>

የሰውነት ክፍሎችን አገልግሎት ከማያውቅ ባለሥልጣን ይሰውራችሁ!! (ዳግማዊ ጉዱ ካሣ)

የሰውነት ክፍሎችን አገልግሎት ከማያውቅ ባለሥልጣን ይሰውራችሁ!!

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ


የዚህን መጣጥፍ ርዕስ ላደርግ ያሰብኩት “አማራንና ኢትዮጵያን መሳደብና ማንጓጠጥ – የወቅቱ ፖለቲካ የይለፍ ቃል” የሚል ነበር፡፡ ግን ረዘም ስላለብኝ ቀየርኩት፡፡ ይህን ጽሑፍ ላዘጋጅ የተነሣሁት ልጓም የሌለው አንደበት ምን ያህል የሚቀረናና አካባቢን የሚበክል መጥፎ ጠረን (ሽታ) ሊያወጣ እንደሚችል በተግባራዊ ምሣሌዎች ለማሳየት ነው፡፡ የሀገራችን አለመታደል የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው – በተለይ ካለፉት 30 እና 40 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያንና አማራን መሳደብና ማዋረድ ወደፖለቲካው መድረክ ለመግባት የይለፍ ቃል (ፓስወርድ) መሆኑ ከማሳዘን አልፎ ነገርዬው የሰውን ልጅ የንቃተ ኅሊና መውረድ በገሃድ የሚጠቁም እጅጉን አሣፋሪ ነው፡፡ የኞቹ ተሳዳቢዎች ደግሞ በእንግሊዝኛው አገላለፅ “adding an insult to injury” እንደሚባለው በሲዖላዊ እቶን ከሚጠብሰን ድርጊታቸው ጎን ለጎን አእምሯችን እንዳያርፍ በስድብ ያጥረገርጉናል፡፡ እንደእውነቱ አፍን ይመገቡበታል፤ አፍን ነፍስና ሥጋን የሚያለመልም ንግግር ያወጡበታል፤ አፍን ይመክሩበት ይገስጹበታል እንጂ እንደወያኔዎችና ኦህዲዶች እንዲሁም የነርሱ ባርያ እንደሆነው ብአዴን አይጸዳዱበትም፡፡ ዋናው መልእክቴ ይህኛው ነው፡፡

በወታደራዊው የዕዝ ጠገግ ውስጥ የነበራችሁ ሰዎች የምታውቁትን አንድ ነገር እዚህ ላይ ላስታውስ፡፡ በወታደራዊ ካምፖች ውስጥና ዙሪያ በአሳቻ ጊዜ መንቀሳቀስ አይፈቀድም፡፡ ለሆነ ሥራ ጉዳይ የሚንቀሳቀስ ካለ ግን የዕለቱን የይለፍ ቃል ማወቅ አለበት፤ “ኮድ” ወይም የ“ይለፍ ቃል” ይባላል፡፡ ተንቀሳቃሹ ሰውዬ ኮዱ ይሰጠውና ሲጠየቅ ያን ቃል አስተካክሎ መጥራት ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ  ጠላት ነው ተብሎ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰድበታል፡፡ ተረኛው ወታደር ለቅኝት ሲዞር የሚያገኘውን ሰው “አንበሣ ነኝ፤ ማን ልበል?” ሲለው የዕለቱ ኮድ (የይለፍ ቃል) – ለምሣሌ – ቀጭኔ ከሆነ “ቀጭኔ ነኝ” ይልና ያልፋል፡፡ አሁን ባገራችን እንዳለው ሁኔታ አማራን በስድብ ካጥረገረግህ ሥልጣን ቤትህ ድረስ መጥቶ ሣሎንህ ውስጥ ቀድሞ እንደሚጠብቅህ ማለት ነው፡፡ ይሄ የሥነ ልቦና ደዌ ዓይነትና ብዛት እኮ ይገርማል፡፡ አገርና ማኅበረሰብ ካልተሳደቡ ሹመትና የደሞዝ ዕድገት የማይታሰብባት ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆን አለባት፡፡ 

የጎሣ ፖለቲካ በሀገራችን ከታወጀ ወዲህ የሚመጡት መሪዎች አንድ ናቸው፡፡ ጋላቢ ተለወጠ እንጂ ፈረሱ ያው ነው፡፡ ፈረሱ ስልህ ህገ መንግሥቱና ከርሱ በታች የሚገኙት ሌሎች ተያያዥ ሀገር በታኝ ደምቦች፣ መመርያዎችና ፖሊሲዎች ማለቴ ነው፡፡ አቢይ አህመድ መፈንቅለ መንግሥት ለመባል ምንም ያህል ባልቀረው ብልጣብልጥነት ሚሊዮኖች የተሰውለትን ለውጥ የእናቱን “ትንቢት” ለመፈጸም ጠምዝዞ ወደራሱ ካስገባ በኋላ ለ27 ዓመታት የነበርንበትን የዘረኝነት ክርፋት አጠናክሮ ቀጥሎበት የአንዱን ጎሣ በሌላኛው ጎሣ አመራሮች ለውጦ በአዲስ ጉልበት ፍዳችንን ማሳየት ከጀመረ እነሆ ከአንድ ወር ከ17 ቀናት በኋላ አራት ዓመት ሊሞላው ነው፡፡

“ማንነትህን እንድነግርህ ጓደኞችህን ንገረኝ” የሚባል ግሩም አባባል አለ፡፡ አንድ ሰው ቢጤውን ይመስላል፡፡ ሰካራም ከደህና ሰው ጋር፣ ሌባ ከጤናማ ጋር፣ ውሸታም ከሃቀኛ ጋር፣ ወዘተ. የመጎዳኘት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ “ግም ለግም አብረህ አዝግም” የምንለው ለዚህ ነው፡፡ ፈረንጆቹም `Birds of the same feather flock together.` ሲሉ “ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች በአንድነት ይበራሉ” ማለታቸው ነውና ከኛው አባባል ብዙም አልራቁም፡፡ ውሸታምና ውሸታም ይስማማሉ፤ ሌባና ሌባ ይተባበራሉ፤ አመንዝራና አመንዝራ መንገዳቸው አንድ ነውና አይገፋፉም፡፡ ብልጣብልጡና የዘር ፖለቲካ አራማጁ አቢይ አህመድም ሰዎችን ለሹመት ሲመርጥ ልክ እንደሱ ያሉ ዋሾዎችንና አጭቤዎችን፣ እርሱ የቆመለትን ኢትዮጵያንና አማራን እያዋዙ የማዋረድና በሂደት የማጥፋት ዓላማ ለማስፈጸም የሚተጉ አለብላቢቶችን ነው፡፡ ምሁራንንና ሀገር ወዳዶችን ለሥልጣን ሳይሆን ለከርቸሌ ያጫቸዋል፤ ለቁም ነገር ሳይሆን ለእሥራትና እንግልት ይዳርጋቸዋል፡፡ እርሱ የሚፈልገው ጭፍን ታዛዦችን ብቻ ነው፡፡ ጭፍን ታዛዥ ደግሞ አንጎል የሚባል ነገር የለውም፤ ሆዱ ከሞላ ያ ለርሱ ትልቁ የሕይወት ጥሪ ነው – የተፈጥሮ መክሊቱ፡፡ ለዚህ ነው ብአዴንና ጭፍራው ወይንም መንጋው ሆዱ እስከሞላ ድረስ ባሕር ዳርንና ጎንደርን ይቅርና ልጆቹንና ሚስቱን ሳይቀር ባወጡ ከመቸብቸብ የማይመለሰው፡፡ ሆድ መጥፎ ነው፡፡ እንኳንስ ከኋላችን አልሆነ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ከኋላችን ቢሆን ኖሮ ማን ያውቃል ብዙዎቻችንን እያዳፋ ገደል ይከተንና ይሄኔ ምድር ላይ ጥቂቶች ብቻ በቀሩ ነበር፡፡ 

በመሠረቱ መሳደብ የትንሽ አእምሮ ውጤት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ተሳዳቢ ሰው አእምሮው ማደግን ያቆመና አስተሳሰቡ የቀነጨረ ነው፡፡ እንደመለስና ልጁ አቢይ ዓይነት ተሳዳቢ፣ አቃቂረኛና አሽሙረኛ ሰው የመንግሥትን ሥልጣን ሲይዝ ምን ዓይነት ተከታዮችን እንደሚያፈራ ከአቢይ ፖለቲካዊ ጉዞ በሚገባ እየተረዳን እንገኛለን፡፡ ይህ ጠ/ሚኒስትር ከየት ከየት እየለቃቀመ እንደሚያመጣቸው አይታወቅም – በሕዝብ ተመራጭ ስም ሥልጣን ላይ የሚጎልታቸው ሰዎች አፋቸው ለስድብ የቀደመ ነው፤ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር የስድብ ውድድር ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ፉክክር ላይ የሚገኙም ይመስለኛል ሳስበው፡፡ አለቃቸው ኮሜዲያኑ አቢይም ከረር ያለ ስድብ የሚጠቀምን ላቅ ያለ ሥልጣን በማሻር ውድድሩን አክርሮታል፡፡ የሚሳደቡትም ያንኑ የፈረደበትን አማራና ባለቤት አልባዋን ኢትዮጵያ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ታዲያ ሕዝብ መረጣቸው የሚባሉት እነአንጋሣን መሰል የሰው ወዘና የሌላቸው ሰዎች እንደሚባለው ሕዝብ መርጧቸው ሳይሆን በሕይወት ስለመኖሩ አባላቱ ይቅሩና አቢይ ራሱ የማያውቀው ብልጽግና የተባለ በደመና ውስጥ በምናብ እየቀዘፈ የሚኖር ፓርቲ እየመረጠ ቦታ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ ምርጫን በሚመለከት እውነቱን ለመናገር እንኳንስ እነዚህን ተሳዳቢዎች ብልጽግና ተብዬውንም ማንም አልመረጠውም፤ አይመርጠውምም፡፡ “ብልጽግና በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ነው” መባልን ስሰማ ሀዘኔም ሆነ ንዴቴ ዋጋቢስ ነው እንጂ አዝናለሁ፤ እናደዳለሁም፡፡ ስለብልጽግና ፓርቲም አፍራለሁ፡፡ ሕዝብ ሰዳቢውንና አዋራጁን ሊመርጥ አይችልም፡፡ ተሳዳቢና ስድ አደግ ሰው በሕዝብ እንደማይመረጥ በደምብ ያውቃል፡፡ የሚሳደበው ታዲያ በምን አቋራጭ ወደሥልጣን እንደመጣ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ነው – ሕዝብ ሥልጣን እንዳልሰጠው ስለሚረዳ ማለቴ ነው፡፡ እናም መታወቅ ያለበት ሕዝብ ገዳዩን አይመርጥም፤ ሕዝብ አሳሪውን አይመርጥም፤ ሕዝብ አፈናቃዩንና  ለስደት የሚዳርገውን አይመርጥም፡፡ ሕዝብ የኑሮ ውድነት እንደራሴዎችን ሊመርጥ አይችልም፡፡ ሕዝብ እርስ በርስ የሚያባላውን የጅቦች መንጋ አይመርጥም፡፡ በማጭበርበር ራሱን መንግሥት እድርጎ ያስቀመጠው ብልጽግና የሚሉት ከሀፍረትም ከይሉኝታም የተፋታ አካል ነው፡፡ ይህንን እውነት ይበልጥ ለመረዳት የባልደራስ ፓርቲን የቅድመና ድኅረ  ምርጫ ጥናታዊ ዘገባ ማንበብ ይጠቅማል፡፡ የአቢይ መንግሥት ዐይኑን በጨው አጥቦ በሕዝብ ተመረጥኩ ይበል እንጂ በ“አንቺው ታመጪው፣ አንቺው ታሮጪው” ሥልት ራሱ ባዘጋጀውና ራሱ ባካሄደው ቁጭ በሉ የምርጫ ሂደት ሥልጣኑን የተቆጣጠረው ራሱ ለራሱ ባስቀመጣቸው የምርጫ አስፈጻሚ አካላት ነው፡፡ ያ ምርጫ እንኳንስ ምራቅ የዋጠን ሰው ሕጻናትንም ማታለል አይችልም፡፡ በዚያ ምርጫ ሰውን አታልላለሁ ብሎ አቢይ መነሳቱ የራሱን ጅልነት ያሳያል፡፡ ሰውን ለማታለል እኮ የተወሰነ ብልኃት ያስፈልጋል፡፡ ዝም ስለተባልክም ማታለል ቻልክ ማለት አይደለም፡፡ ሰው ሌላ ምርጫ አጥቶ ቢያጨበጭብልህ እውነት አይምሰልህ፡፡ ሰካራም ባሏ በወጣ በገባ ቁጥር በእርግጫና በጥፊ እያላጋት ለልጆቿ ስትል ወይም አማራጭ አጥታ የሆዷንም በሆዷ ቻል አድርጋ በስቃይ የምትኖረውን ሚስት ቤቱ ይቁጠረው፡፡ የኛም ሕይወት ከዚህች ዓይነቷ ምስኪን ሴት ኑሮ ቢብስ እንጂ አያንስም፡፡ ኢትዮጵያ ልክ እንደፀጉራም ውሻ ናት – አለች ሲሏት የሌለች፡፡ ፎቅና ሕንጻ ወዲያ ማዶና ወዲህ  ማዶ ስለተገተረ፣ የአስፋልት መንገድና የመናፈሻ ሥፍራ እዚያና እዚህ ስለታዬ ጤናማ ሀገራዊ ሕይወትን ሊያሳይ አይችልም፡፡ ልትፈነዳ የደረሰች ሀገር እየመራ የሚኮፈስ ወፈፌ መሪ ይዘህ ደግሞ የትም አትደርስም፡፡  

እናም ወደነዚያ የቀደሙ ሰዎቻችን እንመለስና እነዚህ በሃይማኖት ይበልጡን ፕሮቴስታንት፣ በጎሣ ይበልጡን ኦሮሞ፣ በዕድሜ ይበልጡን ወጣት፣ በዕውቀት ይበልጡን ደናቁርት ማይም፣ በፆታ ይበልጡን ቆነጃጅት ሴቶች፣ በተሞክሮ ይበልጡን ባዶ የሆኑ ባለሥልጣኖች ከቀድሞ የወያኔ ሰዎች ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ የኢትዮጵያን ሕዝብና የአዲስ አበባን ነዋሪ በስድብ መሞላጫቸውን ተያይዘውታል፡፡ ይህ ከጭንቅላት የጀመረ ብልሽት እስከታች ወርዶ ሁሉንም የብልጽግና ፓርቲ አባላት ያበከተና ሥርዓቱን እንዳለ ከጥቅም ውጪ ያደረገ የብልግና ጫፍ ነው፡፡ ይህ በሽታ በምንም ዓይነት መድኃኒት ታክሞ የሚድን ወይም በጠበል የሚለቅ አይደለም፡፡ እንደነቀርሣ ተቆርጦ መጣል ያለበት አገር ገዳይ አደገኛ ደዌ ነው፡፡ መወገዱ ባይቀርም ለጊዜው ግን እጅግ እየጎዳን ነው፡፡

እንጂ በመሠረቱማ “የአዲስ አበባ ኗሪ እናቱን እንጂ አባቱን የማያውቅ የሴተኛ አዳሪ ልጅ ነው” ብሎ በአደባባይ መናገር በራሱ አነሰ ቢባል ዕድሜ ይፍታህ የሚያስፈርድ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ይህን የተናገረው ሰውዬ አሁን የምክር ቤት አባል ነው፡፡ ወደ ወቅቱ የፖለቲካ ምኅዋር ለመግባት አብዛኛው ሕዝብ አማራ ወይም አማራ ቀመስ መሆኑ የሚነገርለትን የአዲስ አበባ ነዋሪ መሳደብ የሚያሾምና የሚያሸልም መሆኑን ያወቁ ሰዎች ይህን ወርቃማ ዕድል በሚገባ እየተጠቀሙበት ናቸው – የአቢይን የትንሽነት ሥነ ልቦና ቀመር በደምብ ነው የተገነዘቡት፡፡ አቢይ ደግሞ እኛ ስንሰደብለት ሃሤት ያደርጋል – የአጋንንት ጠባይ ይሄው ነውና፡፡ ስለሆነም የሰደበንና እያሰደበን ያለው አቢይ አህመድ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ አንድን ሕዝብ በስድብ መሞለጭ ደግሞ ሓሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር ሊያያዝ አይችልም፡፡ እንኳንስ የስድብ ቃል ተንፍሰው በአግባቡ ግዛን ብለው የተናገሩ እነእስክንድርንና ታምራት ነገራን የመሰሉ ድንቅ ዜጎች በሚታሰሩባት ኢትዮጵያ የአዲስ አበባን ሕዝብ ፈርሳም የሚሉ ሰዎች በሥልጣን ላይ ማየት ያሳፍራል፡፡ የመለስና የአቢይ ሌላው የሚያመሳስላቸው ዕንቆቅልሽ ደግሞ አማራ ሴት አቅፈው እያደሩና ከአማራ ሴት ልጆችን እየወለዱ ፀረ አማራ ሆነው መገኘታቸው ነው – የራሳቸው አማራነት በታሳቢነት ተይዞልኝ ነው ታዲያ፡፡

ለማንኛውም ለታሪክ ፍጆታ ያህል የሰውነት ክፍሎቻቸውን በአግባቡ መጠቀም ከማይችሉ የተወሰኑ ባለሥልጣናት የጥቂቶቹን ቀጥለን ለማየት እንሞክር፡፡ የሰውነት ክፍልን አገልግሎት በወጉ አለመረዳት ሲባል ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠብኝ ድረስ ለምሣሌ አፍን መልካም ነገር፣ የሚያንጽ ቁም ነገር ለመናገር ይጠቀሙበታል እንጂ በስሜት እየተነዱ የሞቅታ የአውሊያ ፈረስ የወለደውን ሁሉ ቢዘላብዱ ተናጋሪውን ያቀላል፤ ተሰዳቢ ወገንንም ያስቀይማል ለማለት ነው፡፡ ልጓም የሌለው አፍ ከእሥር እንደተፈታች ጥጃ ያደርጋል፡፡ ሀብትም ሆነ ሥልጣን፣ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃም ሆነ ታላቅ ተሰሚነት፣ ያሻንን ማድረግ የሚያስችለን ኃይልም ሆነ ጉልበት … ብቻ ምንም ነገር ይኑረን – ለአንደበታችን ግን ጥንቃቄ ይኑረን፡፡ ዱላ እኮ ይሻላል ወንድሞቼ! በስንት ጣሙ፡፡ የዱላ ሰምበር ይለቃል፤ የምላስ ወለምታ የሚያመጣው ዳፋ ግን ትውልዶችን ይሻገራል፡፡ ምላስ ለሰበረው ወጌሻ የለውም፡፡ 

 1. አቦይ ስብሃት ነጋ – “አማራንና ኦርቶዶክስን ገድለን ቀብረናቸዋል፡፡”
 2. መለስ ዜናዊ – “አማራ ቁጭ ብሎ ሲለምን ማየት ደስ ይለኛል፡፡” (የሥልጣን ዘመኑን ኢትዮጵያን በስሟ ሳይጠራ “ሀገሪቱ” በማለት ብቻ ይጠቀም እንደነበረ መዘንጋትም አይገባም፡፡ ካለፉት 31 ዓመታት ወዲህ የሚገጥሙን የሀገር መሪዎች ሀገርንና ሕዝብን የሚጠሉ ሥልጣንና ሀብትን ግን የሚያፈቅሩ መሆናቸው ምሥጢር እንደሆነ አለ፡፡)
 3. ኢሳይያስ አፈወርቂ – “አማራ አጠገብ ሆነ መለመን ራሱ ያሳፍራል፡፡” (ይታያችሁ የጥላቻ ጥግ! ከማን አጠገብ ሆኖ ቢለምን ይሆን የማያሳፍረው? አየህ፤ አንዳንዴ ንግግር አማረልኝ ብለህ ጠርዝ የለቀቀ አገላለጽ ውስጥ መግባት እንደማይኖርብህ ከዚህ ንግግር መማር አለብህ፡፡ ደግሞም ለጸጸት የሚዳርግ ነገር እንዳታደርግ  ከሰው ጋር ስትጣላ ዕርቅ መኖሩን አትዘንጋ፡፡)
 4. ሌንጮ ለታ – “ኦሮሞን የማትቀበል ኢትዮጵያ ከሽህ ቦታ  ትበጣጠስ፡፡” ( ኦሮሞ የሚመራት ኢትዮጵያ ኦሮሞን አልቀበልም ያለችው መቼ እንደሆነ ሌንጮ ብቻ ያውቃል፡፡)
 5. ጄኔራል  ሣሞራ የኑስ  –  “አርቀን የቀበርነውን አማራን ለቦርድ ሰብሳቢነት መምረጥ የለብንም፡፡” (በአንድ የግል ባንክ የቦርድ አባላት ምርጫ ላይ አማራ ሲጠቆም ከተናገረው፡፡)
 6. ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል (ከሌሎቹ ወያኔዎች ጋር የሚጋራው ሃሳብ) – “ከአማራ ይልቅ ሱዳንና ግብጽ ይቀርቡናል፡፡ ከአማራ የበለጠ እነሱ ወንድሞቻችን ናቸው፡፡”
 7. ጌታቸው ረዳ (ጌቾ ምላሱ) – “እሳትና ጭድ ያደረግናቸው አማራና ኦረሞ ‹ኦሮማራ› የሚል ኅብረት መፍጠራቸው የኛ ድክመት ነው፡፡ (በደምብ አላናቆርናቸውም ማለቱ ነው)
 8. ብዙ የትግሬና ኦሮሞ ባለሥልጣናት – “አማርኛን ለመማር ያጠፋሁት ጊዜ ይቆጨኛል፡፡”
 9. ብዙ የኦሮሞ ሴቶች – “ኦሮሞ ወንዶቻችን ሆይ! የአማራ ሚስቶቻችሁን ፍቱና እኛን አግቡን፤ እኛም ሴቶች ነን፡፡ ባል እንፈልጋለን፡፡ እነሱ የያዙትን እኛም ይዘነዋል፡፡”
 10. አለምነው መኮንን – (አማራ ነኝ የሚል የወያኔና ኦህዲድ የቤት አሽከር – “ኮንዶም” ልል ነበር ቃሉ ቀፈፈኝና ተውኩት፡፡”) – “ለሃጫም አማራ በባራባሶ እየሄደ ….” ብሎ ሰድቦናል ባለፈው፡፡
 11. ዘላለም ሙላቱ – “አዲስ አበባ ከርሷን ስትሞላ ፈርሷን ወደኦሮምያ ትልካለች” ብሎ ሰሞኑን በአፉ ተጸዳድቷል – የአዲስ አበባው የዕዳነች ዕባቤ ም/ቤት አባል፡፡
 12. አቢይ አህመድ – “ኦሮሞ ዝኆን ነው፡፡ ዝኆን ትልቅ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ በኢትዮጵያ ዝኆን የማይፈቅድለት ሰው ወደሥልጣን አይመጣም፡፡” (ቃል በቃል ባልለው ይቅርታ፡፡ አንዱን ነገድ ዝኆን ካለ ሌላውን ቁጫጭና ጥንቸል ማለቱ እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት ተጋሩን ሰብስቦ “እንኳን ከእናንተ ተወለድን” ብሎ ከተናገረው ጋር በቀጥታ ይመሳሰላል፡፡ እነዚህን ዓይነት መሪዎች ፈጣሪ ሳይቀር የሚጠየፋቸው አንዱን የሰው ዘር በጎሣና በነገድ ስለሚከፋፍሉ ነው፡፡)
 13. ሽመልስ አብዲሣ – “አባይን ተሻግረን ኮንቪንስ ወይም ኮንፊውዝ በማድረግ ቁማሩን በልተነዋል፡፡ አማራንና አማርኛን ከሥራ ውጪ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረግን ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ እስክንሆን ጥቂት ጊዜ ታገሱን፡፡ ድሉ የኛው ነው፡፡)
 14. ሕዝቅኤል ጋቢሣ – “እግዚአብሔር መጀመሪያ ኦሮሞን ከውኃ ፈጠረ፡፡ ከዚያ በኋላ ሌሎች ተፈጠሩ፡፡” 
 15. አንጋሣ – “የአዲስ አበባ ሕዝብ እናቱን እንጂ አባቱን የማያውቅ የሴተኛ አዳሪ ልጅ ነው፡፡”
 16. አብዛኛው ሕወሓትና የሕወሓት ጀሌ – “አማራ አህያ ነው”፡፡ (የአሜሪካ ዴሞክራት ፓርቲ ዓርማ ቀብራራዋ እመት አህይት መሆኗን ቢያውቁ ኖሮ ይህን ስድብ ይለውጡ ነበር፡፡)
 17. አሁን ትዝ ያሉኝን ጠቃቀስኩ እንጂ ብዙ ናቸው፡፡ እኔ የረሳሁትን አንባቢ ወይም አድማጭና አስደማጭ ይሙሉት፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልን ዘመናችን የሰጠንን እፉኝቶችና እንሽላሊቶች እንለይ፤ እርጥቡን ከደረቅ – ምርቱን ከገለባ አበጥረን በማውጣት የወደፊቱ ትውልድ እነዚህን ከመሰሉ ጉግማንጉጎች ራሱን መጠበቅ ይችል ዘንድ በታሪክ ማኅደር በጥንቃቄ እንሰንድ፡፡

ምስኪኗ ኢትዮጵያ የዕንቆቅልሽ ምድር፡፡ ጨዋ ያሳደገው ወደጓዳ ተወርውሮ ስድና ባለጌ፣ ከፊደል ዘር ጋር የተጣላ ማይምና ደንቆሮ ሥልጣን የሚይዝባት አሳዛኝ ሀገር፡፡ ጣርሽ በዛ – ትንሣኤሽን ያሳየን፡፡

 

Filed in: Amharic