የከተራ በዓል ታሪካዊ አጀማመር.. !!!
ጴጥሮስ አሸናፊ
በየዓመቱ ጥር 10 ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተርና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ውኃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው፡፡
በየሰበካው ቦታ ተለይቶና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ ‹‹ባሕረ ጥምቀት››፣ ‹‹የታቦት ማደርያ›› እየተባለ ይጠራል፡ ባሕር፡- የውኃ መሰብሰቢያ (ምእላደ ማይ፣ የውኃ መከማቻ (ምቋመ ማይ) ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ‹‹የውኃ አገር›› /መካነ ማይ፣ ዓለመ ማይ/ ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በቅዱስ ላልይበላ ዘመነ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር እየተመላለሱ በብሕትውና እና በስብከተ ወንጌል ያገለግሉ የነበሩት ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በአክሱም፣ በመቐለና በመርጡለ ማርያም እየተዘዋወሩ ባሕረ ጥምቀቱን ባርከዋል፡፡ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (1260-1275 ዓ.ም) በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት (1203-1204 ዓ.ም) አሳሳቢነት የተጀመረው ሥርዐተ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዐዋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ታቦታቱም በሕዝብ ጥበቃና ክብካቤ ተደርጎላቸው በየጥምቀተ ባሕሩ እንዲያድሩ ወስነዋል፡፡ የበዓሉ አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋና አድማሱ ብሔራዊነትን እየያዘ መጣ፡፡ ከዐፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በ15ኛው ክ/ዘመን በደገኛው ኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1426-1460 ዓ.ም) አማካኝነት ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ፣ አገሩን በኪደተ እግር ይባርኩም ዘንድ በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ በዐዋጅ ወሰኑ፡፡ ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1486-1500) ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ከአወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ ።/ሐመር ጥር/የካቲት 1998 ዓ.ም/ ታቦታት ከአንድ በላይ ሆነው ወደ ከተራው ስለሚሄዱ እግዚአብሔር አምላክ ለነብዩ ሙሴ “የታቦት መኖር ከእናንተ ጋር የመኖሬ ምልክት ነው” ዘፀ 25÷1 እንዳለው ታቦተ ሕጉን ተሸክመው ዮርዳኖስን እንደ ተሻገሩት ካህናተ ኦሪት፤ ካህናቱ የማይለወጠውን ታቦተ ሕጉን በራሳቸው ተሸክመው የብሉዩን ሥርዓት ከሐዲስ ኪዳን ጋር አንድ አድርገው የሐዲስ ኪዳን መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስን እያሰቡ፤ ካህናተ ሐዲስም ወደ ከተራ (ዮርዳኖስ) ይጓዛሉ፡፡ ሊቃውንቱም እንዲሁ ለበዓሉ የሚስማማውን ቃለ እግዚአብሔር እያደረሱ ያድራሉ፡፡
የከተራ ዕለት ጥር 10 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሄደበትን ለማዘከር ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ኃዳፌ ነፍስ ለጻድቃን የሚለውን ዋዜማ ይቆማሉ፡፡ የዋዜማው ቀለም ከቀኑ በአራት ሰዓት በመላው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ይጀመራል ከዚያም የዋዜማው ሥርዐት ቅዱስ ተብሎ እስከ ሰላም ያለው ቀለም ይደርሳል፡፡ በዕለቱም ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ ታቦተ ሕጉን የሚያነሡት ሰሞነኛ ካህን ከምግበ ሥጋ ተከልክለው ለዕለቱ የሚገባውን ጸሎት ያደርሳሉ፡፡
በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ ታቦተ ሕጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅና በብር መጎናጸፊያ እየተሸፈኑ በተለያየ ኅብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመጾር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት /ምጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በዐጸደ ቤተ ክርስቲንና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ‘’ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ …’’ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡
ታቦቱ ከመንበረ ክብሩ ሲነሱ ‹‹ዮም ፍስሀ ኮነ›› ተብሎ ከተጸነጸለ በኋላ ታቦቱ ወጥቶ ወረደ ወልድ እምሰማያት ውስተ ምጥማቃት የሚለው ሰላም በሊቃውንቱ ይዘመራል፣ ይጸነጸላል፣ ይመላለሳል፡፡ የወርቅ ካባና ላንቃ የለበሱ ቀሳውስት፣ መነኮሳት ጥላ የያዙት ከታቦቱ ጎን መስቀልና ጽና የያዙት ከታቦቱ ፊት ይሄዳሉ፡፡ እንደ ቀሳውስቱ ተመሳሳይ ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ዲያቆናት ጥላ፣ መስቀልና ቃጭል ይዘው እያቃጨሉ ከቀሳውስቱ ፊት በመሆን ያጅቧቸዋል፡፡ ከነዚህም ሌላ ካባ፣ ላንቃ ጥንግ ድርብ የለበሱ መዘምራን የብር፣ የነሐስ መቋሚያና ጸናጽል ይዘው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለውን አመላለስ እያሸበሸቡ ዲያቆናቱን ቀድመው ይሄዳሉ፡፡
የደብር አለቆችና አበው ካህናት ታቦቱን ተከትለው ይጓዛሉ፡፡ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎችም በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አልባሳት ተውበው ትርዒት እያሳዩ “ወረደ ወልድ፣ እግዚኡ መርሐ፣ ሆረ ኢየሱስ” እና ሌሎችንም የአማርኛ መዝሙራትን እየዘመሩ፣ እናቶች “ነይ ነይ እምዬ ማርያም” እያሉ ሌሎችም ምስጋናዎችም እየቀረቡ ጉዞ በዝግታ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሆናል፡፡
የከተራ በዓል ማክበሪያ ቦታ እንደደረሱ ታቦታቱ በድንኳኑ አጠገብ ቆመው ‹‹ወረደ ወልድ›› የሚለው ሰላም ተመርቶ በአግባቡ ከተለዘበ በኋላ ጸሎት ተደርጎ የዕለቱ ትምህርተ ወንጌልና ዝማሬ ከቀረበ በኋላ ውዳሴ ማርያም፣ መልክዐ ኢየሱስ ተደግሞ ታቦታ ሕጉ ወደ ተዘጋጀላቸው ድንኳን ይገባሉ /ሠርግው፤ 1981፣ 9/፡፡ በሁለተኛ የአገልግሎት ክፍል ካህናቱ ስብሐተ እግዚአብሔር ሲያደርሱ ያድራሉ፡፡ በመንፈቀ ሌሊትም ሥርዐተ ቅዳሴው ተጀምሮ ከሌሊቱ በ9፡00 ሠርሆተ ሕዝብ ይሆናል፡፡ በነጋታው የሥርዐተ ጥምቀቱ መርሐ ግብር ይቀጥላል፡፡
የከተራ በዓል ምሳሌያት
በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ የታቦታቱ ወደ ወንዝ መውረድና የባሕረ ጥምቀቱ መዘጋጀት ሃይማኖታዊ ታሪክና ምሳሌ አለው፡፡የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብሮ መጓዝና ወደ ወንዝ መወረድ የተጀመረው በአሮን ልጅ በአልዓዛር ጊዜ ነው፡፡ ኢያሱ በሙሴ እግር ተተክቶ ሕዝበ እስራኤልን እየመራ ከዮርዳኖስ ወንዝ ሲደርስ ባሕሩ ከሁለት ይከፈልና ወራጁም ይቆም/ይከተር/ ነበር፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ወደ ምድረ ርስት ለመግባት የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሻገሩ፡- ድንኳን ጥለው የቃል ኪዳኑን ታቦት በድንኳን ውስጥ አድርገው ሌዋውያኑ በዙሪያው፣ ካህናቱ ደግሞ በውስጥ ኾነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ አድረው በማለዳ ተሻግረዋል /ኢያሱ 3÷8-9/፡፡ ካህናቱ የቃል ኪዳኑን ታቦት አክብረው የወንዙን ዳርቻ በረገጡት ጊዜ እንደ ክረምት ማዕበል ይወርድ የነበረው ውኃ ግራና ቀኝ ተከፍሎ እንደ ግድግዳ ወደ ላይ ቆሟል፡፡ ሕዝቡ ተሻግሮ እስከሚያበቃ ታቦተ ጽዮንን ያከበሩት ካህናት ከወንዙ መሀል ይቆሙ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ‹‹ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት›› ይህም ‹‹የካህናት እግሮቻቸው የዮርዳኖስን ውኃ በመርገጣቸው እንደ ጥምቀት ሆናቸው›› በሐዲስ ኪዳነ ጌታችን ለመሠረተው ሥርዐተ ጥምቀት ምሳሌ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የጥምቀትን ዋዜማ ከተራ ብላ የጠራችው ከዚህ በመነሣት ነው፡፡ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ የዮርዳኖስ ወንዝ የላይኛው ሸሽቶ ወደ ላይ ተመልሶ ሽቅብ ፈሷል፡፡ የታቹም ወደ ታች ሸሽቷል፡፡ የላይኛው ፈሳሽ ተቋርጦ እንደ ክምር ተቆልሎ ቀርቷል። ቅዱስ ዳዊት የተመለከተውም ይህንኑ ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ በዘር ይወርድ የነበረው ፍዳ መርገም በክርስቶስ ቤዛነት ተቋርጦ ፤ የታቹም ፈጽሞ መድረቁ ኃጢአተ አዳም የመጥፋቱ ምሳሌ ነው፡፡ እስራኤል ፈለገ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ኢያሪኮ መሔዳቸው ምእመናን በጥምቀት ከኃጢአት ቍራኝነት ተላቀው እግራቸውን ወደ ልምላሜ ገነት ወደ ዕረፍት መንግሥተ ሰማያት አቅንተው ለመሔዳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ኢያሱ የጌታ፣ እስራኤል የምእመናን፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ ምድረ ርስት የገነት መንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡
ታቦቱን አክብሮ የሚሔደው ካህን የቅዱስ ዮሐንስ፣ታቦቱ የጌታችን፣ ባሕረ ጥምቀቱ የዮርዳኖስ ወንዝ፣ ታቦታቱን አጅበው የሚሔዱትና በዓሉን የሚያከብሩት ምእመናን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ እየመጡ የንስሐ ጥምቀት ሲጠመቁ የነበሩት ሰዎች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸውና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱንና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያጠይቃል፡፡ ‹‹ጥምቀት የሞቱና የትንሣኤው ምሳሌ ነው፡፡ ከኃጥአን ጋር ተቆጥሮ እንዲጠመቅና እንዲሰቀል የተጻፈውን ቃል ንስሐና ጥምቀት የማያስፈልገው ሲሆን ነገር ግን ፍጹም ኃጥእ መስሎ በዮሐንስ እጅ ጥምቀትን ለመፈጸም በማየ ዮርዳኖስ እግር ተጠመቀ፡፡›› /ኪ.ወ.ክ ፤517/፡፡
ጌታችን የተጠመቀበት ወርኀ ጥር በእስራኤላውያን ዘንድ የዝናብ፣ የበረዶ ወራት ነው፡፡ ከወንዝ ዳር ያለ መጠለያ መዋልና ማደር አይቻልም፡፡ በመኾኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር፡፡ በዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖች ዳሶች ይጣላሉ፡፡
በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተለይ በአክሱም የንግሥት ሳባ መዋኛን ‹‹ማይ ሹም›› በጎንደር የዐፄ ፋሲል መዋኛን፣ በላስታ የላሊበላ መዋኛን፣ በሸዋ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ፍርድ መስጫ አደባባይን፣ አርባ አራት ታቦታት የሚያድሩበትን የሸንኮራ ሜዳን “ራቡቴ ወንዝ” በአዲስ አበባ ደግሞ ጃንሆይ ሜዳን /ጃንሜዳን/ ወዘተ ለአብሕርተ ምጥማቃት እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እኒህ ቦታዎች ዛሬም ድረስ ተከብረው ይገኛሉ፡፡እኛ በዚህ ወቅት ታቦት ይዘን፣ ከወንዝ ወርደን፣ ድንኳን ተክለን በማክበራችን ይፈጸማል፡፡
ፈጣሪያችን በዓሉን የበረክት የረድኤት ያድርግልን፡፡