>

ይድረስ፡ ያቶ ደመቀ ኦነጋዊነት ለማይታያችሁ ዓይነ ግንባሮች! (መስፍን አረጋ)

ይድረስ፡ ያቶ ደመቀ ኦነጋዊነት ለማይታያችሁ ዓይነ ግንባሮች!

መስፍን አረጋ


አቶ ደመቀ መኮንን ወሎ የኦሮሞ ነው በሚለው በኦነጋዊው በዐብይ አሕመድ ስብከት ታውሮ ወደ ኦነጋዊነት ተቀይሮ፣ ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ ከራሱ ከዐብይ አሕመድ በላይ ጽንፈኛ ኦነጋዊ ሁኖ፣ የኦነጋውያንን ፀራማራ አጀንዳ ከዐብይ አሕመድ በበለጠ ጽንፈት እያራመደ እንደሆነ፣ ጉዳዩ በይበልጥ ለሚመለከተው ለአማራ ሕዝብ በተለያዩ ጦማሮች ለማሳሰብ የተቻለኝን ሞክሬያለሁ፡፡  የአማራ ሕዝብ እየተመራ ያለው የሕልውናው ቀንደኛ ጠላት በሆነ ኦነጋዊ ነው በማለቴ ደግሞ የተወሰኑ ሰወች መረጃህ ምንድን ነው ሲሉ ጠይቀውኛል፡፡  

ከጠየቁኝ ሰወች ውስጥ አብዛኞቹ ዐብይ አሕመድ ጥቁሩን ነጭ ቢላቸው ምንም ሳያንገራግሩ አወ ነጭ ነው የሚሉ ዓይኔን ግንባር ያርገው ባዮች እንደሆኑ ባውቅም፣ ጥቂቶቹ ግን ቅና አሳቢወች ሊሆኑ ስለሚችሉ ጥያቄውን ማስተናገድ የግድ ነው፡፡  ጥያቄው ግን የመረጃን ምንነት በውል ካለመረዳት የመነጨ (እንደ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ብሽቅ ጥያቄ ባልልም) የዋህ ጥያቄ ነው፡፡  

አብዛኛው ሰው መረጃ ሲባል የሚያስበው በድበቅ የወጣ ንግግር ወይም ቪዲዮ ነው፡፡  ከመረጃወች ሁሉ የሚበልጠው ትልቁ መረጃ ግን በዐይን በብረቱ የሚታይ፣ ማንም ሊክደው የማይችል የተግባር ውጤት ነው፡፡  ያቶ ደመቀ መኮንን የተግባር ውጤት ደግሞ ያለምንም ጥርጥር የሚመሰክረው ግለሰቡ የለየለት ፀራማራ ኦነጋዊ መሆኑን ነው፡፡  የአማራ ሐዝብ መሪ ነኝ እያለ፣ ይህ ሁሉ የኦነግና የወያኔ መርገምት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲወርድበት ዝንብ የሞተ ሳይመስለው ድመጹን አጥፍቶ የተቀመጠው ፀራማራ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ 

ዐብይ አሕመድ የአማራን ሕዝብ ረክዞ ከወያኔ ጋር ካርታ የሚጫወት ቁማርተኛ ሲሆን፣ ጆከሩ ደግሞ ደመቀ መኮንን ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ ስልጣን ላይ ከወጣበት ዕለት ጀምሮ፣ በአማራ ሕዝብና መሪወች ላይ የፈጸማቸውንና ያስፈጸማቸውን ሁሉንም ወንጀሎች፣ አንዳቸውንም ሳይቀር ሊፈጽምና ሊያስፈጽም የቻለው ጆከሩን ደመቀ መኮንንን ስለያዘ ብቻና ብቻ ነው፡፡  ባጭሩ ለመናገር ዐብይ አሕመድ የአማራን ሕዝብ አይንቁ ንቀት ንቋል፡፡  ትልቁን የአማራን ሕዝብ የናቀውን ያህል እጅግ አናሳ ናቸው የሚባሉትን አኝዋኮችን ወይም ኔኡሮችን አልናቀም፡፡  የአማራን ሕዝብ በዚህ ደረጃ ሊንቅ የቻለው ደግሞ የአማራ መሪ ነው የሚባለው ግለሰብ፣ ሲጠራው አቤት፣ ሲልከው ወዴት የሚል አፋሽ አጎንባሹ፣ ንከስ የሚለውን የሚነክስ፣ ላስ የሚለውን የሚልስ ታዛዥ ውሻው እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ርግጠኛ ስለሆነ ነው፡፡    

ዐብይ አሕመድ የደመቀ መኮንንን ሙሉ ድጋፍ ባያገኝ ኖሮ ከዲባቶ አምባቸው ህልፈት በኋላ ጃንደረባወቹን እነ ተመስገን ጡሩነህን በአማራ ክልል ላይ በመሾም ክልሉን የኦነጋውያን መሳቂያና መሳለቂያ ለማድረግ ባልቻለ ነበር፡፡  ዐብይ አሕመድ በደመቀ መኮንን ሙሉ በሙሉ ባይተማመን ኖሮ አማራወች በወለጋና በመተከል ባሰቃቂ ሁኔታ እስኪጨፈጨፉ እየጠበቀ፣ ምንም እንዳልተፈጠረ በመቁጠር በዕለቱ ወይም በማግስቱ እየወጣ ሕንጻ በመመረቅና አበባ በመትከል በአማራ ሕዝብ ቁስል ላይ እንጨት አይሰድም ነበር፡፡  ዐብይ አሕመድ የደመቀን እሽታ ባያገኝ ኖሮ፣ ወያኔና ኦነግ ድሽቃ በታጠቁበት ሰዓት የአማራን ጓንዴ ለመንጠቅ ባልዛተ ነበር፡፡  

ዐብይ አሕመድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከደመቀ መኮንን ጋር ሙሉ ስምምነት ባይኖረው ኖሮ፣ የአማራ ሕዝብ በወያኔ እሳት እየተለበለበ ባለበት ሰዓት፣ በጀርባ በኩል ከወያኔ ጋር ለመደራደር ባልደፈረ ነበር፡፡  አለበለዚያማ አቶ ደመቀ መኮንን እንደ ዐምዱላ (ኮሎኔል) ጎሹ ወልዴ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን በፈቃዱ ለቆ ብአዴንን ከብልጽግና በማስወጣት የዐብይ አሕመድ መንግሥት እንዲንኮታኮት ማድረግ ይችል ነበር፡፡    

እርግጥ ነው፣ ዐምዱላ ጉሹ ወልዴና አቶ ደመቀ መኮንን ሰማይና መሬት ናቸው፣ ዱባና ቅል እየቅል እንዲሉ፡፡  ደመቀ መኮንን፣ በእውቀቱ ብዙም ያልገፋ በዚያ ላይ ደግሞ የሚያውቃትን በደንብ መግለጽ የማይችል አንደበተ ግድር (challenged) ከመሆኑም በላይ በራስ መተማመን የሚባል ነገር ምናምኒትም እንደሌለው በግልጽ ያስታውቅበታል፡፡  በዚያ ላይ ደግሞ ኃላፊነትን እንደ ጦር የሚፈራ የጃግሬነት (የተከታይነት) ሰብዕና የተጠናወተው ሰው ነው፡፡  አንድ ታዋቂ ግለሰብ ‹‹ አቶ ደመቀ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ሁን ቢሉት፣ ምን አመጣችሁብኝ ብሎ የቤተ መንግስቱን አጥር ዘሎ ይጠፋል›› ሲል የተናገረው ንግግር የአቶ ደመቀን ሰብዕና ቁልጭ አድርጎ ይገልጻል፡፡  ያቶ ደመቀን ዓይነት ለጀሌነት የተፈጠረ ሰው በሐሰተኛ ትርክት አደንዝዞ ፍጹም ተከታዩ ለማድረግ ደግሞ በሐሳዊ ተዋኝነት (con artist) ወደር ለሌለው ላጭበርባሪው ዐብይ አሕመድ በጣም ቀላል ነው፡፡  

የዐብይ አሕመድ ቋሚ መርሕ በሬ ሆይ ሞኙ ሆይ ነው፡፡  ዐብይ አሕመድ አያሌ አንቱወችን እንዲያምኑት እያደረገ በደንደሳቸው የጣለ ጮሌ ፈረስ ነው፡፡  በመሆኑም፣ እንኩቶውን ደመቀ መኮንን ባፍጢሙ ደፍቶ በኮቴው እየረጋገጠ ኦነጋዊነትን አምኖ ተቀብሎ፣ እሱን (ማለትም ዐብይ አሕመድን) ዋቆ እንደቀባው እንደ ሰባተኛው ሉባ ተመልክቶ ፍጹም ታዛዡ እንዲሆንለት ለማደረግ ምንም አያስቸግረውም፡፡ 

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በተኛበት ይጨፈጨፍ የነበረው የአማራ ሕዝብ፣ ተጨፍጭፎ ከማለቁ በፊት መነሳሳት መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡  ሆ ብሎ ከተነሳና ትክክለኛ መሪ ካገኘ ደግሞ ወያኔና ኦነግ እድሜያቸው ከሳምንታት ቢበልጥ ከወራት እንደማይዘል እነሱ ራሳቸው ያውቁታል፡፡  የአማራ ሕዝብ የሕልውናው ቀንደኛ ጠላት በሆነ ኦነጋዊ መመራቱን እስከቀጠለ ድረስ ግን ሕልውናውን ማጣቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ 

ስለዚህም፣ የአማራ ሕዝብ ለሕልውናው ሲል አስቀድሞ ማድረግ ያለበት ከዐብይ አሕመድ ወይም ከደመቀ መኮንን አንዱን ከጫንቃው ላይ ማውረድ ነው፡፡  የአማራ ሕዝብ ዐብይ አሕመድን ከጫንቃው ላይ ካወረደ፣ ደመቀ መኮንንና ብአዴኖች ድምጥማጣቸው ይጠፋል፣ ብአዴን ለጀሌነት እንጅ ለመሪነት አልተፈጠረምና፡፡  የአማራ ሕዝብ ደመቀ መኮንን ከጫንቃው ላይ ካወረደ ደግሞ ዐብይ አሕመድ ይንኮታኮታል፣ ዐብይ አሕመድን ሙሉ በመሉ ቀጥ አድርጎ የያዘው የደመቀ መኮንን ብአዴን ነውና፡፡ 

ዐብይ አሕመድ አማራን ቆረጣጥሞ እየበላ ያለ ኦነጋዊ አውሬ ቢሆንም ጥርሶቹ ግን ሙሉ በሙሉ ብአዴኖች ናቸው፡፡  ከጥርሶቹ ውስጥ ደግሞ ክራንቻወቹ (ማለትም አማራን የሚዘነጣጥልባቸው በግራና በቀኝ ያገጠጡት ሁለቱ የፊት ጥርሶቹ) ደመቀ መኮንን እና ተመስገን ጥሩነህ ናቸው፡፡ 

EMAIl:  መስፍን አረጋ mesfin.arega@gmail.com

Filed in: Amharic