>
5:21 pm - Saturday July 20, 8869

ክብር የሚገባው ለእኛ ሳይሆን ሀገር አንድነት እየተጋደሉ ላሉት ነው!!! (የታላቁ እስክንድር መልእክት - ወንድወሰን ተክሉ)

ክብር የሚገባው ለእኛ ሳይሆን ሀገር አንድነት እየተጋደሉ ላሉት ነው!!!

የታላቁ እስክንድር መልእክት
 
«ክብር የሚገባው ለእኛ ከእስር ቤት ለወጣነው ሳይሆን ለአንድ ኢትዮጲያ ብለው የተሰውና አካላቸውን ላጡ ባለውለታዎቻችን ይሁን»  እስክንድር ነጋ ወደ ቤቱ ሲገባ ከተናገረው!!
*** ወንድወሰን ተክሉ***

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ መስራችና ፕሬዚዳንት ታላቁ እስክንድር ነጋ በበርካታ አዲስ አበቤዎች እና ከትግል አጋሩ ስንታየው ቸኮል ታጅቦ አንመካም በጉልበታችን እግዚአብሄር ነው የእኛ ኋይላችን መዝሙር እየተዘመረ ለቤቱ በቅቷል።
እስክንድር ነጋና ባልደረቦቹ ከቅሊንጦ እስርቤት የተፈቱት ከምሽት  አስራ ሁለት ሰዓት ቢሆንምና ይፈታሉ ተብሎ በይፋ ያልተነገረ በመሆኑ መፍታቱን ሰምተው ለመቀበል የተገኘው ሰው ቁጥር ግን ቀላል ግምት የማይሰጠው በመሆኑ አስደናቂ ከመሆኑም በላይ ቦሌ አካባቢ ሲደርሱ አዲስ አበቤ ግልብጥ ብሎ በመውጣት አቀባበል ሲያደርግለት ታይቷል።
እግዚአብሔር ኋይላችን ነው በሚዘምሩ አድናቂና ደጋፊዎቹ ታጅቦ መኖሪያ ቤቱ የደረሰው ታላቁ እስክንድርና የትግል አጋሩ ስንታየሁ ቸኮል ወደ ቤት ከመግባታቸው በፊት ለደጋፊዎቻቸው አጭር ንግግር ያደረጉ ሲሆን ንግግራቸውንም  በእስክንድር የአንድ ደቂቃ  የህሊና ጸሎት ጠያቂነት ለሀገራቸውና ለወገናቸው ብለው ለተሰውና ዛሬም በመታገል ላይ ላሉ ኢትዮጲያዊያኖችን በማሰብ የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማድረግ ንግግራቸውን ጀምረዋል።
«ከሁሉም በፊት ክብርና ምስጋና የሚገባው እኛን ጠብቆ ለዚህ ላበቃንና ሀገራችንንም እየጠበቀ ላለው ለታላቁ ፈጣሪ እግዚአብሔር  ነው» በማለት ንግግሩን የጀመረው እስክንድር የእግዚአብሄርን ጠባቂነት አዳኝነትን እና ታማኝነቱን በጥልቅ ስሜት ተሞልቶ ሲገልጽ ተደምጧል።ይህንን የእስክንድርን ጥልቅ ከፈጣሪ ጋር ያለውን ቁርኝት ለ1 ዓመት ከ7 ወር በቃሊቲና በቅሊንጦ አብሮት የታሰረው ስንታየሁ ቸኮል « በዚህ አንድ ዓመት ከሰባት ወር የእስር ቆይታ ስለአስክንድር ካወቅኩት ነገር ፕሬዚዳንታችን የፖለቲካ መሪና አዋቂ ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊ ትምህርትንም አዋቂና አስተማሪ መሆኑን በተግባር ያየሁበት መሆኔን ለእናንተ ልመሰክር እወዳለሁ» በማለት የእስክንድርን መንፈሳዊ ብርቱነትን ለተሰበሰበው ሕዝብ  ምስክርነቱን በመጨረሻ ንግግሩ ላይ  አስደምጧል።
ቀጥሎም እስክንድር ነጋ በማያያዝ  « በመቀጠልም ክብርና ምስጋና የሚገባው ለእኛ ከእስር ቤት የወጣነው ሳይሆን የሀገራቸውን ህልውናን ለማስጠበቅ ብለው በየዱር በየገደሉ ውድ ህይወታቸውን ለሰውና አካላቸውን ላጡ ውድ የህዝብ ልጆች ይሁን። ከፍለን እማንጨርሰው እጅግ ታላቅ ኋላፊነትን እና ውለታን ጥለውን ያለፉ ባለውለታዎቻችን ናቸው» በማለት በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ትግልና ትንቅንቅን እያደረጉ ላሉ ተዋጊዎች በሙሉ ነጥሎና ለያይቶ ስም ሳይጠቅስ እንዳለ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ህልውና የተሰውቱን አካላቸው የጎደሉትን እና በመታገል ላይ ያሉትን ከፈጣሪ ቀጥሎ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል በማለት ነው ታላቁ እስክንድር የተናገረው።
ክብርና ምስጋና ለባልደራስ ፓርቲ አመራሮች አባላትና ደጋፊዎች !!!
እስክንድር ቀጥሎም ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ብሎ የጠቀሳቸው ይህንን ያህል መስዋእትነትን የከፈለበትን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲን ህልውና ጠብቀው ላቆዩት የባልደራስ አመራሮችና እንዲሁም ምንም ሳይሰለቹና ሳይታክቱ ስራቸውን እየተው ፍርድ ቤት ሲመላለሱ ለቆዩ የባልደራስ አባላትና ደጋፊዎች ክብርና ምስጋና ይገባችኋል በማለት አመስግኖ የገለጸው «ከእውነት ጋር ወግናችሁ ለፍትህ ለሀቅ ለእውነት በመቆማችሁ ከልብ የመነጨ ክብርና ምስጋናዬን አቀርባለሁ » በማለት ነው።
ኢትዮጲያ አትፈርስም!!!
እስክንድር ይህንን ምስጋናውን ለባልደራስ አባላት ደጋፊዎችና ለአዲስ አበቤ ከገለጸ በኋላ ለዚህ ታላቅ ስራና ተግባር በምንድነው የምንክሳቸው ብሎ መጠይቅ ካነሳ በኋላ « ይንንን በምንድነው የምንክሰው ለሚለው ጥያቄ  ከማንኛቸውም  በላይ የኢትዮጲያን አንድነት እናስቀድማለን። በዚህ ላይ ምንም አይነት ድርድር የለም። ይህ መልእክት ሊደርሳቸው ለሚገባ ሁሉ ይድረሳቸው። ከኢትዮጲያ ህዝብ ህልውና የምናስቀድመው ነገር የለም። ኢትዮጲያአትፈርስም።ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጲያን እናስቀድማለን። ለኢትዮጲያ አንድነት እንታገላለን» በማለት በአጽንኦት ከገለጸ በኋላ «ግን በዚያ ላይ አናቆምም » በማለት ንግግሩን የቀጠለው እስክንድር « አንድ ኢትዮጲያ ስትኖር ደግሞ አንድ ኢትዮጲያ እንድትቀጥል ዴሞክራሲ የግድ ያስፈልጋል። ሁለቱ የአንድ ሳንቲም ግልባጮች ናቸው። የግድ ደግሞ ለዴሞክራሲ እንታገላለን። አንዲት ትንፋሽ ለመውስድም እንኴን ሳናርፍ ለአንዲት  ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጲያ እንታገላለን » በማለት ከእስር ቤት ሲፈቱ ሊቀበላቸው ለተሰበሰበ የአዲስ አበባ ህዝብ የቀጣይ ፖለቲካዊ ትግሉን አቅጣጫ ዛሬውኑ ከእስር ቤት በተፈታበት እለት ወደ ቤቱ እንኴን ሳይገባ ደጁ ላይ ቆሞ በጥሩ መንፈስና ሞራል ተሞልቶ መልእክቱን አስተላልፏል።
፠  በኢትዮጲያ አንድነት ላይ አንደራደርም!!!
ከሰኔ 2020 ጀምሮ መጀመሪያ በማእከላዊ ቀጥሎም በቃሊቲ ለጥቆም በቅሊንጦ ከአንድ ዓመት ከሰባት ወር በላይ በእስር የማቀቁት የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ስንታየሁ ቸኮል፣አስቴር ስዩምና አስካለ  ዛሬ ለመፈታት በቅተዋል። «በእስር ቤት ውስጥ ስንታየሁ ቸኮልን የመሰለ አጋር ወንድም ባላገኝ ኖሮ ይህንን አመት ከመንፈቅን እስር እንዴት እንደምወጣው አላውቅም ነበር» ያለው እስክንድር አጋሩን ስንታየሁ ቸኮልን ያመሰገነ ሲሆን ስንታየሁም በበኩሉ « ትናንት ከአንተው ጋር በታማኝነት ከጎንህ ቆሜ እንደታገልኩ ዛሬም በዚህ ህዝብ ፊት ቆሜ ቃል የምገባልህ ከጎንህ ሆኜ በሙሉ ታማኝነት ለመታገል ነው» በማለት ታማኝነቱን በይፋ በመግለጽ እስክንድር ላደረገውና እያደረገ ላለው ሁሉ ምስጋናውን አቅርቦለታል።
የህሊና እስረኞቹ የባልደራስ አመራሮች በመንፈሳቸው የበረቱ  በሞራላቸውም የጠነከሩ መሆናቸውን ከሁለቱ መሪዎች በኩል ማየት ተችሏል። እስክንድር እንዳለው አንዳችም አፍታዊ እረፍት ሳያስፈልገን ለአንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጲያ ህልውና እንታገላለን በማለት አስተጋብቷልና በቀጣይ የምንጠብቀው የተጠናከረ ሁለገብ ትግል እንደሚሆን ይታመናል- እያልኩ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኴን ለጌታ ልደት በዓል አደረሳችሁ ስል ለአዲስ አበቤ ለባልደራስ እውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራር አባላትና ደጋፊዎች እንኴን ደስያለን ለማለት እወዳለሁ።
Filed in: Amharic