>
9:07 pm - Wednesday February 8, 2023

የማለዳ ወግ ...[ነቢዩ ሲራክ]

 አስገራሚው ትዕይንት “በተስፋዋ” የአረብ ምድር በሳውዲ !

* የገቡት ይወጣሉ ፣ የወጡት ተመልሰው ይመጣሉ
* የሳውዲ መንግስት “ህገ ወጦችን” የማጽዳቱ ዘመቻ ቀጥሏል
* ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዜጎች ከሞት ጋር ተፋጠው እየተሰደዱ ነው
* የሳውዲ መንግስት ማስጠንቀቂያና እርምጃ …

የሳውዲ መንግስት የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውንና ህጉ በማይፈቅደው መንገድ የመኖሪያ ፈቃዳቸው ካለው ሙያ ውጭ የሚሰሩ የማናቸውንም ሀገር ዜጎች በመላ ሀገሪቱ ለማጽዳት የተደራጀ ዘመቻ ከተጀመረ ወር ደፍኗል። በየቀኑ በመንግስትና በግል መገናኛ ብዙሃን የሚለቀቁት የማስጠንቀቂያ መረጃዎች ከበድ ከበድ ያሉ ናቸው ።

ዛሬ ማለዳ ” ህገ ወጦችን ጠራርገን እናስዎጣለን ” ያሉትን የሰራተኛ ሚኒስቴር አድል ፈቂን ይዞ የወጣው አረብ ኒውስ ሚኒስትሩ ሃገራቸው ለህገ ወጥ ሰራተኞች ቦታ እንደሌላት በአጽንኦት መጠቆማቸውን ያስረዳል። የሰራተኛ ሚኒስትሩ በማከልም መንግስት ህገ ወጦችን እግር በእግር እየተከታተለ በመያዝ የማስወጣቱን ስራ እንደሚገፋበት ሲያስታውቁ 150 የሚደርሱ ተጨማሪ የሴት ተቆጣጣሪዎች ስልጠና ተሰጥቷቸው ህገ ወጦችን በማጣራቱ ስራ መሰማራታቸውን አስረድተዋል። ተቆጣጣሪዎች ስራቸው ሲከውኑ በተአማኒነት ፣ በሃላፊት ፍትሃዊ በሆነ አግባብ ባለው መንገድና ስርአት መሆን እንደሚገባው ሚኒስትር አድል ፈቂ አሳስበዋል። የሰራተኛ ሚኒስቴር አድል ፈቂ በቤት ሰራተኛ አቀጣጣጠር ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታታ ከ200 የተለያዩ ሃገር ዜጎች ጋር መምከራቸውንና በጠቃሚው ምክክር የተገኙትን መፍትሄ ሃሳቦች በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉ አሳስበዋል።

ዘመቻው …

ወር በደፈነው በዚህ መጠነ ሰፊ ዘመቻ ኢላማዎች ፈርጀ ብዙ በሆነ ምክንያት ሳውዲ ገብተው በህገ ወጥነት የሚኖሩትን ጨምሮ በኮንትራት ቪዛ መጥተው ከአሰሪዎቻቸው የጠፉትን ያጠቃልላል። ዘመቻው ጅዳ ደርሶ በተለያዩ አካባቢዎች በየመኖሪያ ቤቱ አሰሳው ተጠናክሮ መቀጠሉን የሳውዲ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት ነው ። እስካሁን በቀጠለው በዚህ ዘመቻ በኢትዮጵያን ላይ ሲያዙ ማንገላታትም ሆነ የተለየ ጥቃት መስተዋሉን አልሰማሁም። መኖሪያ ፈቃድ ያላቸው ቢያዙም እየተጣራ ተለቀዋል። ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውና ለአሰሪያቸው የጠፉት ግን እየተያዙ ተወስደዋል። ዘመቻው ግን አሁንም ቀጥሏል … በዘመቻው የተያዙት በርካታ ዜጎችን ስልክ እየደወሉ እንደገለጹልኝ ከሆነ ” በፍተሻው ስንያዝ የረባ ልብስ እንኳ አልለበስንም ፣ ለአመታት ያፈራነው ንብረታችን አልሰበሰብንም ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ቢያንስ ሻንጣችን ይዘን የምንገባበትን መንገድ ያዘጋጅልን ” ሲሉ ተደጋጋሚ ምሬታቸውን ገልጸውልኛል !

ወደ ” ተስፋዋ ምድር ” ያላባራው ጉዞ …

ወደ “ተስፋዋ” የአረብ ሃገር ምድር ወደ ሳውዲ የሚደረገው ጉዞ አላቆመምም። የእኛ ደላሎች ከሳውዲ እስከ ሀገር ቤት ትላልቅ ከተሞች፣ ገጠርና የወረዳ ከተሞች በዘለቀ የእዝ ሰንሰለት ተደራጅተው በወገናቸው ስደት ተጠቃሚ ሆነዋልና በማን አለብኝነት ሰውን እያጋዙት ይገኛሉ ። አምና ካቻምናና ዘንድሮ በአሳር በመከራ ሀገር ቤት የገቡት ኢትዮጵያውያን እነሱ ” የተስፋ ምድር ” ወደሚሏት ሳውዲ እየጎረፉ ነው። ባሳለፍነው ወር በተደጋጋሚ የየመን የቀይ ባህር ዳርቻ የቅርብ ርቀት ባህር ከበላቸው ወገኖች ባልተናነሰ በየበርሃው በአሸጋጋሪ ደላሎች ታግተው አሳር መከራቸውን የሚያዩትን ወገኖች የከፋ የስቃይ ስደት ህይዎት ያማል ።

Ye maleda weg by Nebiyu Sirakእነ ሞት አይፈሬዎች የእኛ ዜጎች አሳምረው የሚያውቁትን የሞት ጉዞ ተከትለው ፣ ሞትን ዳግም ለመፋጠጥ ቆርጠው ፣ ከቀያቸው ነቅለው የመጡ ይመስላል። እነሱን በአደጋ አስከብቦ እዚህ ስላደረዳቸው ምክንያት አብዛኞችን ስንጠይቃቸው ጣራ የነካው የኑሮ ውድነት ፣ ድህነት ፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋውን አማረው ይነግሩናል። አንዳንዶች ከተጠቀሰው ምክንያት አዳምረው በሀገር ቤት የፖለቲካው ትኩሳት ሙቀት የመለብለቡ ፍርሃቻን እንደ ምክንያት ያቀርቡታል። ያን ሰሞን ሃገር ቤት ለእረፍት የሄዱ የቤተሰብ አባሎቸንና ወዳጆቸን ሀገር ቤት ስላለው የኑሮ ውድነትና ኑሮ ጠይቄያቸው የእድገት ምጥቀቱን ፣ ገንዘብ ላለው ሀገር ቤት የመመቸቱንና አንገቱን ደፍቶ ልስራ ላለ ስራ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል አጫውተውኛል። ታዲያ ሰው ለምን ይሰደዳል? ለሚለው ጥያቄየ ግን መልሱ ” እሱ ግራ የሚያጋባ ነው! ” የሚል ነው ። እርግጥ ነው ይህ ምላሽ አጥጋቢ ሆኖ አላገኘሁትም … ሀገር ቤቱ እውነታ እድገት ምጥቀቱ ፣ ገንዘብ ላለው ሀገር ቤት የመመቸቱንና አንገቱን ደፍቶ ልስራ ላለ ስራ ሰርቶ መለወጥ እየተቻለ አስከፊውን ስደት የማያውቁትን ቢያጓጓም ከሞት ጋር ተፋጠው ተሰደውና ወደ ሀገር ቤት በዘመቻ ተመልሰው የገቡት እንዴት የመከራ ሰቀቀኑን የአረብ ሀገር ስደት መረጡት? ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል ፣ ለዚህም ሁነኛ የሆነ መልስ ሰጭ አካል አልተገኘም ! ይህ ምላሽ እስኪያገኝ ግን ወደ “ተስፋዋ የአረብ ምድር ” የሚደረገው ስደት ተጠናክሮ ቀጥሏል …
ላለፉት ሶስትና አራት ተከታታይ አመታት የሁለት ሃገራት ውል ባልተደረገበት ፣ ቅድመ ዝግጅት ባልተደረገበት ሁኔታ በኮንትራት ስራ ስም ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ አብዛኛው ሴት እህቶቻችን ወደ ሳውዲ ገብተዋል። ምንም እንኳን የተሳካላቸው በተወሰነ መንገድ እራሳቸውን ረድተው ቤተሰቦቻቸውን እየረዱ ነው። መብት ጥበቃ የጎደለባቸው ፣ ያለተሳካላቸው ከአሰሪዎቻቸው ጠፍተው ህገ ወጥ ነዋሪነቱን ሲቀላቀሉት በአንጻሩ ምንም ማድረግ ያልቻሉት በለየለት ወንጀል ተዘፍቀው ስማችን አክፍተውታል። የቀሩት አሁን ድረስ የገሃነም ኑሮን እየኖሩ ነው። የዚህ ሁሉ ክስተት ምክንያት ህጋዊ ውል በሌለበት ፣ የመብት ጥበቃው ባልተጠናከረበት ሁኔታ የኮንትራት ስራ መጀመሩ መሆኑን ገና ኮንትራት ሊጀመር ነው ሲባል እኔም ሆንኩ ያገነባናል ያልን ባቀረብናቸው ጭብጥ መረጃዎች እንደ ዜጋ ከነ ነባሬ መፍትሄ ሃሳቡ ጥቁመ ነበር ። ያ ሰሚ ሳያገኝ ቀርቶ እዚህ ደርሰናል። ይህ በመሆኑ ትልቅ ስህተት ተሰርቷል ባይ ነኝ።

ዛሬም ” ከስህተቱ ተምረናል ” ብለን እያቀነቀንን ፣ ግን ከስህተቱ ያለመማራችን ጠቋሚ መረጃ እየሰማን ነው ። ከአመት በፊት የተዘጋው የኮንትራት ስራ ሊከፈት ረቂቅ ደንብ ወጥቷል ተብሏል። ያን ሰሞን ኤጀንሲዎች በረቂቁ ዙሪያ ሲመክሩ በዜጎች መብት ማስጠበቅ ዙሪያ ያሉት ነገር ባይሰማም ስለሚያስይዙት ገንዘብ አማረው ሲናገሩ ሰምተናል። በውይይቱ የገንዘቡ ከፍ ማለት “ህገ ወጥ ስደቱን ያባብሰዋል” ያሉት ኤጀንሲዎች ስለየትኞቹ ህገ ወጥ ስደተኞች እንደሚያወሩ ባይገባኝም ብለውናል። ባህር ቆርጠው በየመን እየገቡ ያሉት አብዛኛው ወንድ ወንድሞቻችን የገጠር ልጆች የኮንትራት ስራ ቪዛው ተጠቃሚ አድርጎ መውሰዱና አግባብ ነው አልልም። ያም ሆኖ በየመን ፣ በሱዳንና በዱባይ የጉብኝት ቪዛዎች ሽፋን እየተሰጣቸው አሁን ድረስ ለሚሰደዱትን መላ አልተገኘለትምና ጉዞው አላቆመም ። የኤጀንሲዎች ህገ ወጥ ጉዞን ያበረታታል ለማለት የሰጡት ምክንያት እኒህኞቹን ለመታደግ ከሆነ ደግሞ እንደ ዜጋ ኤጀንሲዎች አዲሱ ረቂቅ ከገንዘብ ማስያዙ በላይ ቀድሞውንም ባላስጠበቁት መብት ላይ መነጋገር እንጅ በየጣለባቸው ግዴታ ላለማሟላት ጉንጭ አልፋ ምክክር ማድረጋቸው አያስደስትም ።

ማጠቃለያ

የኢትዮጵያ መንግስት በአረብ ሃገሩ ስደት ጉዳይ ላይ ከፕሮፖጋንዳ ያለፈ ጥልቅ ጥናት ባላደረገበት ሁኔታ የሚሰራውን ስራ ቆሞ ሊመረምር ግድ ይለዋል ! በሃገር ቤት ወደ አረብ ሃገራት ለመሰደድ የቋመጠው ወገንም ከፊት ለፊቱ ያለውን አደጋ ሊያስተውልና ሊመረምረው ይገባል ! በባህር እና በበርሃው በባዕድ ምድር ደመ ከልብ ሆኖ ከማለፍ በወገን መካከል በሃገር የመጣውን ችሎ ማለፉ ይበጃል ባይ ነኝ ! ባለጊዜ ባለጸጋዎች ደላሎች ሆይ ፣ ላንድ አፍታ ወደ ነፍሳችሁ ተመልሳችሁ በወገኖቻችሁ በተለይል ለአቅመ አዳም በደረሱና ባልደረሱ እህቶችን ላይ ቅቤ እያነጎታችሁ በማማለል እየፈጸማችሁት ያለውን ዘመን የማይሽረው ግፍና በደል ተረጋግታችሁ አስቡት ! ጊዜው ቢያልፍም ፣ በሰራችሁት በደል ጠያቄ እንኳ ቢታጣ ውሎ አድሮ ከማይተዋችሁ የህሊና ጸጸት ለመዳን ስትሉ ከክፉው ምግባራችሁ ራሳችሁን ለመግታት ሞክሩ ! ሌላ ምን እላለሁ !

ቸር ያሰማን !

ነቢዩ ሲራክ
ታህሳስ 8 ቀን 2007 ዓም

Filed in: Amharic