>

ጦርነቱ አለቀ የሚባለው መቼና የት ላይ ሲደርስ ነው? (ነፃነት ዘለቀ)

ጦርነቱ አለቀ የሚባለው መቼና የት ላይ ሲደርስ ነው?

ነፃነት ዘለቀ


ጠ/ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ዘግይተውም ቢሆን ጦርነቱን በአመራር ሰጪነት መቀላቀላቸውን ይፋ ካደረጉ በኋላ በጦርነቱ ሂደት ለውጥ እየታዬ መሆኑን ከሚዲያዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህም በተያያዘ የቅርቧን ሸዋሮቢትን ጨምሮ እነላሊበላና ሰቆጣ፣ ጋሸናና ቆቦ ከወያኔ ምድራዊ ሲዖል መገላገላቸው እየተሰማ ነው፡፡ ይህ በራሱ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ ያለቁት አልቀው፣ የወደመው ሀብት ንብረት ወድሞ የቀሩት ወገኖቻችን እንዲተርፉ የተጀመረው አዲሱ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉ ለሁላችንም ኅልውና ወሳኝ ነው፡፡

ጅምሩ በየአቅጣጫው ተጠናክሮ ከቀጠለና ሁሉም በአንድ ልብ ተናብቦ ካለሤራና ሸፍጥ ከተራመደ የወያኔ ዕድሜ ከቀናት አያልፍም፡፡ ዱሮውንም ቢሆን በግርድፍ ግምት ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ 110 ሚሊዮን ሕዝብ አሸንፋለሁ ብሎ ሳይሆን አቅሙ እስከቻለ ድረስ በወረራ የያዘውን ሕዝብና መሬት በማራቆት እልሁን ለመወጣት ነበር ወያኔ የገዛ ሕዝቡን ይበልጡን በማስገደድና በዘረፋ በሚገኝ ሀብት ንብረት በማባበል ከጎኑ አሰልፎ ቀድሞ ወደሚያገኘው የአማራው አካባቢ እንደአንበጣ የተመመው፡፡ አሁን የተጀመረው ማጥቃት በአግባቡ ከቀጠለ የኢትዮጵያ የማይቀር ነፃነትም በጥቂት ሣምንታት ውስጥ መበሠሩ አይቀርም፡፡ ችግራችን መለያየታችንና በየልቦቻችን የመሸገው የግል ፍላጎትና ዓላማ እንጂ በአንድነት ከተነሳን እንኳንስ ወያኔና ሌላም ኃይል ከፊታችን ሊቆም እንደማይችል ታሪክ ራሱ ምስክር ነው፡፡ ወያኔ የዘራውን የዘረኝነትና የጎሠኝነት እሾህ አሜከላ ነቃቅለን ከጣልን ኢትዮጵያ እንኳንስ ለኢትዮጵያውያን ለአፍሪካም የሚበቃ የተፈጥሮ ሀብት አላት፡፡

ይህ ጦርነት ከመቀሌ ሸዋሮቢት የደረሰበትን ምክንያት አሁን መደርደሩ ጥቅም የለውም፡፡ ነገር ግን አሁን በአዲስ መልክ የተጀመረው ሁልአቀፍ ዘመቻ እስከመጨረሻው ይቀጥላል ወይ የሚለው ነው ወሳኙ ጥያቄ መሆን ያለበት፡፡ ከዚህ ጥያቄ ጎን ለጎን በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች በተለይ አማራው ላይ እየተካሄደ ያለው የዘር ጭፍጨፋ ከሰሜኑ ጦርነት ባልተናነሰ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግንጥል ጌጥ ማለት ነው፡፡ በአንድ ጆሮ ጉትቻ ማጌጥ እንደማይቻል ሁሉ አንዱን ፀረ ኢትዮጵያ ኃይል የፈለገውን እንዲያደርግ ፈቅዶ በሌላው ላይ መዝመት ውኃን እንደመውቀጥ ነው፡፡ የራስ ወገን ብለው የፈረጁት ሞልቃቃ ኦነግ-ሸኔ እንዳሻው በሀገርና በወገን ላይ ሲሰለጥንና ዘር እየመረጠ ሲያጠቃ ዝም ማለት፣ ከዚያም ባለፈ ውድ ውድ የመግደያ መሣሪያዎችንና የጦር አልባሳትን እየገዙ በጎን በማቀበል ጃዝ ማለት የክፋት ድርጊቱ ተባባሪና አስፈጻሚ መሆንን በግልጽ ያሳያልና ይህ ዓይነቱ “ዳብል ስታንዳርድ” (አድልዖ) መወገድ አለበት – በአንድ ሀገር ሥር የምንተዳደር ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ ከእስካሁኑ ሸውራራ አተያይና ጠማማ ጉዞ ከተማርን የነፃነት ትግሉን አጭርና ውጤታማ ማድረግ እንችላለን፡፡ በሸርና በተንኮል መጓዛችንን ከቀጠልን ግን በቆፈርነው ጉድጓድ ለመግባት የሚቀድመን አይኖርም፡፡ ሸር በፍጹም አያዋጣም!!

ይህ በወያኔ የተጀመረ ጦርነት ከሸዋሮቢት እንዲመለስ መደረጉ እውነት ከሆነ መጨረሻው የት ሊሆን እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ ወያኔዎች ሸዋሮቢትን አልፈው የት ድረስ ሊሄዱና ምን ጥፋት ሊያደርሱ ይችሉ እንደነበር በተግባርም በአንደበትም እነሱ ራሳቸው በተደጋጋሚ ገልጸውታልና ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡ ወያኔን የሚያባርር ኃይል ደግሞ በተቃራኒው ምን ማድረግ እንዳለበት ማጤን አለበት፡፡ ወያኔ ቢቀናት ኖሮ ከሰሜን ሸዋ አልፋ ሌላውን የኢትዮጵያ አካባቢ ሁሉ ጃርት የበላው ዱባ ታስመስለው ነበር፡፡ በአማራው ብቻም ሳትቆም መላዋን ኢትዮጵያ የዶግ ዐመድ ከማድረግ የምትመለስ አልነበረችም፡፡ ወያኔ ማለት ባጭሩ ጭራቅን የምታስንቅ ወደር-የለሽ ዐረመኔ ናት፡፡

አሁን ፀረ ወያኔ ትግሉ በየአቅጣጫው ተፋፍሞ መቀጠልና ይህችን እርጉም ኤርትራ ድንበር ድረስ መሸኘት ይገባል፡፡ ለወያኔ መራራት ራስን በራስ እንደማጥፋት ይቆጠራል፡፡ የወያኔ ጀሌ መላዋን ኢትዮጵያ ለመቆጣጠርና ፍርስራሽዋን ለማውጣት ሲገሰግስ የነበረ ዐውሬ ነው፡፡ አሁን ነገሮች ተገልብጠው ወያኔን ማጥቃት ከተጀመረ የማጥቃቱ ወሰን አነሰ ከተባለ የኤርትራ ድንበር በዛ ከተባለ ደግሞ ቀይ ባህር ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ ኮረም ድረስ ወይም ተከዜ ወንዝ ድረስ የሚለው አይሠራም፡፡ ትንሽም ብትሆን አንጎል ካለቻቸው እነሱም ሆኑ ሌላው አሽቃባጫቸው እንዲህ ለማለት የሚደፍሩም አይመስለኝም፡፡ ለነሱ ሲሆን የሚሻር ለኢትዮጵያውያን ሲሆን ግን የሚከበር ሁለት ጎናዊ ህግ  ሊኖር አይችልም፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ተብዬውም አፍ የለውም፡፡ ላለፉት አምስትና ስድስት ወራት ወያኔ እንደፈለገች ስትሆን ዝም ብሎ አሁን እርሷ ስትጠቃ ከዚህ መልስ ከዚያ መልስ የሚል ወገን ካለ “ቀበጥ አማት ሲሶ ብትር አላት” እንዲሉ ነውና እርሱም የዱላው ተካፋይ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በዱላ ባይገኝ በጥሩ የዲፕሎማሲ ዘመቻ ማደባየት ተገቢ ነው፡፡ “ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ” ብሎ ነገር ከእንግዲህ ሊሠራ አይገባም፡፡ ለወያኔ ሲሆን የጥቃት ድንበሩ አዲስ አበባን አልፎ ኬንያና ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ ስታጠቃ አሸንጌና ተከዜ ሊሆኑ አይችሉምና ወሳኙ የውጊያ አቅምና ችሎታ እንጂ እስካሁን ተደፍጥጦ የነበረ ህግና ሥርዓት ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ይህ ጦርነት ኢትዮጵያውያንን የገደለውንና ያጎሳቆለውን ወያኔ ቢቻል በነፍስ ይዞ ወደ ፍርድ ለማቅረብ ያ ባይቻል ወደመረጠው የሲዖል ሀገረ መንግሥቱ ለመሸኘትና የተዘረፈውን ንብረት ወደቦታው ለመመለስ ታስቦ መከናወን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ መልስ የሚቆም ውጊያ ከሽንፈት አንድ ነው፡፡ የሞቱ ወገኖቻችንን ሕይወት መመለስ ባይቻል የተዘረፈ ሀብት ንብረትን ግን ከገባበት ገብቶ መመለስ ይቻላልና በዚህ ረገድ ይታሰብበት፡፡ በመሠረቱ ጨካኝ ጠላትህን እገባበት ገብተህ እንዳያርመው አድርገህ መደቆስ እንጂ ዛሬ ብታዝንለት ነገ መመለሱ አይቀርም፡፡ በዚህ አጋጣሚ አማራ ሆነው በገንዘብ በመገዛት የገዛ ወገናቸውን ሲያስጨርሱ የነበሩ ይሁዲዎችን በተጨባጭ ማስረጃ አረጋግጦ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይገባል፤ “ጠላትማ ምንጊዜም ጠላት ነው፤ አስቀድሞ መግደል አሾክሹዋኪውን ነው” እንደተባለው ለነዚህ ዓይነቶቹ ልበ ደንዳና ሆዳሞች የሚራራ አንጀት ሊኖረን አይገባም፡፡ ከዚህ ነጥብ አንጻር ብዙ እየሰማን ነውና በግምባር ያላችሁ ወገኖች በተለይ በነዚህ ሰዎች ላይ መረር ያለ እርምጃ ልትወስዱ ይገባችኋል፡፡ አለበለዚያ ታጥቦ ጭቃ ነው፤ እነዚህን መሰል ሰዎች በመሃላችን እስካሉ ድረስ የነፃነት ቀንዲል መጨበጥ እንዳማረን ይቀራልና ከምንጊዜውም በበለጠ እንጠንቀቅ፡፡ ወያኔ ይህን ሁሉ ግፍና በደል ስትፈጽም ያገዛት ተልእኮውን ከፈጸመላቸው በኋላ ራሱም መገደሉ የማይቀርለት ሆዳሙ አማራ ነው፡፡ … የብአዴን ጉዳይ ራሱን የቻለ በመሆኑ ታሪክ የራሱን ፍርድ ይሰጣልና አንቸኩልም፡፡ እንጂ ለዚህ ውርደት ያበቃን ይህ ለሆዱ ሲል የማይሸጠው ነገር የሌለው ወያኔ-ሠራሽ አሻንጉሊት ቡድን ነው፡፡ 

በዚህ ጦርነት ሀብት ንብረታቸውና ገንዘባቸው ሳያሳሳቸው ከጅምሩ አንስቶ ሲዋደቁ የነበሩ ባለሀብቶችንና ታዋቂ ግለሰቦችን ማመስገን ተገቢ ነው፡፡ ሀብትም ሥልጣንም፣ ዕውቀትና ዕውቅናም የሚገኘው ሀገር ስትኖር ነው፤ ይህን እውነት በሚገባ የተገነዘቡ በጣም ጥቂት ሀብታሞች በዚህ በጭንቅ ወቅት ከሀገራቸው ጎን አልተለዩም፡፡ ከዚህ አኳያ በተለይ አቶ ወርቁ አይተነው እያደረገው ያለውን ሀገርን ከጥፋት ኃይሎች የመታደግ ግለሰባዊ እንቅስቃሴ በበኩሌ በእጅጉ አደንቃለሁ፡፡ ስንትና ስንት ገብጋባና ቦቅቧቃ ሀብታሞች ፈርተው ተደብቀው ምንም አስተዋፅዖ ሳያደርጉ ይህ ግለሰብ ግን በቆላ በደጋ እየተጥመነመነ ለእናት ሀገሩ በመታገል ላይ ነው፡፡ ስለሀገር ምንነትና ስለወገን ደኅንነት የገባው ሰው ነው፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው ይባላል፡፡ ብዙ ባለሀብቶች አንድ ቀን አንሶላ ለሚጋፈፏት ኮረዳ ሴት ቤትና መኪና እየገዙ የሀገርን ሀብት ሲዘባነኑበት የሀብታቸው ምንጭ የሆነው ምስኪን ሕዝብ ግን መከራ ፍዳውን ሲያይ ዘወር ብለው አያዩትም፡፡ እውነቱን ለመናገር በርካታው ባለሀብት ድፍን ቅል ነው – በሀገራችን ሀብትና አንጎል እምብዛም አይገናኙም፤ ለነገሩ ሀብት ለማከማቸት ጭካኔን እንጂ ቀና አስተሳሰብን እምብዝም አይፈልግም – በአብዛኛው ማለቴ እንጂ ለእውነት የተጠጉ ባለፀጋዎች የሉም ማለቴ አይደለም፤ ቁጥራው ያን ያህል ባይንም በሃቀኛው መንገድ ለፍተውና ደክመው ሀብታም የሚሆኑ እንደገብረየስ ቤኛ ያሉ የሀገር ባለውለታዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንኳንስ ለሀገር፣ ለቀጠረው ሠራተኛም ደንታ የማይሰጠው ድንጋይ ራስ ሀብታም ሞልቷል፡፡ ወደ ሀብት ጫፍ ያደረሱትን የገዛ ሠራተኞቹን በከፋ የኑሮ ውድነትና በክፉ አስተዳደር እያስለቀሰ እርሱ አውሮፓና አሜሪካ ከነቤተሰቡ ገንዘብ አፍቃሪ ቁራኛው በል ባለው ጊዜ ሁሉ እየተመላለሰ የሚዝናና ከብት ሞልቷል – አገር ቤት የርሱ ቅጥር ሠራተኛ በርሀብ አለንጋ እየተገረፈና ቢታመም ለራስ ምታት ማስታገሻ የሚሆን አስፕሪን መግዣ አጥቶ በስቃይ እየተቆራመደ ሣለ እርሱ ግን ዱባይንና ሻንጋይን የውኃ መንገዱ ያደረገ ስንትና ስንት ገልቱ ሀብታም አለ – የአእምሮ ድሃ የገንዘብ ሀብታም የሆነ፡፡ በዚህ ረገድ ቢያወሩት ታሪኩ ብዙ ነው፤ በተለይ ከሀብት ክፍፍል አኳያ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙም የታደልን አይደለንም፡፡ የሰው ልጅ ደግነቱ ዕድሜው አጭር መሆኑ በጄ እንጂ ይህ ችግራችን ብዙ ያናግራል፡፡ አንዳንድ ደንቆሮ ሀብታም እንዲያውም ሀገር ለድሃው ብቻ የተፈጠረች ሳይመስለው አይቀርም፡፡ ሀገር ግን የሁሉም ናት፡፡ በተለይ ደግሞ የብዙ ነገሮች ባለቤት የሆነው ሀብታሙ አብዝቶ ሊጨነቅላት ይገባል – ድሃውማ ምን ሲያጣ! ብቻ ዕንቆቅልሽ ነው ብዙው ነገር ሲታይ፡፡ ለማንኛውም ወርቁ አይተነው ልጅ ይውጣለት፡፡ ሌሎቻቸውም የርሱን አርአያ እንዲከተሉ እንጸልይ፡፡ ለባለሥልጣኖቻችንም ማስተዋልን እንዲሰጥልን ጭምር፡፡ ….

ብቻ …. በዋናነት ሀገራችን ከተደገሰላት የመከራ ድግስ ትዳን፡፡ ሌላው ይደረስበታል፡፡ መልካም የድል ዘመን ያድርግልን፡፡ ድሉ የኢትዮጵያ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ጥያቄው መቼና በማን በኩል የሚለው ነው፡፡ የሚጠበቀው ድል በማንም ይምጣ ከዚህች ዓመት ባያልፍ ግን በበኩሌ ደስ ይለኛል፡፡ ይደረግልናል ብለን እንመን ይደረግልናል፤ ሻሎም፡፡   

Filed in: Amharic