>

ዐቢይ አሕመድ የተናጠል ተኩስ ያወጀው ትግራይ ክልል ውስጥ እንጂ "አማራ ክልል" ውስጥ አይደለም!  (አቻምየለህ   ታምሩ)

ዐቢይ አሕመድ የተናጠል ተኩስ ያወጀው ትግራይ ክልል ውስጥ እንጂ “አማራ ክልል” ውስጥ አይደለም! 

አቻምየለህ   ታምሩ

ዐቢይ አሕመድ ከአንድ ወር በፊት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጌያለው ያለው ትግራይ ክልል ውስጥ እንጂ “አማራ ክልል” ውስጥ አይደለም። ወያኔ ባለፉት ጥቁት ሳምንታት ውስጥ ከትግራይ ውጭ ባካሄዳቸው የዘር ማጥፋት ወረራዎችና ውጊያዎች ያለ ምንም መከላከል ብዙ ወረዳዎችን በቁጥጥሩ ስር እያስገባ ያለው ዐቢይ አሕመድ የተናጠል የተኩስ አቁም ባላደረገበት “በአማራ ክልል” ውስጥ ነው።
በአለም ቅርስነት የተመዘገቡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት የሚገኙበትን የላሊበላ ከተማን ጨምሮ በርካታ የሰሜን ወሎ ወረዳዎችን ወያኔ ቅርስ ወርሮ እያወደመና የዘር ማጥፋት እያካሄደ የሚገኘው ዐቢይ አሕመድ የተናጠል የተኩስ አቁም ባደረገበት በትግራይ ክልል ውስጥ ሳይሆን የተናጠል የተኩስ አቁም ባላደረገበት “የአማራ ክልል” ውስጥ ነው።
ከመጋረጃ ጀርባ በሕዝብ ላይ እየተሸረበ ያለ ድብቅ ሴራ ከሌለ በስተቀር ወያኔ ላሊበላን ጨምሮ በርካታ የሰሜን ወሎ ወረዳዎች  ትቆጣጥሮ ቅርስ እያወደመና የዘር ማጥፋት እያካሄደ መከላከያው ለምን ዝም ብሎ ያያል ተብሎ ሲጠየቅ “መንግሥት ያወጀውን የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት እያከበረ  ስለሆነ ነው” እየተባለ በአገዛዙ በኩል የሚሰጠው  ማስተባበያ ውኃ የሚቋጥር አይደለም።
አገዛዙ  ከአንድ ወር በፊት የተናጠል ተኩስ አቁም አወጅሁ ያለው ትግራይ ክልል ውስጥ እንጂ አማራ ክልል በሚባለው ውስጥ አይደለም። ስለዚህ አገዛዙ የተናጠል ተኩስ አቁም ባላደረገበት “አማራ ክልል” ውስጥ ወያኔ የሚያካሂደውን ወረራና ውድመት መከላከያው ለማስቆም አለመቻሉን ወይም አለመፈለጉን “አማራ ክልል” ውስጥ ያልታወጀው  የአገዛዙ የተናጠል ተኩስ አቁም ጉዳይ እንደ ምክንያት ሊቀርብ አይችልም።
ከላሊበላ በውስጥ መስመር የተላከ. . .  
“ሰላም ወንድሜ አቻሜለህ፤ ይህን መልዕክት የምጽፍልህ ከላሊባላ ከተማ ትንሽ ወጣ ብዬ ነው። የሕወሓት ተዋጊዎች ያለማንም ከልካይነት ላሊበላን  የያዙት ትናንትና ከ11፡30 ጀምሮ ነው። በአሁኑ ወቅት በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚገኙ ለብዙ ሺ ዘመናት የኖሩ ጥንታዊ መጽሐፍትንና ቅርሶችን እየዘረፉ ይገኛሉ። ትናንትና ማታ ከጨለመ በኋላ እኔ ወዳለሁበት ቦታ ሸሽተው የቤተክርስቲያኑ እንደነገሩኝ ተዋጊዎቹ ቅብ መጽሐፍትን፣ የብራና መጽሐፍትንና ሌሎችንም ብርቅዬ ቅርሶችን ማታ ሲያስወጡ እንዳመሹ ደም እያነቡ ነገሩኝ።  እሳቸው በድብቅ ቤተ ክርስቲያኑን ለቀው ለመንግሥት ለመጮህ በወጡበት ወቅት ከሞትንም እንሙት ብለው እዚያው ያልሸሹ አባቶችን የደበቃችሁት የወርቅ ቅብና የብራና መጽሐፍትና እንዲሁም ብርቅዬ የአለም ቅርስ አለ፤  ከደበቃችሁበት አውጡት እያሉ እየደበደቡ ነበር አሉኝ።  እስካሁን ድረስ የክልሉም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ኃይል የላሊበላን ዘረፋ፣ ውድመትና ምዝበራ ለማስቆም ወደዚህ አልመጣም። እጅግ ልብ ይሰብራል።
*    *    *
የህወሓት አማጺያን ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ የላሊበላ ከተማን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ
ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በከተማዋ አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች የአማጺያን እንቅስቃሴ መኖሩ ሲነገር መቆቱን ቢቢሲ ያናገራቸው የላሊበላ ከተማ ነዋሪዎች ዛሬ ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰም የህወሓት አማጺያን ሐሙስ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ “ገነተ ማርያም ተብሎ በሚጠራው በኩል ወደ ከተማዋ ገብተዋል” ሲሉ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሮይተርስ የዜና ወኪልም የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ከትግራይ ክልል የተነሱት ኃይሎች በተባበሩት መንግሥታት በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙባትን የላሊበላ ከተማን መቆጣጠራቸውን ዘግቧል።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ የምትገኘው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ከክልሉ ዋና ከተማ ባሕር ዳር በስተ ምሥራቅ 310 ኪሎ ሜትሮች እንዲሁም የህወሓት አማጺያን መቀመጫ ከሆነችው መቀለ በስተደቡብ 348 ኪሎ ሜትሮች ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት።
አማጺያኑ ወደ ከተማዋ ሲገቡ ምንም አይነት ውጊያም ሆነ ተኩስ እንዳልነበረ ከንቲባው ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን አማጺያኑ “ከተማዋን ይዘዋል” በማለት በርካታ ለደኅንነታቸው የሰጉ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እወጡ መሆናቸውን ምክትል ከንቲባው ገልፈዋል።
ጨምረውም በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተኩስ ድምጽ እንደማይሰማ የተናገሩት ከንቲባው፤ “የህወሓት ታጣቂዎች በከተማዋ የሚገኙ ጥንታዊ ቅርሶችን ያወድማሉ የሚል ስጋት መፈጠሩን” ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከላሊበላ ከተማ ውጪ እንደሚገኙ የተናገሩት ከንቲባው፤ “ከፌደራል እና ከክልል መንግሥት ጋር ኃይል እንዲገባ እና ቅርስ እንዲታደግ ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል።
“ይህ የመላው ዓለም ሕዝብ ቅርስ ስለሆነ የዚህ ቅርስ ደኅንነት እንዲረጋገጥ ግፊት መደረግ አለበት” ብለበት ሲሉ ምክትል ከንቲባው ስጋታቸውን ገልፈዋል።
ከአለት ተፈልፍለው የተሰሩት የጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት መገኛ የሆነችው የላሊበላ ከተማ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ትልቅ ከተሞች መካከል አንዷ ስትሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቱሪስቶችን የምታስተናግድ ከተማ ናት።
ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ በህወሓት ኃይሎች እጅ መግባቷን በተመለከተ የአማራ ክልልም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት አስካሁን ያሉት ነገር የለም።
በትግራይ ክልል ውስጥ ለስምንት ወራት የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት ከአንድ ወር በፊት የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ያስወጣ ቢሆንም የህወሓት ኃይሎች የጥቃት አድማሳቸውን ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልል በማስፋት የተለያዩ ቦታዎችን መያዛቸው ይታወሳል።
አማጺያኑ ጥቃት ከሰነዘሩባቸውና ከተቆጣጠሯቸው የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከ200 ሺህ በላይ እንዲሁም በአፋር ክልል ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉ የክልሎቹ ባለሥልጣናት ይናገራሉ።
የህወሓት ኃይሎችን አመራር ናቸው የሚባሉት ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ከቀናት በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በኩል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየሰነዘሩ ያሉት የተኩስ አቁም ለማድረግ ያስቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች የፌደራሉ መንግሥት እንዲቀበል ጫና ለማሳደር መሆኑን ተናግረው ነበር።
Filed in: Amharic