>

በኢትዮጵያ ስለተከሰተው ጦርነት አለም ማወቅ ያለበት እውነት! (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

በኢትዮጵያ ስለተከሰተው ጦርነት አለም ማወቅ ያለበት እውነት!

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

<<ምክንያቱን ካላወቅን እውነቱን ለማወቅ አይቻለንም >> – አሪስቶትል

“We do not know a truth without knowing its cause” –Aristotle 



የግጭቱ ዋነኛ ምክንያት ምን ነበር ?

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ከሚገኙት ሀገራት ሁሉ ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች እና ነጻነቷን ጠብቃ የቆየች ሀገር ኢትዮጵያ ስለመሆኗ ምንም የሚያከራክር አይደለም፡፡ ከዚህ ባሻግር ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት እውን መሆን ተምሳሌታዊት ሀገር ናት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በርካታ ባህላዊ እሴት ያላት ሀገር ብትሆንም፣የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ነገዶች የሚገኙባት ሀገር መሆኗ የታወቀ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ለብዙ ክፍለ ዘመናት በሰላምና በፍቅር እንዲሁም በአንድነት ኖረዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ1991 ጀምሮ ማለትም የወያኔ ኢህአዲግ የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን ከተቆጣጠረ ወዲህ ባሰፈነው(በተከተለው) የታመመ የፖለቲካ ስርአት ምክንያት(መሰረቱን ጎሳ ላይ ያደረገው የፌዴራል ስርዓት ማለቴ ነው፡፡) የኢትዮጵያን አንድነት አላልቷል፡፡ በህዝቡ የዘመናት የፍቅርና መቻቻል እሴት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ቸልሶበታል፡፡ ጎበዝ አንድ ልብ ልንል የሚገባን ቁም ነገር ያለ ይመስለኛል፡፡ ይሄውም በኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያ በውጭ ወራሪ ሃይላት ለጥቃት በተዳረገችበት ዘመን የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ ውሰጥ ገብቶ አያውቅም፡፡ በሌላ አነጋገር በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ከወያኔ አገዛዝ በቀር የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ ከቶ የሚያውቅ የኢትዮጵያ አገዛዝ አልነበረም፡፡ አሁን ባለንበት ግዜ ግን ( ከ2010 ወዲህ ) የኢትዮጵያን አንድነት በተመለከተ የቀድሞውን እውነት እየደገመ ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የውጭ ሀይሎች በሀገሩ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት በመሞከራቸው የቀድሞውን የአንድነት መንፈስ እንዲያድስ አድርገውታል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የውጭ ወራሪዎች ሉአላዊነቱን ለመድፈር ሲሞክሩ አንድነቱን ማደሱ እሙን ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የአፍሪካውያን ችግር የሚፈታው በአፍሪካውያን ብቻ ነው በሚል መፈክር ተነስተው የሀገራቸውን ሉአላዊነት ለማስከበር ቆርጠው የተነሱ ይመስላሉ፡፡ African solutions to  African problems.”  

የቀድሞው የተባበረችው አሜሪካ ዋና ጸሃፊ ማይክ ፖምፒዮ  እንደመሰከሩት እና ከሌሎች የዜና ምንጮች እንደተሰማው ከሆነ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት መሪዎች እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ህዳር 3 2020 ሚሊሻዎቻቸው የሀገር ዳር ደንበር ሲጠብቅ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ጭካኔና ፍርሃት በተሞላበት ሁኔታ ጥቃት በማድረሳቸው ነበር፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ሁነኛ ክፍል ማለትም በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት የከፈቱበት ምክንያት የኢትዮጵያን የመከላከያ ሰራዊት ለማዳከምና ኋላም የኢትዮጵያን ማእከላዊ መንግስት ከስልጣን ለማውረድ እንደሆነ ብዙዎች የፖለቲካ ጸሃፊዎች በጽሁፎቻቸው ያመላከቱት እሙን ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ከፍተኛውን የሀገር ክህደት ፈጽሟል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አንድ ሰው በሀገሩ ላይ የሚፈጽመው ከባዱና ትልቁ ወንጀል ነው፡፡ በምላሹ የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው እርምጃ ወንጀለኞችን በፍትህ አደባባይ ለማቅረብ እንደሆነ በርካታ ግለሰቦች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡ ግን በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ውስጥ እንዲህ አይነት ክህደትና የጦር ወንጀል ተፈጽሞበት ምላሽ የማይሰጥ ሀገር ይኖር ይሆን ?

የግጭቱ የኋላ ታሪክ

የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ኢትዮጵያን ለሃያ ሰባት አመታት ተቆጣጥሮ ነበር፡፡( እ.ኤ.አ.1991-2018) በወያኔ ኢህአዲግ የአገዛዝ ዘመን የተመዘገበ እድገት ሰለመኖሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በሀገሪቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በስፋት ታይተዋል፡፡ ይህ የሚካድ አይመስለኝም፡፡ በውጭ እርዳታ ላይ የተንጠለጠለ ትልቅ የኢኮኖሚ እድገት ተመዝግቧል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያ ህዝብ ተሰቃይቷል፡፡ ምክንያቱም ወያኔ ኢትዮጵያን በጎሳ መስመር ስለከፋፈላት ነው፡፡ ምንም እንኳን በመጀመሪያዎቹ የወያኔ ኢህአዲግ የስልጣን አመታት በተለይም አንዳንድ የውጭ ሀገራት ምእራባውያን ፖለቲከኞች የጎሳ ስርዓት ተራማጅ እና ፍትሃዊ ነበር በማለት ቢደግፉም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቸኛዋ የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርዓት ተከታይ የሆነች ሀገር አድርጓታል፡፡ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ወደ ታሪክ ቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ የወረወሩትን የጎሳ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ገቢራዊ መደረጉ ውድቀትን እንጂ እድገትን እንዳላመጣ አሁኑ ትውልድ ቋሚ ምስክር ነው፡፡

በነገራችን ላይ የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ ይከተለው የነበረው የጎሳ ፌዴራሊዝም የአፓርታይድ ተምሳሌት ከመሆኑ ባሻግር ያረጀውን ያፈጀውን ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ይከተሉት የነበረውን ከፋፍለህ ግዛ ስርዓት የሚያስታውስ ነበር፡፡ የወያኔ ኢህአዲግ የተበላሻ ፖሊሲ የጎሳ ግጭቶች እንዲስፋፉ፣ ጎሳን መሰረት ያደረጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዲጨምሩ፣በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ የነገዶች ግድያ እንዲፈጸም ዋነኛ ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ እውነት ነው፡፡ እውነት ነው የኢኮኖሚ እድገት ነበር፡፡ ሆነም ግን ይሁንና ኤድዋርድ አቢዬ የተባለ አዋቂ እንዳለው ‹‹ አድገት ለእድገት ብቻ ከሆነ የርእዮት አለም ሴል ካንሰር  ነው፡፡ ››

Edward Abbey rightly put it “Growth for the sake of growth is the ideology of the cancer cell”. 

በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ አብዛኛዎቹ ግጭቶች ነዳጅ የሚርከፈከፍባቸውና ስፖንሰርድ የሚደረጉት በወያኔ አሸባሪ ቡድን እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ቡድኑ እንዲህ አይነት መሰሪ ሴራዎችን በመጎንጎን እድሜውን አራዝሟል፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ ህዝብ አጠቃላይ ቁጥር 5 ፐርሰንቱን የትግራይ ህዝብ እወክላለሁ የሚለው አሸባሪ ቡድን የማእከላዊ መንግስቱን ለሃያሰባት አመታት ተቆጣጥሮ ኢትዮጵያን በጡንቻ ገዝቶ በነበረበት ግዜ አለም አቀፍ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል በየክልሉ እሺ ባዮችን አመራር እንዲሆኑ መሰየሙ የታወቀ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር የሀገሪቱን ወታደራዊ ሀይሉን፣ኢኮኖሚውን፣በመቆጣጠር የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ የኢትዮጵያን ሀብት እና የግንኙነት መረብ networks በብቸኝነት ለመቆጣጠር አስችሎታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የወያኔ ቡድን በስልጣን በነበረበት ግዜ ህጋዊ እውቅና እንዳለው የማፊያ-ጋንግስተር ቡድን ይንቀሳቀስ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ዛሬም የነበረው ክፉ ባህሪ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ለአብነት ያህል እድሜአቸው ለውትድርና ያልደረሱ ታዳጊ ህጻናትን በጦር ሜዳ አሰልፎ ነበር፡፡ ሽማግሌ አዛውንቶችንም በጦር ሜዳ አሰልፎ ነበር፡፡ በሰብዓዊ ጋሻነት ስምና በህዝባዊ ንቅናቄ ስም የጦር ወንጀል ፈጽሟል፡፡ ለአብነት ያህል በማይካድራ ከተማ የጎሳ ማጽዳት አስከፊ ወንጀል ስለመፈጸሙ አመንስቲ ኢንተርናሽናል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ፣የጎንደር ህክምና ሳይንስ ኮሊጅ በማስረጃ በተደገፈ ያወጡት ሪፖርት ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳላ በአፋር ጋሊ ኮማ ሴቶች እህቶቻችንን አስገድዶ ደፍሯል፡፡ የመንግስትና የግለሰቦችን ንብረትና እንሰሳትን ጭምር ዘርፏል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው መልኩ በተለይም የምእራቡ አለም የወያኔ አሸባሪ ቡድን የሚፈጽማቸውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ አይቶ እንዳላየ፣ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኗል፡፡ በነገራችን ላይ የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ የታሪክ መሰረት ስለመሆኑ ለማወቅና ለመረዳት የአሁኑ ትውልድ የታሪክ መጽሐፍትን እንዲመረምር ሳስታውስ በታላቅ አክብሮት ይሆናል፡፡ ከዚህ ባሻግር አብዛኛዎቹ የትግራይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በሰላምና በፍቅር የኖረም ነው፡፡ ከወያኔ አሸባሪ ቡድን አባላትና መሪዎቻቸው፣እንዲሁም ከደጋፊዎቻቸው ባሻግር ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የትግራይ ወንድሞቻችን በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ጥያቄ እንደሌላቸው እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያሉ ጎምቱ ምሁራን የመሰከሩት እውነት ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የሚገኘው የወያኔ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ የማያባራ እሳት ለመጫር ሲል፣የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሲል የትግራይን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ለመለየት ውስብስብ ሴራ ጎንጉኗል፡፡ ከዚህ ባሻግር የትግራይ ህዝብ ብቸኛ አዳኝ እኔ ነኝ ማለቱ በሚሊን የሚቆጠሩ አባላትን አፍርቶለታል፡፡ ይህ ግን እንደማያዋጣ ቀደም ባሉት አመታት እውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በህይወት በነበሩበት ግዜ ምክረሃሳባቸውን አቅርበው ነበር ሆኖም ግን ይሁንና ሰሚ አላስገኘላቸውም፡፡ ዛሬም ጠቃሚ ትምህርት ስለሆነ እጠቅሰዋለሁ፡፡ (ሰሚ ከተገኘ ማለቴ ነው፡፡)

የወያኔ ለትግራይ ህዝብ ጠላት የማራባት ዘመቻ !

(ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ ማርያም)

<<ወያኔ የጀመረው ለትግራይ ሕዝብ ጠላትን የማራባት ዘመቻ የትግራይን ሕዝብ ያጠፋዋል ፡ ይህንን ሳንጠራጠር ልንቀበለው ይገባናል፣ ብንደብቀው አይጠቅመንም፡፡ 

ስለዚህ የመጀመሪያው ደረጃ መፍትሔ የጠላትነት እሳት እንዳይቀጣጠልና ትግራይን እንዳይበላ መከላከል ነው፡፡

ይህንን የመጀመሪያ ደረጃ መፍትሔ ለመጀመር የትግራይ ሕዝብ ግምባር ቀዳሚ መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ የገጠመውን የተቆላለፈ ችግር የትግራይ ሕዘብ በትግሬነት እፈታዋለሁ ብሎ ከተነሳ ያባብሰዋል እንጂ በጭራሽ ሊፈታው እንደማይችል መቀበል የትግሉ መነሻ ይሆናል፡፡ 

ኢትዮጵያ ያለትግራይ ከሲታ ሆና መኖር ትችል ይሆናል ፡ ትግራይ ያለኢትዮጵያ ከሲታ ሆና መኖር ይቻላል??? 

ችግር የሚፈታው ችግሩን አውቀው ሲጋፈጡት ብቻ ነው፡፡>> 

ምንጭ: ፍትሕ መጽሔት

ውድ የትግራይ ወንድሞቻችን ዛሬም በጣም ሳይረፍድ የፕሮፌሰር መስፍንን ግዜ የማይከዳውን የአባትነት ምክር እንድትቀበሉ ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡

በእውነቱ ለመናገር በወያኔ ኢህአዲግ የአገዛዝ ዘመን ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የትግራይ ክልል ወንድሞቻችን፣አህቶቻችን ህይወታቸው የተመሰረተው በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ላይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ወደ ውጭ ሀገር ባንኮች በማሸሽ ያስቀምጡ ነበር፡፡ ይህን ከርጥባን የተገኘውን ዶላር እንደ ግል ሀብታቸው በመቁጠር ልጆቻቸውን ወደ ታወቁ እና ውድ በሆኑ የምእራባውያን ዩንቨርስቲዎችና ትምህርት ቤቶች ልጆቻቸውን በመላክ አስተምረዋል፣ የምእራቡን አለም አንዳንድ ፖለቲከኞች ምልጃ ሰጥተው የአላማቸው ምርኮኛ አድርገዋቸዋል፣እውነቱን፣ሀሰት፡፡ ሀሰቱን እውነት በማስመሰል እንዲዘግቡላቸው የምእራቡን አለም አንዳንድ  መገናኛ ብዙሃኖችንና ቡድኖችን, (lobbying groups) ለማማለል የሚችሉ ቀስቃሾችን በገንዘብ ገዝተዋል፡፡ የወያኔ ቡድን ስልጣን ጨብጦ በነበረባቸው ጥቂት አመታት ማለትም አንድ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ2000-2009 (the  Global Financial Integrity Report በመባል የታወቃል፡፡) ባወጣው አመታዊ ሪፖርት መሰረት ከኢትዮጵያ ግዛት በህገ ወጥ መንገድ የተዘረፈው የገንዘብ መጠን 11.7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይገመታል፡፡ ከዚህ ባሻግር እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2017 ፎርቤስ የተሰኘው አለም አቀፍ እውቅና ያለው መጽሔት ባወጣው ጥናት ከኢትዮጵያ የወጣው አጠቃላይ የብር መጠን 30 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይገመታል፡፡ (Forbes (2017) estimated capital flight from Ethiopia  at $30 bn and in 2017) በተጠቀሰው አመት (እ.ኤ.አ. 2017) የአውሮፓ ኮሚሽን በአውሮፓ ለሚገኙ ባንኮች ባስተላለፈው መልእክት በኢትዮጵያ ህገወጥ የገንዘብ ህትመት ሊካሄድ የሚችልበት እድል ሰፊ መሆኑን ከጠቀሰ በኋላ በወቅቱ የነበሩት ባለስልጣናት ወደ አውሮፓ ባንኮች የሚልኩትን ገንዘብ በተመለከተ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቦ ነበር፡፡

ይህ በአንዲህ እንዳለ ስልጣንና ሀብት በጥቂቶች አጅ ስር በመወደቁ፣እኩይ የሆነ አምባገነናዊ ስርዓት ስር በመስደዱ ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን በአደባባይ ያሰሙ ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የቄሮ ወጣቶች፣የፋኖ ወጣቶች፣ እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ ወጣቶች ያደረጉት ሰላማዊ ትግል የወያኔ ጨካኝ አገዛዝ እድሜ እንዳይኖረው አድርጎታል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ወያኔ የስልጣን እድሜው ከማጠሩ በፊት በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በእስር ቤት አሰቃይቷል፣ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉትን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ አስገድሏል፡፡( እንዲገደሉ ፈቅዷል፡፡) ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች ደብዛቸው እንዲጠፋ አስደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸመው ወያኔ ግን በምእራባውያን ምንም አይነት ውግዘት ሲደርስበት አልታየም፡፡ ምእራባውንያን የወያኔን ክፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪኮርድ በተመለከተ ዝምታን መርጠዋል፡፡ ታሪክ አይሸፈጥም፡፡ በነገራችን ላይ የወያኔ ጭካኔ የህዝቡን አመጽ አቀጣጠለው እንጂ ሊያዳፍነው አላስቻለውም፡፡ ኋላም የወያኔ አገዛዝ ስልጣኑን እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ የወያኔ ከስልጣኑ መገርሰሱ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሌላ መልካም እድልን ከማስገኘቱ ባሻግር ለኢትዮጵያ ህዝብ እና በውጭ ሀገር ለሚኖረው ኢትዮጵያዊ  እፎይታን ያስገኘ ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ የግዜው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን ከለቀቁ በኋላ የቀድሞው ኢህአዲግ ዛሬ ‹‹የብልጽግና›› ዶክተር አብይ መሀመድ ሀገሪቱን እንዲመሩ መምረጡ ይታወሳል፡፡ ( ምርጫው እስኪጀምር እ.ኤ.አ. 2020 ድረስ ነበር ዶክተር አቢይ ሀገሪቱን እንዲመሩ የተመረጡት፡፡ ሆኖም በኮቪዲ በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ አመት ተራዝሞ ነበር፡፡) ሆኖም ግን ይሁንና የወያኔ ቡድን የሀገሪቱን ህግ በመጣስና ያለ  ኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ እውቅና ክልላዊ የምርጫ ወድድር ? በማካሄድ ፓርቲው አሸናፊ መሆኑን ከማወጁ ባሻግር ከመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችና በተለያዩ የእድሜ ደረጃዎች የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችን በመመልመል ወታደረዊ ስልጠና መስጠቱ ለጦርነት ዝግጁ መሆናቸውን በግዜው የአደባባይ ሚስጥር ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት ሰዎች የሰሜኑ ግጭት ከመከሰቱ በፊት የአስታራቂነት ሚና ለመጫወት ጥረት ማድረጋቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የወያኔ ቡድን የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች የሰላም ጥረቱን አልተቀበሉትም የሚል ዜና ነበር ከመገናኛ ብዙሃን የተሰማው፡፡ ይህን ተከትሎ በትግራይ ምድር ለ20 አመታት የሀገር ዳርድንበር ሲጠብቅ በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍተው የጦር ወንጀል ፈጽመዋል፡፡ የአለምን ህዝብ ጆሮ ለማግኘት በሚፈልግ መልኩ ወደ ኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ላይ አንዲሁም የባህርዳር ከተማ ሮኬት ተኩሰዋል፡፡

በወያኔ የጭካኔ እርምጃ የተበሳጩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ( በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍልና ደረጃ የሚገኙ) ከፌዴራል መንግስቱ እና ከፌዴራል ጦር ጎን ቆመዋል፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው የኢትዮጵያ የፌዴራል ወታደሮችና የክልል ልዩ ሀይሎች ( በተለይም የአማራ ክልል ልዩ ሀይል) በአደረጉት ተጋድሎ የትግራይ ክልል ዋና ከተማን መቀሌ ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ በጦርነት ሂደት መፈናቀል እውነት ስለሆነ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ ወንድሞቻችን ከመኖሪያ ተፈናቅለዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያውያን ለትግራይ ተወላጅ ወንድሞቻቸው ሰብዓዊ እርዳታ አቅርበዋል፡፡ ከእነኚህ ውስጥ ለኢትዮጵያ ታማኝ የሆነው ታማኝ በየነ ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮ ወደ ትግራይ የላከው ሰብዓዊ እርዳታ የማይዘነጋ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ መሰረት  በትግራይ በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ አድርጓል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ የሚሸፈጥ አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ከ70 ፐርሰንት በላይ የትግራይ ተረጂ ወገኖቻችንን የረዳ ነው፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2021 በሀምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የአንድ ወገን ተኩስ ማቆም ውሳኔ በማድረግ የትግራይን ክልል ለቆ በመውጣቱ ምክንያት የተነሳ ይሁንታና ብርቱ ነቀፌታ ደርሶበት ነበር፡፡ የመንግስትን የአንድ ወገን የተኩስ ውሳኔ የደገፉት አካላት የሚሰጡት ምክንያት ጦርነቱ በርካታ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፣ዜጎችን አፈናቅሏል፣ ነብረቶችና መሰረታዊ የልማት አውታሮችን አውድሟል፣ ስለሆነም የመንግስት የአንድ ወገን ተኩስ አቁም ውሳኔ ምክንያታዊ ነበር ባይ ናቸው፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን የመንግስት የአንድ ወገን ተኩስ አቁም ውሳኔ ስህተት ነበር ይላሉ ፡፡ ለዚህ የሰላ ትችታቸው የሚያቀርቡት ምክንያት ደግሞ የትግራይ አሸባሪ ቡድን ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ( ማለትም በአማራ ክልል በሚገኙት ሰሜን ወሎና ሰሜን ጎንደር፣ደቡብ ወሎና፣ደቡብ ጎንደር፣ሰሜን ሸዋ፣ እንዲሁም በአፋር ክልል፣ ወረራ ላይፈጽም ይችላል ባይ ናቸው፡፡) ሆኖም ግን ይሁንና የምእራቡ አለም መንግስታት የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደውን የአንድ ወገን የተኩስ ማቆም ውሳኔ በተመለከተ እውቅና መስጠት አልፈለጉም ነበር፡፡ አንዳንድ ሀገራት ደግሞ እንደ ወታደራዊ ሽንፈት የቆጠሩ ከመሆናቸው ባሻግር አዲስ አበባ ነገ ተነገወዲያ በአሸባሪው ቡድን ልትወድቅ ትችላላች በማለት በታወቁ የመገናኛ ብዙሃኖቻቸው ወሬውን ሲያስተጋቡ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የወያኔ አሸባሪ ወራሪ ሀይል ከአመታት በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የፈጸመው መራር ግፍ አልበቃህ ብሎት ዛሬም አሰቃቂ ወንጀል መፈጸሙ ሲስተዋል የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ አሸባሪውና ወራሪው የህውሃት ሀይል ከ2ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን አፈናቅሏል፡፡ ዛሬ ግን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት አስከባሪው የሰብዓዊ መብት ተመልካች ድርጅት አሸባሪውና ወራሪው ህውሃት በአማራና አፋር ክልል በያዛቸው መሬቶች ሲቪል ዜጎችን በጅምላ ጨፍጭፎ እንደነበር፣የመንግስትና ግለሰቦችን ንብረት እንደዘረፈ፣ ሴቶች እህቶቻችንን አስገድዶ እንደደፈረ፣ ባወጣው መግለጫ ለአለም ህዝብ አሳውቋል፡፡ ይህ ቡድን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ለተረጂዎች እንዳይደርስ የሚያደርገው ሴራም ቢሆን ቀላል አይደለም፡፡ ሌላው አሳዛኝ ሁነት ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ እህል የጫኑ ተሸርካሪዎችን የዘረፈውን ወራሪው ሃይል የትኛውም አለም አቀፍ ድርጅት ከባድ ጫና ሊያሳድሩበት አልፈለጉም፡፡ በሌላ አነጋገር  አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የተባበሩት መንግስታት ጭምር ሳይቀር ዝምታን መርጠዋል፡፡

የዚህ ጦርነት ባለድርሻ አካላቶች እነማን ናቸው ?

አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን፣ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው አፍሪካውያን እንደሚያምኑት ከሆነ ይህ ጦርነት የሚካሄደው አሸባሪው የወያኔ ቡድን ዳግም የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን ለመቆጣጠር አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይህ ጦርነት ገጸ ብዙ ይመስላል፡፡ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች በጥናት እንደደረሱበት ከሆነ ይህ ጦርነት ክፍለ አህጉራዊና አለም አቀፍ ተጫዋቾች እጃቸውን የዶሉበት ነው፡፡ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን በደረሱበት ድምዳሜ ከሀገር ውስጥ የወያኔ አሸባሪ ቡድን የትሮይ ፈረስ ሚናን በመጫወት የኢትዮጵያን አንድነት ለማላላት፣ከተሳካለት ደግሞ ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል፡፡ .  Amajority  of Ethiopians consider the TPLF as a Trojan-horse strategy to destroy Ethiopia from within

የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ( በተለይም ግብጽና ወዳጆቿ የምእራቡ አለም) በቅኝ አገዛዝ ዘመን የተፈረመውን የቅኝ ገዢዎች ውርዴ ወይም ቅሪት ስምምነት በተጻረረ መልኩ እየተገነባ ያለውን የታላቁ የአባይ ግድብን የግንባታ ሂደት ማዳናቀፍ፣ከዚህም እልፍ በማለት የቀይ ባህርን ኮሪዶር መቆጣጠር ነው፡፡ በነገራችን ላይ ግብጽ እና ስትራቴጂክ ወዳጆቿ ምእራባውያን በተለይም የተባበረችው አሜሪካ እና ታላቋ ብሪታንያ የታላቁን የአባይ ግድብ ግንባታ እንደ አንድ የጦር ግንባር ነው የሚመለከቱት፡፡ ሰለሆነም እነኚሁ አካላት( ምእራባውያን ማለቴ ነው) ይህን ድብቅ ግባቸውን እውን ለማድረግ አሻንጉሊት መንግስት ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህንኑ ፍላጎታቸውን የእነርሱ አሻንጉሊት መንግስት ለመሆን እና ከቻለም ፍላጎታቸውን ገቢራዊ ለማድረግ የሚፈልገው የወያኔ አሸባሪ ቡድን ብቻ ነው፡፡ አያድረገውና የኢትዮጵያ ክፉ እጣ ፈንታ ለአፍሪካም የሚተርፍ ሲሆን፣አዲስ ክስተት ወይም ዘመን በአፍሪካ እንዲፈጠር የሚያደርግ፣የአፍሪካን የነጻነት አርማ ሊገፍ እንደሚችል ፣ እንዲሁም አፍሪካን በድጋሚ ለመቀራመት በር ስለመክፈቱ በተመለከተ በበርካታ የፖለቲካ አዋቂዎች ጥናታዊ ጽሁፎች  ላይ ሰፍሮ የሚገኝ መራር እውነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከብዙ አመታት በፊት የተዋጋችው ጦርነት የአፍሪካን ጦርነት ነው፡፡ ዛሬም የገጠመቸው ጦርነት ለአፍሪካ ነጻነት የሚከፈል መስእዋትነት ነው፡፡ ስለሆነም እጅግ ከመዘግየቱ በፊት አፍሪካውያን አንድነታቸውን በማጠንከር ከኢትዮጵያ ጎን መቆም አለባቸው( ወይም ኢትዮጵያን መርዳት አለባቸው) የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ሁላችንም ይህን አባባል ማስታወስ አለብን ‹‹ በፍጥነት መልስ የሚሰጥ ሁለት ግዜ መርዳት ይችላል፡፡››

We all should remember, “he gives twice who gives quickly.” 

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የስነልቦና እና የዲፕሎማቲክ ዘመቻ

ኢትዮጵያውያን ምንግዜም ቢሆን (ሁል ግዜ) ምእራባውያን የኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ወዳጆች ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ምእራባውያንንም ደግፈው ቆመዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አብዝሃውን ኢትዮጵያዊ በአስደነገጠ ሁኔታ ምእራባውያን በተለይም የተባበረችው አሜሪካ ከወያኔ አሸባሪ ቡድን ጎን ቆሟል፡፡ ወይም ጭፍን ድጋፉን ሰጥቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንት ዶናልድ ትራምፕ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ግብጽ በቦምብ እንድትመታ ይሁንታ መስጠታቸው ለኢትዮጵያውያን እንደ ቀይ መብራት የሚቆጠር ከመሆኑ ባሻግር የተባበረችው አሜሪካ አጋርነት ከማን ጋር ነው ብለው መጠየቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ይህን ተከትሎ የፕሬዜዴንት ባይደንን አደገኛ ንግግር በመቃወም ኢትዮጵያውያን በተባበረችው አሜሪካ መዲና ዋሽንግተን የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ የሚገኙ ሌሎች ደግሞ የተባበረችው አሜሪካ ፕሬዜዴንትን ለማሳሳት የተለያዩ ተጨባጭ የሌላቸው መረጃዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች መሰራጨታቸው እሙን ነው፡፡

ፕሬዜዴንት ባይደን ወደ ነጩ ቤተመንግስት ከገቡ ጀምሮ ኢትዮጵያን ከዲፕሎማቲክ አኳያ ለመነጠል ያላቸውን የገንዘብ ሀብት እንደመሳሪያ ተጠቅመው ነበር፡፡ የተባበረችው አሜሪካ የዲፕሎማቲክ ጫና አንዱ ክፍል የሆነው እና አዲስ አበባ መቀመጫውን ያደረገው የተባበረችው አሜሪካ ኤምባሲ በየግዜው በሚያወጣው መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ የአሸባሪዎች ጥቃት እውን ሊሆን ይችላል የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ማውጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር አዲስ አበባ በቅርብ ቀናት በአማጺው ሀይል ቁጥጥር ስር ልትወድቅ ትችላለች የሚሉ የውሸት ዘገባዎች ከምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን ይሰሙ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የተባበረችው አሜሪካ ሱዳንን ከአሸባሪነት መዝገብ መሰረዟ ብዙዎች ኢትዮጵያውያንን ያስደሰተ ጉዳይ ቢሆንም፣ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር በወረራ መያዟ ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገገር ኢትዮጵያ ላይ ምን ያህል የውጭ ሀገራት በተለይም በምእራቡ አለም ሴራ እንደሚጎነጎንባት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው አስገራሚው ሁነት የምእራቡ አለም በተባበረችው አሜሪካ ውትወታ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከ12 ጊዜያት በላይ ቁጭ ብሎ መነጋገሩ ይመስለኛል፡፡ በቅርቡ ደግሞ የተባበረችው አሜሪካ ሁነኛ ባለስልጣን የሆኑት ብሊንከን በኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር በአለ ሲመት ላይ በተገኙት ሶስት የአፍሪካ ሀገራት አድርገውት የነበረው የስራ ጉብኝት እንደው ዝም ብሎ በመላ የተነደፈ የውጭ ሀገራት ጉብኝት አልነበረም፡፡ ጉብኝቱ የሚያተኩረው ኢትዮጵያን በዲፕሎማቲክ መስመር አኳያ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለመለየት ያለመ ነበር፡፡ ይህ አንዱ ኢትዮጵያን ከዲፕሎማቲክ አኳያ ከአፍሪካ ለመነጠል የተባበረችው አሜሪካ የምታደርገው የዲፕሎማቲክ ትግል ነው፡፡ ይህ ሁሉ ዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው በደመነብስ አልነበረም፡፡ በተጠና እና ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ ነው፡፡ ምእራባውያኑ ኢትዮጵያን ከቀሪው አለም ለመነጠል ሲሉ  የከፈቱት የዲፕሎማቲክ ዘመቻ እንዲሳካለቸው እንደ አልጀዚራ፣ሲኤንኤን፣ቢቢሲ የመሳሰሉትን የታወቁ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኖች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያወጡት መረጃዎች በውሸት የታጀሉ፣እንዲሁም አሸባሪው የወያኔ ቡድን የፈጸመውን አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲደብቁ ተደርገው ነበር፡፡ ኢትዮጵያን አጠልሽተው ነበር፡፡ አለምንም ግራ አጋብተው ነበር፡፡ የወያኔ አሸባሪ ቡድን ደግሞ የሞራል መሰረት አለው በማለት የሀሰት ትርክት በሰፊው ይናኙም ነበር፡፡ እውን እነኚህ የታወቁ መገናኛ ብዙሃን በመሬት ላይ ያለውን የኢትዮጵያ እውነት አጥተው ነበርን? አይመስለኝም፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ የውሸት መረጃ ለጠባብ አላማ ውጤታማ ›› ስለሆነ ነው የምእራባውያን የዜና አውታሮች ኢትዮጵያን በተመለከተ ሰርክአዲስ በውሸት የታጀሉ ዜናዎችን ለአለም የሚያሰሙት፡፡

Disinformation is most effective in a  very narrow context. 

የወያኔ አሸባሪ ቡድን የፖለቲካ ፊትአውራሪዎችና የፕሮፓጋንዳ ማሺነሪ አፈቀላጤዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በአደባባይ እንደዛቱት ‹‹ ኢትዮጵያን ከምድረገጽ ለማጥፋት ሲኦል መውረድ ካለብን ገቢራዊ እንዳርገዋለን›› በማለት ብዙዎች ኢትዮጵያውያንን አሳዝነዋል፡፡

if necessary, they will go to hell  to destroy Ethiopia.” 

ይህ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ልብ የሰበረ ንግግር ቢሆንም እንደተመኙት መልካም የገሃነም ጉዞ እንዲሆን እንመኝላቸዋለን፡፡ ጦርነቱ ከትግራይ ምድር አልፎ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ከተዛመተ ከ5 ወራት በላይ ቢያስቆጥርም የምእራባውያኑ የዜና አውታሮች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ቢደሰኩሩም የተባበሩት መንግስታትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳልተፈጸመ የሚያሳይ ሪፖርት ይፋ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር የኢትዮጵያ መንግስት በብዙ ቦታዎች ላይ ድልን በሚጎናጸፍበት ግዜ የተኩስ አቁም ስምምነት እውን መሆን አለበት በማለት የሚዘግቡት የምእራቡ አለም የዜና አወታሮች አሸባሪው የወያኔ ቡድን በርካታ ከተሞችንና የገጠር ቀበሌዎችን በወረረበት ግዜ ደግሞ ለአሸባሪው ቡድን ጠቀሜታ ያላቸውን ወሬ ለአለም ይናኙ ነበር፡፡

በምጣኔ ሀብት አኳያ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የተወሰዱ እርምጃዎች፡-

  • የተባበረችው አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የሁለትዮሽ እርዳታ ሰርዛለች
  • ከአለም ባንክ የሚሰጡ አንዳንድ ድጋፎችን ይሁንታ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለችም
  • ኢትዮጵያን ከአፍሪካ እድገት እና እድል ( ከቀረጥ ነጻ የሆኑ ሸቀጦችን) እድል ሰርዛለች) (removed Ethiopia from African Growth and Opportunity Act.)

ከላይ የሰፈረው በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ላይ ከባድ ጫና ለመፍጠር በተባበረችው አሜሪካ የተወሰደው እርምጃ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎችና በተባበረችው አሜሪካ ነዋሪ የሆኑ የአሜሪካን ፕሬዜዴንት እንዲመረጡ ያደረጉት ክህደት እንደተፈጸመባቸው ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር በምእራባውያንና በወያኔ አሸባሪ ቡድን መሃከል በርካቶች ምን አይነት ድብቅ ሚስጥር ይኖር ይሆን? በማለት እንዲደነቁ አድርጓል፡፡ እውን የምእራቡ አለም ወዳጅነቱ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነው ወይንስ ከጥቂት ቡድኖች ጋር ነው  አብዛኞቹ ሰዎች የኖርዌጂያኑ የኖቤል ሰላም ሽልማት ኮሚቴ ለጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ የአለም ኖቤል ሰላም ሽልማት የሸለማቸው ኢትዮጵያ ስትወረር የሀገራቸውን አንድነት እንዳያስከብሩ ለመከልከል አልነበረም፡፡ የቀድሞው የሀብታሟና ሃያሏ ሀገር የአሜሪካ ፕሬዜዴንት ባራክ ኦባማ አሸባሪዎችን በመፋለማቸው የአለም ሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን መርሳት የለብንም፡፡ ሆኖም ግን በድህነት የምትታወቀው ሆኖም ግን ገናና ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ መሪ የሆኑት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሸባሪነት የተፈረጀውን የወያኔ ቡድን መከላከያ ሰራዊቱ እንዲቀጣው በማዘዛቸው ምክንያት ለምን በምእራባውያን ይወገዛሉ ?

ምን ይበጀናል ?

የውጭው አለም ሰዎች ኢትዮጵያ የአሸባሪውን የወያኔ ቡድን በምንም አይነት ለመቀበል ዝግጁ አለመሆናቸውን ማወቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ አሁን የምንገኘው በ2021(እ.ኤ.አ.) ላይ እንጂ 1991(እ.ኤ.አ.) አይደለንም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔ የማያልቅ ውሸት ሰልችቶታል፡፡ በአጠቃላይ ለ27 አመታት እድል ተሰጥቶት ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማስፈን ያልቻለ አሳፋሪ እና ወንጀለኛ ድርጅት ነው ወያኔ፡፡ ወያኔ ‹‹ በአዲስ ጠርሙስ የቆየ ወይን ጠጅም ›› መሆን ያልቻላ ነው፡፡ ምክንያቱም ለኢትዮጵያ አዲስ ነገር ይዞ መምጣት ባለመቻሉ ነው፡፡ ጦርነት ከመከሰቱ በፊት ከማእከላዊ መንግስት ጋር የሰላም ድርድር ቢጀመር ኖሮ እንዴት ጥሩ በሆነ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አልሆነም፡፡ ጦርነት ለአንዲት ሀገር እድገት የሚበጅ አይደለም፡፡ ግን ሆነ፡፡ በእውነቱ የኢትዮጵያ እድል ያሳዝናል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ፍትሃዊ ጦርነት ሊካሄድ ይችላል፡፡ ሀገርን አፈርሳለሁ፣ኢትዮጵያን እንጦርጦስ አወርዳለሁ በማለት ኢትዮጵያን የወረረውን ወያኔ ለመመከት ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ጦርነት ማካሄዷ እውነት ነው፡፡

A war is only just if it is fought for a reason that is justified, and that carries  sufficient moral weight”.

ምእራባውያን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን መቆም ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ምእራባውያን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ትብብር( አሸባሪዎችን ለማጥፋት፣በንግድ፣ህገወጥ ስደትን ለመቆጣጠር)  ቢያደርጉ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ምእራባውያን የራሳቸውን ዴሞክራሲ ከልብ እና እውነት መሰረት ላይ ሆነው አፍሪካን(ኢትዮጵያን) ቢረዱ ከሰሩት ከባድ ስህተት እንደተማሩ የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡ የአፍሪካ ህዝብ ተምሯል፡፡ ስለሆነም አውሮፓውያን ከእንቅልፋቸው ይነቁ ዘንድ እንማጸናለን፡፡ ጫካው የለም ጦጣዋ ግን አሁን ድረስ አልተለወጠችም፡፡ The Forest has  changed but the Monkeys are still the same.”

በግልጽ ለመናገር አሁን በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ጦርነት አለማው ኢትዮጵያን ለማዳከም ነው፡፡ ጦርነቱ የስልጣን ጥም ለማርካት ቢሆን በሰለጠነ መንገድ ፣በንግግር መፍታት የሚቻል ነበር፡፡ ደም በመፋሰስ መሆን አይችልም ነበር፡፡ ስለሆነም የአፍሪካ ወንድሞችና እህቶች በዚህ የታሪክ መታጠፊያ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲቆሙ ታሪክ ግድ ብሏቸዋል፡፡

አጼ ሀይለስላሴ በቀድሞው የመንግስታቱ ማህበር ስብሰባ ላይ  ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን ስትወረር ዝምታን በመረጠው ማህበር ላይ ትንቢት መሰል ንግግር አሰምተው ነበር፡፡ ይሀውም ‹‹ ዛሬ በእኛ ላይ የተፈጸመው ግፍ ነገ በእናንተ ላይ መድረሱ አይቀሬ ነው፡፡›› ዛሬ ኢትዮጵያ ብቻዋን አይደለችም፡፡ የአፍሪካ ህብረት ከጎኗ አለ፡፡

As Emperor Haile Selassie stated to the League of  Nations when the world turned its back on Ethiopia during its fight against fascism, “It is us today.  It will be you tomorrow.” Today, Ethiopia is not alone as it was in the 1930s. We now have the  African Union

እንደ መደምደሚያ

በሳምንቱ መጨረሻ ቀናቶች ቅዳሜ ወይም ሰንበት ላይ ከአንድ ወዳጄ ጋር አራት ኪሎ ከሚገኙት በአንዱ ካፍቴሪያ ውስጥ በመገናኘት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለሶስት(3) ሰዓታት ያህል መወያየት ከጀመርን አመታት ተቆጠሩ፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊ ወንድሜን ካወኩት 20 አመታቶች ነጎዱ፡፡ አሁን ድረስ የየት አካባቢ ሰው እንደሆነ ጠይቄው አላውቅም፡፡ እርሱም እንዲሁ ጠይቆኝ አያውቅም፡፡ በቅርቡ ከወራት በፊት በአንድ አጋጣሚ አዲስ አበባ ሾላ ላምበረት አካባቢ እንደተወለደ አውግቶኛል፡፡ ስለ ታላቁ ኢትዮጵያዊ የጂብራልተሩ አለት አቶ ይደነቃቸው ተሰማ እና ስለ መንፈሰ ጠንካራው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣የአለም ኦሎምፒክ የፕሬስ አታሼ የነበሩት ኢትዮጵያዊው አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ  ልእለ ስራዎች አንስተን በተወያየንበት አንድ አጋጣሚ ደግሞ እኔ አዲስ አበባ መሃል አራዳ( ፒያሳ) ተወልጄ ነፍስ እንዳወኩ ያወጋሁት መሆኔን እዝነልቦናዬ ያስታውሰኛል፡፡ ለማናቸውም ከወዳጄ ጋር ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ሰርክአዲስ ስናወጋ እጅጉን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ግንዛቤ ከጨበጥን ሰነበተ፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ አላየንም፣አልሰማንም ካላልን በቀር ኢትዮጵያ በአደገኛ የታሪክ መታጠፊያ ላይ የምትገኝ ሀገር መሆኗ እሙን ነው፡፡ ዛሬ የወያኔ አሸባሪ ቡድንና የአላማው ተጋሪዎች ፣ አዲስ አበባ ላይ የሚቆምሩት ቁማር፣ታሪካዊ ጠላቶቻችን ደግሞ የአዲስ አበባን አለም አቀፍ የዲፕሎማትና አለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫነቷን ለመንጠቅ የሚያደርጉት የረቀቀ ሴራ ሲስተዋል የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡

 በመጨረሻም ኢትዮጵያ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ከባድ ተግዳሮት ውስጥ መዶላችንን፣እንዲሁም የአሸባው ወያኔ ቡድንና የትሮይ ፈረሶቹ አልፋና ኦሜጋ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትንና ፍልስፍና ማርከስና ማጥፋት መሆኑን እያስታወስኩ፣ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያን ለማዳን  በድጋሚ የሕብረት ችቦ እንድንለኩስ በመማጸን ልሰናበት፡፡

Filed in: Amharic