>

ብልጽግዎችና ¨ዘፋኞች¨  ሆይ ! ሰንደቅ ዓላማችንን አትፈታተኑ! (ፊልጶስ)

ብልጽግዎችና ¨ዘፋኞች¨ ሆይሰንደቅ ዓላማችንን አትፈታተኑ!

 

ፊልጶስ


 የአንድን አገር ህዝብ በውስጡ  የተለያየ ሃይማኖት፣ቋንቋና ነገድ ቢኖርም፤ በአንድነት የሚያቆመውና እንደ አንድ ጥላ ሆኖ ከሚያሰባሰበው  አንዱ  መለያ አርማው ወይም ምልክቱ ሰንደቅ ዓላማ ነው። ሰንደቅ ዓላማ ክቡር ነው። የያንዳንዱ አገር ዜጋ ለሰንደቅ ዓላማው ክብር ይሞታል! ይገላለ! ይጋደላል። ለሰንደቅ ዓላማቸው የተሰው ሁሉ በክብር ይታውሳሉ፤ በመሰዋ’ት ላይ ላሉም የክብር ሜዳሊያ ይሸለማሉ።

ታዲያ እኩይ ገዥዎች  የአንድን  አገር ህዝብ ለያይተው ማጥቃትና አንድነቱን መናድ፣ ብሎም ክብሩን ማዋረድ ሲፈልጉ ከሚወስዱትርምጃዎች ውስጥ አንዱ፤ ለአንድነት ምልክትና ዓርማ ለህዝብ የጋራ እሴት  ለሆነው የፈጠራ ታሪክ በመፍጠር፣  ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጭ ትርክት- መተረክ፣ ማጥቆር፣ ማበላሸት፣ መቀየር፣ ከቻሉም የህዝቡን የልብ ትርታ እይተከተሉ መቀየርና ማጥፋት ነው።

ይኽን በደንብ የተጠቀምበት ቡድን ቢኖር ትላንት ወያኔ፣ ዛሬ ደግሞ ኦነጋዊ ብልጽግና ኦሮማማ በተለይም  በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ነው።

ሚሊዎኖች መሰዋ’’ት የከፈሉለት፣ አጥታቸውን ከስክሰው ደማቸውን ያፈሰሱለት፤ ሰንደቅ ዓላማችን አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ቀለማት ነው።

መቼም ትውልድን ማደናገር የገዥዎቻችን ተክኖ ነውና የሚታወቅ ሃቅ ቢሆንም  ሰንደቅ ዓላማችን ፤

 አረጓዴው ፤ ልምላሜ፣ ተስፋና  ሃብት 

ብጫው፤ ሃይማኖትና ባህል

ቀዩ፡ ፍቅርር፣ መስዋእትነትና ጀግንነት ነው።

ታዲያ የጥንቱን እንተወውና  በቅርቡ እንኳን፤

 

  • አረንጓዴ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማ አይደለም ወይ አደዋ ላይ የተውለበለበውና መሰዋትነት የተክፈለለት? በዚህ አንጸባራቂ የአፍሪካዊን ድል የትኛው  ነገድ ወይስ ጎሳ ነው ለአረንጓዴ ብጫና ቀይ  መሰዋአት ያልሆነው?
  • በአምስቱ ዓመቱ ጦርነት ጅግኖች በጫካ፣ በዱር-በገደሉ ይዘውት የተከራተቱና አናስደፍርም ብለው የተዋደክቁለት ባለኮከቡ ወይስ በለ አምባሻው ነወ?
  • በሱማሌ ጦርነት ሰንደቅ ዓላማቸውን አቅፈው በርሃው የበላቸው ኢትያጵያኖች ለአረንጓዴ ብጫና ቀይ  ዓርማቸው እንጂ ለየትኛው ነው? 
  • ሌላው ቢቀር የዛሬውን አያድርገውና ኤሪትራዊ ወገኖቻችን ”ኢትዮጵያ ወይና ሞት”  ይሉ የነበረ አረንጓዴ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማቸውን እያውለበለቡ ኦኮ ነበር። ስንቶቹ የኤሪትራ ወገኖቻችንስ ለአረንጓዴ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማ መሰዋት ሆነዋል?

 

ወያኔ ከኦነጋዊ ጋር ሆኖ  ህዝብንና አገርን አፍርሶ  ማንነትን ለማጥፋትና ህዝብን-ከህዝብ ለማቃቃር ከቀበሩት ፈንጅ እንዱ  ለአረንጓዴ ብጫና ቀይ ሰንደቅ ዓላማችን፤ ተራና መናኛ የሆነ ታሪክ በመፍጠር ባለ አምባሻውን  በህዝብ ላይ መጫናቸው ነው።

ለዓለም  ጥቁር ህዝቦች ዓርማ፣ ፣ በጭቆና ውስጥ ላሉት ደግሞ  የነጻንተና የአንድነት ምልክት የሆነነውን አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማችን ለማጥፋትወያኔዎችና ኦሮማማዎች  የሄዱበት ርቀት ፤ እንኳን ኢትዮጵያዊንን ታሪካችን የሚውያቅ ሁሉ እንቅልፍ የሚነሳ ነው። የሚሳዝነው ይህ ዓይነት ፍጹም እኩይነት ከኢትዮጵያ አብራክ በውጡ የእፍኝት ልጆቿ መፈጸሙ አንሶ፤ አሁንም ስለኢትዮጵያ እንድነትና ክብር፡ ስለጅግኖቿና ስለ ህዝብ አንድነት እንዘፍናለን፡ እንሰብካለን የሚሉ ዜጎቿም  አረንጓዴ ብጫና ቀይ ሰንደቃችን ወደ ጎን ብለው፤ ባለ አምባሸውን ይዘው ሲውራጩ ማየቱ ነው።

የገዥዎች ይሉንታ ቢስነትን የሚያሳየውና ህዝብም ልብ ሊለው የሚገባ ነገር ቢኖር ፤ ወያኔ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የፈጸመውን ፤ ተረኛው ኦሮማማም መፈጽሙ ነው።

ወያኔ በባድሜ ጦርነት ወቅት ጦሩም ሆነ ሌላው ዘማች ይጠቀም የነበረው  አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማችን ነበር። ድል አደረግን ካሉ በኋላም ባድሜ ላይ ያውለበለቡት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ነበር። ከድል በኋላ ግን ወደ አምባሻቸው ተመልሱ፤ ጭራሽ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማ  ይዞ የተገኘ በህገ- እንደሚቀጣም  አዋጅ አስነገሩ። በተመሳሳይ ሁኔታ ኦነጋዊ ብልጽግናም   በተለይም ባለፈው አንድ ዓመት ከወያኔ ጋር በተደረገው ጦርነት አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማ ከባላባሻው ጋር ጎን ለጎን   ሲጠቀም ቆይቶ፤  ዛሬ ገና ባልይተጠናቀቀ ጦርነት ፣ ግን በግብዝነት ድል ያደረግ ሲመስለው፤ ልክ እንደ ወያኔ ”አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማ ይዞ የተገኘ ይቀጣል” ሲል   አወጀልን። ማወጅ ብቻ አይደለም ካዲሪዎቹንና ሸኔዎቹን ልኮ በመርካቶ ነጋዴ ሱቅ እየዞረ ” የትኛው ሰንደቅ ዓላማ ነው ያላችሁ?” እያለ ሲፈትሽ ማየት፤ ንቀት ብቻ ሳይሆን፤ ”ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ”  የሚለውን ህዝብ  መፈታተን ነው።

አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማችን በኢትዮጵያን ልብ ውስጥ ያለና የሚኖር መሆኑን፣ የጡት አባታችሁ ወያኔ ሊነግራችሁ በተገባ ነበር። ሰንደቅ ዓልማችን ለማጥፋት ወያኔ ያልፈነቀለው ድንጋይ፣ ያልቆፈረው ጉዳጓድ የለም፤ ግን አልተሳካላትም፣ እናንተም እንደማይሰካላችሁ ከወዲሁ እወቁት።

ጀግኖቹ ወያኔን የተፋለሙት አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማቸውን እይውለበልቡ መሆኑንና  የ’ናንተንም የአገዛዝ ዘመን እንዳራዘምላችሁ ያደረገ ወያኔ ሰፍቶ የሰጥችሁ ባላባሻው እንዳልሆነ ልባችሁ ያውቃል። እናም በአረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማችን ምክንያት እየፈለጋችሁ አተፈታተኑን።

የኢትዮጵያ ህዝብም ልብ ሊለው የሚገባው ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ካመነ፤ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ለሃይማኖት ቀን  ወይም ለሰላማዊ ሰልፍ ወይም በልብሳችን ላይ የምንለጥፈው ብቻ ሳይሆን ፤ የነጻነታችን ፣ የእንድንታችን፣ የክብራችን፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያዊነት ማንነትቻን፣ የሚልዮኖች እያቶቻችንና አባቶቻችን ደምና አጥንት የታተመበት እንጂ፤ በተረኛ ገዥዋቻችን ስንታተዝና ሲኖሩ፣ የምንሰቅለውና የምናወርደው፤  የምንይዘውና የምንጥለው አይደልም። ዛሬም ሆነ ነገ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማችን አክብረን ማስከበር ኢትዮጵያዊ ነኝ ከሚል ዜጋ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደልም። 

በዚህ አጋጣሚ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አንድንትም ሆን ክብር፤ ስለ ጀግና ልጆቿ መሰዋትነት የምትዘፍኑ ዘፋኞች በሁለት ቢላዋ ለመቁረጥ አትሞክሩ። ለዘፈናችሁ  በምትጠቀሙበት ”ክሊፕ” ላይ፤ እስቲ አስቡት፤ ስለ አደዋ እየዘፈናችሁ፣  ስለ አምስት ዓመቱ  ጀግኖቻችን እየተቀኛችሁ፤ መደርተኝነትንና ጎሰኝነትን እያወገዛችሁ ፤ ባለ አምባሻውን ስታውለበልቡ ህሊናችውስ ምን ይላችኋል? 

 ”የጥበበ ሰዎች ነን” የምትሉ ጥበብ ክቡር ነውና፤ ”በወያኔ ዘመን ምን አድርገን ነበር? አሁንስ በተረኞቹ ዘምን ምን እያደረግንና ምን ማድረግ አለብን ? ” ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። የጥበብ ሰው ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ማማ ወርዶ ፤ ለጎሰኝነትና ለመንደርተኝነት ሲያደር ጥበብን ያረክሳል። መጸሃፍ እንደሚለው፤”— ነፍአም ትጸየፈዋለች—”።  

ነገ -ከነገወዲያ ኢትዮጵያ ወደ ክብሯ ትመለሳለች፡ ያኔ እውነተኛ ሰንዳቅ ዓልማዋን አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  በክብር  በመላው ኢትዮጵያ ታውለበልባለች።  ታዲያ ያኔ ” ለእንጀራ ብለነው?፣ ተርኞች አስገድደውን ነው? ወ፡ዘ፡ተ፡   ከታሪክ ተጠያቂነትና ከጸጸት  አያድናችሁም።

ትላንት በወያኔ ዘመንም ሆነ አሁንም በተረኞች አገዛዝ ከኢትዮጵያዊነት ማማ ያልወረዱ፤ አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማ  ውጭ፤ ሌላው ሲያልፍም የማይነካቸው፣ የተከበሩና መሰዋአት የከፈሉ፣  እየከፈሉም ያሉ  ዘፋኞችና የጥበብ ሰዎች ዛሬም ሆነ ነገ  በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የክብር ቦታቸውን የሚነፍጋቸው ማንም የለም። በኢትዮጵያዊንም ልብ ሁሌም ይኖራሉ። ከሁሉም በላይ የህሊና ”ረፍት አላቸው።

ስለዚህም ቡክራንውን ለቁራሽ እንጀራ እንደሸጠው እንደ ኢሳው አንሁን።  የሚያልፍ ግዜ፤ የማያልፍ ትዝብትና ታሪክ ይቅር የማይለው ጠባሳ ጥሎ ያልፍልና። አረንጓዴ ብጫና ቀይ  ሰንደቅ ዓላማችን የኢትዮጵያዊነታችን ማንነት ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!

ፊልጶስ E-mail: philiposmw@gmail.com

Filed in: Amharic