>

እውነተኛው የነፃነት ትግል ትናንትና ማታ ተጀመረ!! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

እውነተኛው የነፃነት ትግል ትናንትና ማታ ተጀመረ!!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


በተለይ ክርስቲያን ወገኖቼ፣ በአጠቃላይ ደግሞ የየትኛውም እምነት ተከታይ የሆናችሁ ኢትዮጵያውያን ወንድም እህቶቼ እንኳን ለ2014ዓ.ም የገና በዓል (በሰላም?) አደረሳችሁ፡፡ ለቀጣዩ የጥምቀትም ሆነ መሰል የሙስሊም ወንድም-እህቶቻችን ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል በሰላም እንዲያደርሰን የወል ፈጣሪያችንን እንለምነው፡፡

ዜናውን እንደሰማሁ – አልደብቃችሁም – ከመጠን በላይ ደንግጫለሁ፡፡ እየቆየሁ ስመጣ ግን አንዳች መንፈስ በውስጤ ገብቶ የሚያጽናናኝ መሰለኝና ወደመረጋጋቱ ተመለስኩ፡፡ እንጂ እንደዜናው ክብደትና አይጠበቄነት ቢሆን ኖሮ ለእኔን መሰል ድንጉጥ የሀገሩን ሁኔታ ተከታታይ ዜጋ ሊለቅበት የሚችለው የብስጭት ሞገድ ቀላል አልነበረም፡፡ አንድ ጥሩ መጽሐፍ ቅዱሣዊ አባባል አለ – “ሁሉም ነገር ለበጎ ነው”፡፡ አዎ፣ ለበጎ ነው፡፡

በእንግሊዝኛ “a blessing in disguise” የሚባል ፈሊጣዊ አነጋገር አለ፡፡ ወደ አማርኛ ሲመለስ ምን ሊሆን እንደሚችል ብዙም አላውቅም፡፡ ምናልባት “ሳይደግስ አይጣላም” ቢባል በመጠኑ የሚያስኬድ ይመስለኛል፡፡ ዐረቦችም “እከክን የሰጠ ጥፍርን አይነሳም” የሚል አባባል እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ ለማንኛውም አንድ ችግር ሲፈጠር በውስጡ መፍትሔም ይዞ እንደሚመጣ ግልጽ ነውና በሚፈጠር ችግር ሁሉ ተደናግጦ አቅልን መሳትና ለብስጭት መዳረግ ደግ ባለመሆኑ የኔ ቢጤ ተናዳጆች ቀዝቀዝ እንበል፡፡ ወፈፌው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሞቅ ባለው ቁጥር በሚወስነው ውሳኔ ሁሉ ማበድ አይገባንም፡፡ የዚህን ሰውዬ ማንነትና ምንነት ለብዙ ጊዜ ለመግለጽ ብንሞክርም ሰሚ አጥተን አውላላ ሜዳ ላይ ብቻችንን ስንጮህ ባጅተናል፡፡ አሁን ግን አንድዬ ፈቅዶ ይህ ሰው ሁሉንም የዚህች አገር ጉዳይ ራሱ ብቻውን እንደሚያቦካና እንደሚጋግር ግልጽ መረጃ የሚሰጥ ክስተት በትናንትናው ምሽት ተከስቷል፡፡ ያ አስገራሚና አስደንጋጭ ክስተትም እንደዚያ መሆን ካለበት እንኳን ፓርላማ ወይንም የሚኒስትሮች ካቢኔ ተሰብስቦ ሳይወያይበትና ሳይወስን ሀገር ያወቃቸው ወንጀለኞች በምሕረት ስም ከእስር እንዲፈቱ በብጣሽ ወረቀት ብቻውን ወይንም ከተወሰነ የጥፋት ቡድን ጋር መክሮ መወሰኑ ነው፡፡ የሀገር ጉዳይ የሰንበቴ ወይንም የዕድር ማኅበር ይመስል በአንድ ሮጦ ባልጠገበ ጎረምሣ እንዲህ ሲጨመላለቅ ማየት በእጅጉ ቢያናድድም የዞረ ድምር ውጤቱ ግን ለሀገራችን ትንሣኤ ከፍተኛ ግብኣት በመሆኑ ብዙም አንከፋ፡፡ ይህ አጋጣሚ የመንግሥትን ሦስትዮሻዊ ቁርኝት መዛባት ያሳያል፡፡ በልማድ የሚታወቀው ህግ አውጪ፣ ህግ ተርጓሚና ህግ አስፈጻሚ አካላት ሙሉ በሙሉ አቢይ ትከሻ ላይ መውደቃቸውንና የያንዳንዳችን እስትንፋስ በአቢይ እስትንፋስ የሚለካ መሆኑን ተረዳን፡፡ አቢይ ከሌለ አዲዮስ! የዲክቴተር ፊልም ተዋናይ ጄኔራል አላዲን፣ የእንስሳት ዕድሩ ዓሣማ ጓድ ናፖሊዮን፣ የዩጋንዳው ኢድ አሚን፣ የዛየሩ ቦካሣ፣ የኢራቁ ሣዳም – አቢያችን!

በመሠረቱ በተለይ በበዓላት ወቅት እስረኞች በምሕረት መፈታታቸው ያለና የነበረ ነው፡፡ በዚህ አቢይ አህመድ በተከተለው መንገድ ግን አይደለም፡፡ የሀገሪቱ ፓርላማ በሚገባ ተከራክሮበትና ተወያይቶበት፣ ከእስር ቤት ወይም ከማረሚያ ቤት ስለታሳሪዎች የጠባይ መሻሻል መረጃ እንዲመጣ ተደርጎ፣ ለምሕረት የታጩ ሰዎች በሠሩት ወንጀልና ጥፋት መፀፀታቸው ታውቆ፣ ሰዎቹ በእርግጥም ተለውጠውና ሀገርንና ወገንን ለመካስ የተዘጋጁ መሆናቸው ተረጋገግጦ፣ ወዘተ. በሚመለከተው የሀገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል በአብላጫ ድምጽ ሲወሰን ዜጎች በምሕረት ይፈታሉ፡፡ አንድ በሞቀበት ዘፋኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬ የሆነ መንፈስ ሾጥ ባደረገው ቁጥር ወንጀለኛን መፍታት ግን የመናፈሻ ቦታን የመገንባት ያህል ቀላል እንዳልሆነ በበኩሌ እረዳለሁ፡፡ ይህ ሰው ገና ብዙ ጉድ ሳያሳየን አይቀርም፡፡ ሀገር ሲያረጅ ጃርት ማፍራቱን አሁን በትክክል እየተገነዘብኩ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የምታህል ታላቅ ታሪካዊት ሀገር በዚህ መልክ መመራቷ በርግጥም ሀገራችን ለይቶላት ጃጅታለች፡፡ 

አቢይ አህመድ አማራን የጎዳ መስሎት – ልክ እንደዚያች ባሏን የጎዳች መስሏት የገዛ ሰውነቷን በጋሬጣ እንደወጋችው ጅላጅል ሚስት – ሀገር አፍራሽ ዜጎችን ከእስር መፍታቱ ማንን እንደሚጠቅም ወይንም እንደሚጎዳ ብዙ ሳንቆይ የምናየው ነው፡፡ አገኛለሁ ብሎ የሚያስበውን ጥቅም እንደማያገኝ ግን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ በሚስተር ፊልዚማንም (Filthyman or Feltman?) ይሁን በሌላ የአሜሪካና አውሮፓ ባለሥልጣን ይመከር ይህ አቢይ የሚባል በሻህ ዘለሌ ይህን ውሳኔ መወሰን አልነበረበትም፡፡ ይህ የሚጠቁመው አቢይ ሥልጣን ሰለቸው ማለት ነው፤ ብቻውን ቆላ ደጋ ሮጦ ሮጦ አሁን ላይ ደከመው ማለት ነው፤ በቶሎ መወገድን ፈለገ ማለት ነው፤ በውታፍ ነቃዮቹና በአሽቃባጭ ምሁራን መመለኩ ሁለመናውን አሳውሮት ኅሊናውን ሳተ ማለት ነው፡፡ ለኔ የሚሰማኝ እንደዚህ ነው፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ቡድኑ ጋር በሌሊት መክሮና ዘክሮ አማራን ለማናደድ ወይንም የዓላማ አጋሩን ወያኔን ለማስደሰት ወይንም የአማራን ጠላቶች ጮቤ ለማስረገጥ ብሎ እነዚህን ሰዎች መፍታቱ ለርሱ ሥውር ቢሆንም ለኛ ግን የኢትዮጵያ እውነተኛ ትንሣኤ መቃረቡን የሚያበስር ተከፍሎበት እንኳን ሊገኝ የማይችል ታላቅ ክስተት ነው፡፡ ዝርዝሩን መናገር ጥቅም የለውም፡፡ እውነቱ ግን ይሄው ነው፡፡

ወያኔ እንኳን ባቅሟ በነዚህ ሰዎች መፈታት አላግጣበታለች አሉ – ክፉኛ ነው አሉ ያሽሟጠጠችው፡፡ አቀብ ቁልቁል ወጥተው ወርደው መዋጋት የማይችሉ ቶርቶራ ሽማግሌዎችን መፍታት ወደህክምና ማዕከል ከማመላለስ ይሻለኛል ብሎ እንጂ ለማንም ጥቅም ብሎ እንዳልፈታቸው ወዲያውኑ ነው እያሾፉ በሚዲያቸው የተናገሩት አሉ፡፡ የወያኔ ሽርደዳ ለሥልት ሲባል ከአንገት በላይም ይሁን ከአንጀት ሰውዬው ግን ለጊዜው ከሁለት ያጣ ጎመን ሆኗል፡፡ ወያኔና የአቢይ ኦህዲድ ኢትዮጵያን በማፈራረስ ረገድ አቋማቸው አንድ ነው – ልዩነታቸው ወያኔዎች እነርሱ በሚመሯት የተጠጋገነች ኢትዮጵያ እንደፈለጋቸው መዝረፍና መክበር ሲሆን ኦህዲዶች ደግሞ በኬኛ ፖለቲካቸው ሁሉንም ጠቅልሎ በኦሮምያ ግዛት ሥር በማድረግ የሌሎችን ባህልም፣ ቋንቋም፣ የዘመናት የወል መስተጋብርም ማጥፋት ነው፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ የሚወድቀው ደግሞ ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም ለሽዎች ዓመታት የተጋመደን የ86 ነገድ የጋራ ኅልውና በአራትና አምስት ዓመት የኦሮሙማ ዘመቻ አትበጥሰውም፤ በአንድ ቤተ መጻሕፍትም አትፍቀውም፡፡ የጋራ ሀገር የሚገነባው በፍቅር እንጂ በጉልበት አይደለም፡፡ ሀገር የሚመሠረተው በፍቅርና በመተሳሰብ ነው፤ ሰዎችን በማረድና በማፈናቀል፣ ሀብት ንብረትንም በማውደም አይደለም፡፡ አማራን በመግደል የተጠመዳችሁ ወገኖች እባካችሁን ስለሀገር ምሥረታ ከታሪክ ተማሩ፡፡    

አቢይ ለምንም ዓላማ እነስብሃትን ይፍታ ገመዱን የጠመጠመው በራሱ ላይ እንደሆነ ከፍ ሲል በግልጽ አስቀምጫለሁ፡፡ እንጂ በመሠረቱና እንደእውነቱም ከሆነ ለእኔና ለእኔያውያን የጃጀ ሽማሌ ስብሃት ነጋ ተፈታ አባይ ወልዱ ታሰረ፣ ጃዋር ተፈታ በቀለ ገርባ ታሰረ ምንም ማለት አይደለም፡፡ “ያዲያቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም” እንዲሉ ሆኖ እንጂ እንዲያውም እነዚህ ሰዎች፣ ሰዎች ሊሆኑ ቢችሉ ከመታሰራቸው ይልቅ መፈታታቸው የተሻለ እንደሚሆን በበኩሌ አምናለሁ፡፡ በሰው መታሰር የሚጠቀም የለም፤ የሚደሰትም ሊኖር አይገባም፡፡ ችግሩ ግን እስሩም ሆነ ፍቺው ህገ ወጥና በአፄ በጉልበቱዎች የሆነ ዓላማ ለማራመድ ሲባል የሚከናወን መሆኑ ነው፡፡ እንግዲያውስ እነዚህ ወንጀለኞች የተፈቱት ለሰላም ነው ከተባለ ያላንዳች ኃጢኣት የታሰሩት ታምራት ነገራና መዓዛ ሞሀመድ ለምን አይፈቱም? ይሄ ታሪክ የሚያስታውሰን የበርባንንና የመጥምቁ ዮሐንስን ታሪክ ነው፡፡ ግንጥል ጌጥ ማለት ይሄኔ ነው፡፡ አቢይ አህመድ ስለሰላም ሊያወራ የሚችልበት አንድም የሞራል ብቃት እንደሌለው ደግሞ ይህን ሌት ከቀን የሚቃዥበትን ሥልጣን በሆነ ምትሃታዊ ኃይል ከተቆጣጠረ ወዲህ በሚያሳያቸው ተግባራቱ መረዳት ይቻላል – ይሄ ጫማ እያነሱ መስጠቱና ዕንባ ከዐይኖች መጥረጉን ተውት – ፊንታ ነው – የተቀነባበረ የማስመሰል ትያትር፡፡ በዚህ ዓይነቱ ማጭበርበርማ የሚስተካከለው የለም፡፡  

ካለብዕር አንዳችም መሣሪያ የሌላቸውን ምስኪን የሕዝብ ድምጾች እስር ቤት አጉሮ እያሰቃዩ ወንጀለኛነታቸውን ለመረዳት ፍርድ ቤት መመላለስና ምስክር መቁጠርም ሳያስፈልገን በአደባባይ የምናውቅላቸውን ዜጎች ከእስር መልቀቅ ማለት ባጭሩ “ወያኔንና ኦነግ-ሸኔን በመሳሰሉ የአማፂያኑ ጎራዎች የተፈጠረውን የአመራር ክፍተት ሄዳችሁ አሟሉ” የሚል መልእክት ያዘለ ይመስላል፡፡ አዎ፣ እነስብሃትን ወደመቀሌ፣ እነጃዋርን ወደ ደምቢዶሎ በመላክ ኢትዮጵያንና አማራን የማጥፋት በሳል አመራር እንዲሰጡ ታስቦስ ከሆነ ማን ያውቃል? “ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር” ይባላል እኮ፡፡ ኢትዮጵያን ለመበታተን ከጫካ እስከቤተ መንግሥት ሲዶልትና ሀገርን ሲያጠፋ የኖረን ሰው፣ መቀሌ ላይ ከጓደኞቹ ጋር በወሰነው ውሳኔ በተለይ የአማራ የጦር መኮንኖችን በውድቅት ሌሊት በተኙበት ያስጨፈጨፈ ሰው፣ ለኢትዮጵያ መፈራረስ ትልቁን አስተዋፅዖ ያደረገ የሀገር ብተና ኢንጂኔር፣ የሀገርን ሀብት ዘርፎና በዘመድ አዝማዱ አዘርፎ ቢሊዮኔር የሆነ ዕድሜ የማያስተምረው ወምበዴ፣ … “ካስፈለገ በጦርም ቢሆን ወይም በሕዝባዊ ዐመፅ መንግሥትን ጥለን የራሳችንን መንግሥት እንመሠርታለን” የሚልን ቅንጡ የከተማ ሽፍታ፣ በሃጫሉ ግድያ ሰበብ በመቶዎች የሚቆጠሩ አማሮችን ነፍስ ያስቀጠፈ የወይዘሮ “ከበቡሽ” ባለሟል፣ በመንግሥት ውስጥ የራሱን መንግሥት መሥርቶ በአንጋቾቹ የፈለገውን የሚሠራን የኢትዮጵያ ሂዝቦላ፣ በሸኔው ያሻውን የሚያደርግ ጀብደኛ … ከእስር መፍታት አደጋው ከአማራ ይልቅ ለማን እንደሚበረታ ጥቂት ሣምንታትን ወይም ወራትን እንጠብቅ፡፡ አማራማ ቁርጥ ያጠግባልና ቁርጡን አወቀ፡፡ “ዘጠኝ ሞት መጣ” ቢሉት “አንዱን ግባ በለው” አለ ይባላል፡፡ 

በወሎም በኩል መጥተው አማራው ሞቷል፤ በአፋርም በኩል መጥተው አፋሩ ሞቷል፡፡ አሁን ደግሞ በጎንደርና በወልቃይት እንዲመጡ አቢይ አህመድ ሰፊ የዝግጅት ጊዜና ምናልባትም የውጊያ ድጋፍ ከነስንቅና ትጥቅ ይሰጣቸዋል፤ እነሱም አያፍሩምና ይመጣሉ፤ ተስፋ የቆረጠና ያበደ ሰው ሀፍርትን አያውቅም፡፡ ተሳክቶላቸው መመለሳቸውን ግን ማንም እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይችልም፡፡ አማራው አሁን ይበልጥ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ያቺ በላይነሽ አመዴ የምትባል ድሮን ከአሁን በኋላ እስካሁንም እንደምትታማበት ሁሉ የበለጠ ትኩረቷ አማራንና የአማራን ንብረት በማውደም ላይ እንደሚሆን ከሰሞኑ የወንጀለኞች መፈታት ጋር አያይዞ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ አቢይ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ያቺ ሽመልስ አብዲሣ የተናገራትን የኮንቪንስና ኮንፊውዝ የፖለቲካ ቁማር አንርሳት፡፡ በቆፈሩት ጉድጓድ እስኪገቡ ድረስ ሁሉም ጠንቀቅ ብሎ አካባቢውን ይጠብቅ፡፡ በቃ፡፡ 

Filed in: Amharic