>

ከኢትዮጵያ በተቃርኖ ያለው ድብቁ የምእራባውያን አቋም እና አሰፈሪው የዘረኝነት መንፈስ በወፍ በረር ሲቃኝ (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ከኢትዮጵያ በተቃርኖ ያለው ድብቁ የምእራባውያን አቋም እና አሰፈሪው የዘረኝነት መንፈስ በወፍ በረር ሲቃኝ

 

ደረጀ መላኩ  የሰብዓዊ መብት ተሟጋች

 


የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅጡ የሚከታተሉ  የህሊና ሰዎች፣ የገለልተኛ አቋም ያለቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና አክቲቪስቶች፣ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኞች እና ምሁራኖች የምእራባውያንን ለአንድ ወገን ያደላ ትችት እንደማይቀበሉት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መተቸታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በተለይም ሰሜን ኢትዮጵያን በተቆጣጠረው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትና በፌዴራል  መንግስቱ ጦር ሀይል መሃከል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ኖቬምበር ወር ውስጥ ግጭትና ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የምእራባውያን ከኢትዮጵያ በተቃራኒ መስመር መቆማቸው፣ ኢትዮጵያን ለሚያደሙ ሀይሎች ድጋፍ መስጠታቸው ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በታላቅ ሀዘን ውስጥ የዶለ ጉዳይ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምእራባውያን በቀጥታ ከፌዴራል መንግስቱ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ነው የቆሙት፡፡ የተለያዩ ማእቀቦችንም ጥለዋል፡፡ ኢትዮጵን ለመጉዳት ብዙ እርቀት ተጉዘዋል፡፡ የለውጡ መሪ በሆኑት በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አቢይ አህመድ እና በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች መሃከል በተከሰተው ጥልቀት ያለው ልዩነት የተነሳ ለግጭት መንገድ እንደተከፈተ   በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የፈነዳው የትግራይ ሚሊሻ ወታደር በትግራይ ክልል የሀገር ዳር ድንበር በሚጠብቀው የኢትዮጵያ ጦር ሀይል ላይ ድንገተና ጥቃት በመከፍቱ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ በከፈተው መልሶ ማጥቃትና ህግ የማስከበር ዘመቻ ውጤት የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ከነበረበት የጦር ማዘዣዎችና ከተሞች በፍጥነት ለቆ እንዲወጣ ያደረገ ክስተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህ አጭር ግዜ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ድርጅታዊ መዋቅረ ይበተናል ተብሎ አልተገመተም ነበር፡፡ ግን ሆነ፡፡ ለወራቶች ቢሆንም በየጢሻውና ሸለቆዎች ውሰጥ መሸሸግ ግድ ብሏቸው ነበር፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ በሚያሳዝን እና ልብን በሚሰብር ሁኔታ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማለትም ከምግብ እጥረት ጀምሮ ፣የንጹሃን ዜጎች ግድያ፣ የዜጎች ፍልሰት ወደ ጎረቤት ሀገር የዜጎች ፍልሰት ወደ ጎረቤት ሀገራት፣ ይህን ተከትሎ ደግሞ ወታደራዊ ግብግብ ተፈጥሯል፡፡( በሌላ አነጋገር የትግራይን ችግር ለመፍታት ወታደራዊ ሀይል እንደ አንድ ሁነኛ አማራጭ እየተወሰደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት አድርጌአለሁ በማለት መቀሌን ለቅቄ ወጣሁ ባለ ማግስት የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ጦርነቱን ቀጥሎበታል፡፡

ካለማመን  ወደ ግራ መገባት

ድንገተኛ እና ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ የኢትዮጵያ ጦር ሀይል በትግራይ የሚሊሻ ሀይሎች ጥቃት ከተፈተበት በኋላ የኢትዮጵያ ጦር ሀይል ህግ ለማስከበር የመልሶ ማጥቃት ሲከፍት በብዙ ኢትዮጵያውያን እሳቤ ዘንድ ምእራባውያን የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ በበጎ ጎን ሊመለከቱት ይችላሉ የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ግምቱ ፍሬ አላፈራም፡፡

ሆኖም ግን ይሁንና ለሲቪሎች ግድያ፣ሴቶችን አስገድዶ መድፈር፣ አውቆና አስቦ ንብረት ማውደም፣ በመጨረሻም ዘር ተኮር ጥቃትና  የመሳሰሉትን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ ተጠያቂ ያደረጉት የኢትዮጵያን የጦር ሀይል ነው፡፡ ነገሩን የበለጠ ለማወሳሰብ እና አስጨናቂ ለማድረግ ደግሞ የኤርትራ ወታሮችና እና የአማራ ሚሊሻ ወታደሮችን ተጠያቂ ያደርጓቸዋል፡፡ ሁለቱንም ሀይሎች የትግራይ ነጻ አውጪ ወታደሮችና ኤሊቶች ላይ ከባድ ጥላቻ አለባቸው የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር በአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይከሰሳሉ፡፡ የመጨረሻው ውጤት ግን የተገላቢጦሹ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አድራሾች እነደ ተጎጂ ተቆጥረዋል፡፡ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ከፍጥረቱ ጀምሮ አሁን የደረሰበት ግዜ ድረስ ሪኮርዱ እንደሚያሳየው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የሚታወቅ ነው፡፡ የምእራቡ አለም ግን በትግራይ ክልል ለተፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትን ሲከስ አይሰማም፡፡ በጸሃፊው እምነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካላት ሁሉ መጠየቅ አለባቸው የሚል እምነት አለው፡፡ በነገራችን ላይ ጸሃፊው የኢትዮጵያ ጦር ሀይሎች አንዳንድ አባላትም ሆኑ አንዳንድ የኤርትራ ወታደሮች በሰብዓዊ መብት ጥሰት አኳያ ከደሙ ንጹህ ናቸው ነው የሚል እምነት እንደሌለው አንባቢውን ያስታውሳል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በትግራይ ምድር ለተፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምእራቡ አለም የትግራዩን ነጻ አውጪ ድርጅት ከወንጀል ተጠያቂነት ነጻ እንዲሆን የሚያደርገውን ሴራ አጥብቆ ይኮንናል፡፡ ከዚህ ባሻግር ላለፉት 27 አመታት ( በወያኔ አገዛዝ ዘመነ መንግስት ማለቴ ነው) ወያኔ ይፈጽመው ለነበረው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጆሮ ዳባ ልበስ ይል የነበረው የምእራቡ አለም ዛሬ ደርሶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ መቅረቡ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ምእራባውያን ለኢትዮጵያ ህዝበ ሰብዓዊ መብት መከበር የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ግዜ ሳይቀር የተባባረችው አሜሪካ ህግ አውጪ ክፍል ሳይቀር ዝምታን መርጦ ነበር፡፡ አንድም እርምጃ አልወሰዱም ነበር፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያ አቆጣጠር ነሃሴ 2015 ኢትዮጵያን የጎበኙት የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት ባራክ ኦባማ የወያኔን አገዛዝ በዲሞክራቲክ አኳያ የተመረጠ መንግስት ሲሉ ማንቆለጳጰሳቸውን እናስታውሰለን፡፡ ይህ የሚያሳየን ቁምነገር ቢኖር የአለም የዲሞክራሲ ፖሊስ ነኝ በማለት የምትመጻደቀው የተባባረችው አሜሪካ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚታወቀውን የዌኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ለማንገስ ትሻ እንደነበር ነው፡፡ ( በነገራችን ላይ 547ቱ የፓርላማው ወንበሮች በወያኔ ኢህአዲግ አባላት የቴዘ ነበር፣ በርካታ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ወደ ወህኒ አምባ ተወርውረዋል፣ ሰቆቃና ስቃይ ተፈጽሞባቸው ነበር፡፡) ዛሬ ደግሞ ብሶባቸው ይገኛል፡፡ የአማራ ሚሊሻ እና የኢትዮጵያ የጦር ሀይል እያሳደዳቸው በነበረበት ቅስፈት፣ በዘመናዊው የአለም ታሪክ ይፈጸማል ተብሎ የማይገመት አሰቃቂ ግድያ በማይካድራ ከተማ ነዋሪ በሆኑ ኢትዮጵያዊ የአማራ ተወላጆች ወንድሞቻችን ላይ ወያኔ ያደራጃቸው ኢመደበኛ የወጣቶች ስብስብ ቢፈጸምም አንድም ይህን በብዙ ማስረጃዎች የተጋለጠውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲያውግዝ አልታየም ፡፡ ያሳዝናል፡፡ በእውነቱ የምእራባውያን አቋም ልብን ያደማል፡፡ ሆድንም ይበጠብጣል፡፡ የምእራባውያን መንግስታት ዝምታ ብቻ አይደለም ዛሬ የሚስተዋለው፡፡ የምእራበውያን የዜና አውታሮችም ቢሆኑ ወገንተኝነታቸው ከሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር አኳያ አይደለም፡፡እነርሱ የመንግስቶቻቸውን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የቆሙ ናቸው፡፡ የምእራባውያን የዜና አውታሮች የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ወታደሮች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ፈጸሙት የሚሎትን ሰቆቃ በየግዜው ሲዘግቡ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት የሚፈጽመውን ግፍና ሰቆቃ አይዘግቡትም ፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁም ነገር ቢኖር የምእራቡ አለምና የምእራቡ የዜና አውታሮች የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ሁነኛ ወዳጅ ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ወዳጅ አለመሆናቸውን ነው፡፡

የምእራባውያን አቋም ምን ያሳየናል ?

ለማናቸውም ገለልተኛ ተመልካች ግልጽ እየሆነ የመጣው ነገር ቢኖር  በወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ዘመን  ይፈጸም የነበረውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችላ ይሉ የነበሩት ምእራባውያን ዛሬ ፍጹም ገለልተኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ በሚከት አኳያ የሚያሰሙት ጩሀት የሰብዓዊ መብት ጠበቃነታቸውን አያሳይም፡፡ የእነርሱ ጉዳይ የጂኦፖለቲካ ጉዳይ ነው፡፡ በአፍሪካው ቀንድ እና ቀይ ባህር አካባቢ በተለይም ከእነ ቻይና እና ሩሲያ ጋር ለሚያደርጉት የኢኮኖሚ ቁጥጥር ፉክክር ይረዳቸው ዘንድ አጋር ይሻሉ፡፡ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ሊያስጠብቅ የሚችል ሀይል ካገኙ ገሸሽ አይሉም፡፡ ይህ ሀይል በአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚታወቅ ቢሆንም ከመደገፍ ወደ ኋላ አይሉም፡፡

አንደ ምእራባውያን ጥናትና ግምገማ ከሆነ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስትና በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት መሃከል የተነሳው ውጥረትና ግጭት ለአፍሪካው ቀንድ ሰላም መደፍረስ የበለጠ አደገኛ የሚሆነው የኤርትራ ወታደሮች በግጭቱ ውስጥ እጃቸውን ሲዶሉ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር በታላቁ የህዳሴ ግድብ አኳያ ሶስቱ ሀገራት( ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን) የገቡበት እሰጥ እገባ ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ የገቡበት የድንበር ይገባኛል ጥያቄና ሱዳን የኢትዮጵያን ሱዳን በእብሪት መውረሯ በመላው አፍሪካ ሊቀጣጠል የሚችል የጦርነት እሳት ሊነሳ ይችላል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት አስፈሪ ሁነቶች እንዳይከሰቱ ከተፈለገ በትግራይ የተጀመረው ጦርነት በውይይት መፈታት አለበት የሚለው የምእራባውያን አቋም ነው፡፡ ምንም እንኳን ለጦርነት መከፈት ምክንያት የሆነው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የጦር ሀይል ክፉኛ የተደቆሰ ቢሆንም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር እንዲደራደር የምእራባውያን ፍላጎት ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የምእራባውያን መንግስታት ፍላጎት፡፡ አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 2 2021 የቡድን ሰባት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች  በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ተወያይተው ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ከሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ጋር ያለውን ልዩነት በውይይት እንዲፈታ አሳስበውም ነበር፡፡

አንድ ልብ ማለት ያለብን ቁምነገር ቢኖር የምእራባውያን ውትወታ ምክንያታዊ ይመስላል ይህም ማለት  ብሔራዊ እርቅና ውይይት ብሔራዊ ሰላም ለማጎናጸፍ ይረዳል፡፡ ያለመታደል ሆኖ እንዲህ አይነት የፖለቲካ መደላድል ገና አሁን ድረስ አለተፈጠረም፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ውይይት ለማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ምክንያቱ ደግሞ በአብዛኛው የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስለበዙ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ የከፋፍለህ ግዛ ውርዴ ነው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ከአንድ ጎሳ በተወጣጡ የፖለቲካ ኤሊቶች መዳፍ ስር እንዲወደቅ እድሉን ይሰጣል፡ 

ምንም እንኳን የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የተገኘበት የህብረተሰብ ክፍል ከአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ 6 ፐርሰንቱን የሚሸፍን ቢሆንም፣ አንዳንድ አክራሪ ብሔርተኞች ሲጨመሩ፣ሌሎች አንዳንዶች የመገንጠል ስሜት ያላቸው ናቸው፡፡ እኘኚህ ቡድኖች ለኢትዮጵያ አንድነት ጋሬጣ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ እነኚህ የጎሳ ቡድኖችን በብሔራዊ እርቅና ውይይት ለመፍታት አስቸጋሪ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የመገንጠል አቋቸውን ካልቀየሩ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እራስ ምታት መሆናቸው አይቀርም፡፡ የምእራባውያኑ ወገናዊ ጣልቃ ገብነት ሀገሪቱን እንደ ገና ዳቦ እያቃጠላት ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ እድል ሊቢያ ገጥሟት የነበረውን እጣ ፈንታ ያስታውሰናል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የርበርስ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ያሰጋል፡፡ ምእራባውያን በሊቢያ የደረሰውን አሳዛኝና አስከፊ ሁኔታ በኢትዮጵያ ለመድገም ቢሞክሩ ማንም አይቀበላቸውም፡፡ የኢትዮጵያን ህዝብ የረጅም ዘመን ታሪክ መልሰው እንዲመረምሩ እናስታውሳቸዋለን፡፡

ለምንድን ነው ለብዙ ኢትዮጵያውያን ግልጽ የሆነላቸው ነገር ለምእራባውያን መንግስታት ፈንትው ብሎ መታየት ያልቻለው ? አውቆ የተኛን ሲቀሰቅሱት አይሰማም እንዲሉ ምእራባውያን የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያዩት ከጂኦ ፖለቲካ ፍለጎታቸው ጋር ነው፡፡

በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ በምእራባውያን አይን ማለቴ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ያጋጠመውን አለመግባባት ወይም ግጭትና ጦርነት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ካልሆነለት ወደሌሎች ክልሎችም ግጭቶች ሊሰፋፉ ይቻላቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የሚደረጉ የፖለቲካ ንግግሮችና ውይይቶች  ውጤታማ ሊሆኑ የሚቻላቸው የአውሮፓ ህብረትና የተባበረችው አሜሪካ ቁጥጥር ስር ሲወድቅ ብቻ ነው የሚል እምነትም አላቸው፡፡

ይህን በምክንያታዊ አመክንዮ ስንመዝነው ውጤቱ የዜሮ ድምር ነው፡፡ በምእራባውያን ተጽእኖና ፍላጎት ብቻ የሚደረግ ውይይት ሰላምን ያመጣል ተብሎ አይታመንም፡፡

ምእራባውያን የሚያስቀምጡት የሰላም መንገድ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች  የሚከሰቱ ግጭጦች እና ከትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ጋር የሚደረገው ጦርነት መነሻ ምክንያቶች የአክራሪ ብሔርተኞች እርዮት አለም ያመጣው መዘዝ መሆኑን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር  በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚቀሰቀሱት ግጭቶች በአክራሪ ብሔርተኞች ምክንያት ስለመሆኑ የምእራቡ አለም መረዳት አልፈለገም፡፡ በእውነቱ ለመናገር እነኚህ አክራሪ ብሔርተኞች የሚባሉት ቡድኖች በቅን ልቦነ፣ በቀና መንፈስ ተነጋግረው ለመስማማት የተዘጋጁ አይደሉም፡፡ በተቃራኒው እውነተኛው መፍትሔ የሚገኘው ካለው ተጨባጭ ችግር ነው፡፡ በተጨማሪም አሁን ያለውን ማእከላዊ መንግስት ማጠናከር የውስጥ ሰላምን ለማስፈን በእጅጉ ጠቃሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ከውጭ ያለውን የጂኦፖለቲካ ችግር እየታየ የኢትዮጵያ መንግስት ማዋከብና ፊት መንሳት ግብጽና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ የውክልና ጦርነት ለመክፈት ያመቻቸዋል፡፡ በአጭሩ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፈሩን የለቀቀ የምእራባውያን ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ውስጥ ውይይት እና ሰላም ለማምጣት የሚረዳ አይደለም፡፡

ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም በማድረግ ከትግራይ ክልል ለቆ መውጣቱን በአንክሮ መመርመር ይቻላል፡፡ አንድ ምክንያታዊ የሆነ ሰው የኢትዮጵያን መንግስት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት በተመለከተ የምእራቡ አለም መንግስታት በተለይም የተባበረችው አሜሪካ እና ታላቋ ብሪታንያ እንዲሁም የምእራቡ አለም የዜና አውታሮች ይህን የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን ውሳኔ በቀና መንፈስ ይመለከቱታል ብሎ ማሰቡ እውነት ነው፡፡ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ በገሃዱ አለም የተከሰተው ለማመን የሚያስቸግር ነው፡፡ የምእራቡ አለም የወሰደው እርምጃ አሳዛኝም አስተዛዛቢ ነበር፡፡ የምእራቡ አለም መንግስታት በተለይም የተባባረችው አሜሪካ ተወካይ የሆኑ አንድ ባለስልጣን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሰላ ትችታቸውን አውርደውበታል፡፡ አንዳንድ የምእራብ መንግስታት ደግሞ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ማእቀብ ለመጣል ማሰባቸው ተሰምቷል፡፡

ይህ ያልተጠበቀ እርምጃ የተወሰደው ምእራባውያን ካደረባቸው ጭንቀት ይመስለኛል፡፡ ምእራባውያን ብሔራዊ የውይይት መድረክ እንዲፈጠር ይፈልጋሉ፡፡ እነርሱ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔን አይደግፉም፡፡ ምንም እንኳን በቅርቡ በተደረገው ብሔራዊ የምርጫ ውድድር ላይ አሸነፈ የተባለ የኢትዮጵያ መንግስት ቢኖርም አክራሪ ብሔርተኞችና የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅትን ያገለለ መንግስት እንዲኖር ፍላጎት ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በቅርቡ በተደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ ውድድር ላይ አሸናፊ ለነበረው የዶክተር አቢይ መንግስት ድጋፍ ለመስጠት አልፈለጉም፡፡ በአጭሩ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ( ምእራባውያን ማለቴ ነው) የኢትዮጵያ መንግስት ከአክራሪ ብሔርተኞች እና ከትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ጋር እንዲደራደር ምኞታቸው ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ግልጽ ነው፡፡ ከምርጫው በፊት የተባበረችው አሜሪካ ፍላጎት የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ምርጫው ላይ አንሳተፍም ካሉ አክራሪ ብሔርተኞች ጋር ውይይት በማድረግ ሰራሄ መፍትሔ እንዲፈልግ ምኞታቸው ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ስለሆነም ዛሬም ውይይት እንዲደረግ ይፈልጋሉ፡፡

ከዚህ ባሻግር የተባበረችው አሜሪካ ሁነኛ የፖለቲካ ሰው ሚስተር ብሊንከን  ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናጋሩት ከሆነ ‹‹ ምርጫ ብቻውን ለአንድ እውነተኛ የፖለቲካ ለውጥ ዋስትና መሆን አይችልም፡፡ ›› ሆኖም ግን ይሁንና ምርጫው በኢትዮጵያ ሳይሆን በሌላ ሀገር የተካሄደ ቢሆን ኖሮ ( በተለይም የተባበረችው አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅሜን ሊያስጠብቅ ይችላል ብላ ያመነችበት መንግስት  ማለቴ ነው፡፡ ) ይህች የአለማችን የፖለቲካና አኮኖሚ ሁኔታዎችን በተመለከተ ሁነኛ ዘዋሪ የሆነችው የተባበረችው አሜሪካ   የምትሰጠው አስተያየት ለየት ያለ ሊሆን የሚችል ነበር፡፡ ምናልባትም ምንም እንኳን የምርጫ ውድድሩ በርካታ ውጣ ውረዶች ቢኖሩትም በትክክለኛው መንገድ ላይ ነው በማለት ምስክርነቷን ትሰጥ  ነበር፡፡

የስሜት መደበላለቅ

የምእራቡ አለም መንግስታት ( በተለይም የተባበረችው አሜሪካ እና ታላቋ ብሪታኒያ) አስተሳሰብ በየግዜው እንደሚቀያየር ለሀገራት የሚሰጡት  ድጋፍ ደግሞ ቋሚ እንዳልሆነ የምናስታውሰው ጉዳይ ነው፡፡ ( እነርሱ ዛሬ ወዳጅ ያደረጉትን የአንድ ሀገር መንግስት፣ በአንቀልባ ማዘል እስከቀራቸው የሚያንቆለጳጵሱትን መንግስት፣ የሰላም ሃዋርያ እያሉ ሲመሰክሩለት ለነበረ መንግስት ግዜ ጠብቀው አይንህ ላፈር ይሉታል፡፡) ብዙ አመት ሳንጓዝ በቅርብ ግዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ሁነኛ የምእራቡ አለም ወዳጅ ነበረች፡፡ ዛዲያ ለምንድን ነው የምእራቡ አለም መንግስታት የውጭ ፖሊሲ ከዶክተር አቢይ መንግስት ተጻራሪ ሆኖ የቆመው ? እውን የምእራቡ አለም በኢትዮጵያ ላይ ፊቱን ያዞረው በድንገት ነውን ? ከመገናኛ ብዙሃን ዘገባ እንደተሰማው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር የካቲት 5 2021 የተባበረችው አሜሪካ ባለስልጣን የሆኑት ሚሰትር ብሊንከን (Secretary Blinken) ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በነበራቸው አጭር የስልክ ቆይታ እንዳስታወቁት ሀገራቸው አሜሪካ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የለውጥ ጉዞ ለመደገፍ የገባችውን ቃል እንደማትዘነጋ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተደረገውን 6ኛውን ሀገር አቀፍ የምርጫ ውድድር ለመደገፍ ቃል ገብተው ነበር፡፡

ከኢትዮጵያ አኳያ የምእራባውያን የፖሊሲ ለውጥ ከሰብዓዊ ስሜት የመነጨ አይመስለኝም፣ ኢትዮጵያን ባይተዋር አድርገው ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር በእጅጉ የሚቸገሩ ይመስለኛል፣ የጂኦፖለቲካዊ ምክንያትም ቢሆን ለምእራባውያን የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት ለመሆን በቂ አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ አንዲት የምእራባውያን ሁነኛ ወዳጅ የነበረች ሀገር ችግር ውስጥ ስትዶል ፈጥነው ለችግሯ መፍትሔ መፈለግ ይገባቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አላደረጉትም፡፡ ምእራባውያን ኢትዮጵያን ጁኒዬር ወዳጃቸው፣ራሳቸውን ደግሞ እንደ ሲኒዬር ወዳጅ አድርገው የቆጠሩ ይመስላል፡፡ አንድ ታላቅ መንግስት፣የአለም የኢኮኖሚና ፖለቲካ ዘዋሪ መንግስታት ምእራባውያን ኢትዮጵያን እነርሱ በሚፈልጉት አቅድና መንገድ ለመንዳት ይፈልጋሉ፡፡ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ሀገራችን ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ሰላም ድርድር እንዲመጣ ፍላጎታቸው ነው፡፡ ነፍጥ አንግቶ የተነሳው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የሀገር ክህደት፣ የጦር ወንጀለኝነት ወዘተ ወዘተ ሳይጠየቅ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ  ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለድረድር እንዲቀመጥ ይፈልጋሉ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሌሎች አክራሪ ብሔርተኞች ምእራባውያን በሚፈልጉት መንገድ እና ቅድመ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት ጋር እንዲደራደሩ ይፈልጋሉ፡፡ አሁን እየገባኝ ያለው ይሄው ነው፡፡ ምእራባውያን በኢትዮጵያ ፍትህ፣እኩልነትና ነጻነት፣ እንዲሁም የዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች መከበርና የህግ የበላይነት እንዲከበር ጽኑ ፍላጎታቸው ቢሆን ኖሮ የዲሞክራቲክ ተቋማት እንዲጎመሩና በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆሙ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ነበር፡፡ ግና አላደረጉትም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ፣ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ አልሄድ ያላቸውን የኢትዮጵያ መንግስት  አይንህ ላፈር በማለት ሰልፋቸውን በተቃራኒው አድርገዋል፡፡ በነገራችን ላይ ምእራባውያን ለአክራሪ ብሔረተኞች የሚያደርጉት ድጋፍ ለአካባቢው የጂኦፖለቲካ ሁኔታ መረጋጋትን አይፈጥርም፡፡ የአክራሪ ብሔረተኞች ጡንቻ መፈርጠም የርስበርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ከማድረግ ውጭ የሚያመጣው ፋይዳ የለም፡፡ በተዳከመችና አንድነቷ ባላላ በኢትዮጵያ ምድር እንደፈለግነው አዛዥ ናዛዥ በመሆን እንዳሻን እንፈነጫለን በማለት አስልተው ከሆነ የሚያውቁት ራሳቸው ይሆናሉ፡፡

በአንድ በሌላ ሀገር፣በድህነት በምትታወቅ ሀገር፣በብዙ ማህበራ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ፍዳዋን በምትቆጥር ሀገር ወዘተ ወዘተ ( ይህ የብዙ አፍሪካዊ ሀገሮች ችግር ነው) ዲሞክራሲ ሰፈነ አልሰፈነ፣ ሰብዓዊ መብት ተከበረ አልተከበረ የምእራባውያን ራስ ምታት ያልሆነበት አንዱ ምክንያት ከዘረኝነት መንፈስ የመነጨ ነው ለሚሉ የፖለቲካ ሰዎች አንድ ጥያቄ አለኝ፡፡ ለዘረኝነት አባዜ ማነው የበላይነት የሰጠው ? ምእራባውያን የበላይ ነን በማለታቸው ብቻ ሌሎች ሀገራት እኛ ያልናችሁን መንገድ ብቻ ተከተሉ የሚለው አመክንዮ ከየት የሚመነጭ ነው ?

በመጨረሻም ለማስታወስ የምፈልገው ቁምነገር ቢኖር ምእራባውያን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም አኳያ ተጻራሪ የሆነ አቋም የያዙበት መሰረታዊ ምክንያት ይህ የዘረኝነት አባዜያቸው ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ምእራባውያን የፈለጉትን አቋም ሙሉቡሙሉ መቀበል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት የተነሳ የቆየ የምእራቡ አለም የቆየ ሴራውን ገፍቶበታል፡፡ በአለም ላይ ካሉት የጥቁር ህዝብ መኖሪያ ሀገራት መሃከል የነጭ ትምክህተኞችን አሳፍራ፣አሸንፋ የመለሰች ብቻ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን መዘንጋት የለብንም፡፡ የዘመናት ቂም ቋጠሮ መፍቻው ዛሬ ነው አመቺ ግዜው ብለውም አስበው ይሆናል፡፡ ጥሎ የማይጥል የኢትዮጵያ አምላክ እየጠበቀን እንጂ እነርሱ እንደ እነ ሚስትር ጆን እና ኬሲንጀር፣ሀርማን ኮህን ወዘተ በመሰሉ የፖለቲካ አዋቂዎቻቸው አመሃኝነት ያዘጋጁልን የሞት ድግስ ከግማሽ ክፈለዘመን አለፈው፡፡

ለማናቸውም ምእራባውያን መንግስታት ወደ ህሊናቸው ተመልሰው በኢትዮጵያ ምድር ወገንተኝነታቸው ከዴሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች እና የህግ የበላይነት ጋር እንዲሆን ሁላችንም በገለልተኝነት አቋም ውተወታችንን እንቀጥል በማለት እሰናበታለሁ፡፡

Filed in: Amharic