>

አራጅ የሚኖረው በራሱ ታርዶ ነው! (ዘምሳሌ)

አራጅ የሚኖረው በራሱ ታርዶ ነው !

 


የሰራውን ወንጀል እያብሰለሰለ

ከህሊና ሲሟገት ዘወትር እየማለ

በስጋት ተመልቶ ባጠፋው ነፍስ ጣር

እንቅልፉን እያጣ ስንት አለ የሚኖር

ስብእና የለሽ የዳቢሎስ አምሳል

ሲኦል የሚናፍቅ በቁሙ የሚሳል

ሰው መሳይ በሸንጎ እምነት ተጠልሎ

እያጠፋ ሚኖር የሰው ልጆች ገድሎ

ስንት አለ በኢትዮጵያ ግፍን ሞልቶ ሚኖር

የንፁሀንን ነፍስ ገድሎ የሚቀብር

ስንት አየን በኢትዮጵያ  ሀገር ጠል የሆነ

ጥላቻ ተመልቶ በዘር የመነነ

ከራሱ ተጣልቶ ሰውነቱን ረስቶ

ከአውሬ እየባሰ ሰው ራሱ ሰው  በልቶ

በደም የታጀለ ሴጣን የከነዳ

መግባረ  ብልሹ  ሰውን እየጎዳ

ባለንበት ዘመን እራሱን የካደ

ከእንስሳት አንሶ  መኖር የወደደ

በደመነፍስ ያለ ወንጀል የለመደ

በዘር ጥላ ሚኖር ሕዝብ እየሸወደ

በሰላም መኖርን እንደሰውነቱ

ያልጣመው በምድር ላይ የሚኖር በከንቱ

ስንት አለ ነውረኛ ስንት አየን በእውነቱ

በቁም ሙቶ ሚኖር  ትቶ ሰውነቱ

ጊዜ የማያፈርስው መርዝ በልቦናው ይዞ

ኑሮው ጥፋት ብቻ ሌላን ሰው አውግዞ

ነፍስ አጥፍቶ ሚኖር  ህይወትን ገዝግዞ

በስራው የከፋ ህሊናው  ነውዞ

ወንጀል እያሰበ በመግደል ሚደሰት

በሰውልጆች ሲቃ  በሀሴት የሚዋት

ልቡ የተመላ ጥላቻና ምሬት

በሰላም የማይኖር የሆነበት እሬት

እያረደ ሚኖር አንገትን ከርክሮ

ነፍስን እያጠፋ በሕሊናው  ታስሮ

በየቀኑ ሚሞት ሞልቶናል ዘንድሮ

በኢትዮጵያ የሚኖር ሰውነቱን ቀብሮ!

ዘምሳሌ

 

Filed in: Amharic