>

ከአገር ውስጥ አገር የማዋለድ የደባ ፖለቲካ ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ከአገር ውስጥ አገር የማዋለድ የደባ ፖለቲካ …!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

በወያኔ ተንኮል እና በምዕራባዊያን ከአገር ውስጥ አገር የማዋለድ የደባ ፖለቲካ የከፋ አደጋ የተጋረጠባት አገራችን ያለችበት ሁኔታ ከዕለት ዕለት እየከፋ የመጣ ይመስላል። የትግራይ ገበሬዎች እንዲያርሱ እና ሕዝቡም የጥሞና ጊዜ እንዲያገኝ የተወሰነው የተናጠል ተኩስ አቁም ወያኔን ላሊበላ አድርሷታል። የትግራይ ገበሬ እንዲያርስ መፈቀዱ መልካም ሆኖ ሳለ የወሎ ገበሬና የአፋር አርብቶ አደር ወያኔን ሽሽት ከከተማ ከተማ መሰደዱና እንዲንከራተት መደረጉ ደግሞ ግራ የሚያገባ ነገር ነው። ጦርነቱም ከትግራይ ክልል አልፎ ወደ ሌሎች የአገሪቱን ክፍሎች መስፋፋቱ ቀጣዩን የአገራችንን ሁኔታ የከፋ ሊያደርገው ይችላል። ኢትዮጵያን ከወያኔና ከምዕራባዊያኑ የደባ ፖለቲካ መታደግ የሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጏላፊነት ቢሆንም የመንግስት አካሄድ ግልጽነት የጎደለው መሆኑ ግን ሁኔታውን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል።
የላሊበላን መያዝ የአለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲያወሩት እስከ አሁን ከመንግስት የተሰማ ነገር የለም።  የክልሉ ብልጽግና የሰጠው መግለጫ እጅግ ግራ የሚያጋባ ነው። ወያኔ ከመነሻዋ እየራቀች ወደ መሀል አገር መምጣቷ ሞቷን ለማፋጠን ይረዳል የሚል የስልታዊ ማፈግፈግ እንደ አማራጭ መወሰዱን የሚጠቁም ነው። ይህ እጅግ አደገኛ አካሄድ ይመስለኛል። በመሀል ብዙ ንጹሀን ዜጎች ከቀያቸው ይፈናቀላሉ፣ ለወያኔ የጭካኔ በትር ይጋለጣሉ፣ አሸባሪ ለተባለ ቡድን ሕዝብን አሳልፎ መስጠት ለከፋ የሰብአዊ ቀውስ ይዳርጋልም።
Filed in: Amharic