>

ይድረስ ለሰላማዊ ታጋይ ለአቶ እስክንድር ነጋ (ከኒቆዲሞስ)

ይድረስ ለሰላማዊ ታጋይ ለአቶ እስክንድር ነጋ

ከኒቆዲሞስ


ሰላምን እሻ ተከተላትም…

ሰላም ማለት ፀጥታ፣ ዕረፍት፣ እርጋታ፣ እርካታ ማለት ሲሆን የእርስ በእርስ ስምምነት በአንድነት አብሮ መኖር መቻልና የዕረፍት ስሜት እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ያስረዳል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “ሰላምን እሻት ተከተላትም” ብሎ ከመናገሩ አስቀድሞ የመጽሐፉን ክፍል ወደ ኋላ መለስ ብለን የተነሳንበትን ኃይለ ቃል ሙሉ አሳቡን ለመረዳት ስንመለከተው እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፡፡

‘‘… ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል ከንፈሮችህም ሸንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ፤ መልካንም አድርግ፤ ሰላምን ሻት ተከተላትም፡፡” ይላል፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት፤ “ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው?’’ ብሏል፡፡ ከላይ እንዳየነው ሕይወትን ለማግኘት የሚሻ በጎ ዘመንንም ለማየት የሚፈልግ ጥበብን (ማስተዋልን) ገንዘብ ያደረገ ሰው ነው፡፡ በመሆኑም ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የሚሻ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት ስንመለከትም ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይመክራል፤

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንዳለው ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የምንሻ ሁሉ ሰላምን መሻት ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም ሰላምን መሻት ብቻ ሳይሆን መከተል ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም መሻት ብቻውን ዋጋ ሊኖረው ስለማይችል፡፡ መሻታችን ወደ ማግኘት የሚደርሰው የምንሻውን ነገር ለማግኘት ወደ መገኛው መጓዝና መቅረብ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰላምን እሻት ካለ በኋላ ተከተላትም በማለት በሰላም መንገድ መጓዝ፣ የሰላም ወሬ ማውራት፣ ለሰላም የሚስማማ ሥራ መሥራት የራሳችን ሰላም መጠበቅና የሌላውንም ሰላም አለማደፍረስ ማለት እንደሆነ የሚነግረን፡፡

ይህን እውነታ ይዘን አቶ እስክንድር እና እርሳቸው በሊቀመንበርነት የሚመሩት የባልደራስ ፓርቲ ከሰሞኑን ባወጡት መግለጫ፤ ሺሕዎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ያለቁበትና ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት ጦርነት መቆም የለበትም፤ መቀጠል አለበት የሚል መግለጫ አውጥተዋል፡፡ አቶ እስክንድር ነጋ ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ሰላማዊ ታጋይ ነኝ ሲሉና በእጄ ያለው ብዕር ብቻ ነው በሚል የታወቁ ሰላማዊ የፖለቲካ ታጋይ እንደሆኑ ነበር የምናውቃቸው፡፡ ስለሆነም አቶ እስክንድር ነጋ ለጊዜውም ቢሆን ከፖለቲካ ተሳትፎ አረፍ ብለው ከሃይማኖት አባቶች ጋር ቀርበው የምክር እገዛ ቢያገኙ መልካም ነው፡፡ በምንም ዓይነት መንገድ የወንድማማቾች እልቂት መቀጠል አለበት ብሎ፣ ሰላምን የሚቃረን መግለጫ ማውጣት ከሃይማኖትም ከሞራል ውጪ የሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡

 

መቼም ሰላም ለሁሉ ነገር አስፈላጊና ሁሉን ለማድረግ የምንችልበት የመልካም ነገር ሁሉ በር ነው፡፡ ሰላምን መፈለግ ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንንም ለማየት ያስችላል፡፡ በዓይነቱ ሰላምን በሁለት መልኩ እናየዋለን፡፡ እሱም የውስጥ ሰላምና የውጭ ሰላም ወይም ውስጣዊ ሰላምና ውጫዊ ሰላም ብለን እንመድበዋለን፡፡

የሰው ልጅ ለመኖር ውስጣዊ ሰላምም ሆነ ውጫዊ ሰላም ያስፈልጉታል፡፡ ውስጣዊ ሰላም የምንለው አንድ ሰው ከፍርሃት፣ ከጭንቀት፣ ከመረበሽ፣ ከሥጋትና… ወዘተ ነጻ ሆኖ መኖር ሲችል ውስጣዊ ሰላም አለው ይባላል፡፡ ይህም የውስጥን ሰላም ከሚያደፈርሱ፣ አእምሮን ከሚረብሹ፣ ልብን ከሚያቆስሉ፣ የጸጸት እሮሮን ከሚያስከትሉ ነገሮች ስንርቅና ለአእምሮ የሚመች ሥራ ስንሠራ ውስጣችን ሰላም ይሆናል፡፡

ውጫዊ ሰላም የምንለው ደግሞ፡- ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት፣ ከሀገራት ጋር ተስማምተንና ተግባብተን ተቻችለንና ተረዳድተን በፍቅር ተሳስረን መኖር ነው፡፡ በመሆኑም ሰላም ከጥል፣ ከመለያየት፣ ከመጠላላት፣ ከመገፋፋት፣ ከመነቃቀፍ ተቆጥበን የጠብንና የጦርነትን ወሬ ባለመስማትና በስምምነት ተግባብቶ በመኖር የሚገለጥ ነው፡፡  ስለዚህ ሰላም ለሁሉ እንደሚያስፈልገው ካወቅን የሰላም መገኛ ማን እንደሆነና ሰላም ከየት እንደሚገኝ ማወቅ ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡

የሰላም መገኛ

ሰላም የሚገኘው የሰላም ባለቤት ከሆነው ከልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጠው እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር ይገኛል፡፡ እርሱ የሰላም አምላክ ነውና (ሮሜ. 15፥33)፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ ተብሏል፡፡ “ሕፃን ተወዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ. 9፥6) እንዲል፡፡

ስለሆነም አቶ እስክንድር ነጋ ምክሬ የሚያስደስታቸው ከሆነ ልበ አምላክ፣ ንጉሥ ዳዊት እንዳለው ‘‘ሰላምን እሻት ተከተላትም’’ የሚለውን መንፈሳዊ ምክር ቢከተሉ መልካም መሆኑን ወንድማዊ ምክሬን ልለግሳቸው እወዳለኹ፡፡ 

ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለምድራችን!

Filed in: Amharic