>

"ከትላንቱ ስህተት አለመማራችን ዋጋ እያስከፈለን ነዉ...!!!" (ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ)

“ከትላንቱ ስህተት አለመማራችን ዋጋ እያስከፈለን ነዉ…!!!”
ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ

የፌዴራሉ መንግስት ህግ ለማስከበር ሲባል በትግራይ ክልል መንግስት ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ባለፈው አመት መሪ ድርጅቱ ትህነግም ከህጋዊ ፓርቲነት እንዲሰረዝ ተደርጓል። በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ ህጋዊ የሆነ ፓርቲም ሆነ መንግስት የለም። እናም በክልሉ ውስጥ ህገ ወጥነት ነግሶ ሕዝም ባይተዋር ለመሆን ተዷል።
የፌዴራሉ መንግስትም መቀሌን እንደተቆጣጠረ በትግራይ ተወላጆች አማካኝነት ጊዜያዊ አስተዳደር አደራጅቶ ክልሉን እንዲመራ ለማድረግ ቢሞክርም አብዛኛዎቹ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላትም ሆኑ የስራ ሀላፊዎች የትህነግ አባላትና ደጋፊዎች ስለነበሩ ውጤታማ የሆነ ስራ መስራት አልቻሉም። በተቃራኒው ትህነግን ለማጠናከር ተንቀሳቀሱ።
ይህንን ሁኔታ ተከትሎም አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ከትህነግ ጎን ተሰልፎ የመከላከያ ሠራዊቱን ማጥቃት እንደጀመረ የመንግስት ባለስልጣናት በግልጽ መናገር ጀመሩ። ብዙም ሳይቆዩ የመከላከያ ሠራዊቱ ከትግራይ ክልል እንዲወጣ በማድረግ ትግራይን ለአሸባሪው ትህነግና እሱ ለሚመራው መንግስት ማስረከብ ተቻለ። ስህተት አንድ በሉ፣
በዚህም ምክንያት መላው ትግራይን ብቻ ሳይሆን መላው ወሎን፣ ከፊል ጎንደርን፣ ከፊል ሰሜን ሸዋንና ከፊል አፋርን በመቆጣጠር ያሻውን ገደለ፣ የቻለውን ያህል ሀብትና ንብረት ዘርፎ ቀሪውን አወደመ። በተቃራኒው የፌዴራል መንግስትም ሆነ የአማራ ክልል የእነዚህን አካባቢ ሕዝቦች ከአሸባሪው ትህነግ ጥቃት መከላከል ሳይችሉ ቀርተው ለወራት ተሰቃዩ።
የኋላ ኋላ የጥምር ጦሩን ሞራልና አደረጃጀት ለማጠናከር በተደረገው ጥረትና የትህነግም ጉልበት መዛል ታክሎበት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሰሜን ሸዋና አብዛኛውን የወሎ አካባቢ ነጻ ማውጣት ቢቻልም አሁንም በትህነግ ቁጥጥር ስር ሆነው የሚሰቃዩ የአማራ አካባቢዎች እያሉ ጦርነቱ እንዲቆም ተደረገ። እናም ሁለተኛው ስህተት ተፈጸመ።
በዚህም ምክንያት የትህነግ ሠራዊት ንብረቱንና የራሱን ሰዎች በመያዝ ጭምር እየፈረጠጠ ከነበረበት ሁኔታ ወጥቶ ትንፋሽ በመውሰድ የለቀቃቸውን ከተሞች ያለውጊያ መልሶ መቆጣጠር ቻለ። ታሪክ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው አምና ሰኔ ላይ የተፈጸመው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ስህተት አሁንም በግልጽ ተደገመ። ሶስተኛው ስህተት አትሉም።
እንዲህ እያልን ብዙ ስህተቶችን ማንሳት ይቻላል። ከሁሉም በላይ ግን በጣም አሳሳቢው ነገር ከስህተት ለመማር አለመቻሉ ነው። በዚህም የአማራ ሕዝብ በአጠቃላይና የራያ ሕዝብ በተለይ ለጥቃት ሰለባ እየሆነ ይገኛል። ከትላንት ጀምሮ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው። ትህነግ የልብ ልብ ተሰምቶት በዋጃ-ጥሙጋ አካባቢ ውጊያ ጀምሮ ሕዝብ እየተፈናቀለ ነው።
Filed in: Amharic