ዕድለኛዋ ከተማ…!!!
ዘመድኩን በቀለ
… አስተዳዳሪ ማለት እንደ ወላጅ አባት ያለ ማለት ነው። ለልጆቹ ህይወት መሻሻል እንቅልፍ አጥቶ እንደሚባክን አባት፣ ቤተሰቡ ተኝቶ እሱ የሚሠራ፣ የማያርፍ አባት እንደ ማለት ነው። ዐመለ ብዙ ልጆቹን አቻችሎ የሚያስተዳድር። ያጠፋ ቀጥቶ፣ የበረታውን ሸልሞ መርቆ የሚያሻግር አባት ማለት ነው። በቤተሰብ ደረጃ ስናየው የጥቂቶች፣ በሰፈር፣ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በከተማና በሃገር ደረጃ ስናየው ደግሞ የሺዎች ወይም የሚሊዮኖች አባት እንደ ማለት ነው። አባት የቤት አጥር ቅጥርም ነው። አባት ደግሞ ሞገስ ነው። መኩሪያ መመኪያም ነው። አስተዳዳሪም እንደዚያው።
… እንዲህ ዓይነት አባት የሚያገኙት ደግሞ ሲበዛ ጥቂቶች ናቸው። ያውም ዕድለኞች የሆኑ። አባት ጠላት ሲመጣ አይሸሽም። ቤተሰቡን አጋፍጦም አይሮጥም። አያመልጥም። ልጆቹን ሚስቱን ለአውሬ አይሰጥም። እሳትም ጎርፍም፣ ጠብም ቢሆን ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ከፊት ለፊት ቆሞ ይወጣዋል። ለልጆቹም ብርታት ነው። ወኔም ነው የሚሆናቸው።
… በዚህ ረገድ አሁን በኢትዮጵያ የወልድያ ከተማ ዕድለኛ ሆና ተገኝታለች። እንቅልፍ አልባ አስተዳዳሪ አግኝታለች። ሲሾም በገባው ቃል መሠረት ታች ወርዶ የሚሠራ፣ የማያሸብር፣ የማያስበረግግ። የሚመጣውን ሁሉ በፅናት እንወጣዋለን የሚል፣ ከህዝቡ ፊት ለፊት ቆሞ በርቱ፣ አይዟችሁ፣ ከእናንተ በፊት እኔን ያስቀድመኝ የሚል ጊዜ አምጦ የወለደው ጀግና አግኝታለች። ወልድያ እንዲህ ያለ ጽኑዕ አስተዳዳሪ ማግኘቷን ሁላችን ምስክር እየሆንን ነው። የተሾመበትን ቃልኪዳን የጠበቀ መሪ ነው ያገኘችው።
… አብዛኛው የብአዴን ባለሥልጣን ቤተሰባዊ ነው። የአማች፣ የቤተ ዘመድ ሥልጣን ነው። የውርስ ሥልጣን የብዛዋል። የአቶ ገዱ ቤተሰብ፣ የበረከት ቤተሰብ፣ የእገሌ ቤተሰብ እያለ መሳሳብ ይበዛዋል። የጦርነትም ሆነ የሰላምም መረጃ ቀድሞ የሚደርሰው ይሄው ቤተሰብ አስተዳደር ነው። ከአዲአርቃይ ቀድሞ የሸሹት አስተዳዳሪዎቹ ናቸው። ህዝቡ ጠዋት ሲነሣ ለህዝቡ እንኳን ጠላት እንደመጣበት ሳይነግሩት ጎንደር ነው የገቡት። በመንግሥት መኪና፣ በህዝብ ሀብት። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደሮችም እንዲሁ ቀድመው ነው ነቅለው የወጡት። የቀሩት ተረሽነዋል። የአላማጣ መሪዎች ቆቦ ቀድመው መጥተው ህዝቡን እንዲሸሽ የቀሰቀሱት እነርሱው ናቸው ተብሏል። የቆቦዎቹማ ጭራሽ እንደሰማችሁት ቤታቸው ሲፈተሽ ከህወሓት ጋር የሚገናኙበት መንግሥት የማያውቀው የመገናኛ ራድዮና ባንካቸው ሲፈተሽ ደግሞ በሚልዮን የሚቆጠር ብር ነው የተገኘው። እንዲህ ዓይነትም በድን ከሀዲ አስተዳዳሪም አለ።
… ወደ ወልድያ ስንመጣ ግን ከዚህ የተለየ ነገር ነው የምናገኘው። ጀግና፣ ቃልኪዳኑን የጠበቀ። ልክ እንደ ሃይማኖተኛ ባል ከሳሽ ጠቆርሽ፣ አጣሽ ነጣሽ ብዬ ላልከዳሽ ቃል ገብቻለሁ እንደሚል ባል ወልድያ ሽብር በተነዛባት ወቅት ያልከዳ፣ ሸሽቶ ሽሹ ያላለ። ተሸብሮ ያላሸበረ፣ በጽናት የቆመ። ሌሊት ሳይቀር እንቅልፍ አጥቶ ወጣቶችን ያደራጀ። የመራ፣ ያስተባበረ ጀግና መሪ ነው የተፈጠረው።
… አስተዳዳሪው አቶ መሐመድ ያሲን ይባላል። አቶ መሐመድ በመጀመሪያ የወሰደው “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ነውና በመጀመሪያ ወሬ የሚወራበትን ቦታ ነው ሁሉ የዘጋው። ዋነኛው የወሬ ምንጭ የሚመረትበትን የጀበና ቡና የሚሸጥባቸውን ስፍራዎች በሙሉ አስነሣ። ጠረቀመ። ፀጉረ ልውጦቸን እየለቀመ፣ በተለይ ከተማ መሃል ቆመው ስለ ህወሓት ጀግንነት፣ ስለ ራያ ህዝብ መዘረፍ፣ መገደል፣ መረሸን በአደባባይ ልክ እንደሰባኪ ህዝብ ሰብስበው የሚደሰኩሩ፣ ፍርሃት የሚነዙ፣ ህዝቡ ወልድያን ለቅቆ እንዲሰደድ ያበረታቱ የነበሩትን ወሬኞች በሙሉ እያሳፈሰ አስገባቸው። ቀድሞ የሸሸው እንጂ ኋላ ላይ ለመሸሽ የተዘጋጀው ሁሉ የስነ ልቦና ጦርነት የሚያመርተው ምንጭ ስለደረቀ ተረጋጋ። በምትኩ ጀግኖቹ አየሩን ተቆጣጠሩት።
… የወልድያ ህዝብ ሌላው የፈጸመው ጀግንነት መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ሆነው አስቀድመው ጦሩን ይዘው ከተማ ውስጥ በመግባት ድንገት ታንኩን፣ ኦራሉን ወታደሩን ይዘው በግርግር ህዝቡን አስደንብረው የሚያስወጡትን የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ መንገድ በመዝጋት የት ነው የምትሄዱት? ለማን ጥላችሁን ነው የምትሸሹት? በማለት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንጥፈው ወንድ የሆነ ረግጧት ይሂድ በማለት መከላከያውን አንገት አስደፍተው ወደ ጦር ግንባር እንዲመለስ አደረጉት። ይሄ ነው ጀግንነት።
… ቀጥሎ ያደረጉት ነገር መደራጀት ነው። ከተማዋን ጉራንጉሯ ድረስ ሮንድ ያደርጋሉ። ፀጉረ ልውጥ ሲገኝ ወደ ሕግ ያቀርባሉ። የደቦ ፍርድ የለም። ወልድያን ጠላትም ወዳጅም እንዳይከሳት አድርገው ነው ያጠሯት። የወሬ ቦታዎችን ጠርቅመው ዘጉ። በፌስቡክ ገጻቸው በየሰዓቱ መረጃ ለህዝብ ያቀርባሉ። የወልድያ ትልቁ ጀግንነት ይሄም ነው። ወልድያ ተያዘች ተብሎ ሲወራ የወልድያ አስተዳደር በፍጥነት ወጥቶ “ውሸታም” በማለት ያለውን ነባራዊ አሁናዊ እውነታ ለህዝብ ያቀርባል። ተራሮችን፣ መግቢያ መውጫዎችን ያስጠብቃል። በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ሃገር የጎደለውን ትኩስ መረጃ ለህዝብ በፍጥነት አድርሶ የማረጋጋት ሥራውን ጉድለት የወልድያ አስተዳደር በጀግንነት ተወጥቶታል። ምስጋናም ሲያንሰው ነው።
… ሌላው የሃይማኖት አባቶች ሚና ነው። ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስና ብፁዕ አቡነ ቄርሎስም ፈጸሙት የተባለው ነገርም አስደናቂ ነው። በተለይ አረጋዊው አባት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ” በኋላ የተባሉት ሽፍቶች የገቡ እንደሆን እንዳይቸገሩ እርስዎ እንኳን ወደ አዲስ አበባ ይሂዱ” ሲባሉ በፍፁም አላደርገውም፣ የሚመጣውን ሁሉ ከህዝቤ ጋር እዚሁ አብሬ እቀበለላለሁ ብለው መቅረታቸው ነው የተነገረው። ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስም ህዝቡን የትም እንዳትሄዱ በማለት ሲያጽናኑ፣ ዛሬም ህዝቡን በምህላ በጸሎት በቃለ እግዚአብሔር ሲያንፁት ማርፈዳቸው ተሰምቷል። ዓለማዊው ህዝብ አስተዳዳሪው አቶ መሐመድ ያሲንን አይቶ። መንፈሳዊው ህዝብ ሊቃነ ጳጳሳቱንና ሼኪዎቹን አይቶ እንዴት ሊፈራ፣ ሊሰደድ ይችለል?
… የእግዚአብሔርም ቃል እንዲህ ነው የሚለው። “… እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ ።” ዘካ 13፥7። እረኛው ከተመታ በጎቹ መበተናቸው የግድ ነው። ጀነራሉ ከሸሸ፣ አዋጊ ኮሎኔሉ ከሸሸ፣ የከተማው አስተዳደሪ ከሸሸ፣ የሃይማኖት አባቶች ወደ አዲስ አበባ ከፈረጠጡ፣ ህዝብ ምን ያድርግ? ፖሊስ ከሌለ፣ ሚኒሻ ከሌለ፣ ህዝቡስ ምን ይሠራል? ለኢትዮጵያ ልክ እንደ አቶ መሐመድ ያሲን ያሉ መሪዎችን ይስጥልን። ዐማራ በሙሉ እንዲህ እንደ ወልድያ የወልድያን ተሞክሮ ወስዶ ቢንቀሳቀስ ድሉ ቅርብ በሆነለት ነበር። መሳሳብ፣ መካሰሱን አቁሞ ወልድያን መምሰል ነው። ለህወሓት 4 ኪሎ ሳይሆን ወልድያ መግባት ነው የከበዳት። ውሻና ፈሪ ከሮጡለት ይባል የለ። እንደዚያ ነው።
… ሰላም ሲሰፍን እንደተለመደው ህዝቡን አጋፍጠው የፈረጠጡት የሃይማኖት አባቶችና የመንግሥት ሹመኞች ሁሉ በአጀብ ተመልሰው አስተዳዳሪ እንሁን ማለታቸው አይቀርም። በመከራ ጊዜ የከዳን አስተዳዳሪ በሰላም ጊዜ መቀበል ኃጢአት ነው። ጠብቁ ብቻ።
… ድል ለኢትዮጵያ ሃገሬ። ውድቀትና ጥፋት ለጠላቶቿ።