>

የኢትዮጵያን አንድነት የማስከበር ምክንያትና መንገዱ ምን ይሆን ? (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

የኢትዮጵያን አንድነት የማስከበር ምክንያትና መንገዱ ምን ይሆን ?

ደረጀ መላኩ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


እንደ መግቢያ

አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ ጠንካራ ሉአላዊት ሀገር መሆኗ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ከጠላቶቿም ሆነ ከወዳጆቿ ጋር የምታደርገው ንግግርም ሆነ ውይይት በመከባበር ላይ የተመሰረተ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ከሁሉም ሀገራት ጋር ቁጨ ብላ ለመደራደር ችሎታ ታገኛለች፡፡ አንድነቷ የላላ ኢትዮጵያ ግን ደካማና የወደቀች ሀገር የመሆኗ እድል የሰፋ መሆኑ አይቀሬ ሀቅ ነው፡፡

የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ አላማ አንደነት ለኢትዮጵያ አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ ለማሳሰብ ነው፡፡አንደነቷ የተጠበቀች ኢትዮጵያ የተረጋጋች፣ ሰላም የሰፈነባትና የምጣኔ ሀብቷ እየጎመራ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ወደ መለያየት የሚወስደውን አሜኬላ መንገድ መከተል፣ ልዩነትን ብቻ አጉልቶ ማጮህ ህሊናን የሚረብሽ ብቻ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ስለ መለያየት ብቻ የሚደረግ ዲስኩር ለኢትዮጵያ አይበጃትም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ኢትዮጵያን ከከሸፉ ሀገራት ተርታ ጎን ሊያሰልፋት ይቻለዋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ጽሁፍ ላይ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለመመርመር እሞክራለሁ፡፡ እነኚህም የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. ኢትዮጵያ የፌዴራል ስርዓት ተከተለች አልተከተለች ኢትዮጵያ አንድነቷ የተጠበቀች ሀገር እንድትሆን የተፈለገው ለምን ይሆን ?
  2. የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ የአጭር ግዜም ሆነ እረጅም ግዜ መንገዱ ምን ይሆን ?

ኢትዮጵያ አንድነቷ የተጠበቀ ሀገር እንድትሆን የተፈለገበት ምክንያት

ኢትዮጵያ አንድ ሀገር እና አንደነቷ የጠበቀ ሀገር እንድትሆን የተፈለገው በሚከተሉት መሰረታዊ ምክንያቶች ናወ፡፡

  • ዋነኛውና መሰረታዊ ምክንያቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዘመናት አብሮ ተፋቅሮ፣ተከባብሮና ተቻችሎ መኖሩ
  • ለብዙ ዘመናት በተመሳሳይ የጂኦግራፊ ክልል ፣በተቀራረበ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ ህዝቡ መኖሩ፡፡
  • ከኢትዮጵያ የታሪክ እውነት እንደምንማረው የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ዘመናት ከጥላቻ ይልቅ በትብብር መኖሩ፡፡
  • ተገንጣዮችና አክራሪ ብሔርተኞች እንደሚደሰኩሩት እና የሀሰት ትርክት እንደሚያቀርቡት ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት በፍቅርና አንድነት መንፈስ ነበር የኖረው፡፡

እኔ ዛሬ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ክለሳ እያደረኩ አይደለም የምገኘው፡፡ስለ የጋራ ታሪካችንንም ለመከለስ አይደለም የተነሳሁት፡፡ በብዙ የታሪክ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ የብዙ ክፍለ ዘመን የአንድነት ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በዚህ የረጅም ዘመን የታሪክ አውድ ውስጥ ግጭቶች አልንበሩም ማለት አይደለም፡፡ በብዙ ምክንያቶች የርስበርስ ጦርነቶች ተካሂደው ነበር፡፡ ይህ ግን የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ውስጥ ጥሎት አያውቅም፡፡ ይህ ታሪካችን አንዱ አካል ነው፡፡ እኛ ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር ከባለፈው ውድቀታችን በመማር ያንኑ ተመሳሳይ ስህተት ላለመደግም ቢሆን መላካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የተለያዩ ነገዶች ለዘመናት ሲኖሩ የራሳቸው ቋንቋ በመናገር፣ ከራሳቸው ባህል ጋር ያለምንም ጣልቃ ገብነት እንደኖሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በሌላ በኩል ያለምንም ጦርነትና ግጭት መፍታት የሚቻሉ ችግሮቸን በሰላማዊ ድርድር መፍታት እየተቻለ መገንጠልን የሚያቀነቅኑ አክራሪ ብሔርተኞች ወደ ግጭት፣ ጦርነት ውስጥ በየግዜው መግባታቸው ሲታይ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ በኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት የሚታገሉ አንዳንድ ድርጅቶች፣ ከጦር መሳሪያ ይልቅ በሰለማዊ ንግግር ቁጭ ብለው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ለመነጋገር ቢሞክሩ ለኢትዮጵያ አንድነት ይበጃል ብዬ አስባለሁ፡፡ የእኔ ፍርሃት አሁን በህይወት ያሉት የነጻ አውጪ ግንባር መሪዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶቻቸውን ከመሰረቱት መሪዎች በበለጠ ስሜታዊና  በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር ሆነው አለን የሚሉትን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመወያየት ያመነታሉ፡፡ ፍላጎታቸው ወሰን ያለው አይመስልም፡፡ የነጻ አውጪ ግንባሮች ብረት አንስተው መታገል ግብራቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ አይበጃትም፡፡ ኢትዮጵያ የምሻው የሰለጠነ ንግግርና ውይይትን ነው፡፡

በእኔ አስተሳሰብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሚያለያያቸው ነጥቦች ይለቅ አንድ በሚያደርጋቸው ነጥቦች ቢያተኩሩ ይሻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከህይወት ልምዳችን በመነሳት እንደተማርነው አብዛኛው የሰው ልጅ ፍላጎት ሰላምን መሻት ነው፡፡ ሰላም ካለ ሁሉም በተሰማራበት ሙያ ላይ ለመሰማራት እድሉን ያገኛል በመጨረሻም የስራው ውጤት ተቋዳሽ መሆኑ አይቀሬ ይሆናል፡፡

አንድ ግለሰብ ወይም ማህበረሰብ የስራውን ፍሬ ማግኘት ከቻለ ደግሞ ሀገር ወደ እድገት ጎዳና እንደምጓዝ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ስለሆንመ ኢትዮጵያውያን በጎሳ ፖለቲከኞች ሃሳብ ሳይጠለፉ ከልዩነታቸው ይልቅ በአንድነት ላይ እንዲያተኩሩ እንማጸናለን፡፡

ሁለተኛው መሰረታዊ ምክንያት ( ማለቴ የኢትዮጵያ አንድነት መጠበቅ አለበት በማለት የተነሳሁበት ሌላው ሁነኛ ነጥብ ማለቴ ነው፡፡) ከአንደኛው ምክንያት ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ በብዙ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ጥናት መሰረት በአሁኑ የምጣኔ ሀብታቸው መሰረት በኢትዮጵያ ግዛት ከተካለሉት ክልሎች መሃከል አንዳቸውም ለብቻቸው ሆነው ራሳቸውን በኢኮኖሚ አኳያ አይችሉም፡፡ ሁሉም ይህንን መራር እውነት ያውቁታል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አክራሪ ብሔርተኞች የጦርነት ታምቡር በመምታት እራሳችንን መቻል አያቅተንም ይላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ሃላፊነትን እንደ አለመወጣት ብቻ የሚቆጠር አይደለም፡፡ ከባድ ወንጀልም ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንኳን እኛ ድህነት ቤቱን የሰራብን ኢትዮጵያውያን ቀርቶ የሰለጡንት አውሮፓውያን ተለያይተው መኖር አልቻሉም፡፡ ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆኑን የቀድሞዋ ሦቪዬት ህብረት አባል የነበሩት በርካታ የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ሪፕብሊክ ግዛቶች የነበሩት ( እንደ ካዛኪስታን፣ኪሪጊስታን..ወዘተ ወዘተ ) የደረሱበትን አሳዛኝ ሕይወት ማስተዋሉ አዋቂነት ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ሰሞኑን ህዳር 1 ቀን 2014  ዓ.ም. ከአለም አቀፍ የዜና አውታር እንደሰማሁት የቤልሩስ ዜጎች ወደ ጎረቤት ሀገር ፖላንድ የጥገኝነት ጥያቄ ለማግኝት የሚያደርጉት ተስፋ አስቆራጭ መንፈስን ይረብሻል፡፡ ውድ ኢትዮጵያውያን ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ እንዲሉ በፍጥነት ከሌሎች ሀገር ዜጎች መከራ እንድንማር እማጸናለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ከጦርነት የትኛውም ሀይል ተጠቃሚ አለመሆኑ እየታወቀ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ለያዥና ገላጋይ ያስቸገር የርስበርስ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑ ሲስተዋል የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ ጦርነት የሚጠቅመው የጦር መሳሪያ አምራቾችን እና የጦር መሳሪያ ደላሎችን ኪስ ለመሙላት እንጂ ለተፋላሚ ወገኖች የሚያፈይደው ቁም ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ( በተለይም የወንድማማቾች ጦርነት ትርፉ በትውልድ ላይ ጠባሳ ከመጣል በቀር የሚፈይደው ምንም ነገር የለም፡፡) ሁሉም የጦርነት ናፋቂዎች ( በተለይም የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ አክራሪ ብሔርተኞች) የጦርነት ፍሬከርስኬነትን ቢረዱትም ይሄን መራር ሀቅ መቀበል አይፈልጉም፡፡ ይህን ይክዱታል፡፡ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት መጠበቅ ለምጣኔ ሀብት እድገት እንደሚበጅ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህ የሚካድ አይደለም፡፡ ቀሪው አለም፣የሰለጠነው አብዛኛው አለም ወደ አንድነት፣ወደ ህብረት በሚሄድበት በዚህ ግዜ በኢትዮጵያ ያሉ የተገንጣይ ሀይሎች የተቃራኒውን መንገድ በመከተል፣ወደ መለያየት ማዘንበላቸው አስገራሚ እና የሚያሳዝን ነው፡፡ በመጨረሻም አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ ሉዓላዊት፣ 

እንዲሁም ጠንካራ ከመሆኗ ባሻግር በማናቸውም መስፈርት (ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ) ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ማለቴ ነው) ከወዳጆቿም ሆነ ከጠላቶቿ ጋር የምታደርገው ውይይት በእኩልነት መንፈስ ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አንድነት በላላባት ሀገር ውጤቱ ደካማ መሆንና መፈረካከስ ይሆናል፡፡ ይሄም ብቻ የተለያዩ ደካማ አዲስ ሀገር ለመሆን ወጉ የደረሳቸው ( እንደወግ ከተቆጠረ ማለቴ ነው) በቅርብ ግዜ ውስጥም ሆነ የሀይለኞችና ሀብታም ሀገሮች ሰትራቴጂክ ጥቅም ለማስጠበቅ የሚየደርጉት ጨዋታ ውስጥ መዘፈቃቸው አይቀሬ እውነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የውጭ ሀገራት ቱጃሮች ጥቅም ማስጠበቃቸው አይቀሬ እውነት ነው፡፡ ዛዲያ ለምንድን ነው የተገንጣይ ሀይሎች ይህንን መራር እውነት መረዳት ያቃታቸው፡፡ ሩቅ ምስራቅ ሳንሄድ እዚሁ አፍንጫችን ስር የሐይለኞች ጥቅም መራኮቻ የሆኑ ሀገራትን ማየት ብልህነት ነው፡፡  ይህ ከላይ የሰፈረው ጠቃሚ ሃሳብ የኢትዮጵያ አንድነት በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት መከበር እንዳለበት ማሳያ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት እንዴት ማስከበር ይቻላል የሚለውን የግል አስተያየቴን ከመሰንዘሬ በፊት ለምንድን ነው የአክራሪ ብሔርተኞች ድምጽ ከፍ ብሎ የተሰማው የሚለውን ሃሳብ ለማየት እሞክራለሁ፡፡

ለመሆኑ የመገንጠል ትርጉሙ ምንድን ነው ? የአማርኛ አጭር ትርጉሙ የራስን እድል በራስ ለመወሰን ፍላጎት ማሳየት የሚል ነው፡፡ የእንግሊዝኛ ትርጉሙ የበለጠ ገላጭ በመሆኑ ለአንባቢው ግንዛቤ ስለሚረዳ አስፍሬዋለሁ፡፡ ‹‹ Separatism, i.e. the desire for self-determination ›› የራስን እድል በራስ የመወሰን ጽንሰሃሳብ በኢትዮጵያ መንሸራሸር ከጀመረ ግማሽ ክፍለ ዘመን አለፈው፡፡ ይህ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዲከበርላቸው ለሚጠይቁ ቡድኖች በዲሞክራሲያዊ አካሄድ ገቢራዊ የሚሆን ከሆነ በእኔ በኩል ችግር ይጋብዛል ብዬ አላስብም፡፡ ለሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በህግ የተቀመጠ እኩል እድል፣እኩል ጥበቃ፣ የሚሰጥ ከሆነ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እዳው ገብስ ነው፡፡ በእኔ የግል አስተያየት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ችግር ውስጥ የሚወድቀው ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሁም ጠንካራ ተቋማት ሳይኖሩ ሲቀሩ ነው፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ገቢራዊ ከመደረጉ በፊት የዲሞክራሲ ተቋማት በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም አለባቸው፡፡ የህዝቡ ነጻነት መከበር አለበት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በእኛ ሀገር እንደ እንጉዳይ የበቀሉ የጎሳ ፖለቲከኞችና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል የሚለው መብት መከበር አለበት በማለት በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ሳይቀር ያካተቱ ስለ ህዝቡ ነጻነትና ዴሞክራያዊ መብት መከበር እውን መሆን የሚጨነቁ አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ አኳያ በአብዛኛው የመገንጠል ጥያቄ የሚያቀነቅኑት የጎሳ ፖለቲካ መሪዎችና አባላቶቻቸው ናቸው፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው ምን እንደሆነ፣ፍላጎቱ ምን እንደሆነ አንድም ግዜ በነጻነት ተጠይቆ የሚያውቅ አይደለም፡፡ የእከሌን ነገድ ወይም ብሔር እንወክላለን የሚሉ የፖለቲካ ኤሊቶች ግን በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጣቢያዎች፣እንዲሁም በስብሰባ መድረኮች ላይ ብቅ በማለት የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል የሚለው የእነ ጆሴፍ ስታሊን  ፍልስፍና ገቢራዊ እንዲሆን ሲወተውቱ የተሰማ ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህል አሸባሪው የወያኔ ቡድን ከውልደቱ አሁን ድረስ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ገቢራ አደርጋለሁ ብሎ ሲነሳ ወክየዋለሁ የሚለውን የትግራይ ህዝብ እውነተኛ ፍላጎት ለማወቅ ጥረት አላደረገም፡፡ በሌላ አነጋገር ይህ የለየለት ዘረኛ እና አሸባሪ ቡድን  ዴሞክራሲን ሳያሰፍን፣የህዝቡን ነጻነት በመግፈፍ፣ በሃይል፣ በጉልበትና በጠመንጃ ነው የምፈልገውን አስፈጽማለሁ በማለት የተነሳው፡፡ ከዚህ ባሻግር ማንኛውንም ዋጋ በመክፈል፣በማኪያቫሌ ስልት(ከፋልህ ግዛ ፖሊሲ ገቢራዊ በማድረግ)  የኢትዮጵያን ህዝብ ለ27 ዓመታት እንደ ሰም አቅልጦ፣እንደ ብረት ቀጥቅጦ ገዝቷል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የአሸባሪዎች ቡድን ሰፊውን የትግራይ ህዝብ ስቃይና መከራ ውስጥ የዶለ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በትግራይ ክልል ብቻ ከ5ሚሊዮን በላይ ህዝብ በርሃብ አለንጋ እየተገረፈ መሆኑ ሲታሰብ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር ደም አቃባ እንጂ የፈየደው ቁምነገር የለም፡፡( እዚህ ላይ ግን ከወያኔ አሸባሪ ቡድን ጎን ቆመው(ተሰለፍው) ኢትዮጵያን ያደሙ የትግራይ ተወላጆች የሉም ማለት እንዳልሆነ አስታውሳለሁ፡፡ ሞለተው ተርፈዋል፡፡) ግራም ነፈሰ ቀኝ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ታሪክ ይቅር የማይለው ከባድ ስህተት፣ለሌሎች አክራሪ ብሔርተኞች ትምህርት ሊሆናቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የወያኔን ካርታ የሆነውን የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል የሚለውን መብት ለማስከበር ተነስተናል የሚሉ አክራሪ ብሔረተኞች ከወያኔ አሸባሪ ቡድን ከባድ ስህተት እንዲማሩ እንማጸናለን፡፡

የኢትዮጵያ አንድነት የሚጠበቅበት መንገድ

አሁን ወደዛሬው ዋናው የጽሁፌ ዋና ጭብጥ ልውሰዳችሁ፡፡ ኢትዮጵያ የበለጠ አንድነቷ እንዲጠበቅ፣የተረጋጋች ሀገር እንድትሆን፣ ሰላሟ እንዲጠበቅ፣ በኢኮኖሚ እድገት የተሳካላት እንድትሆን ምን አይነት መንገድ መከተል ያዋጣት ይሆን ? እስቲ በየአካባቢችሁ፣በትምህርት አምባዎች ቅጥር ግቢ ተወያዩበት፡፡ በእኔ የግል አስተያየት አራት የሚሆኑ የመፍትሔው አካል ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ፣በአይምሮዬ ጓዳ የሚመላለሱ ሀሳቦችን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡( በነገራችን ላይ እኔ የማቅረበው አስተያየት ምሉሄ በክሉሄ ነው የምል ግብዝ ሰው አይደለሁም፡፡ የጸሃፊው አላማ የሃሳብ ብልጭታን፣የሃሳብ ፍጭትን መፍጠር ሲሆን፣ከእኔ የተሻለ ሃሳብ ያላቸውን ቅን ሰዎችን በመጋበዝ ትምህርትን መቅሰምና ለኢትዮጵያ የሚበጃትን የሃሳብ ጅረትን እውን ለማድረግ መሞከር መሆኑን አንባቢውን አስታውሳለሁ፡፡) 

 አራቱ የመፍትሔ ሐሳቦች

  1. በጎሳና ቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፌዴራል ስርዓት በሌላ የዴሞክራሲ መሰረት ላይ በቆመ የፌዴራል ስርዓት እውን የሚሆንበት መንገድ በፖለቲካ አዋቂዎች የውይይትና ሃሳብ ፍጭት እዲዘጋጅ የመንግስት ፈቃደኝነት ከታከለበት የፖለቲካዊ ችግራችን መግፍኤ ምክንያት በከፊል ምላሽ ያገኛል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡( በሌላ አነጋገገር የክልሎች አወቃቀር በጎሳ ወይም በቋንቋ ላይ መሰረት አድርጎ መከለል ሳይሆን ያለበት፣ በሌላ በመልክዓ ምድር ላይ የተመሰረተ የክልሎች አወቃቀር ሊሆን ይችላል ወይም በሌላ የኢትዮጵያን ህዝብ ሊያስማማ የሚችል ቢሆን መልካም ነው ፡፡ ሆኖም ግን ውሳኔው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆኖ ሌላ ሁሉንም የኢትዮጵያ ዜጎችን የእኩልነት መብት በፍትህና ርትእ መሰረት ላይ ቆሞ ማስከበር የሚያስችል የክልል አወቃቀር እውን ቢሆን እዳው ገብስ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡)
  2. የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሌላ የፖለቲካ ፓርቲ አይነት ቢተኩ ( ለአብነት ያህል በርእዮት እና ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ፓርቲዎች እውን የሚሆኑበት መንገድ ቢፈለግ)
  3. በክልሎች ስር የተደራጁ የልዩ ሀይል አባላትና ሚሊሻ ወታደሮች የኢትዮጵያ የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት አባል የሚሆኑበት መንገድ ቢፈለግ
  4. ስለ አንድነት ጥቅም የሚሰብኩ ተቋማትን መፍጠር፡፡ ካሉም የበለጠ ጥንካሬ እንዲያገኙ ማበረታት፣ ድርጅታዊ ነጻነታቸው እንዲጠበቅ መርዳት

የመጀመሪያው ነጥብ ላይ የተቀመጠው የፌዴራል ስርዓቱ እንደገና በሰለጠነ መንገድ፣በውይይት፣በሰከነ መንፈስ  የሚከለስበትን መንገድ መጠቆም ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች ለአብነት ያህል በአርባጉጉ፣አሰቦት ገዳም፣አሩሲ አቦምሳ፣ሻሸመኔ፣ጉራፈርዳ፣ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ምስራቅና ምእራብ ወለጋ፣ምእራብ ሸዋ ዞን ግንደበረት፣ሶማሌ ክልል ወዘተ ወዘተ ይኖሩ በነበሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ በየግዜው የተፈጸሙ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያቶቹ በርካታ ቢሆንም መሰረታዊ ምክንያቱ እናንተ መጤ ናችሁ ፡፡ ክልሉ ተወላጆች አይደላችሁም የሚሉ አክራሪ የጎሳ ፖለቲከኞች በሚሰነዝሩባቸው የጥቃት ሰበዝ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በአጭሩ የጎሳ ክልሎች ሙሉ መብት የሚሰጡት ነባር ነዋሪ ወይም የክልሉ ተወላጅ ለሚሉት ነው፡፡ ለአብነት ያህል ኑሮ እያዳፋው ወደ አንድ ክልል የሄደ ኢትዮጵያዊ ከኑሮው መፈናቀል ሊገጥመው ይችላል፡፡ከክልላቸው ውጭ በሚኖሩ በበርካታ የአማራ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ አፈርገፊ ዜጎች ላይ የደረሰው መጥፎ እድል እንደ ትምህርት ሆኖ ከአሁን በኋላ  ኢትዮጵያዊ ዜጎች ሁሉ በሚፈልጉት በማናቸውም የሀገሪቱ ክፍሎች ተሰማርተው መስራት እንዲችሉና ኑሮአቸውን እንዲያሻሽሉ ሰፊ ነጻነት እውን መሆኑ አጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡ ክልሎች ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጎች ሁሉ እኩል ለማገልገል በሚችሉበት መንገድ እንደገና የሚዋቀሩበት መንገድ በአዋቂዎች እንዲጠና ጸሃፊው ያስታውሳል፡፡ ነጻነታቸው የተጠበቀ ክልሎች፣ የፌዴራሉ መንግስት በውስጥ አሰራራቸው ጣልቃ የማይገባባቸው ክልሎች ኢትዮጵውያን ሁሉ በእኩልነት መንፈስ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን ማስከበር የሚችሉባቸውን ክልሎች ኢትዮጵያ ዛሬ ትሻለች፡፡ በስዌዘርላንድ፣በተባበረችው አሜሪካ፣ህንድና ካናዳ የፌዴራል ስርዓትን አንብረው ምሉሄ በክሉሄ ነው ተብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ባይቻልም የዜጎቻቸውን መብት ማስከበር ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያም የተጠቀሱትን ሀገራት ወይም ሌሎች አፍሪካዊ ሀገራትን እንደ ናይጄሪያ፣የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክን ዱካ መከተል ሊሆን ይችላል በፍጥነት ከቋንቋና ጎሳ ተኮር የፌዴራል ስርዓት ለመውጣት በሰለጠነ መንገድ መወያየት ግዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ማንም ሰው ቢሆን የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን መጋፋት ወይም መቃወም አለበት ብዬ አላምንም፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ሳይቀር አለ፡፡በሁሉም ሀገራት ህገመንግስት ውስጥም ተካቶ ይገኛል፡፡ በሁሉም ሀገራት ህገመንግስት ውስጥ የማይገኘው ሀረግ ‹‹ እስከመገንጠል ›› የሚለው ቃል ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ውጤታማ የሚሆነው ‹‹በጎሳ ፌዴራሊዝም ›› ስርዓት ብቻ አይደለም፡፡ ሌሎች የፌዴራል ስርዓቶች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት ባሻግር ሌላ አይነት የፌዴራል ስርዓት መከተል አለባት ባይ ነኝ፡፡ ከዚህ ባሻግር በኢትዮጵያ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መከበር የለበትም የሚል አምደምታ ያለው መልእክት ለማስተላለፍ እንዳልተፈለገ አንባቢውን ሳስታስ በአክብሮት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ክልሎች፣አውራጀዎች፣ወረዳዎችና ቀበሌዎች በዴሞክራሲ አኳያ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዳላቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት በእኩልነት መንፈስ መሰጠት ያለበት በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ሁሉ መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡ ለአብነት ያህል ‹‹ ሀ›› ተብሎ በተሰየመ ክልል የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት ተጠይቆ ገቢራዊ ከሆነ የመብቱ ተጠቃሚዎች መሆን ያለባቸው በ‹‹ሀ›› ክልል የሚኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጎች መሆን አለባቸው፡፡

አንድ የታሪክ እውነት አለ፡፡ ኢትዮጵያ ላለፉት ብዙ መቶ ክፍለዘመኖች በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ለበርካታ ግዜያት የድንበር መከፋፈል መደረጉ የታወቀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የግዛት አስተዳደር ስምና ስያሜ ለብዙ ግዜ ተቀያይሮ ነበር፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ የጂኦግራፊ አወቃቀር እንዲህ በመጽሔት ላይ በሚሰጥ አስተያየት ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡የፌዴራል ኢትዮጵያ መንግስት፣ ኢትዮጵያዊ የመለልክአ ምድር አጥኚዎች፣የፖለቲካ ሰዎች፣የማህበረሰብ አጥኚዎች፣የሀገር ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣የዩንቨርስቲ ምሁራን፣የሲቪል ማህበረሰቡ የስራ ሃላፊዎች በሰከነ መንፈስ ከተነጋገሩ እና የመፍትሔ ሃሳብ የሚሉትን ቁምነገሮች ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ህዝቡ በነጻነት ውሳኔ የሚሰጥበትን መንገድ ማመቻቸቱ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሁለተኛው ነጥብን በተመለከተ የሚያተኩረው በጎሳ ላይ መሰረት ባደረጉ ፓርቲዎች ላይ ይሆናል፡፡ ማንም ሰው በመሰለው የፖለቲካ ፓርቲ የመደራጀት መብት ያለው እንደሆነ ቢታወቅም፡፡ ጸሃፊውም ቢሆን የማናቸውም የፖለቲካ ድርጅቶች ነቃፊም ደጋፊም ባይሆንም (መሰረታቸው በጎሳ ወይም የዜግነት(ርእዮት) ዓለም የሆኑ የማናቸውም ፖለቲካ ደርጅቶች አሸርጋጅ ወይም ነቃፊ አይደለሁም) ኢትዮጵያን ለከፋ የፖለቲካ ውደቀት ካደረሷት አንዱና ዋነኛው የጎሳ ፖለቲካ አደረጃጀት እንደሆነ በርካታ ስመጥር የፖለቲካ ተንታኞች በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ የደረሱበት ጉዳይ ነው፡፡ ጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች መፍትሄ ማምጣት አልተቻላቸውም፡፡ እንደ ጥሩ አብነት የሚጠቀሰው አሸባሪው የወያኔ የጎሳ ቡድን፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን በትንሹ ላለፉት 50 አመታት ኢትዮጵያን ያደማ እኩይ ቡድን ነው፡፡ በእርሱ አምሳል የተፈለፈሉ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶችም ቢሆኑ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጉዞ ከድጡ ወደማጡ ዶሉት እንጂ ለኢትዮጵያ አልጠቀሟትም፡፡ ( የስም ህበረብሔራዊ የፖለቲካ ድርጅቶችን ታሪካዊ ስህተት ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡) በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ዋነኛ አላማ ቆመንለታል የሚሉትን ነገድ ወይም ብሔር መብት ማስከበር እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡( ይህም ቢሆን በወረቀት ላይ የተጻፈ እንጂ ገና በተግባር አልታየም፡፡ ቢያንስ ስልጣን ላይ ቁጢጥ ካሉትና ደጋዎቻቸው በቀር የአብዛሃውን የኑሮ እድገት ማሻሻላቸው አልታየም፡፡)

በእኔ የግል አስተያየት ወይም ሃሳብ ‹‹ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት›› በደንብ በአዋቂዎች ተጠንቶ፣ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጎች በሚጠቅም መልኩ በህገ መንግስቱ ውስጥ ቢካተት የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች አስፈላጊነት ጠቀሜታ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች በፖለቲካ ህይወት ውስጥ መኖር አለብንም ካሉ ራሳቸውን ወደ የርእዮት አለም ፓርቲ ቢቀይሩ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህም ማለት የቆየውን አስተሳሰባቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ለሀገር አንድነት የሚበጅ አስተሳሰብ ይዘው ለሀገር መድህን ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ሁላችንም በጽኑ እንደምናምነው የጎሳ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ አሽን እንዲፈሉ ያደረገው  የቀድሞው የወያኔ ኢህአዲግ መንግስት ስልጣኑን ለብቻው ለመቆጣጠር እንዲያስችለው ስለመሆኑ ክርክር የሚያጭር አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፣በተለይም የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳዊ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰላሳ አመታት የተጓዘችበትን የፖለቲካ መንገድ ተከትላ ለወደፊቱ መሄድ እንደሌለባት የሚስማማ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም በወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ዘመን የነበረውን የጎሳ ፖለቲካ ተሸክማ የምትቀጥል ከሆነ እንደ ሀገር ለመቆየት የሚያስችላት ህልውናዋ ከባድ አረንቋ ውስጥ ይዘፈቃል ብዬ በብርቱ እሰጋለሁ፡፡ስለሆነም የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት የገጠመውን የህልውና ጦርነት መቋጫ ካበጀለት በኋላ ከጎሳ ፖለቲካ ለመላቀቅ የሰለጠነ መንገድ መከተል ታሪካዊ ግዴታው ነው፡፡ 

ሶስተኛው የአንድነት መሳሪያ ጠንካራ እና እውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ያለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት መገንባት ነው፡፡ የወያኔ ዘረኛ ቡድን የደርግ ሰራዊት በሚል ስንኩልና በበቀል ላይ ተመስርቶ የበተነውን የኢትዮጵያ የጦር ሀይል አሁን በቅርብ ከሶስት አመት ወዲህ በተጀመረው መልኩ ማወቀሩ አማራጭ የለውም፡፡ በተለይም ሙሉ በሙሉ በወያኔ መንግስት ፈርሶ የነበረውን የኢትዮጵያን ባህር ሀይል እንደገና ማወቀሩ ለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከታችኛው እርከን እስከ ከፍተኛው ወታደራዊ አመራር ድረስ እንደ ችሎታቸው መጠን የኢትዮጵያን ልጆች ሁሉ የወከለ መሆን እንዳለበት ብዙዎች የኢትዮጵያ የጦር አታሺዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ወያኔ የማእከላዊ መንግስቱን በተቆጣጠረ ማግስት ኢትዮጵያ በውጭ ሀገር እና ሀገር ውስጥ ከፍተኛ ወጪ በማድረግ ያስተማረቻቸውን የጦር ገበሬዎችንና መላ ሰራዊቱን የደርግ ሰራዊት በሚል ጭፍን ጥላቻና የበቀል ስሜት ከበተኑ በኋላ አብዛኛውን ወታደራዊ ሃላፊነት ከአንድ ክልል በተለይም በአንድ ከተማ ውስጥ ለተወለዱ የወያኔ ታጋዮች መስጠታቸው ለግዜው የጠቀማቸው ይመሰል እንጂ በመጨረሻ ከውድቀት አላዳናቸውም፡፡ ይህ የወያኔ ከባድና ታሪካዊ ስህተት ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡(በነገራችን ላይ ከአንዳንድ የጥናት ወረቀቶች ላይ ባገኘሁት መረጃ መሰረት 98 ፐርሰንቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ስልጣንን ተቀጣጥረው የነበሩት ከአንድ ክልል የተገኙ የኘበሩ ሲሆን፣96 ፐርሰንቱ ደግሞ ከዛው ክልል በሚገኝ ከአንድ ከተማ የተገኙ ነበሩ) በሌላ በኩል የክልል ልዩ ሀይል እና የሚሊሻ አባላት መደበኛ ወታደራዊ ስልጠና የሚያገኙበት እድል ተመቻችተላቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል የሚሆኑበት እድል በወታደራዊ ባለሙያዎች ከተጠና በኋላ ቢመቻች ለኢትዮጵያ አንድነት መከበር እንደ አንድ መድህን የሚቆጠር ነው፡፡ ከዚህ በሻግር ችሎታ ሳይሆን ነገድን እየቆጠሩ በየመንግስት መስሪያ ቤቱና የሲቪል ማህበር ውስጥ መሳሳቡ ለኢትዮጵያ አንድነት የሚበጃት አይደለም፡፡ ደጋግሜ ለማስታወስ እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ ወታደራዊ ሀይል መገንባት ያለበት በኢትዮጵያ ምድር በአራቱም አቅጣጫ ከሚገኙ ልጆቿ መገንባት ያለበት ይመስለኛል፡፡ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሀይል ውስጥ የአይምሮ ምጥቀት እና አካላዊ ብቃት ላይ ተመስርቶ ስልጣን ለኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ በእኩል ደረጃ ላይ መከፋፈል ያለበት ይመስለኛል፡፡ እንዲህ አይነት አሰራር ገቢራዊ መሆኑ ብዙ ነገዶች የሚኖሩባተን ኢትዮጵያ አንደነቷን ለማምጣት በብዙ መልኩ የሚጠቅም ቁምነገር ነው፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እርስበርሱ የሚከባበር ከመሆኑ ባሻግር ኦትዮጵያውያን ርስበርሳቸው ይሞጋገሳሉ፡፡ በሀገራቸው መከላከያ ሰራዊት ክብርና ሞገስ ይሰማቸዋል፡፡ ለደህንነታቸው ስጋት አያድርባቸውም፡፡ የሀገሪቱ የመከላከያ ሀይል ስብጥር ከአድሏዊነት አሰራር ከጸዳ፣ አንዱን ባይተዋር፣ሌላውን ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ገቢራዊ የማይሆን ከሆነ የመከላከያ ሰራዊቱ ለኢትዮጵያ አንድነት ያለው አበርክቶት መጠነ ሰፊ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚህ በተቃረነ መልኩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ስብጥር እና አሰራር ገቢራዊ የሚሆን ከሆነ ግን ለሀገሪቱ አንድነት በምንም አይነት መልኩ የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዘመኑ በዋጀው የሚሊተሪ ሳይንስ እውቀት መካን ያለበት ከመሆኑ ባሻግር ዘመናዊ የጦር መሳሪያ መታጠቁ አማራጭ የለውም፡፡ ከዚህ ባሻግር የክልል ሚሊሻ እና ልዩ ሀይሎች አወቃቀር እንደገና የሚከለስበት መንገድ መፈለጉ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚቀላቀሉበት መንገድ በወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች ተጠንቶ ቢቀርብ የኢትዮጵያን አንደነት የበለጠ ያጠናክረዋል የሚለው የግል አስተያየቴ ይሆናል፡፡ በነገራችን ላይ በቅርብ ግዜ ውስጥ እንዳየነው ለኢትዮጵያ አንድነት ስጋት የሆነው የወያኔ አሸባሪ ቡድን ያሰለፈው ዋነኛ ተዋጊ ጦር ስብጥሩ በአብዛኛው የትግራይ ክልል ልዩ ሀይልና ሚሊሻ የተወጣጣ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

በመጨረሻም አንድን ክልል ወይም ነገድን (ብሔርን) የተሻገረ፣ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያቅፍ  ብሔራዊ ተቋም ለኢትዮጵያ መረጋጋት፣አንድነቷን ለማስጠበቅ፣የሀገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ በእጅጉ የሚረዳ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ብሔራዊ ተቋም ኢትዮጵያ ከማናቸውም የአፍሪካ ሀገራት በበለጠ  እና በተለየ መልኩ ያስፈልጋታል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ብሔራዊ ተቋማት ብዙ ሃሳቦች ሊኖሩት ይገባል፡፡ ለአብነት ያህል በብሔራዊ ተቋሙ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን በአብዝሃው ህዝብ ተቀባይነት ያላቸውን ሃሳቦች ማካተት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ሌላው በአይምሮዬ የሚመላለሰው ቁምነገር በደርግ ዘመን ተካሂዶ እንደነበረው አይነት ብሔራዊ የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ እና ብሔራዊ የጤና አገልግሎት ቢጀመር፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች ባህልና ቋንቋ ትውውቅ እንዲያደርጉ ይረዳ ዘንድ የብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት ገቢራዊ ቢሆን ለኢትዮጵያ አንድነት በእጅጉ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ አይነት የብሔራዊ አገልግሎት በቀድሞው ግዜ በአጼ ሀይለስላሴ ዘመነመንግሰት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች በመላው የኢትዮጵያ ግዛቶች ተሰማርተው ይሰጡት የነበረውን የአንድ አመት ብሔራዊ አገልግሎት ያስታውሰናል፡፡ (የአጼ ሀይለስላሴ ዘመን የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የዩንቨርስቲ የአራተኛ አመት ትምሕርታቸውን ከማጠናቀቃቸው በፊት፣በግዜው አጠራር በአስራ አራቱ ጠቅላይ ግዛት ኤርትራን ጨምሮ በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተሰማርተው ወጣቶችን ያስተምሩ እንደነበር የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡) እንዲህ አይነት የብሔራዊ አገልግሎት እና ሌሎች ተመሳሳይ ብሔራዊ ፕሮጄክቶች፣ እርስበርስ ለመተዋወቅ ብቻ የሚረዱ አይደሉም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኢትዮጵያ ህዝብ መሃከል ያለውን የአንድነት መንፈስ በይበልጥ የሚያጠናክር ይሆናል፡፡

ከናይጄሪያ ምን እንማር ?

ናይጄሪያ በኢኮኖሚ እና በህዝብ ብዛት በአፍሪካ ትልቋ ሃገር ናት። የህዝብ ብዛቷ ከአፍሪካ ትናንሽ 34 ሃገሮች የህዝብ ብዛት ጋር እኩል ነው። (የህዘብ ብዛት 206 ሚሊየን)

ደራሲዎቿ አለምአቀፍ ታዋቂነትን ያተረፉ ናቸው። ቺንዋ አቼቤ የመጀመሪያው በስነፅሁፍ ኖቤል የተሸለመ አፍሪካዊ ነው። ቤን ኦክሪ፣ ዎሌ ሶይንካ፣ ኬን ሳሮዋዊ፣ ቡቺ ኢመቼታ፣ ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቺ ሌሎች ዝነኛ የናይጄሪያ ደራሲዎች ናቸው።

የፊልም ኢንደስትሪዋ በአፍሪካ ትልቁ ነው። ኖሊውድ በየአመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ፊልሞችን ያመርታል። የናይጄሪያ ፊልሞች በጭብጥ ተመሳሳይነት ዘወትር ቢተቹም በአፍሪካ ግዙፉን የፊልም ኢንደስትሪ መገንባታቸው አይካድም።

እግር ኳሷ እንደ ሌሎች የምእራብ አፍሪካ ሃገሮች የረቀቀ ነው። በኦሎምፒክ የእግር ኳስ ዋንጫን በማሸነፍ በአፍሪካ ብቸኛ ሃገር ናት።

የግዜያችን የአፍሪካ አንደኛ ቱጃር ሰው ናይጄሪያዊ ናቸው። አሊኮ ዳንጎቴ ይባላሉ። ዳንጎቴ በአለም ትልቁ የሆነውን የነዳጅ ማጣሪያ ፕላንት በናይጄሪያ እየገነቡ ነው። ናይጄሪያውያን በኢኮኖሚ እመርታቸው ለተቀረው አፍሪካ ሁሉ ሞዴል የሚሆኑ ናቸው። ሌጎስ ከአለም ታላላቅ ሜትሮፖሊታኖች አንዷ ናት። ግዙፏ ሌጎስ 23 ሚሊየን ናይጄሪያውያንን በእቅፏ ይዛ ታኖራለች።

የናይጄሪያ ጂዲፒ በ1.3 ትሪሊየን ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም 23ኛ ነው። በአፍሪካ ውስጥ በኢኮኖሚ ግዙፍነት ናይጄሪያን የሚገዳደሩት ሌሎቹ የአፍሪካ አንበሶች ደቡብ አፍሪካና ግብፅ ናቸው። 

ብዙ ግዜ መታዘብ እንደሚቻለው ማንኛውም ሃገር ሲያድግ እድገቱ በግርድፉ ሁለንተናዊ ነው። ይህም ማለት ኢኮኖሚው ሲያድግ ቴክኖሎጂውም አብሮ ይመነደጋል፣ ባህሉ ያብባል፣ መከላከያ ሃይሉ ይዳብራል፣ የኑሮ ዘይቤ ይቀየራል። ስነፅሁፍ እና ስነጥበብ ይጎለምሳል። ናይጄሪያ፣ ግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ከፍታዎች ናቸው። አኗኗራቸው ከተቀረው አፍሪካ የሰለጠነ ነው። ቴክኖሎጂዎቻቸው እና ከተሞቻቸው እየተራቀቁ ነው። ከባህል እሴቶቻቸው ስነፅሁፉን መርጠን ለምሳሌ ብንመለከት እንኳን በአፍሪካ የዳበረ ስነፅሁፍ ያላቸው ሃገሮች ሶስቱ ናቸው። የናይጄሪያዎቹን በጨረፍታ ስለተመለከትን አልመለስበትም። ግብፅን ብናይ ናጂብ ማህፉዝን የሚያህል እጅግ የተዋጣለት የልብወለድ ደራሲ እንዲሁም ቶፊቅ አልሃኪምን የሚያህል ፀሀፊ ተውኔት አላት። ደቡብ አፍሪካም አለን ፓተንና ኦሊቭ ሽራይነንን የመሰሉ የበቁ ደራሲዎች አሏት። 

ለማንኛውም ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ ናይጄሪያ ከጎሳ ፖለቲካ ተገላግላ የተሻለ ፌዴሬሽን ለመገንባት የቻለች አፍሪካዊት ሀገር ናት፡፡ ምእራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናይጄሪያ የብዙ ነገዶች ሀገር ስትሆን የግዛት ክልሏን በጎሳ ወይም ቋንቋ ላይ መሰረት ሳታደርግ የፌዴራል ስርዓት የገነባች ሀገር በመሆኗ የተሻለ ተራማጅ ህገመንግስት ለማዘጋጀት በመብቃቷ ከአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ የተሻለ ኢኮኖሚ መገንባት የቻለች ናት፡፡ ናይጄሪያን በኢኮኖሚ እድገት የምትበልጣት የደቡብ አፍሪካዊት ሪፐብሊክ ብቻ ናት፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ኢኮኖሚው በጎመራበት ቦታ ሁሉ ስነጥበብ አብቦ የሚታየው ያለ ምክንያት ወይም በአጋጣሚ አይደለም። ስነጥበብ የስልጣኔ ትሩፋት ነው። ስልጣኔ ሲያሽት ስነጥበብ ያፈራል። የጥበብ ፍሬ ሲዘራም እልፍ ስልጣኔ ያሽታል። ተመጋጋቢ ናቸው። ናይጄሪያ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በተለይም ነዳጅ እንዳላት ቢታወቅም ፣ ሙስና የተንሰራፋባት ሀገር ብትሆንም፡፡ ናይጄሪያ ጠንካራ የምጣኔ ሀብት ባለቤት ናት፡፡ ምእራባውያን በፈጠሩት ሴራ የብክሃራም እንቅስቃሴ ስጋት ላይ ቢጥላትም፣ ናይጄሪያ አንደነቷ የተጠበቀ ሀገር ናት፡፡ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስትና የፖለቲካ ሀይሎች ከናይጄሪያ ህገመንግስት እና ከፌዴራል ስርዓቷ በመማር ናይጄሪያ አንድነቷን ለማስጠበቅ የሄደችበትን መንገድ ቢከተሉ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

እንደ መደምደሚያ

የዛሬውን ጽሁፌን የምቋጨው እንደ ዛሬው ሳይሆን እንደበፊቱ በዩንቨርስቲ ህይወቴ ያጋጠመኝን መራር ሀቅ በማስታወስ ይሆናል፡፡ በእኛ የትምህርት ዘመን ለመጀመሪያ አመት የዲግሪ ተማሪዎች የኢትዮጵያ ታሪክ እና የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ ለተማሪወች ይሰጥ ነበር፡፡( የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ መግቢያ) መጽሀፍ እና የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር መጽሀፍ የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ አባት በነበሩት እውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ነው፡፡( ነብሳቸውን ከደጋግ አባቶቻችን ጎን ያሳርፈው ፡፡) ለማናቸው ወደ ጽሁፌ መደምደሚያ ልወሰዳችሁ፡፡ ታሪኩ የሚከተለውን ይመስላል፡፡

በ1980 ዓ.ም. በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበርኩ ሲሆን በተጠቀሰው ዓመት የ12ኛ ክፍል መለቀቂያ ፈተና ላይ ብቀመጥም ወደ ዩንቨርስቲ መግቢያ ፈተና ውጤት ማግኘት ባለመቻሌ በቀጥታ ግዜዬን ሳላባክን የጤና እረዳት ትምህርት በመከታተል መለስተኛ ዲፕሎማዬን ጨብጬ በምእራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው አሶሳ ከተማ ዙሪያ ከሚገኙት በአንዱ መገሌ 37 የሰፈራ መንደርና አሶሳ ሆስፒታል ለሶስት አመታት ካገለገልኩ በኋላ በግል የ12ኛ መልቀቂያ ፈተና ላይ ተቀምጬ ከፍተኛ ውጤት በማምጣቴ(3.6)  ትምህርቴን ለማሻሻል በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ባህርዳር ፔዳጎጂካል ሳይንስ ኮሌጅ በቀኑ ክፍለጊዜ እማር ነበር፡፡ የአንደኛ አመት ተማሪ እያለሁ የኢትዮጵያን ታሪክ ያስተማሩን አንጋፋው የታሪክ ምሁር ጋሼ ታረቀኝ የታሪክ መምህራችን ነበሩ፡፡ የታሪክ መምህራችን ምን ብለው ጥያቄ ይጠይቃሉ « ምድረ ነጭ ገና ከዋሻ ሳይወጣ ከአለም በፊት የላሊበላን የአክሱምን የጎንደርን ሀውልት ያቆምን፣የሀረር ግንብን የገነባን፣ ቀድመን በዝሆን ጥርስና በወርቅ መገበያዬት የጀመርን፣ ቀድመን ልብስ የለበስን…. አሁን ምን ሆነን ነው የአለም የመጨረሻ ኋላ ቀር አገር የሆነው?» ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ሁሉም ተማሪ የመሰለውን መልስ ሰጠ፡፡ በጦርነት ምክንያት— የአገራችን ተፈጥሮዋዊ አቀማመጥ ወጣገባ መሆን….» መምህሩ የሁሉንም መልስ ካዳመጡ በኋላ አንድ ምሳሌ ሰጡ፡፡« ጆን፣ ጆርጅና ስሚዝ ዋሻ ውስጥ ሲኖሩ–ጆን ከዋሻው ወጥቶ ቤት ሰራ፡፡ ጧት ጆርጅ የጆንን ቤት ሲያይ ጆርጅ የሰራቸውን ስህተቶች በማረም የራሱን ቤት የተሻለ አድርጎ ስራ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ስሚዝ ሲነሳ ሁለቱ ጓደኞቹ ቤት ሰርተው በቤት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ስሚዝ ሁለቱንም ቤቶች ተዟዙሮ አይቶ የሱን ቤት ከሁለቱ በተሻለ መልኩ ሰራ፡፡ ያስችላል ፣ሀጎስና ሁንዴሳ በጫካ ሲኖሩ አንድ ቀን ያስችላል ከጫካ ወጥቶ ቤት ሰራ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ሀጎስ የያስችላልን ቤት መስራት ሲያይ እኔ ቤት ሳይኖረኝ እንዴት ያስችላል ይኖረዋል ብሎ ሳያየው ቤቱን በሳት አቃጠለበት፡፡ አያችሁ ነጮች ከኋላችን ተነስተው የበለጡን ለዚህ ነው፡፡ አንዱ ሲስራ ሌላው አሻሽሎ በመስራት፡፡ ሰው በተፈጥሮው ራሱን በጣም ስለሚወድ ምቀኛ ነው እንደሆነ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል፡፡ የነጮች ምቀኝነትና ተንኮል የሌላው ሰው መሞት የእነሱን ህይወት መለወጥ እስከቻለ ድረስ ሊገሉ ወይም ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች፣በብዙ ኢትዮጵውያን የሚስተዋለው ምቀኝነት ግን ተፈጥሮዋዊ አይደለም( ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ሁሉ በደምሳሳው እንዲህ አይነት ባህሪ ማላበስ ከባድ ስህተት ነው፡፡) እሱ ወይም እሷ ለምን አገኘ(አገኘች) የሚል ነው፡፡ የእሱ መጥፋት ለእኔ ምን ይጠቅመኛል ሳይሆን እሱ ለምን ተጠቀመ የሚል ሰይጣናዊ ምቀኝነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ከፊት ቀድመን ከኋላ የምንጎተተው» አሉን፡፡ ይችን አባባል በወቅቱ ለመቀበል ተቸግሬ ነበር፡፡ እኔ የማውቀው ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንግዳ ተቀባይ፣ የዋህ፣ ለሰው አዛኝ ርሁሩህ እንድሆነ አይቼ ነው ያደኩት፡፡ ጎሬቤቶቻችን ሁሉ ወላጆቻችን እስኪመስሉን ድረስ ድህነትም ቢኖር ፍቅር የተሞላበት በአዲስ አበባ በአንዱ አካባቢ ነው ያደኩት፡፡ ከፒያሳ ወደ አራት ኪሎ፣ከስድስት ኪሎ፣ኢዮበልዩ ገነት ልኡል ቤተመንግስት፣ከመሃል አራዳ ፣ወደ ካምቦሎጆ፣ከዳጅች ውቤ ሰፈር ወደ መርካቶ ሲኒማ አዲስ ከተማ በእግሬ ስኳትን መኪና እንዳይበላኝ መንገድ የሚያሻግሩኝ የነበሩት ሰው ግፋ ቢል ኢትዮጵያዊ መሆናውን ነበር የማውቀው፡፡ የአንዱ ልጅ የሁሉም ሆነን ነው የኖርኩት፡፡ ነብስ ያወኩት፡፡ እንዲህ ሆኖ ላደገ ሰው ከላይ የተባለውን አባባል ለመቀበል ቢቸግር አይገርምም፡፡ ቀስ ብዬ ሳስበው ግን የመምህሬ አባብል ስሜት እየሰጠኝ መጣ፡፡ በተለይ የደርግን ዘመን ሳስታውስ ለስልጣን ሽሚያ አንድ ትውልድ ማለቁ አሁን ደግሞ በባሰ መልኩ በጎጥ ተከፋፍሎ የጎሪጥ( የግርምቢጥ) መተያያቱና የአንዱን ሞት ሌላው መመኘቱ የመምህሬ አባባል እግር አውጥቶ የሚሄድ ሀቅ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ከዚህ የጎጠኝነት ማጥ ውስጥ ወጥተን እጅ ለእጅ በፍቅርና በመተማመን ተያይዘን መጓዝ እስከ አልቻልን ድረስ መቸም ጊዜ አናድግም—- መቼም!! ለማናቸውም የኢትዮጵያን ክፉዋን አያሳየን፡፡ ( እኔ ኢትዮጵያ የምላት የማትጨበጠውን፣የማትዳሰሰውን ሳይሆን፣ለሁላችንም የምትሆነውን ኢትዮጵያን ነው)

Filed in: Amharic