>

ንስሃ ሳይገቡ ምህረት....!!! (ኦሀድ ቢንአን)

ንስሃ ሳይገቡ ምህረት….!!!

ኦሀድ ቢንአን

ይህ የምህረት ውሳኔ ሌላ ችግር ይዞ ከመጣ አይን ለአይን መተያየት ከባድ የሚሆን ይመስለኛል፤ የህወሓት ምርኮኞችን መፍታቱ ግርምት ፈጥሮብኛል፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ እነሱን ለመያዝ ዋጋ የከፈለውን ወታደር ድካም፣ ላብ እና ህይወት ትክክለኛ ግምት ካለመስጠት ይሆን? ከዚህ በኋላስ በሚኖረው ውጊያ ላይ ምን አይነት እንደምታ ሊያሳርፍ ይችላል? እነደብረጺዮንን፣ ጻድቃንን እና ጌታቸው ረዳን የመማረክ አጋጣሚው እጁ የገባ ወታደርስ ይዞ ለመንግስት ያስረክባል ወይስ የነስዩም መስፍንንና አባይ ጸሓዬን ቀን ይሰጣቸዋል? ሌሎች ተራ የፍትሓብሔር ክስ ተጠርጣሪዎችስ ምን አይነት የሞራል ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ? ዛሬ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ዜናውን የሚሰማው እና አነስዩምን እዛው ላይ እርምጃ የወሰደባቸው ወታደር ምን ያክል እርካታ ይሰማው ይሆን?
ህወሓት እነ ታማኝ በየነ መለስ ዜናዊን የሚያንቋሽሽ የቪዲዮ ክሊፕ ሰራችሁ ብሎ ሞት ፈርዶባቸው ነበር፡፡ የምህረት ደርዙ ከየት እስከ የት ነው? ትላንት እንደፈለጉ ሞት ሲፈርዱና ሲገድሉ የነበሩ ሰዎችን ዛሬ ዝቅ ሳይሉና ባይያዙ ኖሮ በጥፋታቸው መቀጠላቸውን የማያቆሙ “የደም ወንጀለኞችን” የምህረት ክብር መስጠቱ እውነት ሃገርን የሚክስ ጎን አለው? ጦርነቱ ባይነሳስ እነዚህ ሰዎች የሚጠየቁበት ወንጀል አልነበራቸውም ይሆን? የጲላጦስ እጅ የነበራቸው ሰዎች ነበሩ እንዴ? እነዚህ ሰዎች ከአገር የመውጣት መብታቸው እንደተጠበቀ ከሆነ በውጭ አገር ያስቀመጡትን ገንዘብ እንደገና ለሌላ የዲፕሎማሲ ጉቦ ተጠቅመው ሊወጉን የማያስችል ስብዕና ይኖራቸው ይሆን? እንደገና ከመውጋት ወደኋላ የማይመለስ ስርነቀል ፍልስፍና የተጋተን አጁዛ እንደሚበቀልህ እያወቅክ ትለቀዋለህ እንዴ? እኔ አልገባኝም፤ ዝም ማለት ኃጢያት የሚሆንበት ሁኔታ ውስጥ ያስገባኝን ውሳኔ ዝም ብዬ ላልፈው አልችልም፤ ልዩነት ለዘላለም ይኑር፤
ዛሬ ከህወሓት ጎን ሆነው የወጉንን “ንስሓ ሳይገቡ” የምህረት ቸርነት ማከናነቡ ከባድ የሞራል ጥያቄ የሚፈጥር ነው፤ በዚህ ውሳኔው መንግስት ከፍተኛ ነጥብ የጣለበትን ድርጊት የፈጸመ ይመስለኛል፡፡ ይህ የምህረት ውሳኔ ሌላ ችግር ይዞ ከመጣ አይን ለአይን መተያየት ከባድ የሚሆን ይመስለኛል፤ አንዳንዴ አይገባህም፤ እና ዝም ብለህ ውጤቱን ትጠብቃለህ፤ ከዛ እንደሁኔታው ትቀጥላለህ፤ “Sometimes life is not fair. Really it is not fair.” ብለን እንለፈው ይሆን?
Filed in: Amharic