>

ከዋናው ጁንታ ነጋዴው ጁንታ ባሰ!! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

ከዋናው ጁንታ ነጋዴው ጁንታ ባሰ!!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


ኅሊና ሲጠፋ ሆድ የሰውነታችን ገዢ ይሆናል፡፡ ሆድ ገዢ ሲሆን ሀፍረትና ይሉኝታ፣ ሃይማኖትና የሞራል ዕሤቶች፣ ባህልና ትውፊት ገደል ይገባሉ፡፡ ሆድ አምላኪነት ሲነግሥ ወንድማማችነትና እትማማችነት የሉም፡፡ በዐይናችን የሚመላለሰው ቀፈት የሚሞላው የምግብ ዝርዝርና የምንገዛው ዘመናዊ አውቶሞቢል እንዲሁም የምንሠራው የህንጻ ዲዛይን ብቻ ነው፡፡ ሰውነት ይረሳና ቁሣዊነት ዋና መገለጫችን ይሆናል፡፡ በዘመነ ሆድ እርስ በርስ መባላት ተራ የየዕለት ገጠመኝ ነው የሚሆነው፡፡ ይህንን እውነት ከእኛ ከኢትዮጵያውያን የወቅቱ ሁኔታና ከጅቦች ተፈጥሯዊ ጠባይ መረዳት ይቻላል፡፡ ጅቦች በሆዳምነታቸው ይታወቃሉ – በጉልበታምነትና በፍጥነታቸውም ጭምር፡፡ ጅብ ከራበው የገዛ ወገኑን አይለቅም አሉ፡፡ ለዚህም ነው ጎን ለጎን እንጂ ፊትና ኋላ ሆነው አይሄዱም የሚባለው፡፡ የሰው ጅብ ከመሆን ያውጣን! ሀገራችን የሰው ጅቦች መናኸሪያ ሆናለች፡፡ ከሌሎች እንስሳት በእጅጉ የሚያንሱ የሰው ጅቦች፡፡

በዚያን ሰሞን በርበሬ ተሰቅሎ ከነበረበት 400 እና 500 ብር ዋጋ ወርዶ ሁለት መቶ ብርን ሊጠጋ መሆኑ ሲነገር ሰማሁና ማንጠግቦሽን አዋየኋት – ባለቤቴን፡፡ ስንወያይ የበርበሬ ወቅት ትሳስ ነውና ከዚህም ሊወርድ ስለሚችል ትንሽ እንጠብቅ አለችኝ፡፡ እስታሁን ብልኅ ነበረች፡፡ እንዳለችው ጠበቅን፡፡ ነገር ግን ማንኛውም ሎጂክና ምክንያታዊነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገባ ድራሹ እንደሚጠፋና የእውነት ኮምፓስ ለአሁኒቷ ኢትዮጵያችን እንደማይስማማት ሁሉ በርበሬም መቀነሱ ቀርቶ በ10 ቀናት ውስጥ ብር 350 ገደማ መግባቱን ትናንት ማታ ሰዎች አረዱን፡፡ የምትገርም ሀገር ከሚገርሙ ነጋዴዎች ጋር፡፡ ደርግ ቆፍጣናው ወድዶ አልነበረም ሦስቱን የበርበሬ ነጋዴዎች በጥይት ዘርሮ በርበሬ ጥምቡን እንዲጥል ያደረገው፡፡ አሁንማ ማን ነክቷቸው! ሁሉም የመንግሥት የሥራ ኃላፊና ፖለቲከኛ ካድሬ ሌባና ከነጋዴው ጋር አብሮ በሊታ ነው፡፡ ሁሉም ዋሾና ኅሊና ቢስ ከርሳም ነው፡፡ ሰው ገድለህ ብትታሰር እኮ ገንዘብህን ይጭነቀው እንጂ ፋይልህ እንዲጠፋ ይደረግና ነፃ ትወጣለህ፤ ከፈለግህም – ራስህ የገደልከውን ወይ ያስገደልከውን ሰውዬ – ሟቹን ራሱን በጥፋተኝነት ልታስፈርድበትም ትችላለህ፤ ገንዘብና ዘረኝነት የማይሠሩት ተዓምር የለም – (ወይ ኢትዮጵያ – እናትዬ ጉድሽ!!) ሁሉም ባለሥልጣን ዜጎች ቢቀቀሉ ቢገነተሩ ግድ የለውም፡፡ እውነተኛ የሕዝብ ዳኛና አስተዳዳሪ በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ጩኸታችን ሁሉ የቁራ ጩኸት ነው፡፡ በብሂሉ “በጨለማ ቢያፈጡ በባዳ ቢቆጡ” እንዲሉ ዓይነት ነው አሁን ያለንበት የጨለማ ዘመን፡፡ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ታድለው!! በነገራችን ላይ ይህ የምጠቅሰው ዋጋ ለአንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ እንጂ ለፈረሱላ እንዳይመስላችሁ፡፡ አንድ ፈረሱላማ ከብር ስድስት ሽህ በላይ ነው፡፡ ዱሮ እኮ በብር 20 እና 30 የምንገዛው ነው! ወይ ጊዜ፡፡ አንድ ኪሎ ጥቁር ገብስ ስንት እንደሆነ ሰማህልኝ? 55 ብር!!

ትናንት ደግሞ በፊት ጊዜ በሣንቲሞች እገዛው የነበረውን ባለ 1.5 የኤሌክትሪክ ገመድ ለሆነ ጉዳይ ልገዛ ሱቅ ሄጄ ብጠይቅ በሜትር ብር 30 አሉና ጆሮየን  አጋሉት፡፡ ደግሞም አንዲት መናኛ አነስታይ ሶኬት ፈልጌ ነበርና ብጠይቅ ብር 60 አሉኝ – የዛሬ ዓመት እኮ ብር 20 ገደማ ነበረች፡፡ ነጋዴው እምብርት አጥቶ ሊፈጀን ነው – ባንድ እግር ወያኔዎች በጥይት የሚያረግፏቸው ዜጎች ሳይሻሉ ይቀራሉ? አንዴ መሞት እኮ ግልግል ነው – የአቢይ መንግሥት ነጋዴዎች ግን ቀስ በቀስ በርሀብና በጭንቀት ሊጨርሱን ከሁሉም የክፋት ኃይሎች ጋር ተማምለው ተነስተውብናልኝ፡፡ ምን አለፋችሁ ገበያው ጨርቅ ያስጥላል – የአራትና አምስት ወር ደሞዝህ ቢሰጥህም እንኳ አንድ ወር አያኖርህም፡፡ በዚህ ሁኔታ የአንድ ተራ ሠራተኛ የወር ደሞወዝ ከሻይና ዳቦ ላያልፍ ነው – ለሱም ከበቃ፡፡ አንዲት ብጥሌ ብርጭቆ ሻይ በተራ የመንገድ ዳር መሸጫ ብር 5 ወይ 6 መሆኗን ታውቃለህ? አንድ ጉርሻ እማትሆን ፉርኖ ዳቦስ ብር 5 መሸጧን ሰምተህልኛል? ሕዝብ የት ይግባ? ማን አለሁህ ይበለው? በዚያ ላይ በየመሥሪያ ቤቱ ስትሄድ ለአገልግሎት የሚከፈለው ገንዘብ ገና ስትሰማው  ይዘገንንሃል፡፡ሁሉም ቢሮ እንዳሻው እየተነሳ ብር መቆለል ነው – የ10 ብሩን የመንጃ ፈቃድ ዕድሳት – ለምሣሌ – ብር 620 አድርገውታል፡፡ የሕዝብን አቅም ማገናዘብ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሕዝብ እንደባይተዋር ነው የሚታዬው – ከጨረቃ እንደመጣ ባዕድ ነገር፡፡ መብራት ኃይል  አንዱና ዋናው ማጂራት መቺ ነው፡፡ ቴሌ ሁለተኛው ጨቡዴ ነው፡፡ ጅምሩክና አገር ውስጥ ገቢም ዋናዎቹ ደም መጣጭ መዥገሮች ናቸው፡፡ እነዚህና ሌሎቹም የመንግሥት ዘራፊ ድርጅቶች በምንም ዓይነት ህግ አይመሩም፡፡ መሪያቸው ፍቅረ ንዋይ ነው፡፡ ሕዝብን ማስለቀስ የመንግሥት የመቶ ዓመት መሪ ዕቅድ ይመስላል፡፡ ብትጮህ ብታነባ ሰሚ የለም፡፡ በእጅህ ካልሆነ ደግሞ በእግርህ ሄደህ ጉዳይህን የምታስፈጽምበት መሥሪያ ቤት በጭራሽ የለም – ቤተ ክርስቲያንም ቢሆን! – እንዲያውም በዚያ ባይብስ? ከእግዚአብሔርም ከመንግሥትም የተለያዬ ሕዝብ ደግሞ ብዙ መሰቃየቱ አይቀርም፡፡ ዘመኑ የብላ ተባላ ዘመን ነው፡፡ እኔማ የዚህን ሁሉ ጉድ መጨረሻ ለማየት በጣም ጓጉቻለሁ – መጨረሻ ካለው፡፡ ሰው መሃል እየኖሩ ሰውን መናፈቅ፡፡ ባገር ውስጥ እያሉ ሀገር አልባ መሆን፡፡ በመልክና በቅርጽ አንተን በመሰሉ እንጂ በባሕርይና በይዘት አንተን ባልሆኑ ሰዎች መመራት፡፡ የክፍለ ዘመናችን ዕንቆቅልሽ፡፡ 

…. እያንዳንዱን ዕቃ ስትጠይቁ ነጋዴው ከወያኔዎችና ከልጆቻቸው ብልፅግናዎች ጋር ተባብሮ ዜጎችን ደም ለማስነባት የሚተጋ ይመስላል፡፡ ይህን ሁሉ ብር የሚያጋብሱት የት ሆነው ሊበሉት እንደሆነ ቆይተን የምናይ የምናየው ይሆናል፡፡ አሁን ግን መንግሥትም ጤናማ ኅሊናም ስለሌሉ “እገሌ ይህን ያድርግ፣ እገሌ ደግሞ ያን ያድርግ” ብለን አስተያየት መስጠት እንቸገራለን – ጆሮዎች ሁሉ ወደሆድ ወርደው እንዳያዳምጡ ተደርገዋልና፡፡ ጊዜና ፈጣሪ ግን ችግራችንን እንደሚፈቱት ጥርጥር የለኝም፡፡ ይህንን እውነት ልብ አድርጉልኝ ደግሞ – ጅብ ከመሆን አህያ መሆን የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ … ግን ግን ሰው በስድስቱም አቅጣጫ ይወጠራል? በስመ አብ!! 

Filed in: Amharic