እንኳን አደረሰን!
አበባዮሽ እንበል ለእናት ኢትዮጵያ
ለጥቁር ሕዝብ ተስፋ የዘላለም መኩሪያ
ለክርስቲያን ሙስሊሙ ሕብረቱ ማደሪያ
ለወራሪ ሀይሎች ቅዠት መቀበሪያ
ሀገሬ መሬትሽ ድንግል ምድር እንቁ
የውሀ ምንጮችሽ ውስጥሽ የሚፈልቁ
ካንቺ ቢፈልሱ ወጥተው የማይደርቁ
ጥምን የሚያረኩ ሀገር የሚያጠምቁ
ክረምት እያለፈ መስከረም ሲጠባ
ዘመንሽ ዘምኖ ልንል አደይ አባ
ለእንኳን አደረሰን ስንደርብ ካባ
በሰላምታው ቃና አበብሽ አበባ
እንኳን አደረሰን ሲለን ሁሉ ማልዶ
የወጣውም ገብቶ ከውጭ ባህር ማዶ
ሲታይ በሀገርቤት ሲያደርግ መሰናዶ
የአውዳመቱ ሽታው ኢትዮጵያን አውዶ
ወላጅ ከልጆቹ ከቤት ተሰብስቦ
ጎረቤት አዝማዱም ሰላምታ ታጅቦ
ለዘመን መቋጫ ሲያበራ ያን ችቦ
ሁሉ በየቤቱ ደጃፍ ተሰብስቦ
ዋዜማውም ሲደርስ ሽር ጉድ ሚለው
በግ ዶሮ አማርጦ ለሰንጋ ለቅርጫው
አራሹ ገበሬው ገጠሩ ከተሜው
ላውድመቱ ክብር ሆኖ በየስፍራው
አሮጌው ሊከደን አዲሱ ሊገባ
በዕንቁ ጣጣሽ ዕለት በአደይ አበባ
በለጋ ሕፃናቱ ጭፈራ ወሸባ
በአዲሱ አመትበዐል ቀን ልማድና ጀባ
ሀገር ልጅ ሲያከብር መለወጫ ዘመን
አሮጌውም አልፎ ሲሆን አዲሱ ቀን
ፈጣሪያችን ሲባል ክበርም ተመስገን
ሰላምታ ሲለወጥ በእንኳን አደረሰን
ልጅና አዋቂው እመት ወይዛዝርቱ
የሀገር ጠባቂው ጀግና ሰራዊቱ
ቀኑን ሲያወድስው አቤት ማስደሰቱ
ከብረው ይቆዩልን ሲሉ ሕጻናቱ
እንቁ አበባችን ውዷ ሀገራችን
ኑሪልን በሰላም ሆነሽ ለክብራችን
እምዬ ኢትዮጵያ የእኛ እናታችን
እንኳን አደረሰን ሀበሾች ሁላችን !
በዘምሳሌ አብረሐም