>

 "ዶ/ር  ዐቢይ አሕመድ ለጥቁር ሕዝቦች ያቀረቡት ጥሪ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ድጋሚ እንዲያብብ አድርጎታል....!!!" (ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ)

 “ዶ/ር  ዐቢይ አሕመድ ለጥቁር ሕዝቦች ያቀረቡት ጥሪ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ድጋሚ እንዲያብብ አድርጎታል….!!!”

ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገሪቱ ከሕወሓት የሽብር ቡድን ጋርና ሉዓላዊነቷን ከተዳፈሩት ምዕራባውያን ጋር የገባችበትን ጦርነት አስመልክቶ ለጥቁር ሕዝቦች ያቀረቡት ጥሪ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ድጋሚ እንዲያብብ እንደሚረዳ ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ዘካሪያ ገለጹ፡፡

የታሪክ መምህርና የአገር ሽማግሌው ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ ለኢትዮጵያ ፕሬስ እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለጥቁር የአፍሪካ ሕዝቦች ያስተላለፉት ጥሪ ተቀዛቅዞ የነበረው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ዳግም እንዲጀምር ከማድረግ አንፃር የራሱ የሆነ በጎ ተጽዕኖ አለው፡፡

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 1960ዎቹ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነፃ መውጣት የመሠረት ድንጋይ የጣለችና በቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት በኩል ስለ አፍሪካ ብዙ የተሟገተች አገር ስትሆን በዚህም በርካታ የአፍሪካ አገሮች የነፃነት ተምሳሌትና እናት አድርገው እንደሚመለከቷት አውስተዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ ምዕራባውያን ዳግም እያመጡብን ያለውን የባርነት ቀንበር በጋራ እንስበር ከሚል የመነጨ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች በመልካም እየተቀበሉትና በጎ ምላሽ እየሰጡት መሆኑን ሰሞኑን እየታየ ነው ሲሉ ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹በተለያዩ አገራት የሚገኙ አካላት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ጦርነት ብቻዋን እየተዋጋች ነው ከሚል ንግግር አንስቶ የ“ይበቃል” መፈክርን በመያዝ የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ እስከማስተጋባት ደርሰዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት የአፍሪካውያንም ነው የሚል እሳቤ እየተፈጠረ ነው›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አሕመድ፤ ይህ ደግሞ የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ምን ያህል እየተመለሰ እንደሆነ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ ምዕራባውያን አፍሪካውያን ተባብረን እንደግ የሚል መንግሥት ሲነሳ የማፈንና ከሥልጣን እንዲወገድ የማድረግ ልምድ ያላቸው ሲሆን፤ ዶክተር ዐቢይ ደግሞ አፍሪካን ያማከለ የመልማት ሀሳብ ይዞ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ ጥርስ እንደተነከሰበት አንስተዋል፡፡

የታሪክ መምህሩ አክለውም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት ጥሪ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ዳግም በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ የተነሳሱ ሲሆን ይህንን አስፍቶ ሁሉም ዘመቻውን እንዲቀላቀል ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የውስጥ ችግር ቢወጠሩና ልዩነት ቢፈጥሩም ሉዓላዊነታቸውን የሚገዳደር ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያ የሚል አንድ ቃል ተናጋሪ ናቸው፡፡ ተመልከት ዓላማህን! ተከተል አለቃህን! በሚለው ብሂል መሠረት መቆየታቸውን ታሪክ ያረጋግጣል የሚሉት መምህሩ፤ አሁንም ቢሆን ምዕራባውያን አገራት እየቀለቡትና እየነዱት የመጣውን የሽብር ቡድን በጋራ የመመከት አቅም አላቸው ሲሉ ሀሳባቸውን ተናግረዋል፡፡

አላዛር መኮንን

Filed in: Amharic