>

'እስክንድር 'ይጠሙን' ለምትሉ ቅን አሳቢ መካሪዎች ሁሉ...!?!" (ጌጥዬ ያለው)

እስክንድር ‘ይጠሙን’ ለምትሉ ቅን አሳቢ መካሪዎች ሁሉ…!?!”

ጌጥዬ ያለው

እስክንድር ነጋ ከእስር ቤት ከወጣ  በኋላ ‘አረፍ ብሎ የሚያንሰላስልበት የጥሞና ጊዜ ያስፈልገዋል’ የሚል ከቅን ልቦና የመነጨ ምክር ለእስክንድር አስተሳሰብ በጎ ምልከታ ካላችሁ ምሁራን እየሰማሁ ነው። ምክሩ  ክፋት የለውም። ይህንን የምፅፈውም እናተን ለመሞገት አይደለም። ይልቁንም ስለ እስኬው ያላወቃችኋቸውን (ምናልባት) 2 ሃሳቦች ልጨምርላችሁ ነው፦
1. እስር ቤት በነበረበት ጊዜ ስለ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በቂ መረጃ ነበረው። ለዚህ ሌላ ማረጋገጫ ሳያስፈልግ በፍትሕ መፅሔት የፃፋቸውን፣ ለኢትዮ 360 የላካቸውን ትንታኔዎች ማየቱ በቂ ይመስመኛል። አነሰ ካላችሁ በተለያዩ የፌስቡክ ገፆች የወጡ አጫጭር ፅሁፎቹንም ጨምሩበት። በተረፈ የሰዎቹ ቁጥር ይነስና ይብዛ እንጂ በየቀኑ  ከጠያቂዎቹ ጋር ይገናኛል። በበኩሌ በምሄድባቸው ቀናት ሁሉ ዶሮ ወጥ አልነበረም ይዤ የምሄደው፤ ዜና ሸምድጄ እንጂ።
2. እስኬው በ1  ዓመት  ከመንፈቅ የእስር ቤት ቆይታው ሲያንሰላስል ነው  የከረመው። እንዳውም ታላቁ የጥሞና ጊዜው የእስር  ቤት ቆይታው ነበር።
ደግሞም  እስር ቤት ሆኖ የፓርቲው መሪ ነበር። የወረቀት ላይ ብቻ  ፕሬዚደንትም አልነበረም። በየ ድርጅታዊ ውሳኔዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳትፎ ነበረው። ባለፈው ምርጫ ዕጩ  ተወዳዳሪ ነበር።
ስለዚህ አሁን የሚሠራበት እንጂ የሚያቅድበት ጊዜ አይመስለኝም ። እስክንድር  ራሳቸውን በድሎት ከባቢ (Comfort zone) አጥረው  እንደሚታገሉ ፖለቲከኞችም አይደለም። ሁልጊዜም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ይታገላል። ይህንን ደግሞ የወህኒ በር ተከርችሞበት በመታገል አሳይቷል።
Filed in: Amharic