>
5:18 pm - Friday June 15, 5381

ነገረ ግትራን ....!!! (ዘካርያስ ሞሀመድ)

ነገረ ግትራን ….!!!

ዘካርያስ ሞሀመድ

… ለ27 ዓመታት በብቸኝነት ኢትዮጵያን የገዛው ኢሕአዴግ – ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው – መሸነፍን ከነውር የሚቆጥር #ግትር ነበር፡፡ … እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ በሀገር ውስጥ ፖለቲካ ኢሕአዴግ ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን ጋር ተደራድሮ፣ ተለማጭነት (Flexibility) አሳይቶ አያውቅም፡፡ ተለማጭ የኾነ መስሎ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር አንዳች ስምምነት ከተፈራረመም፣ ስምምነቱ ውስጥ ብልጠት የተሞላባት እርሱን “አሸናፊ” የሚያደርግ አንቀጽ መግባቱን አረጋግጦ ነው፡፡ …
… ለ27 ዓመታት ሀገሪቱን በብቸኝነት የገዛው አንድዬው ግትር በ2010 ሲሰነጠቅ፣ በእኔ ዕይታ፣ ከግትሩ ኢሕአዴግ ማኅፀን #ሁለት_ግትራን ተፈጥረዋል፡፡ … ኢሕአዴግ ለሁለት ተሰንጥቆ ሕወሓት ወደዳር ከተገፋ በኋላ፣ በሕወሓት እና በብልጽግና ፓርቲ መካከል የተፈጠረው ችግር እየለዘበ ከመሄድ ይልቅ፣ ዕለት በዕለት እየከረረ ሄዶ ጡዘት ላይ የደረሰው፣ ፍጥጫውን የሚያጋግሉ ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች መኖራቸው እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ፍትጊያው በኢሕአዴግ ግትር ባህርይ ተኮትኩተው ባደጉና ባህርይውን በወረሱ ግትራን መካከል በመኾኑ ነው፡፡ …
የኢሕአዴግ ልጆች ሆይ! …
በአሁኑ ወቅት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኘው ዘንድ አጥብቆ የሚመኘውን ሰላም እውን ልታደርጉለት አልቻላችሁም። እንደ ኢሕአዴግ ለ28 ዓመታት የእናንተ ተገዢ ኾነን እናውቃችኋለን። እንደ ኢሕአዴግ በአንድ ግንባር ስር ኾናችሁ ኢትዮጵያን ባስተዳደራችሁባቸው 27 ዓመታት፣ በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት ስር እንዲሰድድ አንዳችም ልባዊ ጥረት አድርጋችሁ አታውቁም። ከልብ ለሚሻው፣ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት 27 ዓመታት ብዙ ነው። ነገር ግን፣ በ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመናችሁ፣ አንድ ጠንካራ የፖለቲካ ኃይል እንኳ በሁለት እግሩ እንዲቆም ዕድል አልሰጣችሁም። ወግ አጥባቂም ይሁን ለዘብተኛ፣ አክራሪም ይሁን ጽንፈኛ፣ በአቋምና በአስተሳሰቡ ከእናንተ ተቃራኒ የቆመውን ሁሉ እንደ ጠላት ስታዩ ነው የኖራችሁት። ተቃዋሚን እንደጠላት ስለታምዩም፣ የብዙኃን ፓርቲ ሥርዓት አለ ለማስባል ያህል፣ ከመኖር በማይቆጠር ቁመና እንዲኖር እንጂ፣ የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት በነጻነት ተንቀሳቅሶ፣ ሕዝብን አስተባብሮ የመንግሥት ኃላፊነትን ለመረከብ የሚያስችል አቅም እንዲገነባ ለአንድም የፖለቲካ ፓርቲ አልፈቀዳችሁም። የርዕዮተ ዓለምም ይሁን የማስገደጃ ተቋማትን በግልጽና በስውር ተቆጣጥራችሁ ለ27 ዓመታት በነጻ ውድድር ከመሸነፍ ጋር ትውውቅና ተሞክሮ እንኳ ሳታዳብሩ፣ ከጥሬ ኢሕአዴግነት አንዲትም ሳትቀየሩ ነበር የ2007ቱ የኦሮሚያ ሕዝባዊ አመጽ የተቀሰቀሰባችሁ።
ለ27 ዓመታት በአንድ ግንባር አባላትነት፣ በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓት የሚያድግበትን ዕድል በተባበረ ክንድ ስትደቁሱ፣ የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት የማየት ተስፋችንን ስትኮረኩሙ እንዳልኖራችሁ፣ በ2007 የተቀሰቀሰው አመጽ እንዳመረረ ሲገባችሁ ከ27 ዓመቱ ኢሕአዴጋዊ የፖለቲካ ነውር እንደ ጲላጦስ እጃችሁን ታጥባችሁ፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ኃጢኣቶችን በሙሉ ለሕወሓት አሸክማችሁ ራሳችሁን “የለውጥ ኃይል” ካባ አልብሳችሁ፣ ድኅረ-ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ጉዞን፣ ከፊት ኾኖ ለመምራት ተጋችሁ። … ለውጥ የጠማው ሕዝብም አመናችሁ፡፡ …
ነገር ግን፣ ኮትኩቶ ያሳደጋችሁ ኢሕአዴግ ያወረሳችሁ አንድ ቁልፍ ባህርይ ዛሬም አልለቀቃችሁም። ዛሬም፣ ከግትርነት ባህሪያችሁ አልተላቀቃችሁም። “ሁልጊዜም እኛ ብቻ ነን ትክክል” የሚል ባህሪያችሁ ዛሬም ሕያው ነው። ተቃዋሚያችሁን እንደ ጠላት የማየት ባህሪያችሁ ዛሬም ሕያው ነው። ላለመሸነፍ የፍትኅ ተቋማትን የፖለቲካዊ ዓላማ መሣርያ አድርጎ ከመጠቀም ኢሕአዴጋዊ በሽታችሁም ቢኾን አልዳናችሁም። ምን እያልሁ እንደኾነ በትክክል ትረዱታላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢሕአዴግነት ዘመናችሁ ለ27 ዓመታት የሠራችሁበትን በደል ይቅር ያለው፣ የትናንት ቁስልን ከማከክ ይልቅ፣ የተሻለ ነገን ተስፋ ባደረገ ንፁኅ የይቅር ባይነት መንፈስ ነው፡፡… በዚህ የይቅር ባይነት መንፈስ የተጀመረው የፖለቲካ ሽግግር፣ እውነተኛ የፖለቲካ ሽግግር ይኾን ዘንድ፣ ከሀገር ውስጥም ኾነ ከባህር ማዶ አያሌ የሀገሪቱ ምሁራን መንግሥትን በእውቀታቸውና በልምዳቸው ለማገዝ ፍፁም ዝግጁነታቸውን አሳይተዋል፡፡ አሁን ግን ብዙዎቹ፣ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ተስፋ እየቆረጡ ነው፡፡ … ለዚህ አባባሌ፣ አንድ ምሳሌ ልስጥና ጽሑፌን ልጨርስ፡፡ …
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ከወጣ በኋላ፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በተቆጣጠራቸው የምዕራብ ትግራይ ወረዳዎች ሳቢያ፣ በሁለቱ ክልሎች መካከል ጦርነት ሊነሳ የሚችልበት ሁኔታ እንደተፈጠረ፣ አንድ ጋዜጠኛ የሥራ ባልደረባዬ፣ ባሕር ማዶ ለሚገኙ በሰላምና እርቅ ሥራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የካበተ ልምድ ላላቸው ኢትዮጵያዊ ምሁር የሚከተለውን አጭር መልዕክት ሰደደላቸው፡
“ጤና ይስጥልኝ፣ ፕሮፌሰር _______________።
የሀገራችን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ በመሄድ ላይ ነዉ። “እገሌ” እና “እገሌ” ጦርነት ለመግጠም አፋፍ ላይ ደርሰዋል። ስለ ሰላማዊ መፍትኄ የሚያወራ ጠፍቶአል። ሀገሪቱ እንደ እርስዎ ያሉ ምሁራንን ሐሳብ በእጅጉ ትፈልጋለች፡፡ እባክዎትን ጊዜዉ ሳይረፍድ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉባቸው መንገዶች ካሉ ሐሳብዎን ያጋሩን፡፡”
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ እኒህ ምሁር ለባልደረባዬ ምላሽ ላኩለት፤ እንዲህ የሚል፦
“ችግሩ የሚባል ነገር ጠፍቶ ሳይኾን፣ አዳማጭ አለመኖሩ ነው። የገደል ማሚቶ መኾን ነው። ጦርነቱን ከሚያራብዱት መካከል ‘ሰላም ለመደራደር ምክር እንፈልጋለን’ የሚሉ የምታውቃቸው ሰዎች ካሉ፣ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ።
Filed in: Amharic