን፣ ከቅድመ-ሁኔታዎች ወጥተን፣ ህዝቦቻችን በሁሉም አካባቢዎች በሠላምና መብታቸው ተጠብቆ፣ በማንኛውም የሚበጃቸው አካል ተዳድረው፣ ለጊዜው እፎይ እንዲሉ፣ እና ሁሉም በየቤቱ ፈጣሪውን አመስግኖ በሠላም የሚያድርበትን ሁኔታ ብንፈጥር – ምን ይመስላችኋል?
ይህን ማድረግ የሚያስወጣ ወጪ የለው! ሰባራ ሳንቲም አያስከፍልም! የሚገበርበት ነፍስ የለ! የሚፈስበት ደም የለ! ደግሞ በተቃቃረ ወገን መሀል የሚደረግ ንግግር ለመጀመር የቱን ያህል እንደ ሰማይ ርቆና እንደ እንቆቆ መርሮ ቢታሰብ፣ አንዴ ሲጀመር ግን የውሃ መንገድ ነው፡፡ የሚያስፈልገው ነገር ደፍሮ የንግግርን መንገድ መጀመር ብቻ ነው! የሚያስፈልገው ነገር ፈቃደኝነት እና ፈቃደኝነት ብቻ ነው!
አፈሙዝ ያነሳችሁ በሁሉም ጎራ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሆይ፡- ስለ ሀገርና ስለወገን፣ ስለ ልጆቻችንና ስለ ወደፊቱ ትውልድ፣ ስለ ፈጣሪ አምላክ፣ ስለተጨነቁት እናቶቻችን ብላችሁ እባካችሁ ይህን የሠላምና የንግግር መንገድ ምረጡ! ጦርነትን፣ ገድሎ መሞትን፣ ባሩድንና እሳትን ሳትፈሩ፣ እንዴት በአምላክ አምሳል የተፈጠረን ቃልን፣ ንግግርን፣ ሰላምን፣ ውይይትን እንዲህ ከጦርነት አብልጣችሁ ትፈሩታላችሁ? ነውር አይደለም ወይ?
ይሄ ቀንስ ያልፍ ያለም ወይ? ገና ስንት ዘመን አብረን እንኖር የለም ወይ? ዓለም ሁሉ ነገ ትጠፋለች የተባለ ይመስል ይሄን ያህል ለብቻ ለመኖር መጋደል ምንድነው? እባካችሁ ለሠላም ድፈሩ! ለንግግር ድፈሩ! ለውይይት ድፈሩ! አብሮ ለመኖር ድፈሩ! ፈቃደኛ ለመሆን ድፈሩ! ግድ የላችሁም ትሩፋቱ የሁላችንም ነው! ግድ የላችሁም ታሪክ ሲያመሰግናችሁ ይኖራል እንጂ አትወቀሱበትም!
ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ ይባርክ፡፡ ለሠላም፣ ለንግግር፣ ለስምምነት፣ ለውይይት፣ ለቃል፣ ለህይወት ያጋደለ ልቦናን ይስጠን! የፈቃድ ድፍረትን ይስጠን! ሰብዓዊውን መንገድ ይምራን ፈጣሪ አምላካችን!
በትዕግሥት ያነበባችሁ ወዳጆች በፈጣሪ ስም አመሰግናለሁ፡፡ መልዕክቱን ለሌሎች የምታጋሩ ወዳጆቸም ካላችሁ በያላችሁበት ፈጣሪ ሠላማችሁን ያብዛላችሁ! ለሁላችሁም ዕድሜ ይስጥልኝ፡፡
Filed in: Amharic