አጎዋ – የሰው ወርቅ አያደምቅ !!!
አይዞሽ ሀገሬ ፤
መስፍን ማሞ ተሰማ
እነሆ ጃንዋሪ 2022 ባተ። በዴሞክራሲ፣ በሰው ልጆች ሠብዐዊ መብትና በህዝብ መሠረታዊ የህልውና ግብዐቶች (ምግብ፣ መጠለያ፣ ሥራ ወዘተርፈ) ካባ አኮኖሚያቸው ባልጠና ነፃ ሀገራት ውስጥ በድሀነት ላይ ድህነትን የምታስቀፈቅፈው፣ በሉዓላዊ መንግሥት ምትክ አሻንጉሊት፣ ሙሰኛ፣ ታዛዥ አፋሽ አጎንባሽ መንግሥት የምትቀፈቅፈው፣ ሀገራትን በመፈንቅለ መንግሥት የምታምሰው፣ ታሪክ ጠገብ ጥንታዊ ሀገረ መንግሥታትን በሀሰት ውንጀላ በጦር የምታፈርሰው፣ የግፈኞች መከታ፣ የአምባገነኖች ካባ፣ በዕምብርቷ ዘረኝነት የሚራባባት፣ ወንጀል ሥራ የሆነባት፣ ሚሊዮናት ዜጎቿ በወህኒ የሚማቅቁባት፣ ነፃነት እኩልነትና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን የሚጠይቁ ዜጎቿን በጥይት ግንባራቸውን የሚትነድለው … ትምክህተኛዋ፣ ተመፃዳቂዋ፣ ጀብደኛዋ አሜሪካ እነሆ ከጃንዋሪ 1/2022 ጀምሮ ያገጠጠ ጥርስዋን የተሳለ ጥፍርዋን በቅድስቲቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ በይፋ አሳርፋለች። ኢትዮጵያን ከአጎዋ አስወጥታለች። ከንቱ የከንቱ ከንቱ እኩያን ሴራና ሥራ !!!
አሜሪካ ከተደጋጋሚ ውድቀቷም ሆነ ከዘመናት እኩይ ምግባሯና ኪሳራዋ ከቶም የማትማር በትዕቢት የተደፈነች፣ ትዕቢተኛ መሪዎች የሚፈራረቁባት ሀገር ናት። አሜሪካ የጀመረችውን የትኛውንም ጦርነት አሸንፋ አታውቅም። አሸነፍኩ ካለችም በደቦ ጋሻ ጃግሬ ሀገሮችን አስተባብራ ኩሩና ሉዓላዊ ሀገረ መንግሥታትን በማፍረስ ህዝብን ለረሀብ፣ ለስደትና ለመከራ በመዳረግ ነው። ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሶሪያ አፍጋኒስታን፣ ሶማሊያ ወዘተ ህያው ምሥክሮች ናቸው።
የቪየትናም ገበሬዎች የአሜሪካንን እብሪተኛ ወራሪ ጦር ለአያሌ ዓመታት የቁም ስቅሉን አሳይተው ‘አርባ ገርፈው’ ድል አድርገውታል!!! ትምክህተኛዋ አሜሪካ የጦር ሜዳ ውርደቷን ለመበቀል በቪየትናም ላይ ከሀያ ዓመታት የዘለቀ የኢኮኖሚ ማዕቀብ አድርጋ በወታደራዊ አውድማ ያጣችውን ድል በኢኮኖሚ እቀባ ልታንበረክካት በብዙ ደክማለች፣ አሳድማለችም!!! ግን አልተሳካላትም! የምዕራብ አውሮፓ አጨብጫቢዎቿም አልተሳካላቸውም!!! ቪየትናማውያን ወገባቸውን ጠበቅ ሀሞታቸውን ከተት አድርገው የጦር ሜዳውን ድላቸውን በኢኮኖሚያቸውም ዕድገት ደግመውት እነሆ ሀፍረተ ቢሷና ተመፃዳቂዋ አሜሪካ ከቪየትናም ጋር ሠላምና ወዳጅነት ለመፍጠር ተገዳለች።
‘የዓለም ፖሊስ’ ነኝ ባይዋ አሜሪካ ኩባን ከሀምሳ ዓመት በላይ ሁለገብ የኢኮኖሚ ማዕቀብና ከበባ አድርጋ ከምደረ ገፅ ልታጠፋት እጅግ ብትደክምም ኩባ ግን ከነጥንካሬዋና በራስ የመተማመን ልዕልናዋ ዛሬም አለች !!
አሜሪካ በቻይና ላይ የጣለችው የኢኮኖሚ ማዕቀብ አነሆ ዛሬ ዘመን መልሶ የራሷን የአሜሪካን አናቷን ሀያሉ የቻይና ኢኮኖሚ እየፈለጣት ይገኛል።
የጥንቷ የኦቶማን አምፓየር ባለቤት የዛሬዋ ቱርክ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ከቶስ ምን አደረሰባት? የትስ አደረሳት ?! ዛሬ ቱርክ አሜሪካንን በኢኮኖሚም ሆነ በዲፕሎማሲም አስፈላጊ ከሆነም በጉልበት መገዳደር የጀመረች ሀገር ሆናለች። በቅርቡ አሜሪካንን ጨምሮ የምዕራብ አውሮፓ ጋሻ ጃግሬ ደጋፊዎቿን ሀገራት አምባሳደሮች “ሀገሬን ለቃችሁ ውጡ” ብትላቸው … ከወገባቸወሰ ጎንበስ ብለው ይቅርታ ጠይቀዋታል!!
ከኒህ ሁሉ ክስረቷና ውርደተ ከቶም ያልተማረችው ተመፃዳቂዋ አሜሪካ በሩሲያ ላይም የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለመጣል እየዛተች ቢሆንም ፑቲን አፀፋውን እንደሚያስታጥቃት ደግሞ በአደባባይ ነግሯታል። በኢራን፣ በሰሜን ኮሪያ፣ በሲሪያ፣ በቬኒዙዌላ፣ በቤሌሩስ፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በሊባኖስ፣ በኒካራጉዋ፣ በሜንማር፣ በየመን፣ በዚምባቡዌ ወዘተርፈ ሀገራት ላይ በአጉራ ዘለሏ አሜሪካ የተጣለው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ሀገራቱን አትንኖ አላጠፋቸውም። ማዕቀቡ የየሀገራቱን ጥሮ ግሮ አዳሪ ንፁህ ህዝብ ከማንገላታትና ከማሰቃየት፣ ድህነትንና ሥራ አጥነትን ከማስፋት ውጪ በቋሚነት በዲሞክራሲም ሆነ በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ለየሀገራቱ የፈየደው አንዳች ቁብ የለም።
አሜሪካ በየደረሰችባቸውና ጣልቃ በገባችባቸው ሀገራት ሁሉ ቤተክርስቲያን ወይም መስጂድ እንደገባ ውሻ ከመጠላትና ከመባረር ውጪ ያተረፈችው አንዳች ፋይዳ የለም። ይህም ሁሉ ሆኖ እንኳን ልበ ድፍን የአሜሪካ ህግ አውጪዎችና መሪዎች ከውርደታቸው መማር አልተቻላቸወም።
ታሊባንን ለማጥፋት ለሀያ ዓመታት በአፍጋኒስታን እጅግ በረቀቁ የጦር መሳሪያዎች ስትዋጋ ኖራ በመጨረሻም በአሳፋሪ የሽንፈት ትዕይንት ካቡልን ለቃለች!!! የቪየትናሙን ውርደት ፎቶ ኮፒ በአፍጋኒስታን ደግማለች … ግን አሜሪካ አታፍርም፣ አትማርም !!!
እነሆ ደግሞ እናት ሀገራችንን ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ጠላት ናዚስት ህወሃትና ከሲዖል ሠራዊቱ ጎን ወግና የውክልና ጦርነት ካስመዘዘችብንና በተባባሪነት ከዘመተችብን ከርማለች። በ2022 አዲስ ዓመት በወርሀ ጃንዋሪ መባቻ የመጀመሪያው ቀን ግብዟ አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ በማስወጣት ኢኮኖማያዊ ማዕቀቧን ጀምራለች። እርግጥ ነው ማዕቀቡ በለፍቶ አደሩ ህዝባችን ላይ የተቃጣ ነውና ይጎዳናል። ጊዜያዊ ጉዳት እንጂ ዘላቂ ስብራት አይደርስብንም። የተያያዝነው ሀገር አቀፍ ዘመቻ – ህዳሴ ግድባችንን ጨምሮ – ከኖርንበት ድህነት ለመመንጠቅ ነውና የአሜሪካን ማዕቀብ ከምናውቀውና እየታገልነው ካለነው የድህነት ችግር የሚጨምርብን ምንም የለም፣ በእልህና በቁጭት እንደ ቪየትናምና እንደ ቻይና ህዝባችንን ለዕድገት እንደ ማዕበል ያነሳሳዋል እንጂ!!!
አሜሪካ ሆይ! በናዚስት ህወሃትና የሲዖል ሠራዊቱ በኩል የከፈትሽብንን የውክልና ጦርነት እየመከትነውና ዓላማና ግቡንም እያመከነው እንደሆነ ሁሉ የአንቺንና የጋሻ ጃግሬዎችሽን አውሮፓውያንንም የኢኮኖሚ ማዕቀብ መክተን በራሳችን የዐሸድገትና የከፍታ ዛቢያ የምንቆም የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን በውድ ሳይሆን በግድ የምትቀበይበት ጊዜው እሩቅ አይሆንም!! ለቅኝ ገዢ ወራሪዎች (Colonialists) ያልተንበረከከችው የአባቶቻችን ኢትዮጵያ በእኛ በልጆቻቸው ዘመን ለእጅ አዙሪ የኢኮኖሚ ቅኝ ገዢዎች (Neo colonialists) አትንበረከክም !! ይህ ትወልድ የኢትዮጵያን ጠላቶች ሴራና ርኩስ ዘመቻ አምክኖ የበለፀገች የታፈረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ያቆማል!!!