>

የክላሽ አብዮት....!!! ሳታማካኝ ብላኝ.....!!! (ኤርሚያስ ለገሰ )

የክላሽ አብዮት….!!! ሳታማካኝ ብላኝ…..!!!

ኤርሚያስ ለገሰ 

ዓብይ አህመድ  እጅግ አነጋጋሪና አስገራሚ ዲስኩር አሰምቷል።
የኢትዮ-360 <<ዛሬ ምን አለ?>> ፕሮግራምም ንግግሩን መሰረት አድርገን ተወያይተንበታል። እስቲ ዓብይ አህመድ ምን ተናገረ?፤ የንግግሩ ጭብጦች
ምንድናቸው? በቀጣይ ሳምንታት ምን ሊፈጠር ይችላል? የሚለውን እንመልከተው።
 
1. ዓብይ አህመድ ምን ተናገረ?
ዓብይ አህመድ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንትን ትከሻ መታ መታ እያደረገ (“ዓብይ የነካው በሙሉ…” የሚለውን ልብ ይሏል) እንደሚከተለው ተናግሯል፣
” የክልል አመራሮች ክላሽ ላይ ያለውን አብዮት አስቁማችሁ ወደ ፓምፕ አምጡ!…ታጠቅ፣ ተደራጅ፣ ዝመት የሚባል ነገር ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም!.
..ታጠቅ ለፓምፕ፣ ለትራክተር፣ ለኮምባይነር!…እኛ ከጠገብን ማን አባቱ ይነካናል?… እየራበህ ክላሽ ብትታቀፍ ድንጋይ እንደመታቀፍ ነው!
ትርጉም የለውም!”
2. የንግግሩ ጭብጦች
በእኔ አተያይ ዓብይ አህመድ ማስተላለፍ የፈለገው ማዕከላዊ መልዕክት ጭብጦች የሚከተሉት ናቸው።
2.1. “የክላሽ አብዮት የሚያቀጣጥሉት የክልል አመራሮች ናቸው! እኔ ዓብይ አህመድ የክላሽ አብዮት ውስጥ የለሁበትም!” እያለ ነው።
(ዲስኩሩ የተነገረው የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ትከሻ ነካ!ነካ! እየተደረገ መሆኑን ልብ ይሏል)
2.2. “ለጦርነት ተነስ! ታጠቅ! ተደራጅ! ዝመት! የሚለው ኢትዮጵያን አይጠቅማትም፤ እኔ ዓብይ አህመድ ለጦርነት ተነስ! ታጠቅ! ተደራጅ! ዝመት!
የሚባለው ዘመቻ ላይ የለሁበትም” እያለ ነው።
( ሽመልስ አብዲሳ የአማራ ክልል አመራሮችን ” እኛ አምርተን እንመግባችኃለን፣ እናንተ ሚሊሻ አምርቱ” ማለቱን ልብ ይሏል።)
2.3. “እኔ ዓብይ አህመድ ተነስ! ታጠቅ! ተደራጅ! ዝመት! የምለው ለሜካናይዜሽን እርሻ ነው፤ ለፓምፕ፣ ለትራክተር፣ ለኮምባይነር!ነው” ይለናል።
(የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ሶስት ዓመት ሙሉ እየዞረ በሺዎች የሚቆጠሩ ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮችና ዘመናዊ ማሽኖች በክልሉ ውስጥ
ማደሉን ልብ ይሏል።)
2.4. “የክላሽ አብዮት አቀጣጣዬች <<የምትበላው የላት፤ የምትከናነበው አማራት!>> አይነት ናችሁ፤ እስቲ መጀመሪያ ቀና ብላችሁ እንድትሄዱ፤
እንዳትደፈሩ ክላሽ ከመያዛችሁ በፊት ሆዳችሁን ሙሉ” ነው ያሉት።
3. በቀጣይ ሳምንታት ምን ሊፈጠር ይችላል?
3.1. በአማራ ክልል ማሕበረሰቡን በማነሳሳት፣ በማደራጀት፣ በማስታጠቅና ማዝመት ላይ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ኃይሎች እርምጃ ሊወሰድባቸው ይችላል።
ይህን ተከትሎ ‘የብአዴን ብልጽግና’ ለሶስት ሊሰነጠቅ ይችላል። አብዛኞቹ (ከ90 በመቶ በላይ) የክላሽ አብዮትን አውግዘው መስመራቸውን ያስተካክላሉ። እምቢ የሚሉ ሚኒስትሮች በሙስና ተጠርጥረው የፀረ-ሙስና ክስ ይላክላቸዋል።
ዋነኞቹ የአማራ አደራጅ ኃይሎች ደግሞ ‘በብአዴን የብልጽግና መንግስት’አስፈፃሚነት እግረ ሙቅ ይጠልቅላቸዋል።
3.2. በኦህዴድ ብልጽግና ውስጥ ታጠቅ! ተደራጅ! ዝመት! የሚሉ አመራሮች ከኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራቸዋል።
(አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢሳት ዜና ውስጥ አድሮ ” የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በሸኔ ተጠልፋል” እንዲባልና የፊት ገፅ እንዲሆን ያደረገውን ልብ ይሏል።)
3.3. የመንግስት፣ የገዥው ፓርቲና ተደጋፊ ተደማሪው ሚዲያ የዘገባ አቅጣጫ ይቀየራል። “እያጠቃን ነው!” የሚለው የፕሮፐጋንዳ አቅጣጫ ወደ “
የተሰነዘረብንን ጥቃት እየተከላከልን ነው!” ወደሚል ይቀየራል። ምናልባትም አንዳንዶቹ አልፈው ሄደው “ውይይት፣ ድርድር” የሚሉበት ሁኔታ ሊፈጠር
ይችላል።
Filed in: Amharic