>

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተጸነሰው ሴራ  !!   (ዶ/ር አክሎግ ቢራራ) 

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተጸነሰው ሴራ  !!

  ዶ/ር አክሎግ ቢራራ 

*….. እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ የምእራብ አገሮች ለጥቁር አፍሪካ ሕዝቦች ሰላም፤ እርጋታ፤ ክብር፤ ነጻነት፤ ፍትሃዊና ዘላቂ ልማት ቆመው አያውቁም። በተለይ፤ ለመላው የጥቁር ሕዝብ ክብርና ነጻነት ተምሳሌ የሆነችውን የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፤ ሉዐላዊነት፤ የስብጥር ሕዝቧን አብሮነት፤ ሰላም፤ እርጋታ፤ ፍትሃዊ፤ ዘላቂ ብልጽግና ደግፈው አያውቁም። የኢትዮጵያ ጠንካራና አገር ወዳድ መንግሥት ለነሱ ብሄራዊ ጥቅም ስጋት ፈጣሪ ነው። ይኼን ሃቅ በአጼ ኃይለ ሥላሴና በደርግ መንግሥት ወቅትም አይተናል
ህወሓት/ትህነግ ጆ ባይደን በተመረጡበት ማግስት ክህደት፤ እልቂት ከፈጸመበትና ጦርነት ከጀመረበት አንድ ሳምንት በኋላ ለዚህ አጥፊ፤ ከሃዲና የውጭ ኃይሎች አገልጋይና አሽከር የሆነ ቡድን ግዙፍ ድጋፍ ይሰጡት የነበሩት የምእራብ “ዲሞክራሲ” ነን የሚሉ ባለሥልጥናት ሴራቸውን በምስጢር ቀየሱ።
ኢላማቸው ሁለት አስኳል ጉዳዮች ነበሩ፤ አንድ የጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አሕመድን መንግሥት መገልበጥና ባለሥልጣናትን ልክ እንደ ሰርቦች ለፍርድ ማቅረብ፤ ሁለት፤ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ዩጎስላቭያና እንደ ሶማልያ እንድትበታተን ማድረግ።
እኛ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በተደጋጋሚ ለምእራብ አገሮች ባለሥልጣናት፤ በተለይ ለአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በተደጋጋሚ እባካችሁ ሚዛናዊ አቋም ያዙ፤ በመሬት ላይ ያለውን ሃቅ አንጸባርቁ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል የትግራይ ሕዝብ ጠላት አይደለም፤ የብሄር ማጥፋት ዘመቻ አያካሂድም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት 70 በመቶ የሚሆነውን ሰብአዊ እርዳታ እየሰጠ ነው ወዘተ እያልን ብንጮህም ሰሚ አላገኘነም ነበር። ብዙዎቻችን ግራ ተጋብተን ነበር ለማለት እችላለሁ። ለምን ጀሩቸውን አይከፍቱም፤ አይናቸውን አይገልጡም? እንል ነበር፡
ከጀርባ በረቀቀ ምስጢር የሚካሄደውን ሴራ በይፋ ያቀረበልን ጅዖፖለቲክስ “C2 fc is using lethal journalism to conduct information warfare and lawfare against Ethiopia” የሚለው ጥናት፤ ምርምርና ዘገባ ነው። የዚህ ዘገባ ይዘት የሃሰት ትርክት እና ሰብአዊ እልቂት ተካሂዷል የሚለው የምእራብ አገሮችና ተቋማት ጸረ-ኢትዮጵያ መርህ ኢትዮጵያን መንግሥት አልባ ለማድረግና አገሪቱን ለማፈራረስ የተቀናጀ እቅድና ሴራ እንደሆነ ያሳያል። በዚህ ድምዳሜ ላይ ብዢታ ሊኖር አይችልም።
እኛ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ስንከራከርና ስንወያይ ለቆየን አገር ወዳዶች የኢትዮጵያ የወደፊት እድል እንዳሁኑ አስጨንቆን አያውቅም። ምክንያቱም፤ ኢትዮጵጵያ የተከበበች፤ በውስጥና በውጭ ኃይሎች ትብብርና ያልተጠበቀ ቅንጅት የጅዖ ፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የመዋእለንዋይ ፈሰስ፤ የንግድ ጫናና የውክልና ጦርነት የሚካሄድባት አገር መሆኗ ነው።
የችግሩ እምብርት ምንድን ነው?
1. በአገር ውስጥ፤ ህወሓት/ትህነግ (ዛሬ የትግራይ መከላከያ ኃይል ተብሎ የተሰየመው) ኢትዮጵያን በበላይነት እየገዛሁ ለመዝረፍ ካልቻልኩ ከአማራው ክልል በኃይል የነጥቅኋቸው ለምና ወሳኝ መሬቶች (ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ) “የታላቋ ትግራ” አካል እንዲሆኑ እስከመጨረሻው ድረስ እዋጋለሁ የሚለው ሲሆን፤ ከዚህ ጋር አብሮ የተዛመደው ደግሞ፤
2. የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካን ቀንድ መቆጣጠር ለምእራብ አገሮች የንግድ፤ የመዋእለንዋይ ፈሰስ፤ የደህንነት፤ የሚሊታሪና የጅዖፖለቲካ የበላይነት ወሳኝ ነው የሚል ስሌት ነው። ይህንን ለቀይ ባህርና ለመካከለኛው ምስራቅ የበላይነት ወሳኝ የሆነ ቀጠና በበላይነት ለመያዝ ደግሞ የአሜሪካንና የምእራብ አውሮፓ አገሮችን ጥቅም የሚያስከብር መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ፤ በተለይ በኢትዮጵያ መኮትኮትና መመስረት ያስፈልጋል። “የሽግግር መንግሥት” የሚለውን የሚያስተናግዱት ለዚህ ነው። ህወሓት/ትህነግ (የትግራይ መከላከያ ኃይል) እና ከዚህ ኃይል ጋር ያበሩ የዘውግ ድርጅቶች አማራጭ ስለሆኑ መርዳት አለብን የሚል ስልት መሆኑ በግልጽ ይታያል። July 29, 2021 ብቻ በአሜሪካ ቤተ መንግሥት “ተቃዋሚ ነን” ከሚሉ ተወካዮች ጋር የተካሄደው ውይይት ለዚህ የአማራጭ ዘዴ ምልክት ነው።
የባይደን መንግሥት የሚከተለውን ፖሊሲ በአጭሩ ላቅርበው። ትራምፕ ፕሬዝደንት በነበሩበት ወቅት ሕወሓት/ትህነግ በኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ላይ በመቀሌ የፈጸመው ክህደትና ግድያ (Treason and massacre of non-Tigrean soldiers and officers) ወንጀል ነው ብለው ተችተውት እንደ ነበረ ታሪክ መዝግቦታል። የፕሬዝደንት ባይደን መንግሥት ስልጣን ከያዘበት ወዲህ ግን በትግራይ ያለው ትርክት እየተቀያየረ፤ ህወሓት/ትህነግ የፈጸማቸው ወንጀሎች ሁሉ ወደ ጎን እየተቀመጡ፤ “በትግራይ ልጃገረዶችና እናቶች ላይ” ግፍና ወንጀል ተፈጸመ፤ የስብአዊ ቀውስ ( humanitarian crisis) ተካሄደ፤ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይሰጥ ተከለከለ ወዘተ ተባለ። ግፉን የፈጸሙት ሶስት አካላት ናቸው የሚለው በተደጋጋሚ በምእራባዊያን መገናኛ ብዙሃን፤ በሰብአዊ መብት ድርጅቶች (በተለይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል)፤ በልዩ ልዩ የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት፤ ቀስ በቀስ ደግሞ ልክ እንደ ሕዳሴ ግድቡ ሁኔታ፤ በተብበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት ውይይት እንዲደረግበት ተደረገ።
በተደጋጋሚ ለጥፋቱና ለወንጀሉ ተጠያቂ ናቸው የተባሉት ሶስት አካላት የኤርትራ መከካለያ ኃይል፤ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና በጠቅላይ ሚንስትር ዶር ዐብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ሆኑ። ጫናውና ግፊቱ እየበረታ ሄደ። በኢትዮጵያ ላይ መጠነኛ ግን አመልካች የሆነ የቪዛና የእርዳታ እቀባ ተደረገ። የሚቀጥለው እርምጃ ምን ይሆናል? ብለን መዘጋጀት አለብን።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጫናውን ለመከላከልና የትግራይ ገበሬዎች ወደ እርሻቸው እንዲመለሱ ለማድረግ በአንድ ወገን ብቻ የተጠራ የጦር አቁም ውሳኔ አደረገ (unilateral ceasefire). ይህንን ውሳኔ ሲያደርግ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ቅድመ ዝግጅት አላደረገም የሚሉ ብዙ ታዛቢዎች አሉ። በተጨማሪ ቅድመ ሁኔታወችን በግልጽ አላስቀመጠም። ለምሳሌ፤ የትግራይ መከላከያ ተመሳሳይ እርምጃ ውሰድ፤ የጦር አዋጅክን አቁም የሚል የጊዜ ገደብ አልተሰጠውም።
በህወሓት የተጀመረው ጦርነትና ግፍ አልቆመም። እንዲያውም የጦርነቱ ቀጠና ተስፋፋ፤ የውጭ ኃይሎች የሚሳተፉበት የውክልና ጦርነት መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ። የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከንና ቃል አቀባያቸው በተደጋጋሚ አሁንም ችግሩ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያ መንግሥት ናቸው። የአማራ ልዩ ኃይል ከነጠቃቸው “የምእራብ ትግራይ” መውጣት አለበት በሚል በኃይል በሕወሓት የተነጠቁትን መሬቶች የትግራይ አካል ናቸው የሚል የተሳሳተና አደገኛ ውሳኔ አስተጋባ።
በአንድ ወገን የተደረገው የጦር አቁም ውሳኔ ከተደረገ በኋላ ትርክቱ ተቀይሮ “የትግራይ ክልል” ተከቧል (Tigray encircled)፤ የትግራይ ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጧል የሚሉ የተቀነባበሩ ትርክቶች ይካሄዱ ጀመር። የትግራይ የመከላከያ ኃይል ራሱን አጠናክሮ ሌላ ጦርነት በአማራውና በአፋሩ ክልሎች ማካሄዱን ጀመረ። ከዘጠኝ ዓመት እድሜ በላይ ያሉትን የትግራይ “ወጣት ወታደሮች” እያስገደደና እያባበለ ወደ ጦር ግንባር ላካቸው። መስዋእት የሆኑትን ቁጥር ባላውቅም፤ ይህ ወንጀል መሆኑን ግን አውቃለሁ። የባይደን መንግሥትና የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ለዚህ ወንጀልና የረድኤት ድርጅቶች የድጋፍ አቅርቦት ዋናው መሰናክልና ተጠያቂ የትግራይ መከላከያ ኃይል አባላት ናቸው የሚል አቋም አልወሰዱም። ያልወሰዱበት ምክንያት ከላይ የችግሩን ይዘት ሳብራራ እንዳሳየሁት፤ አላማው ሕዝባዊ እልቂትን ለማቆም፤ ሰላምና እርጋታ እንዲመሰረት ለማድረግ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትቀጥል ለማመቻቸት ሳይሆን የአሜሪካን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር መሆኑን ያጠናክራል።
የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት ሃላፊ ሴማንታ ፖወር ወደ ኢትዮጵያ ስለሚሄዱ አንዱ መሰረታዊ ጥያቄ መሆን ያለበት የአሜሪካ መንግሥት የመጨረሻ አላማው ምንንድን ነው? ሰብአዊ እርዳታ ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት የተቻለውን አድርጓል፤ ጦርነቱን ለማቆም ወስኗል፤ ሌላው የሚፈለገው ምንድን ነው? አሁንም ሽብርተኛውን ቡድን የምትደግፉበት ዋና ምክንያት ምንድን ነው? ይኼ ድጋፍ ለአሜሪካ ዘላቂ ጥቅም ፋይዳ አለው ወይ?
በኔ እምነት፤ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የትግራይ፤ የአማራ፤ የሶማሌ፤ የኦሮሞ፤ የጉራጌ ሆነ የወልያታ ወዘተ ህጻናት፤ ልጃገረዶች፤ እናቶችና አባቶች በገፍ ቢያልቁ ደንታ የላቸውም። በሶሪያ፤ በኢራክ፤ በአፍጋኒስታን፤ በሊቢያ፤ በየመን ወዘተ ሊረሱ የማይችሉ በአሜሪካ ኃይል የተፈጠሩ ቀውሶችንና ያስከተሉትን የማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ ውድመት ማስታወስ ይገባል። አሜሪካኖች ከፈለጉና ከመረጡ፤ የሚንከባከቡትን፤ በመረጃና በሌላ የሚደግፉትን፤ ትርክቱን እንደራሳቸው አድርገው የሚያስተጋቡሉትን የከሃዲውን፤ የጠባብ ብሄርተኛውን፤ የሽብርተኛውን የሕወሓት/ትህነግ/የትግራይ መከላከያ ኃይልን የባይደን መንግሥት ባይደግፍ ኖሮ፤ አጥፊው ቡድን የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች ሁሉ ጠቅሶ አዋጅህን ሳብ፤ ጦርነትክን አቁም፤ ይህንን ካላደረግህ ግን በዓለም ፍርድ ቤት ያስከስስሃል፤ ተጠያቂ ትሆናለህ ሊለው ይችል ነበር። የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሳያውቁ ሳይሆን እያወቁ የሚሰሩት ነው። ኢላማው የኢትዮጵያን መንግሥት ማስወገድና ኢትዮጵያን መበታተን ነው።
መሳሪያዎቹ ምንድን ናቸው (What are the tools for regime change and to fracture and weaken any country?)
ጦርነቱ በኢኮኖሚው ላይ ያስከተለው ጫናና ቀውስ ቀስ በቀስ ይታያል። ከሁሉም በላይ በመሬት የሚታየው አደጋ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ ተዳክሞ የኢትዮጵያ ተራ ሕዝብ በራሱ መንግሥት ላይ እንዲማረርና እንዲነሳ የሚያመቻቹ ኃይሎች መኖራቸው ነው። ግብጽና ሱዳን የሚያደርጉት የውክልና ጦርነት ዋናው ሲሆን የምእራብ አገሮች፤ በተለይ የባይደን መንግሥት የሚያስተጋባው ትርክት ከስልቂቱ ጋር አብሮ የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያን ለማዳከም ኢኮኖሚዋን ማዳከም ዋናው ስልት ነው።
ልዩ ልዩ የውጭ ቲንክ ታንኮችና ተቋማት የአደጋውን ስፋትና ጥልቀት ከሌሎች አገሮች ታሪክ ጋር አያይዘው በማሳየት ላይ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር ያካሄዱትን እንድትመለከቷቸው ከዚህ ትንተና ጋር አያይዣቸዋለሁ። በተለይ ትኩረት እንድተሰጡት የምፈልገው ኢትዮጵያን የማፈራረስ የሴራ እቅድ ጅዖፖለቲክስ፤ ከባስማ ወደ ኢትዮጵያ የሚለው ጥናትና ምርምር የሚጠቀስ ነው። ባስማ ማለት በኢስራኤል የምተገኝ መንደር ናት፤ ስያሜው ከቀይ ባህር፤ ከመካከለኛው ምስራቅ፤ ከናየል ወንዝ፤ ከህዳሴ ግድብና ከአፍሪካ ቀንድ የበላይነት ጋር መሆኑን እገነዘባለሁ። ከላይ በመግቢያ ላይ እንዳሳየሁት፤ የጥናቱ ይዘት የተሳሳተ መረጃ የመጠቀምንና በኢትዮጵያ ሰላምና እርጋታ እንዳይመሰረት፤ ኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ እንዲወድም የተደረገውን ግምገማ ያመላክታል። የትጋራይ መከላከያ ኃይል ጦርነቱን ወደ አፋር፤ ከዚያ ወደ ሶማሌና ጅቡቲ ቀጠና እንዲስፋፋ ያደረገበት መሰረታዊ ምክንያት ኢኮኖሚውን ለማዳከም ከጠቆምኩት ዘዴ ጋር የተያያዘ ነው።
ምንም ስጋት ሳይሰማን በውጭ አገሮች የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን የሚያሰጋት ነገር የለም፤ ሕዝቡ ሙሉ በሙሉ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ተነሳስቷል ለምትሉት “ወገኖቸ እባካችሁ ስከን ብላችሁ፤ ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትታችሁ የሚደረገውን የተቀነባበረ ሴራ በያላችሁበት አጋልጡ” የሚል ምክር አቀርባለሁ። በአጭሩ ለማስቀመጥ፤ ኢትዮጵያን አፍራሽ የሆነ የኢኮኖሚ ማነቆ እየተደረገባት ነው። የሕዝቡን ጉረሮ ለማነቅና ሕዝቡን እንዲነሳ ለማድረግ እየተሴረባት ነው (Economic and financial strangulation). በዚህ ፈታኝ ወቅት፤ ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ባላችሁ አቅም ሁሉ ድረሱ የሚል ምክር እለግሳለሁ፤ እኔም ድርሻየን ለመወጣት በመሳተፍ ላይ ነኝ።
 
ትኩረቱ ከምን ላይ ይሁን? 
ጠንካራ መንግሥት የሌለው አገር ሁሉ ለአደጋ ይጋለጣል። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት “የሽግግር መንግሥት አይደለም”። ምርጫው እንከን የለበትም ለማለት ባልችልም እንኳን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ ካሄደ በኋላ የሽግግር መንግሥት ለምን? ለማን? የሚለውን መጠየቅ አለብን። ይህንን አማራጭ ለማስተናገድ የሚቻለው ኢትዮጵያን ካስቀደምንና ህልውናዋን ካረጋገጥን በኋላ እንጅ ዛሬ ሊሆን አይችልም። በዘላቂነት ሲገመገም ግን፤ ለችግሩ መጋቢ የሆነው፤ አንቶኒ ብሊንከን የሚጠቅሰው ሕገ-መንግሥት፤ በተለይ አንቀጽ 39 እና የክልሎች መብትና ግዴታ በባለሞያዎች ጥናትና ምርምር ተደግፎ መቅየር እንዳለበት አምናለሁ። ወቅቱ ግን አሁን አይደለም። አሁን ያለው አንደኛና ዋና ትኩረት ኢትዮጵያን እንደ ሃገር እንድትቀጥል መረባረብ ነው።
 ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለማዳን፤
 
1. ጠንካራና የማይበገር ብሄራዊ መንግሥት እና ስልታዊ አመራር፤ 
 
2. በየ እርከኑ ራሱን ከሰላዮች፤ ከህወሓቶችና ከሰርጎ ገቦች ያጸዳ የደህነትና የስለላ መረብ ያጸዳና፤ 
 
3. ከሁሉም ዘውጎችና እምነቶች የተወጣጣ፤ የሰለጠነ የመከላከያ ኃይል ያስፈልጋታል። 
ለዚህ ደግሞ ከጀርባ ሆኖ ድጋፍ የሚሰጥ ሕዝብ ያስፈልጋታል። የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ከዘውግና ከእምነት በላይ በገፍ በየክልሉ እየወጣ ለአገሩና ለመከላከያ ኃይሉ የሚያሳየውን ድጋፍ ማስተጋባት ወሳኝ ነው። በብዙ ሽህ የሚገመት ወጣት “ክተት” ብሎ የወጣ ይመስላል። ህወሓት/ትህነግ/ የትግራይ መከላከያ ኃይልና የውጭ መንግሥታት ተጣምረውና እየተናበቡ የሚያካሂዱት ሴራ ኢላማው “በአማራው” ላይ፤ በተለይ በአዲሱ የህወሓት ትርክት “በጎንደር ልሂቃን” ላይ ሳይሆን በኢትዮጵያና በመላው ሕዝቧ ላይ መሆኑን ተገንዝቦታል። ኢትዮጵያ ልክ እንደ ዩጎስላቭያና እንደ ሶማልያ ከሆነች ማንም ዘውግ አሸናፊና ተጠቃሚ እንደማይሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ተገንዝቦታል። በአዲስ አበባ ብቻ ከአንድ ሚሊየን ሕዝብ በላይ ድጋፉን ሲሰጥ ከዚህ በላይ ምን ምልከት ያስፈልጋል? የኦሮሞው ወጣት ከወንድሙ ከአማራው፤ ከወላይታው፤ ከሶማሌው፤ ከአፋሩ፤ ከጉራጊው ወዘተ ወጣት ጋር አብሮ ሲነሳ ከዚህ በላይ ምን መረጃ ያስፈልጋል? ይህ እድል ከፋች ነው።
ዲያስፖራው (አገራችንን ለቀን የወጣን ማለትን እመርጣለሁ) ከኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ከመከላክያ ኃይሉና ኢትዮጵያን ከሚመራት መንግሥት ጋር እጅና ጓንት የሚሆንበት ወቅት አሁን ነው። ባለፈው ባቀረብኩት ትንተናና ምክር እንደ ጠቆምኩት፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን ሌላ እድል አግኝተናልና ይህንን እድል አናባክነው።
ህወሓትና አጋሮቹ፤ ፈረንጆችን ጨምሮ የፈጠሩት ስርዓት ወለድ እና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች መኖራቸው አይካድም። አሁን ግን ኢትዮጵያ ከፈራረሰች እነዚህን ተግዳሮቶች ልንፈታ የምንችልበት እድል ባዶ ይሆናል። ዝንጀሮ እንዳለችው፤ “መጀመሪያ መቀመጫየን” ሆኗል። መጀመሪያ ኢትዮጵያን ከመፈራረስ አደጋ እናድናት። ከዚያ በኋላ በጨዋነት ወደ ሌሎች መሰረታዊ አማራጮች ለመሄድ እንችላለን።
ለማጠቃለ፤ የጠቅስኳቸውን ምክሮች እንዴት ለማጠናከር ይቻላል? 
1. የኢትዮጵያ የአቅም መሰረት ሕዝቧ ነው። በተለይ እድሜው ከሰላሳ ዓመት በታች የሆነው፤ 70 በመቶ የሚገመተው ወጣቱ ትውልድ እምቅ ኃይል ነው። ሁለተኛ ደረጃና ኮሌጅ ጨርሰው፤ ለጊዜውም ቢሆን የስራ እድል የሌላቸው ፈቃደኞች ሁሉ ልዩ ሥልጠናና እንክብካቤ ተሰጥቷቸው በደህንነት፤ በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ ተቋማት እንዲሰራጩ ማድረግ ወሳኝ ነው። ይህ ስልጠና ወደ ፊት ለሚደረገው ድህነትን ቀርፎ ልማትን ለማጠናከር ለሚደረገው ጉዞ ይረዳል። ይህን ምክር የሚያጠናክሩ እንቅስቃሴዎች ስላሉ ይህ ብሄራዊ ጥሪ አስቸጋሪ አይሆንም። ወጣቱ ትውልድ፤ ማንም ኃይል ሳያስገድድው ለኢትዮጵያ መስዋእት እየሆነ ነው።
2. የቀድሞ የደህነትና የመከላከያ ተቋማት አባላት ለአገራቸው ያላቸው ፍቅርና ተቆርቁሪነት እጅግ የሚያኮራ ነው። በአማራው ክልል አመራር ጥሪ ብቻ ጥሪውን የተቀበሉት ተምሳሌትና አርአያ  ናቸው። እነዚህ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ወጣትቱን ግዙፍ ኃይል እንዲያሰለጥኑ ማበረታት አስፈላጊ ነው። ጥራትና ብቃት ሊጨመርበት የሚችልበትን ሁኔት ሊፈጥሩ ይችላሉ።
3. የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት አመራር አሁን የያዘውን ቅጥና አቅጣጫ የማያሳይ፤ ያዝ ለቀቅ ዘዴ ወደ ጎን ትቶ ኢትዮጵያን የመታደግ ብሄራዊ ጥሪ ማድረግ አለበት።
4. በውጭ የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትተን ኢትዮጵያን ለመታደግ ለሚደረገው የሞት የሽረት ትግል በአንድነት፤ ለአንዲት ታሪካዊ አገር መቆም አለብን።
የውጭ ግንኙነት መርሃ ግብርና ፍኖተ ካርታ አስፈላጊ ሆኗል።
5. በአሁኑ ዓለም በተሳሰረበት ወቅት፤ የውጭ አገር ግንኙነት በዳበሳ ሊሰራ አይችልም። ኢትዮጵያን ከጎዷት አስኳል ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ራእይና ፍኖተ ካርታ አልባ የሆነው የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት መርህ ምሰሶዎች (Pillars and anchors of foreign policy and diplomacy) ምንድን ናችው ተብየ ብጠየቅ እኔ መልስ የለኝም።
6. በተለይ ለኢትዮጵያ ህልውናና ብልጽግና አጋር የሚሆኑ የጎረቤት አገሮች የትኞቹ ናቸው? ቢባል ከጂቡቲ፤ ሶማልያ፤ ኤርትራ፤ ኬንያ፤ ደቡብ ሱዳን፤ ዩጋንዳ ወዘተ? መካከል ትኩረት የሚሰጣቸው የትኞቹ ናቸው? እትዮጵያ ከምእራብ አገሮች ጋር፤ በተለይ ከመቶ ሃያ ዓመታት በላይ መልካምና ተደጋጋፊ የሆነ ግንኙነት ከነበራት ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ወደፊት ሊኖራት የሚገባው ግንኙነት ምን አይነት ይሆናል? ኢትዮጵያ አማራጮች አሏት፤ ሩሲያ፤ ቻይና፤ ተርኪ ወዘተ፤ ከእነዚህ ጋር ስትራተጂክ ግንኙነት መፍጠር አስፈላጊ ሆኗል።
7. እኛ በምእራብ አገሮች፤ በተለይ በሰሜን አሜሪካ የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵዊያን በአስቸኳይ ሁሉን አቀፍ የምክክር ጉባኤ ማካሄድ አለብን።
በአሁኑ ወቅት የውይይቱ ትኩረት ኢትዮጵያን ከመታደጉ ላይ ይሆናል። ልዩ ልዩ ጥናቶችና ምርምሮች የሚያሳዩን አስጊ ክስተት አለ። ይኼውም የባይደን መንግሥትና አጋር የሆኑት የተወሰኑ የምእራብ አውሮፓ አገሮች ኢትዮጵያ እንደ ሃገር መቀጠል አትችልም ብለው ደምድመዋል። እኔ ይህንን አኛን እንድንሰጋና በራሳችን ላይ እንዳንተማመን የሚደረግ ድምዳሜ አልቀበልም። ግን፤ ጥንቃቄ ማድረግ ብልህነት ነው። ፈረንጆቹ ኢትዮጵያ እንዳተፈራርስ የሚታገሉና በየቀኑ መስዋት በመክፈል ላይ ያሉ አገር ወዳዶች መኖራቸውንና ካላቸው ቁሳቁስ ለእነዚህ አገር ወዳዶች ስንቅ የሚያቀርቡ እህቶችና እናቶች መኖራቸውን ቢገነዘቡ አርቆ አስተዋይነት ያሳዩ ነበር።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ችግሮቻችን ለመፍታት በግልጽ ለመወያየትና መፍትሄ ለመፈለግ መወሰን አለብን። ፈረንጆቹ በተደጋጋሚ አጀንዳ አውጥተው “ሁሉን አቀድ ድርድርና ውይይት፤ የሽግግር መንግሥት” አድርጉ የሚሉት በራሳቸው ዓላማ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን እገነዘባለሁ።
እኛ ግን፤ ከተባበርንና ከተናበብን፤ አጀንዳውን የኢትዮጵያ አጀንዳ የማድረግ ብቃትና ተመክሮ አለን። ለዚህ ሁሉን አቀፍ ውይይትና በየደረጃው በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ኢትዮጵያዊያን ሊያደርጓቸው የሚገባቸውን ተከታታይ የሆነ ውይይት አድርጎ በመጀመሪያ ደረጃ፤ ኢትዮጵያን በማያሻማና ለድርድር በማይቀርብ ደረጃ ለማስቀጠል ብሄራዊ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን ለድርድር ማቅረብ በማያሻማ ደረጃ መቆም አለበት።
በተጨማሪ ለእርቅ፤ ለሰላምና ለፍትህ መሰረት ለመጣል የባለድርሻዎች ጉባኤ ማካሄድ አስፈላጊ ነው።  የዚህ ሃላፊነት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ አይደለም። ከአጥፊና ከሽብርተኛ ቡድን ጋር ለመደራደር አይቻልም። ጌታቸው ረዳ ለመደራደር ዝግጁ ነን፤ ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የኔን ቅድመሁኔታ ያምሟላ የሚለውን ከውሸትና አዘናጊ ትርክቱ ልለየው አልችልም።
1. Statement on Ethiopia by the Senior Study Group on Peace …https://www.usip.org › press › 2020/11 › statement-ethipia.. Nov 5, 2020 — The U.S. Institute of Peace (USIP)
2 and 3  from Geopolitics post
ኢትዮጵያ አገራችን ለዘላለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic