>

የብሔርፖለቲካይታደግ... !! (ቴዎድሮስ ሀ/ማርያም -  ዘብሄረ ኢትዮጲያ )

የብሔርፖለቲካይታደግ… !!! StopEthnicPolitics …!!!
ቴዎድሮስ ሀ/ማርያም –  ዘብሄረ ኢትዮጲያ 

*,,, ለኔ ከየትኛውም ዘር ይምጣ ኢትዮጲያዊ የሆነ ሁሉ እኩል ወገኔ ነው። 
ኢትዮጲያ ከሰማይ በታች ታላቋ የፈጣሪ ስጦታዬ ናትና እተዋት ዘንድ አይሆንልኝም። እክዳት ዘንድ አይቻለኝም። አገሬ ባባቶቼ አጥንት የተማገረች፣ በናቶቼ ደም የቀለመች፣ በክብር ተረክቤ በክብር ለትውልድ አወርሳት ዘንድ በኪዳን የታሰርኩባት አደራዬ ነች።
እነሆ ሀገሬ በብርቱ ታማለች። ዘረኝነት መለመላዋን አስቀርቷታል። ለአመታት የተዘራው የትርክት መርዝ የሰራ አከላቷን በክሏታል። የአንድነት እና የፍቅር ተምሳሌትነቷ በጥላቻና በቀል አራሙቻ ተውጧል። የምስራቋ ፀዳል ኢትዮጲያ የጨለማ በርኖስ አጥልቃለች።
አዎን ዘረኝነት ፍቅርን ገዝግዞ የሚጥል ደዌ ነው። ዘረኝነት ህዝብን ከህዝብ የሚያባላ መርገምት ነው።
እኔ ከኢትዮጲያ በቀር ሀገር ፣ ካንድነቷ በቀር ምርጫ የለኝም። ሀገሬ ተበትና ከማዬት የከፋ ሞት አይታዬኝም። ለዚህ ሁሉ መአት የዳረጋት ዘረኝነት ነውና፣ አምላክ በሰጠኝ አቅም ሁሉ ዘረኝነትን እቃወማለሁ። አገሬን ሳፈቅር ከነ መላ ህዝቧ ነውና በዘረኝነት የተሰናከሉ ወገኖቼን ሳይቀር አፈቅራለሁ። አንድነትን ስላቀነቀንኩ ዛሬ ላይ ይወዱኛል ባልልም፣ በዚህ አቋሜ በፀናሁ ቁጥር ልባቸው ለፍቅር ተሰብሮ መልሰው ይወዱኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፣  በሀገሬና በወገኔ ተስፋ የምቆርጥ ጨለምተኛ አይደሉሁምና።
አገሬ የቱንም ያህል አደጋ ላይ ብትሆን አገሬነቷ አይቀርም። ይልቁንም በፈተናዋ ጊዜ ለሷ ያለኝ ፍቅር፣ ለሷ ያለኝ ስስት ይበረታል። የኢትዮጲያን፣ የእምዬ ሀገሬን መከራ መቀበል ለኔ ቅድስና ነው። ስቃይዋን መሰቅዬት ለልጅነቴ ምሉእነት ነው።
መቼም ቢሆን የሀገሬን ፈተና እቋደስ እንደሁ እንጂ እንዳልክዳት ለራሴ ቃል እገባለሁ። ቃሌን አጥፌ ብገኝ ፈጣሪ ይፍረድብኝ ስል የኪዳኔን ብርቱነት ባደባባይ አውጃለሁ። ማንም ቢተውሽ ሀገሬ ሆይ አልተውሽም። ማንም ቢክድሽ እናቴ ሆይ አልክድሽም። አንቺን ባልኩ እከበር ይሆን እንጂ አላፍርምና በአንደበቴ አወድስሻለሁ፣ በመንፈሴ አነግስሻለሁ፣ ልቤ ላይ እነቀስሻለሁ። ኢትዮጲያ ሆይ ደክመሽም፣ መንምነሽም፣ ተጎሳቁለሽም ለኔ እናቴ ነሽ። ሀገሬ ሆይ ሁሌም ብርቄ፣ ሁሌም ድንቄ፣ ሁሌም ሙሽራዬ ነሽ። ዞሮ መግቢያ ቤቴ ፣ ማኩረፊያ ጥጌ፣ መጎናፀፊያ ጌጤ ነሽና በክብር ለዘላለም ኑሪልኝ።
አምላክ ሆይ አገራችንን፣ እምዬ ኢትዮጲያን ካስፈሪው መአት ጠብቅልን!!!
የዘረኝነትን ክንፍ ስበርልን፣  የጠላቷን ጉልበት ቄጠማ አድርግልን!!!
አምላክ ሆይ ለአንድነቷ የቆሙትን አፅና፣ በዘረኝነት የተነጀሱትን ፈውስ
Filed in: Amharic