>

የአሜሪካ ህዘብ ፣ የፕሬዜዴንት ባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን ጎጂ ፖሊሲ መቃወም ያለበት ? (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ከአፍጋኒስታን እስከ ኢትዮጵያ፣

ለምን ይሆን የተባበረችው አሜሪካ ህዘብ የፕሬዜዴንት ባይደን አስተዳደር ከኢትዮጵያ አኳያ የሚከተለውን ጎጂ ፖሊሲ መቃወም ያለበት ?

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com

የቀድሞው የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት ሚስተር ሬጋን ልዩ ረዳት እና በካቶ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ የነበሩትና‹‹ Foreign Follies: America’s New Global Empire >> የተሰኘውን ዝነኛ መጽፍ ጨምሮ የበርካታ መጽሀፍት ደራሲ የሆኑት አቶ ዶግ ባንዶው (Mr. Doug Bandow ) እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ነሃሴ 31 2021 የፕሬዜዴንት ባይደን የአፍሪካ ቡድን ላይ የሰጡት የሰላ ትችት በድምር ሲጠቃለል የዛሬውን አስተያየቴን ያጠናክርልኛል፡፡ እኚሁ ስመጥርና ጎምቱ የፖለቲካ ሰውነት ያላቸው  የህሊና እና የሞራል ስብእናቸውን የተላበሱ አሜሪካዊ ምሁር የባይደን አሰተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ እንደሚከተለው ነበር የተቹት፡፡ የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ አኳያ የሚከተለው ፖሊሲ፡-

  • አንድ አይነት ያልሆነ( በየግዜው የሚቀያየር)(incoherent)
  • የተሳሳተ (, misguided)
  • የረዥም ግዜ አላማ የሌለውና (shortsighted)
  • አደገኛ የውጭ ፖሊሲ ነው በማለት ነበር የተቹት (dangerous policy towards Ethiopia.)

ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያ የተባበረችው አሜሪካ በአፍሪካው ቀንድና በምስራቅ አፍሪካ ክፍል ለከፈተችው የጸረ ሽብር ዘመቻ ኢትዮጵያ እውነተኛ እና ውጤታማ አጋሯ መሆኑ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ይህ ብቻውን ኢትዮጵያን አሜሪካ ወዳጅ ሀገር መሆን የሚስችላት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካው ቀንድ ስልታዊና ጠቃሚ ሀገር ናት፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ በተጻራሪ አቋም የሚገኘው የተባበረችው የውጭ ፖሊሲ እና የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚወስደው የቅጣት እርምጃ እና ለወደፊትም ቅጣቱን ለመቀጠል መወሰኑ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የሚጎዳው ቀሪውን የአፍሪካውን ክፍል እንደሆነም ነው ሚሰተር ዶግ ባንዶው በጽሁፋቸው ላይ ያስቀመጡት፡፡  ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአንድ ወገን ያደላውን የባይደን አስተዳደር አፍሪካ ቡድን ፖሊሲ ላይ እምነት እንደሌላቸው፣ከገለጹ በኋላ የተባበረችውን አሜሪካ የረዥም ዘመን ፍላጎት እንደማይጠቅም  አበክረው አሳስበው ነበር፡፡

ስለሆነም የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ የተባበረችው አሜሪካ ታሪካዊ ሀገር በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው የተሳሳተ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ወጣት ላይ  የሚያሳድረውን አፍራሽ ተጽእኖ በተመለከተ ግንዛቤ እንዲወስድ እማጸናለሁ፡፡ 75 ከመቶ የሆነው ህዝቧ ወጣት በሆነባት ኢትዮጵያ፣ከአፍሪካ ሀገራት በህዝብ ብዛት ሁለተኛ ስፍራ ላይ በምትገኘው ኢትዮጵያ የህዝቧ አመለካከት በፍቅርና አንድነት መኖር እንጂ ለመገዳደል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ምኞትና ፍላጎት ችጋርን ለማጥፋት፣ነጻነትን ለመቀዳጀት፣በህይወት ለመደሰት፣ በሀገራቸው ምድር ላይ የግል ነጻታቸውን ለማስከበር መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ህዝብ የለጋሽ ሀገራት በተለየም የምእራቡ አለም መዘባበቻ መሆኑ ሰልችቶታል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ካለምእራቡ አለም እርዳታ መኖር አይችልም መባሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ልብ ያደማ መስሎኛል፡፡ በእውነቱ ለመናገር እንዲህ አይነት የምእራባውያን ትምክህት ቀመስ ንግግር መምከን የሚችለው በእግዚኦታ፣ኡኡታ እና ፕሮፓጋንዳ ጩሀት ሳይሆን በአንድነት እና በነጻነት ጠንክረን መስራት ስንችል ብቻ ነው፡፡ በሀገራችን የአምባገነንነት ዘር እየዘራን፣በጎሳ ተከፋፍለን ብንጮህ ሰሚ አናገኝም፡፡ ባለቤቱን ካልናቁ ……እንዲሉ የምእራባውያን መጫወቻ ላለመሆን በሰውነት ደረጃ ላይ ቆመን የስራ አርበኛ መሆን አለብን በማለት ሳስታውስ በታላቅ ትህትና ነው፡፡ እኛ በጠነከርን ቁጥር ወዳጆቻችን ይጨምራሉ፡፡ ይህ እንኳን እውን ባይሆን ማንም ተነስቶ አይጨፍርብንም፡፡ በእኛው አፈርና ውሃ የለማችው ሱዳን፣በውስጥ የፖለቲካ ችግር የምትናጠው ሱዳን ሳትቀር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቃ ገብታ ከልካይ ማጣቷ ሲታሰብ የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ እርስበርስ ተካፋፍለን ከስተን ያየችን ሱዳን በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እሳት ለመጫር መሞከሯ ሲስተዋል ልብን ያደማል፡፡ እኛ የአነዛ የተርቦቹ ልጆች ነንን የሚል ጥያቄን ያጭራል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሱዳን በጊዜያዊ እብሪትና እብጠት ሰክራ የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቃ የጦር ሰራዊቷን በማስፈሯ ምክንያት  (የተነሳ ) የኢትዮጵያን ዳርድንበር ለማስከበር ወድቀው የቀሩ ኢትዮጵያዊ ጀግኖች አጽም ሳይቀር በመቃብር ውስጥ የሚንቀሳቀስ ይመስለኛል፡፡

የጥቁር አፍሪካውያን ተለውጠዋል፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ፖሊስ ከአፍሪካ አኳያ የምትከተለው ፖሊሲ አልተቀየረም

በርካታ የፖለቲካ ሰዎች የአይምሮ ጭማቂዎቻው ዳጎስ ባለ የጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ እንዳፈሩት ከሆነ ቀሪው አለምና አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ዘመን እና ከቀዝቃዛው ጦርነት ከነበረው ነባራዊ ሁኔታቸው ዛሬ ተቀይረዋል፡፡ በቅኝ አገዛዝ ዘመን እና የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የነበሩ ሃያላኖች ዛሬ ተገዳዳሪ ሀገራት ተፈጥረውባቸዋል፡፡ ለአብነት ያህል ጸሐይ አይጠልቅባትም ተብሎ ሲነገርላት የነበረው ታላቋ ብሪታኒያ ዛሬ በእነ ብራዚል፣ህንድ በኢኮኖሚ እምርታ እየተቀደመች ነው፡፡( ይህ ሲባል ግን ታላቋ ብሪታንያ አበቃላት ማለት አይደለም፡፡ ዛሬም ይህች ታላቅ ሀገር በኢኮኖሚ ጠንካራ፣በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጠቀች፣የበለጸገች ሀገር ናት፡፡ ሆኖም ግን እንደወትሮው በሌላ በሶስተኛ ሀገር ጣልቃ ገብታ ብቻዋን አዛዥ ናዛዥ መሆን አይቻላትም፡፡) አፍሪካ ብቻ አይደለም የተለወጠችው፡፡ ይህ እውነት በመካከለኛው ምስራቅ፣ሰሜን አፍሪካ፣ደቡብ ኤሽያ አለ፡፡ ማናቸውም ሀገራት ጣልቃ ገብነትን አይደግፍም፡፡ በአንዲት ሉአላዊት ሀገር የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ውጤቱ አውዳሚ ነው፡፡ ኢራቅ ተወራ ነበር ሆኖም ግን ኢራቅ አሁን ድረስ አልዳነችም፡፡ ያቺ በነዳጅ ዘይት ሀብት የናጠጠችው፣የተረጋጋ ህይወት የሚመራ ህዝብ ይኖርባት የነበረችው ሊቢያ በቦምብ የተደበደበች ሲሆን ውጤቱ ግን አላማረም፡፡ ሊቢያን አሳመማት፣ ከሊቢያም አልፎ ጠባሳው ወደ ቡርኪናፋሶ እና ማሊ፣ከዚህም እልፍ በማለት ዳፋው ሌሎችን የአፍሪካ ሀገራት አዳረሰ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከግብር ከፋዩ የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ላለፉት ሃያ አመታት በአፍጋኒስታን ወታደራዊ ተልእኮ እንዲውል ልእለሃያል ሀገር አሜሪካ በትሪሊዮን የሚቆጠር ዶላር ብትከሰክስም ውጤቱ ያሰበችው አቅድ ሙበሙሉ አልተሳካላትም ነበር፡፡ ምናልባት አለማዋ አፍጋኒስታንን ማዳከምና ማፈራረስ ከሆነ ተሳክቶላት ሊሆን ይቻለዋል፡፡ እርሷ ያቆመችው አሻንጉሊት መንግስት ከሃያ አመት በኋላ ተንኮታኩቶ ወድቋል፡፡ ዛሬ ያቺ ሀገር በአክራሪ እስላሞች እጅ ታሊባኖች ስር ወድቃ ፍዳዋን እያየች ትገኛለች፡፡ የአፍጋኒስታን ህዝብ ዛሬ እንደ ጎርፍ ወደ ኢራን በየቀኑ እየጎረፈ ይገኛል፡፡ በአውሮፓ ምድር ዋና ዋና ስደተኞች ከሚባሉት መሃከል የአፍጋኒስታን ዜጎች ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ በቅርቡ ከቤልሩሲያ ወደ ፖላንድ ለመሻገር አስቸጋሪ ጉዞ ከሚያደርጉት መሃከል የአፍጋኒስታን ዜጎች ይገኙበታል፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር የአሜሪካን በአፍጋኒስታን ጉዳይ ጣልቃ መግባት ያመጣው ነገር ቢኖር በተራው ህዝብ ላይ መዓትና መከራን ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም የተባበረችው አሜሪካ ታክስ ከፋይ ህዝብ እውነታውን መረዳት አለበት ባይ ነኝ፡፡ ከተባበረችው አሜሪካ ህዝብ ግብር ከፋይ ህዝብ ባለፉት ሶስት አስርተ ዓመታት በልማትና ሰብዓዊ እርዳታ ስም ከ10 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ እርዳታ መቅረቡ እሙን ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አብዛኛው የእርዳታ ገንዘብ የወያኔ አገዛዝ ሲሳይ ስለመሆኑ እንደ እነ ፕሮፌሰር አግሎግ ቢራራ የመሰሉ ስመጥር የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በጥናታቸው የደረሱበት ጉዳይ ነው፡፡ በእርዳታ የተሰጠው ብር በአብዛኛው ለጨቋኙ፣ከፋፍሎ ለሚገዛው የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ የመጨቆኛ መሳሪያ ውሎ እንደነበር ብዙዎች የኢትዮጵያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ ኢትዮጵውያን የሚያውቁት መራር እውነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንደ የአለም ባንክ፣የአለም የገንዘብ ድርጅት፣ የተባበረችው አሜሪካ የውጭ ተራድኦ ድርጅት፣የአለሙ መንግስታት ድርጅት ልዩ ወኪሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽሞ የነበረውን አይን ያወጣ፣ ተቋማዊና በአይነቱ ለየት ያለ ዝርፊያን፣ጉቦ፣ ወዘተ ወዘተ በተመለከተ ሙሉበሙሉ በሚባል መልኩ ችላ ማለታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እነኚህ አለም አቀፍ አበዳሪና ተራድኦ ድርጅቶች ሃላፊዎች ሰምተው እንዳልሰሙ፣አይተው እንዳላዩ ሆነዋል፡፡ የአለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች የሀዘን ስሜት አለማሳደር፣ዝምታ እና ሌሎች ምክንቶች ተጨምረውበት የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ የኢትዮጵያን ህዝብ (ሁሉንም የኢትዮጵያ ክልሎች የትግራይንም ክልል ህዝብ ይጨምራል) ለ27 ዓመታት እንደ ሰም አቅልጦ፣ አንደ ብረት ቀጥቅጦ ለመግዛት ጉልበት ሆኖታል፡፡

ባለፈው አመት ህዳር/2013 ዓ.ም. በአለም ባንክ ውስጥ ለሶስት አስርተ ዓመታት ያገለገሉት እውቁ የምጣኔ ሀብት ጠበብት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ ለብይነ መንግስታቱ ማህበር ባቀረቡት አቤቱታ የወያኔ አሸባሪ ቡድን በጦር ወንጀለኝነትና በሰው ልጅ ላይ ስቃይ በማድረስ ወንጀል እንዲጠየቅ በብዙ ደክመው እንደነበር፣ ሆነም ግን ጥያቄአቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ በተቃራኒው የተባበሩት መንግስታት የችግሩ አንዱ አካል እንደሆነ ፣ የብይነመንግስታቱ ማህበር ወቀሳ ማቅረብ እንዳልፈገ፣ በአንድ የጥናት ወረቀታቸው ላይ አስፍረውታል፡፡ ፕሮፌሰር አክሎግ በጽሁፋቸው አክለው እንደገለጹት ከሆነ ቡድኑ ወረራውን በአማራ እና አፋር ክልሎች ውስጥ እንዳስፋፋው፣ ከ7000 በላይ ትምህርት ቤቶችን ከጥቅም ውጭ እንዳደረጋቸው፣በማይካድራ ወዘተ ወዘተ በንጹሃን ሲቪል ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ ግድያ እንደፈጸመ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶች ሳይቀሩ ያጣሩትና በማስረጃ አስደግፈው ሪፖርት ያወጡበት ጉዳይ ነው፡፡

በእኔ የግል አስተያየት የተባበረችው አሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ለግብር የሚከፍለው ገንዘብ አግባብ ባልሆነ መንገድ ሲባክን ለምን ብሎ መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የባይደን አስተዳደር የአንድን ሀገር አንድነት አደጋ ላይ ለመጣል ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያሴረን ቡድን መርዳት ቢፈልግም የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ ፍላጎት ግን ለየቅል ነው፡፡ በነገራችን ላይ የወያኔ ኢህአዲግ ቡድን በስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 አመታት ውስጥ በአፍሪካው ቀንድ የተባበረችው አሜሪካ እውነተኛ አጋር እንደነበር የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር  ሟቹ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሰ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች የወያኔ ቡድን አባላት በሰልጣን ዘመናቸው በርካታ የተባበረችው አሜሪካን ባለስልጣናት የሆኑ ወዳጆችን በተለያዩ ምክንያቶች ማፍራት እንደቻሉ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ በአንድ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ ጠቅሰውታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቡድን ውስጥም ሳይቀር ወዳጆች ማፍራት እንደቻሉ ፕሮፌሰር አክሎግ አክለው በጥናት ወረቀታቸው ላያ ያሰፈሩት መራር ሀቅ ነው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር አክሎግ ጥናት ከሆነ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ከተባበረችው አሜሪካ የፖለቲካ ሰዎች መሃከል ወዳጆችን ማፍራት የቻለው ከኢትዮጵያ ህዝብ በዘረፈው ገንዘብ ጠበቃዎችን (lobbysts) ቀጥሮ ሀሰትን እውነት ለማስመሰል በከፈተው ዘመቻ ምክንያት ነው፡፡

በአጭሩ የተባበረችው አሜሪካ ታክስ ከፋይ ህዝብ ለእርዳታ የሚላከው ረብጣ ዶላር በችጋር ተቀስፎ ለተያዘው የኢትዮጵያ ህዝብ መድረሱን ማረጋገጥ ወይም የማወቅ መብት አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የተባበረችው አሜሪካ ግብር ከፋይ ህዝብ ሀገሩ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የለገሰችውን ረብጣ ዶላር በትክክለኛ መንገድ ስለመዋሉ በቂ መረጃ ያገኘ አለመስልህ አለኝ፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ለኢትዮጵያ የለገሰችው በ10 ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ዶላር ለተቸገረው የኢትዮጵያ ህዝብ በፍትሃዊ መንገድ ቢደርስ ኖሮ የህዝቡ የኑሮ ደረጃ ትርጉም ባለው ሁኔታ ሊለወጥ የሚችልበት ሁኔታ ሰፊ ሊሆን ይችል ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አብዝሃው የኢትዮጵያ ህዝብ የኑሮ ደረጃ መሻሻል አላሳየም፡፡ ትላንትም ሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ በአለም ላይ በድህነትና ጤናማ ካሆኑ ሀገራት መሃከል ግንባር ቀደሟ ናት፡፡ ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ አንድ ተአማኒነት ያለውን የተባበረችው አሜሪካን የጥናት መጽሔት ዋቢ አድርገው በጥናት ወረቀታቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆነ ‹‹ የተባበረችው አሜሪካ ለኢትዮጵያ ከለገሰችው ገንብ ውስጥ 30 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ›› በወያኔ ኢህአዲግ ዘመን(በስልጣን ላይ በነበሩበት 27 አመታት ውስጥ ማለቴ ነው) በወያኔ ቡድን ተዘርፏል፡፡ የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ከአራት አመታት በፊት ሲወድቅ የሀገሪቱ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንደነበር በርካታ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በጥናት ወረቀቶቻቸው ያስቀመጡት ጎምዛዛ ሀቅ ነው፡፡ ይህንን አሸባሪ፣ጨካኝ፣ሞራል አልባ፣ የስነምግባር ደሃ እና ለኢትዮጵያ አንድነት የሚደማ ልብ የሌለውን ቡድን ነው የባይደን የአፍሪካ ቡድን አሁን ድረስ የሚደግፈው፡፡ በእውነቱ የተባበረችው አሜሪካ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ የምትሔድበት መንገድ እጅጉን ያስተዛዝባል፡፡ ፕሮፌሰር አክሎግ የጠመዘበረውን ብር በተመለከተ በእንግሊዝኛ ካቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ እንደሚከተለው በዋቢነት ጠቅሼዋለሁ፡፡

የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ ማወቅ የሚገባው እውነት

የሚስተር ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቡድን የግል ድምዳሜ መሰረት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል፣ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይፈጸም መከላከል የህግ የበላይነት እንዲኖር፣ዴሞክራሲ እንዲያብብ በእጅጉ ይጠቅማል የሚል ግንዛቤ አላቸው፡፡  በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል የሚፌመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እነርሱ ራስ ምታት አይደለም፡፡ ስለሆነም የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች የሰብዓዊ መብት እንዲከበሩ ማገዝ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የሀገራቸው መስተዳድር የተባበረችው አሜሪካ መንግስት በእውነት በኢትዮጵያ ምድር የሰብዓዊ መብት እንዲከበር ስለማገዙ በተመለከተ እውነቱ እንዲገለጽቸው ይጠይቁ ዘንድ ሳስታውስ በታላቅ ትህትና ነው፡፡ በነገራችን ላይ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የሰው ልጆች ሁሉ መብታቸውን እንዲያውቁ  የተጻፉ ሰነዶች ናቸው፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም የሰው ልጆች የተሰጡ ተፈጥሯዊ መብቶች መሆናቸው የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡

የተባበረችው አሜሪካ የአንድ ወገን ወገንተኝነት (በተለይም አሸባሪና ወንጀለኛ ለሆነ ቡድን) የሚያስተምረን ነገር ቢኖር የአሜሪካንን የውጭ ፖሊሲ ክሽፈትን ነው፡፡ የተባበረችው አሜሪካ በኢራቅ፣በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፣ሊቢያ እና አፍጋኒስታን ወዘተ ወዘተ በተከተለው የተሳሳተ የውጭ ፖሊሲ ምክንያት ሀገራቱን ለከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ዳርጓቸዋል፡፡ አሜሪካ ከግብር ከፋይ ህዝቧ የሰበሰበችውን በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከላይ በስም ለተጠቀሱት ሀገራት ውስጥ ትደግፋቸው ለነበሩት ተፋላሚ ሀይሎችና መንግሰታት ብትረዳም ውጤቱ አላማረም፡፡መጨረሻው እልቂትና የሀገር ፍርሰትን ነበር ያስከተለው፡፡ የምእራባውያን አሻንጉሊት መንግስት (በተለይም የተባበረችው አሜሪካ) ለሚራው ህዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ማስገኘት እንዳልቻለ ከአለም የፖለቲካ ታሪክ እንማራለን፡፡ እድሜም የለውም፡፡ ለአብነት ያህል የአፍጋኒስታንን አሻንጉሊት መንግስት ለ20 አመታት የደገፈችው የተባበረችው አሜሪካ ድንገት ወታደሮቿ ሀገሪቱን ለቀው ከወጡ በኋላ የአፍጋኒስታን ማእከላዊ መንግስት እድሜው በአጭር ቀናት ውስጥ ነበር የተቀጨው፡፡ለምንድን ነው የአፍጋኒስታን መንግስት በ11 ቀናት ውስጥ በታሊባን ተዋጊዎች የተሸነፈው ? ለሊቢያ መፍረስ ዋነኛ ተጠያቂው የኦባማ አስተዳደር ነበር፡፡ አሁን ያለው የባይደን አስተዳደር ካለፈው የአሜሪካ ፕሬዜዴንቶች ስህተት ተምሮ ይሆን  በእኔ በኩል የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ እውነቱን ከተረዳ ካለፈው ስህተት የአሜሪካ የፖለቲካ ሰዎች ትምህርት እንዲወስዱ ይጠይቃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በአፍሪካ ምድር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ነጻና ገለልተኛ የምርጫ ውድድር እውን እንዲሆን፣የህግ የበላይነት እንዲከበር፣ማህበራዊና ኢኮኖሚ ፍትህ እንዲሰፍን፣የዲሞክራሲ ስርዓት ሰር እንዲሰድ፣ህይወታቸውን ቤዛ አድርገው አልፈዋል፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን መራር ትግል አድርገዋል፡፡አሜሪካ ለአፍሪካ የዲሞክራሲ ስርዓት ስር መስደድ የሚደማ ልብ ካላት ሰልፏ ከዲሞክራ ጋር እንዲሆን እንማጸናለን፡፡

የተባበረችው አሜሪካ ህዝብና የህሊና ሚዛናቸው ያልተሰበረ የአሜሪካ ኮንግሬስ አባላት የባይደን አፍሪካ ቡድን ጨቋኙን፣በሙስና ከእግር እስከ ጭንቅላቱ የተነከረውን፣ የማርክሲስት ወያኔ አሸባሪ ቡድን፣ጎሰኛውና ጸረ ዲሞክራቲክ የሆነውን የወያኔ አሸባሪ ቡድን  እየደገፉ መሆናቸውን ያውቁ ይሆን እውነቱ ግን ይሄ ነው፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ የባይደን አፍሪካ ቡድን የሚከተለውን የተሳሳተ የውጭ ፖሊሲ በተመለከተ መሞገት ያለበት ይመስለኛል፡፡ የእኔ ምክንያት ቀላል ነው፡፡ ይህ የባይደን የአፍሪካ ቡድን ፖሊሲ የተባበረችውን አሜሪካ ጸጥታ ፣እንዲሁም በኢትዮጵያ እና የአፍሪካው ቀንድ ያላትን ኢንቨስትመንት ፍላጎት ችላ ያለ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፡፡ በአፍሪካ ያላትን ተቀባይነት ይሸረሽረዋል ብዬ እሰጋለሁ፡፡ በአሜሪካን ፈሩን የለቀቀ ጣልቃ ገብነት ከወዲሁ እልባት ካልተገኘለት ሀገሬ ኢትዮጵያ የአፍጋኒስታን አይነት ክፉ እጣ እንዳይደርስባት በብርቱ እሰጋለሁ፡፡ የተባበረችው አሜሪካ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በአ ፍጋኒስታን ምድር 20 አመታት ቆይታቸው ፍትህን፣የሰብዓዊ መብት ፣የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲን ማስከበር ባለመቻላቸው የተጸጸቱ አይመስሉም፡፡ ያቺን ሀገር አፈርድሜ አስግጠው ከወጡም በኋላ መሳሳተቸውን አልተናገሩም፡፡ በእኔ የግል ምልከታ የተባበረችው አሜሪካ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በአፍጋኒስታን ምድር የፈጸሙትን ከባድ ተመሳሳይ ስህተት በኢትዮጵያ እና በቀሪው የአፍሪካ ክፍል በድጋሚ ላለመፈጸማቸው አልነገሩንም፡፡ የተባበረችው አሜሪካ አስተዳደር በተራው የአፍሪካ ዜጎች ኪሳራ የአሜሪካንን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የቆሙ ናቸው፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ብሔራዊ ጥቅሟ እስከተከበረ ድረስ አሸባሪውን የወያኔ ቡድን የመሰሉትን መርዳቷ፣መተባበሯ ሲታሰብ የአሜሪካ ዴሞክራሲን ፖሊስ ነኝ ባይነቷን ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፡፡

ለምን ይሆን የባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቡድን ለትግራይ ያልሰጠው ?

‹‹ ውጤቱ ምን ይሁን ምን የዋሽንግተን መንግስት በማህበረሰቡ ውስጥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በተመለከተ አሜሪካ አሁንም መማር እንዳለበት ያምናል፡፡›› የተባበረችው አሜሪካ በአፍጋኒስታን ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባ የወሰኑ የፖሊሲ ስትራቴጂ ነዳፊ የነበሩ ሰዎች በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ውጤት እንዳላመጣ እያወቁ ዛሬም የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊነት ላይ በየግዜው ሲያነሱ ይሰማል፡፡ ለምን ይሆን የተባበረችው አሜሪካ የፖሊሲ አውጭዎች በአንድ ነጻ ሀገር ላይ ወታደሮቻቸው በሰብዓዊ እርዳታ ስም እንዲገቡ ከወሰኑ በኋላ ውጤት እንዳላመጡ አለም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ሀገሮቻቸው ድንበር ከገቡ በኋላ መጠነ ሰፊ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና የምጣኔ ሀብት ውድቀት ውስጥ የተዘፈቁ በርካታ ሀገራትን ስም ለአብነት መጥቀስ የሚቻል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የሚደረገውን(የሶስትዮሽ ጦርነት) ጦርነት በተመለከተ የተባበረችው አሜሪካን አቋም በተመለከተ እስቲ ሁላችሁም በጽሞና እና በሰከነ መንፈስ በየአካባቢችሁ ተወያዩበት፡፡

በእኔ በኩል ደግና ሩህሩህ ለሆነው የአሜሪካ ህዝብ የማቀርበው ትሁት ጥያቄ አለኝ፡፡ የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ ዳግም የአሜሪካ አስተዳደር በአንድ ነጻ ሀገር ላይ ወታደራዊ ጣልቃ እንዲገባ ይፈቅዳልን?

ይህ በተባበረችው አሜሪካ መሪነት በምእራባውያን ዴሞክራሲ ግፊት እውን እንዲሆን የሚፈለገው ‹‹በሰብዓዊነት ስም››  በተለይም በኢትዮጵያ ወይም ኤርትራ ወይም ሶማሊያ ወይም በየትኛውም የአለማችን ክፍል ውስጥ ወታደራዊ ጣልቃገብነት ገቢራዊ ማድረግ የተባበረችው አሜሪካ መንፈስ ነውን ?

በሶስት ማእዘን ለተነሳው ጠብ መንስኤ ምንድን ነው ?………….ለምንድን ነው የባይደን አስተዳደደር የአፍሪካ ቡድን እውነታውን የሚሸፍነው ?

የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ የሚከተሉትን እውነታዎች ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ሳስታውስ በአክብሮት ይሆናል

  1. የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ መሪዎቹን በነጻነት የመረጠ ህዝብ ነው፡፡(የሚፈልገውን ፕሬዜዴንት በራሱ፣በህዝቡ ፍላጎት፣ማንም ሳያስገድደው የመረጠ ህዝብ ነው፡፡) ስለሆነም የትግራይ አሸባሪ ቡድን ከትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ውጭ በሆኑ የሰሜን እዝ አባላት በነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ የፈጸመውን የጦር ወንጀለኝነት በተመለከተ፣ስለዘረፈው የጦር መሳሪያ፣ኋላም በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል (በተለይም በአማራ እና አፋር ክልሎች) ያደረገውን ወረራ እና የፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ መረጃ ማግኘት አለበት፡፡ኋላም የአሜሪካ መንግስት ይህን አሸባሪ ቡድን ለምን ይደግፋል በማለት ለመጠየቅ ያስችለዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
  2. የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ የአሜሪካ መንግስት የኤርትራ ዋና ከተማ አስመራን ለሶስት ግዜያት ያህል፣የባህርዳር እና ጎንደር ከተሞችን ለተደጋጋሚ ግዜያት ያህል በሮኬት ተኩሶ ስለመደብደቡ በቂ መረጃ አግኝቶ ይሆን አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም በቂ መረጃ ከራሳቸው መንግስት ሊነገረው ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡
  3. የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ ስለጦርነቱ፣በጦርነት ዞን ውስጥ ስለተፈጸመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ውድቀት፣በተራው ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ ስለተፈጸመው እና ስላልተነገረው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት( በተለይም በትግራይ፣በሰሜን ኢትዮጵያ በወያኔ አሸባሪ ወራሪ ቡድን በተወረሩት ሰሜን እና ደቡብ ወሎ፣ሰሜን ጎንደርና ደቡብ ጎንደር፣እንዲሁም በሰሜን ሸዋ አንዳንድ ገጠሮችና ትናንሽ ከተሞች ውስጥ ) ማወቅ፣መጠየቅ አለበት
  4. የተባበረችው የአሜሪካ ህዝብ የሚከተሉትን እውነታዎች ማወቅ መገንዘብ አለበት፡፡ ለአብነት ያህል ከሚታመኑ (by credible), ገለልተኛ፣(independent,)  እና ምክንያታዊ ምንጮች ለማወቅ እንደተቻለው objective sources በኢትዮጵያ ምድር የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችንwar crimes,፣የዘር ማጥፋት ወንጀል genocide ፣ የጎሳ ማጽዳት ወንጀል ethnic cleansing ፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል, rapes ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡

ከዚህ ሞራልን ከሚነካ አደገኛ ሁኔታ መውጫው ምን ይሆን ?

በነገራችን ላይ አይበለውና የተባበረችው አሜሪካ የባይደን ቡድን የሚደገፈው የጦር ወንጀለኛውና አሸባሪው በመረጠው የጦር ሜዳ ላይ የሽንፈትን ጽዋ ላይጎነጭ የሚችልበት እድል ቢፈጠር( በጦር ሜዳ(battle) መሸናነፍ ሊኖር ቢችልም፣ የጦርነት(war) ግን አሸናፊና ተሸናፊ የለውም፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ለባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቡድን በምንም አይነት የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ ምርጫው የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ ቢሆንም፣ ይህ የጦር ወንጀል የፈጸመ ቡድን ነው፡፡ከትግራይ ክልል ውጭ ወረራ በፈጸመባቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል በሲቪል ዜጎች ላይ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸመ አረመኔ ቡድን ነው፡፡ በቢሊዮን የሚቆጠር የሀገር ሀብት የዘረፈም ቡድን ነው፡፡ እርግጥ ነው ምእራባውያን በተለይም የተባበረችው አሜሪካ ኢትዮጵያን የሚጠሉበት ዋና ምክንያት በአድዋ ጦርነት የነጭ ትምክሕተኞችን አሸንፋ፣አሳፍራ የመለሰች ታሪካዊት ሀገር በመሆኗ ቂም ተቋጥሮባታል፡፡የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት ቆርጣ በመነሳቷ አንገቷን ቀና እንዳታደርግ ስለሚፈልጉ ሀገሪቱን ማስጨነቅና ለጠላቶቿ መርዳትና ማገዝ ስራዬ ብለው ተያይዘውታል፡፡

  1. የተባበረችው አሜሪካን ህዝብ ኢትዮጵያ በምትገኝበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሀገራቸው ኢትዮጵያን እንዴት ከገባችበት ማጥ የምትወጣበትን መንገድ የመረጡት የባይደን አስተዳደር ላይ ጫና መፍጠር እንዲችል ማስገደድ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የባይደን አስተዳደደር በፍትህ መሰረት ላይ እንዲቆም የመረጣቸው ህዝብ መጠየቅም አለበት፡፡
  2. በመጨረሻም የተባበረችው አሜሪካ ህዝብ የባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቡድን ገለልተኛ የአጣሪ ኮሚሽን እንዲመሰርት መጠየቁ ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ገለልተኛ ኮሚሽን በኢትዮጵያ እውነተኛ ብሔራዊ እርቅ እና መግባባት እንዲደረግ፣ሰላም እንዲሰፍን በእጅጉ ይረዳል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ይህ ኮሚሽን አሁን እየተካሄደ የሚገኘውን አስከፊ ጦርነት መሰረታዊ ምክንያትና ጦርነቱን ለማቆም የመፍትሔ ሃሳብም ሊያቀርብ ይቻለዋል፡፡ የተባበረችው አሜሪካ የአንድ ወገንተኝነቷን አሽቀንጥራ በመጣል፣ለዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች መከበር ስትል ኢትዮጵያን ከልብ ለመደገፍ ከቆመች በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ይኖራታል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አሁን በጀመረችው መንገድ የወያኔን አሸባሪ ቡድን መደገፏን ከቀጠለች ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት የአንድ ክፍለ ዘመን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት የሚበላሽ ይመስለኛል፡፡ ለማናቸውም ቸር ወሬ ያሰማን፡፡

የጽሁፍ ምንጭ፡-ከላይ የሰፈረውን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ፕሮፌሰር አክሎግ ቢራራ ያቀረቡትን የጥናት ወረቀት ተጠቅሜአለሁ፡፡

 

Filed in: Amharic