ወዴት እየሄድን ነው?!
አንዱ ዓለም ተፈራ
በምኖርበት አገር አሜሪካና፤ በትውልድ አገሬ ኢትዮጵያ አሁን በውስጣቸው የሚታየውን የፖለቲካ ሂደት፤ ትርጉሙን ማወቁ በጣም አስቸጋሪ ሆኖብኛል። የተለመደ የሚባለው ሩቅ ሆኗል። ነገን ቀርቶ ከትንሽ ሰዓታት በኋላ ሊከተል የሚችለውን መገመቱ ዋጋ ቢስ ሆኗል። የፖለቲካ ልሂቃንም ሆኑ የኔ ቢጤዎች እጅና እግሩን መያዝ ያቃተን ኩነት ነግሷል። ወዴት እየሄድን ነው!
ኢትዮጵያ በሶስተኛው ዓለም ውስጥ የምትገኝ አገር ናት። አሜሪካ በአንደኛው ዓለም ከተቀመጡት ግንባር ቀደሟ ናት። ሁለቱም ያሉበት የፖለቲካ ቀውስ ተመሳሳይ ነው። በአሜሪካ፤ የቀድሞው ፕሬዘዳንት፤ በምርጫ ተሸንፎ ሥልጣኑን በመልቀቁ ተናዶና ተቆጭቶ፤ አገሪቱን በዘረኝነቱና በሥልጣን ናፋቂነቱ ጠምዝዞ እየዘወራት ነው። ሕግ አውጪዎቹ ሕግ-ማውጣቱን ትተው፤ ለነገ ምራጫቸው ብቻ በቦታው ተወዝፍውበታል። ጎራቸውን እያጠናከሩ በመካከላቸው ያለውን የፖለቲካ አመለካከት ልዩነት፤ የሞትና የሽረት አድርገው፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የአስተዳደር ችግር ተጋርዶበታል። ባለፈው ዓመት፤ በዚህ በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ፤ በትክክል የተመረጠውን የዴሞክራቶች አስተዳደር፤ ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ሥልጣን እንዳይዝ ለማድረግና የተቸነፈውን ሙሰኛና ዘረኛ የቀድሞ ፕሬዘዳንት በቦታው ለመመለስ ጥረው ነበር። በቀጭን ገመድም ትሁን፤ በአገሪቱ ያለው የዴሞክራሲ መሠረት፤ ይሄን መፈንቅለ መንግሥት ተንገዳግዶ አድኖታል። ከሕግ አንጻር፤ እንኳንስ ዋናዎቹን አቀናባሪዎች፤ ኮት አልባሾችንም መንካት አልተቻለም። በርግጥ እጅ ከፍንጅ የተያዙትን ሙጭጭሊዎች መቆንጠጥ ተችሏል። እናም ይህ ሂደት፤ አሜሪካን በምጥ ውስጥ ያለች አገር አድርጓታል። ስለ አሜሪካው ፖለቲካ ይሄን ያህል ካስቀመጥኩ ይበቃኛል።
በኢትዮጵያ ደግሞ፤ በሥልጣን ላይ ያለው መሪ፤ የሕዝቡን ቁጭትና ቆራጥነት ተጠቅሞና በርግጥም በግንባር ተገኝቶ ወራሪውን ኃይል ወደኋላ እንዲዞር ሠራዊቱን አበረታቷል። የትግሬዎቹን ነፃ አውጪ ግንባር ከፖለቲካ ግቡና የአመራር ሥርዓቱ ጋር ወደ መቃብሩ ሊገባ በመንደርደር ላይ ነው። መሪውና ብልፅግና ፓርቲ አሁን ተመልሰው የኋሊዮሽ በመሄድ፤ ድሉንና አገሪቱን በምጥ ውስጥ አስቀምጠዋታል። መሪውና ፓርቲው የራሳቸውን ዘለዓለማዊ የፖለቲካ ሥልጣን ለማደላደል የተዘጋጁ ይመስላል። በብዙዎቹ ሕይወት እየተገኘ ያለውን ድል፤ ወደ ጎን ገሸሽ እንዲል አድርገውታል። ከምርጫው በፊት ሁሉ የፖለቲካው ሂደት ተሳታፊዎች እንዲስማሙና ትክክለኛ ምርጫ እንዲሆን፤ ሕገ-መንግሥቱ እንዲስተካከልና ተወካዮቹ በትክክል የሚወክሉት እንዲታወቅ ከጣሩትና ከጎተጎቱት እንዱ ነበርኩ። ምርጫው ከተካሄደ በኋላም ምርጫውን ተቀብለው አሁን ዋናውን ጠላት የትግሬዎቹን ነፃ አውጪ ግንባር መከላከልና በዚያ ላይ ማተኮር እንጂ፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ውርጅብኝ አይገባም! በማለት ከቆሙት አንዱ ነበርኩ። የሻጥር መግተልተሉን ካወገዙት አንዱ ነበርኩ። አሁን የተደረገው አንዴ በምህረትና በይቅርታ! ሌላ ጊዜ ደግሞ አገራዊ ምክክሩን አክካታች ለማድረግ በማሰብ! በሚል የቀረበው የፖለቲካ ስሌት ሂደት በጣም አሳዝኖኛል። አልፎ ተርፎ ደግሞ፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዘርፈው የወሰዱት ንብረት እንደሚመለስላቸውና፤ ይሄን የሚቃወም ካለ እርምጃ እንደሚወሰድበት ተዝቷል። ይህ አገሪቷን በምጥ ላይ ማስቀመጥ ነው!
እውነት ግፍና በደል የደረሰባቸው የአፋርና የአማራ ወገኖቻችን፤ በቁስላቸው ላይ ስንጥር መሰንቀር አይሆንም ወይ! ወይንስ እንጃባታችሁ! የፈለጋችሁትን በሉ፤ እኔ የፈለግሁትን አደርጋለሁ ባይ እብሪት ነው! ግራ ያጋባኝ፤ ስብሃት ነጋን ፈትቶ ደብረ ጽዮንን እፈልጋለሁ ማለት! ዋና ዋና የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎችን ፈትቶ ጌታቸው ረዳን ለማሰር መሯሯጥ! ትርጉሙ ምንድን ነው? እስኪ የተፈቱትን እና ወንጀላቸውን እናነፃጽር፤
ስብሐት ነጋ፣ ቅዱሳን ነጋ፣ አባይ ወልዱ፣ አባዲ ዘሙ፣ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ ኪሮስ ነጋ – እኒህ ሁሉ ጌታቸው ረዳ፣ ጻድቃንና ደብረ ጺዮን በተከሰሱበት ወንጀል ነው የተከሰሱት። በጉልበት በሕዝቡ ተመርጦ በኃላፊነት ቦታ የተቀመጠውን ፓርቲና አስተዳደር አሻፈረኝ ብለው፤ ያመጹ፣ እርምጃ የወሰዱ ናቸው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በመነሻው ካረዳቸው የሠራዊቱ አባላትና በትግራይ የሚኖሩ አማራዎች ባለፈ፤ ወረራ ገብቶ በአፋርና በአማራ ክልሎች ካደረሰው ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋና ወረራዉን ለመመከት ሠራዊቱ፣ የክልል ኃይሎችና የአማራ ፋኖ የገበሩት ሕይወትና የንብረት ውድመት ለምንድን ነው! መልሶ ይሄን አሸባሪ ቡድን በትግራይ ላይ ለመጫን! ከተከዜ ወዲህ አንደርስባችሁም ብሎ ለመቀመጥ! እነሱኮ፤ ከተከዜ ወዲህ አትድረሱብን! ብለው አይደለም የዘመቱት! ወሎን አልፈው ሸዋ ገብተው ነበር! ታዲያ ተከዜ ወሰን የሚሆነው ለምንድን ነው! ወዴት እየሄድን ነው!
እግረ መንገዴን የጀዋርንና በሱ መዝገብ የተከሰሱ ሁሉ መፈታታቸውን አብሬ አነበብኩ! ይገርማል! መልዕክቱ፤ በኢትዮጵያ፤ ወንጀል ሠርተህ ነፃ ትሆናለህ ከሆነ፤ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ተቀበሏት። በኔ እምነት፤ እኒህ ሰዎች ከሠሩት ጥፋት የከፋ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ወንጀል የለም! ታዲያ እነሱ ነፃ ከሆኑ፤ ማንን ወንጀለኛ ብሎ ማቅረብና መቅጣት ይቻላል! ለምን በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ያሉትና ከነዚህ አረመኔዎች የቀለለ ወንጀል የሠሩ በሙሉ በነፃ አይለቀቁም! ከነሱ የበለጠ ጤናቸው አስጊ የሆነባቸው እስረኞች የሉም! ከነሱ የበለተ የተሻሉ ክሳቸው ሊታጠፍላቸው የሚገባ እስረኞች የሉም! ማከያና ሚዛን ማስተካከያ እንዲሆን ደግሞ፤ “ኃይልን በመጠቀም መንግሥትን ለመቆጣጠር ሙከራ በማድረግ” የተከሰሱት እስክንድርና በእርሱ መዝገብ የተካተቱት በሙሉ መፈታታቸውንም አነበብኩ። ክስና ፍትኅ ማለት እንዲህ ከሆነ ማላገጥ ትርጉሙን ተነጥቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ያጠፋ እንዲቀጣ፣ የበደለ እንዲክስ የሚያደርግ ሁሉን አቀፍ ፍትሕ በሽግግር እና በተሃድሶ ፍትሕ ዕይታ፣ አገራዊ ባህሎቻችን እና እሴቶቻችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እናሰፍናለን።” ብለዋል። በርግጥ ይሄ የሚደረገው በዋናዎቹ ወንጀለኞች ነው? ወይንስ በአመለካከታቸው ከማንም የማይወግኑ ሀቀኛ ሰዎች ነው? በነገራችን ላይ ሰላም የሚመጣው፤ ያጠፋውን ሁሉ ምህረት በመሥጠት ሳይሆን፤ አጥፊ ተጠያቂ የሚሆንበት ሥርዓት ሲኖር ነው። ይሄን እያየሁ አይደለም! በዚሁ ሂሳብ፤ “ኢትዮጵያ ለዘላቂ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፤ የትኛውንም መሥዋዕትነት ትከፍላለች” በማለት የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስፍረዋል። እኒህ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መሪዎች የትግራይን ወገናችን ይወክላሉ ብሎ መውሰድ፤ በትግራይ ወገናችን ላይ መቀለድ ነው። ካደረሱበት ግፍና በደል በላይ አሁንም በነሱ ላይ ለመጫን መጣሩ ይዘገንናል።
ውጪሰው ኢትዮጵያዊያን በአንድነት አገራችንን በፖለቲካ ዲብሎማሲው ለመታደግ የተነሳነው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መቃብር እንዲገባ እንጂ፤ ተመልሶ የሚያንሰራራበትን መንገድ ለመክፈት አይደለም። በአገር ቤት፤ ትንሽና ትልቁ የተነሳውና የዘመተው፤ ደሙን፣ ንብረቱንና ጌዜውን ለአገሩ የሠጠው፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከሥር መሠረቱ ተመንድጎ እንዲነቀል እንጂ፤ ተመልሶ እንዲያንሰራራ አይደለም። እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ! ብለዋል ቀደምቶቻችን፤ እንደ ትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ያለውን ትክክለኛ ስምና ተግባር ሲገልጡ! የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን ታሪክ እናውቃለን። ምህረት፣ ድርድር፣ ሽምግልና በዚህ ድርጅት ትርጉማቸው ግልጥ ነው። ለአሁን እውነታ የሚጥቅማቸው እስከሆነ ድረስ፤ ውሽትና ክህደት ይላበሳሉ። ይሄንን መሪያችን እና ድርጅታቸው አያውቁም ብሎ የሚከራከር የለም። ታዲያ ስሌቱ ምንድን ነው! ይህ ነው ወዴት እየሄድን ነው? ያሰኘኝ።
ይካሄዳል የሚባለው አገራዊ ምክክርን በተመለከተ፤ በመጀመሪያ ዙሪያውን እንቃኝ። ብልፅግና አቸንፎ የበላይነቱን ይዟል። ምርጫው ሕጋዊና ትክክለኛ ተብሎለታል። የሚያሰጋው ወይንም የሚያስፈራው ምንም ነገር የለም። ስለዚህ፤ አገራዊ ምክክሩ ሥልጣኑን የሚመለከት ሳይሆን፤ በምን መንገድ ትደግፉኛላችሁ? የሚል ጣይቄ ለማቅረብ ነው። እውነት አገራዊ ምክክሩ የሚያስፈልገው፤ አገሪቱን ወደፊት እንዴት እንውሰዳት? ይሄን በሚመለከት የሥልጣኑን ጉዳይ እንዴት እንጋራው? ሕገ-መንግሥቱን እንዴት ቀይረን አገራዊ ሕገ-መንግሥት እናዘጋጅ? አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ ኖሮን፣ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን በመላ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነታችን የመኖር፣ ሀብት የማፍራትና በኅብረተሰቡ ማናቸውም መስተጋብር ሙሉ ተሳትፎ የምናደርግበት ሥርዓት እናብጅ? የሚል አይደለም። ይሄ ያሰጋዋል።
በዚህ አገራዊ ምክክር አቸናፊ የሆኑት የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና አደራዳሪና አስፈራሪ የሆነው አሜሪካ ናቸው። የተደቆሱት ደግሞ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም የአፋርና የአማራ ወገናችን ናቸው። ባንድ በኩል በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ወረራ ተዘርዝሮ የማያልቅ በደልና ለመግለጥ የሚሰቀጥጥ አረመኔ ግፍ ተደርጎባቸዋል። ቀጥሎ ደግሞ ጠላታቸው ድል ሊሆን ሲቃረብ፤ መሪው አቁሙ አለበለዚያ እኔው እንደነሱው እወርድባችኋለሁ አላቸው። ወዴት እየሄድን ነው? ይሄ የማን መንግሥት ነው!