“ጁንታው የትግራይ ሕዝብ ጠላት መሆኑን በግልፅ እያስመሰከረ ይገኛል”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በትግርኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት ጁንታው የትግራይ ሕዝብ ግልፅ ጠላት መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል ብለዋል፡፡
ባለፉት ወራት በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አማካኝነት የትግራይ አርሶ አደር እንዳይቸገር፣ የክረምት እርሻ እንዳይስተጓጎል፣ ምርጥ ዘር እና ዘመናዊ የእርሻ ትራክተሮችን በማቅረብ ቀን እና ሌሊት አበክሮ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ሰብዓዊነትን መሰረት ያደረገ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ሲያሳልፍ፣ የክረምት ወቅት እንዳያልፍ፣ ሕዝቡ እንዲያርስና እንዲዘራ እንዲሁም ሰብዓዊ ደጋፍ በይበልጥ እንዲዳረስ በማድረግ ለትግራይ ሕዝብ ያለንን የማይናወጥ ክብር ለመግለፅ ነበር። ዳሩ ግን “ጊዜ ካለህ ጊዜህን አትስጥ” ነውና ነገሩ፣ የትግራይ አርሶ አደር የዚህ የጥፋት ቡድን እኩይ ዓላማ ከቁብ ሳይቆጥረው፣ ርብርቡን የክረምት የእርሻ ሥራው ላይ እንዲያደርግ ጥሪ አቀርባለሁ ብለዋል።
ሕዝብ እንዳይርበው፣ በቂ የሆነ እህል እንዲያከማችና እንዲደርሰው፣ ተደራሽነቱን በተመለከተም ከመንግሥት ባሻገር ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች እንዲሳተፉ፣ ግልፀኝነትና ተጠያቂነት እንዲኖረው፣ አሠራሮችን በመዘረጋት ያለ ረፍት ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ ጠላት የሆነው ራሱ ጁንታው እንጂ የፌደራል መንግሥቱ ወይም ሌሎች አካላት እንዳልሆኑ አሸባሪ ቡድኑ በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡
ስለሆነም የተጀመሩት የመልሶ ግንባታ ሥራዎች እውን እንዲሆኑ፣ ገበሬው ወደ እርሻው ነጋዴውም ወደ ንግዱ ሠራተኛውም ወደ ሥራው እንዲመለስ እና ሕዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት እንዲያገኝ ለማድረግ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡