>

ኳሷን መቆጣጠር ወይስ ማቀበል ....??? (አባይነህ ካሴ)

ኳሷን መቆጣጠር ወይስ ማቀበል ….???

አባይነህ ካሴ

“መንግሥት ወደ ትግራይ አልገባም ብሎ ያሳለፈው ውሣኔ ችግሩን ከጦርነት ውጭ ለመፍታት ኳሱ ሙሉ በሙሉ በአሸባሪው ሕወሓት ሜዳ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ የሚወሰደው ወታደራዊ ርምጃ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይዘልቅ ወሥኗል።”
እንዲህ ኮተት እያላችሁ እንደምታመጡት ይታወቃል። የምትሉትን ሁሉ የሚጋቱ እንዳሉ ሁሉ ከግብራችሁ ተነሥተው አቅጣጫችሁን የሚረዱም አሉ ብላችሁ እንኳ ማፈር አልፈጠረባችሁም። ከሕወሐት ጋር ለመደራደር ሰነድ ቀርጻችሁ ሲነቃባችሁ እስከ ትናንትናዋ ዕለት ከአሸባሪ ጋር አንደራደርም እያላችሁ ስትንፈራፈሩ ነበር።
ሬድዋን ሁሴን ትናንት ያሉትን እጠቅሳለሁ። “ሀገር አቀፍ ምክክሩ በሕዝቦች መካከል ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር እንጂ ከአሸባሪዎች ጋር መደራደርን ታሳቢ ያደረገ አይደለም” ብለውን ነበር። ትናንት ይህን ያለን አፍ ዛሬ ከጦርነት ውጭ መፍትሔ እያለ መጣ። ከጠሚ ጀምሮ ከአሸባሪ ጋር አንደራደርም ፉከራ ገደል ገባ።
ኹለተኛው ደግሞ ወደ ትግራይ ክልል ላለመግባት የወሠነው መንግሥት ቀብድ አስይዞ መኾኑ ነው። ከሰሜን ወሎ ራያ ባላ፣ ራያ አላማጣ፣ ራያ ኦፍላ እስከ ኮረም፤ ከሰሜን ጎንደር እነ ማየ ፀምር እና ጠለምት ዛሬም በሕወሐት ሥር ኾነው ሳለ   ሠራዊቱ የትግራይ ወሠን ጫፍ እንደደረሰ አድርጎ መነገሩ ሌላው ክሕደት ነው። በገደምዳሜው እነዚህ መሬቶች የትግራይ ክልል ናቸው እያሉ ሊያለማምዱን መኾኑ ነው?
ጥቂት ጥቂት ለመመጽወት የታሰበ ይመስላል። ዛሬም ድረስ ሕዝቡ ይጠይቃል። መንግሥት ግን አይሰማም። መጥኔ ለወገኔ። እየተከዳዳን እስከመቼ?
የኳስ ቅብብሎሽ አይደለም ነገሩ። ኳሷ እገሌ ጋ ናት የሚባለው ልምምድ ቦታ ላይ ነው። ጨዋታ ውስጥ ከኾነ ግን ኳስን በቁጥጥር ሥር ማድረግ ግዴታ አሸናፊ ያደርጋል። ከተቃራኒ እግር ስትገባም ተረባርቦ ማስጣል ነው የጨዋታው ሕግ። በጨዋታ ጊዜ ኳስ ለጠላት የሚያስረክብ እርሱ ስሙ ሌላ ነው።
Filed in: Amharic