>

የአሸባሪው ግብዓተ መሬት እስኪፈፀም ሕዝባችን ትግሉን ይቀጥላል - የሶማሊ ክልል መንግሥት!!

የሶማሊ ክልል መንግሥት. የተሰጠ መግለጫ!!!

 የአሸባሪው ግብዓተ መሬት እስኪፈፀም ሕዝባችን ትግሉን ይቀጥላል 

ኅዳር 24/2014 (ዋልታ) የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ግብዓተ መሬት እስኪፈፀም የሶማሊ ሕዝብ ትግሉን እንደሚቀጥል የሶማሊ ክል መንግሥት አስታወቀ።
የሶማሊ ክልል መንግሥት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ባለፉት ሦስት-አሥርት ዓመታት አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ባደረሰው ዘርፈ ብዙ ችግሮች እና በደሎች መካከል በሶማሊ ክልል ሕዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ እና መከራ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ አዕምሮ የሚጠፋ አይደለም።
አሸባሪው የወያኔ ቡድን በሶማሊ ክልል ከፈፀማቸው ወንጀሎች መካከል ንፁሀን ዜጎች ከነሕይወታቸው ተቀብረዋል፣ ህፃናት እና ሴቶች ተደፍረዋል፣ ክቡሩ የሰው ልጅ ከአውሬ ጋር ታስሯል፣ ወጣቶች ተገድለው በገመድ ተጎትተዋል፣ ይህ ሁሉ ግፍ በአሸባሪው ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት በጄኔራሎቹ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የተፈፀሙ እንደነበር ይታወቃል።
የሽብር ቡድኑ በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማለያየት ይከተል የነበረው የ‘ከፋፍለህ ግዛ’ ፖሊሲ በሶማሊ ክልልም በመተግበር የክልሉን ሕዝብ በጎሳ በመከፋፋል በጥላቻ ላይ የተመሠረተ ግንብ በመገንባት እርሰ በእርሳቸው በጥርጣሬ እንዲተያዩ በማድረግ ሥልጣኑን ለማራዘም ተጠቅሞበት የኖረ አረመኔ ቡድን ሆኖ ቆይቷል።
አሸባሪው ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ የተባበረ ክንድ ከተወገደ በኋላ እኔ ሥልጣን ካጣሁ ሀገር አፈርሳለሁ በሚል በእብሪት ጥቅምት 24/2013 ቀይ መስመር በሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የሆነው የወያኔ እኩይ ተግባር ለመመከት የሀገራችን ሕዝቦች በሠሩት ተጋድሎ የሶማሊ ክልል ሕዝብ በግንባር ቀደምትነት ተሳትፏል፣ የአሸባሪው ቡድን ግብዓተ መሬት እስኪፈፀምም ሕዝባችን ትግሉን ይቀጥላል።
ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በሶማሊ ክልል 10 ዞኖች በተከሰተው ድርቅ የክልሉ መንግሥት ሕዝብና እንስሳትን ለመታደግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆንም፣ ሕዝቡ ከተፈጠረው ድርቅ ጎን ለጎን የሀገር ህልውናና ሉአላዊነትን በማስቀደም አካባቢውን ከአሸባሪዎች በመጠበቅ ትልቅ ተጋድሎን በማድረግ ላይ በመሆኑ ላቅ ያለ ምስጋና የክልሉ መንግስት ያቀርባል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊ ክልል ሕዝብ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን የገባችበት የህልውና ጦርነት የሶማሊ ክልል ተወላጅ ዲያስፖራ ማህበረሰብ በተለያዩ በውጭ ሀገራት ኮንፈረንሶችን አዘጋጅተው ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከመንግስት ጎን በመሆን ድጋፋቸውን በመግለፅ ላይ ናቸው።
በሌላ በኩል በሚኒሶታ የሚኖሩ የክልሉ ዲያስፖራ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ግንኙነትን ፈጥረው በማህበራዊ ሚዲያዎች የሀሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችን እኩይ ሴራ ከማክሸፍ ባለፈ፣ በክልሉ ድርቅ የተከሰተባቸው አከባቢዎች እርዳታ በማድረግ ከሀገራቸው እና ከሕዝባቸው ጎን መቆማቸው በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር  የሚኖረው የክልሉ ሕዝብ በሀገሩ ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንደማይደራደር የሚያሳይ ነው።
የህልውና ጦርነቱን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት በሀገር ህልውናና ሉአላዊነት የማይደራደረው ጀግናው የሶማሊ ክልል ልዩ ሀይል ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከሽብርተኛው ህወሃት ጋር ግንኙነት ያላቸው አሸባሪዎችና የክልሉን ሰላም ለማናጋት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ፣ አጋጣሚውን ተጠቅመው ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በጀግንነት ረዥሙን ድንበር በመጠበቅ አለኝታነቱን በድጋሚ በማሳየት ላይ ይገኛል።
የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ መሀል ሀገር ሰላም ሆኖ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ የሶማሊ ክልል ሕዝብና የፀጥታ ሀይሎች የሀገራችን ዳር ድንበር በመጠበቅ ላይ በመሆኑ የሀገራችን ሕዝብ ምንም አይነት ስጋት እንዳይሰማውና ትኩረቱን ሀገር ማዳኑ ላይ እንዲያደርግ የሶማሊ ክልል መንግሥት ይገልጻል።
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት በተለያዩ ግንባሮች በአሸባሪው ቡድን ላይ የተገኘው ድል የሶማሊ ክልል ሕዝብ የኮራበት ሲሆን፣ ቡድኑ እስኪደመሰስ የሶማሊ ሕዝብ ከጠቅላይ ሚኒስትርና ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አብይ አህመድ ጎን መሆኑን ይገልጻል።
በመጨረሻም ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎች፣ ድርጅቶች ለዘመናት የቆየው የሀገራችን ሕዝቦች የመረዳዳት ባህል የሆነውን በማስቀጠል የተጎዱ ወገኖቻችንን በመርዳት እንዲሁም በሶማሊ ክልል የተፈጠረው ድርቅ ለሕዝባችን የምናደርገውን እርዳታ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድታደርጉ እንጠይቃለን።
የሶማሊ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ
ኅዳር 24 ቀን 2014 ዓ.ም 
ጅግጅጋ
Filed in: Amharic