>

በመርቆርዮስ ቀን መርቆርዮስ ሄዱ...!!! (መምህር ምህረት አብ አሰፋ)

በመርቆርዮስ ቀን መርቆርዮስ ሄዱ…!!!

መምህር ምህረት አብ አሰፋ

 

“…. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አራተኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ከዚህ ዓለም ድካም አረፉ።
በረከታቸው ይደርብን 
 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ፣ 4ኛ ፓትርያርክ ኾነው የተሾሙት፣ ነሐሴ 29 ቀን 1980 ዓ.ም. ሲኾን፣ በፖሊቲካዊ ግፊትና ጫና መንበራቸውን ለቀው ከሀገር ከመውጣታቸው በፊት እስከ ነሐሴ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. ድረስ ለቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ አመራር ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ከ26 ዓመታት ስደት በኋላ፣ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በስሙ በተሠየሙበት በሰማዕቱ ቅዱስ መርቆሬዎስ ክብረ በዓል ወደ ቅድስት ሀገራቸው ኢትዮጵያ መመለሳቸውን፣ ይታወቃል፡፡
ልደት:-
በፊት ስማቸው አባ ዘሊባኖስ ፈንታ የሚባሉት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በጎንደር ክፍለ ሀገር በደብረ ታቦር አውራጃ በአለታ ወረዳ አረጊት ኪዳነ ምሕረት በተባለችው ገዳም ሰበካ፣ ልዩ ስሙ ማር ምድር በ1930 ዓ.ም.፣ ከብላታ ፈንታ ተሰማና ከወ/ሮ ለምለም ገሰሰ ተወለዱ፡፡
መንፈሳዊ ትምህርት:-
ዕድሜያቸው ለትምህርት በደረሰ ጊዜ፣ በተወለዱበት ገዳም መሪጌታ ላቀው ከሚባሉ መምህር፣ ንባብና ዳዊት ተማሩ፡፡ ከዚያም በኋላ አጭታን ኪዳነ ምሕረት በምትባለው ደብር ምዕራፍና ጾመ ድጓ ተምረዋል፡፡
ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ጎጃም ክፍለ ሀገር ሔደው ጎንጅ ቴዎድሮስ በተባለው ገዳም ለኹለት ዓመት ከመሪጌታ ወርቁ፣ ወደ ዋሸራ በመዛወር በቅኔ ዝነኛ ከነበሩት ከመሪጌታ ማዕበል ፈንቴ ለኹለት ዓመት በጠቅላላ በአራት ዓመት የቅኔ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ተመልሰው፣ በደብረ ታቦር አውራጃ እስቴ ወረዳ አጋጥ ደብረ ጽዮን፥ የምዕራፍ፣ ጾመ ድጓና ድጓ ትምህርታቸውን ከመሪጌታ ሙጩ አጠናቀዋል፡፡
ወደ አቋቋም ቤት በመግባት፣ መነጒዘር በሚባለው ደብር፣ ከመሪጌታ ሚናስ ለኹለት ዓመት የአቋቋም ትምህርት ተምረዋል፡፡ ከዚያም ቁት አቡነ አረጋዊ ደብር፣ ከመሪጌታ ውብ አገኝ ለአንድ ዓመት ዝማሬ መዋሥዕት ተምረዋል፡፡ ወደ ደብረ ታቦር አውራጃ ተመልሰው፣ ከጥንቱ መምህራቸው ከመሪጌታ ሙጩ ላቀ ዘንድ የድጓ ትምህርታቸውን በመቀጠል ጽፈውና አመልክተው ከጨረሱ በኋላ፣ በነፋስ መውጫ አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው በስመ ጥሩዋ በቤተ ልሔም አራት ዓመት ቆይተው ድጓ አስመስክረው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡
የድጓ ትምህርታቸውን ካስመሰከሩ በኋላ ወደተወለዱበት ገዳም ሔደው፣ በአረጊት ኪዳነ ምሕረት ገዳም ለሰባት ዓመታት ያህል ድጓ አስተምረዋል፡፡
ሥርዐተ ምንኵስናና መንፈሳዊ አገልግሎት:-
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ መርቆሬዎስ፣ ሥርዐተ ምንኵስናን ከመምህርነት ጋራ አጣምሮ ለመያዝ ያላቸው ፍላጎት ከፍ ያለ ስለኾነ በጣና ገዳም ዳጋ እስጢፋኖስ በመግባት ማዕርገ ምንኵስናን ከመምህር ኃይለ ማርያም(በኋላ የባሕር ዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ መልአከ ገነት) በ1961 ዓ.ም. ከተቀበሉ በኋላ፣ በዚሁ ዓመት ማዕርገ ቅስናን፣ ከጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ተቀብለዋል፡፡
የገዳምን ሥነ ሥርዐት ይበልጥ ማጥናት ስለፈለጉ፣ በባሕር ዳር አውራጃ ልዩ ስሙ ጋሾላ በተባለ ገዳም ገብተው የገዳሙን ሥነ ሥርዐት እያጠኑና ለገዳማውያን እየታዘዙ ለኹለት ዓመት ገዳሙን ረድተዋል፡፡ በገዳሙ በነበሩበት ጊዜ፣ በጸሎተ ማኅበር፣ የልማት ሥራ በመሥራትና አቅመ ደካሞችን በመርዳት ገዳሙን አገልግለዋል፡፡
ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል፣ በቅዳሴና በማሕሌት እያገለገሉ ትርጓሜ ሐዲሳትንና አቡሻኽርን ተምረዋል፡፡ ዘመናዊ ትምህርታቸውንም በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት እስከ ኹለተኛ ደረጃ ተከታትለዋል፡፡ በተጨማሪም ለመምህራን፣ የተደረገውን የስብከት ዘዴ ኮርስ ለኹለት ዓመታት ተምረው የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነት:-
የደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ኾነው በመሾም በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የነበረውን ችግር ተገንዝበው ለአገልጋዮች መኖሪያ ቤት አሠርተውላቸዋል፡፡ የእሑድ(የሰንበት) ት/ቤት ወጣቶችም የመሰብሰቢያ አዳራሽ ስላልነበራቸው አንድ አዳራሽ ከነሙሉ ድርጅቱ አሠርተው በመስጠት ችግራቸውን አቃለውላቸዋል፡፡ ተጀምሮ የነበረው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን እንዲጠናቀቅና በአካባቢው የነበሩ ምእመናንም በሰበካ ጉባኤ እንዲደራጁ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ሢመተ ጵጰስና:-
ባላቸው በቂ የቤተ ክርስቲያን ዕውቀትና ባሳዩትም የመንፈሳዊ አገልግሎትና የሥራ ወዳድነት፣ ቤተ ክርስቲያናችን፣ ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም. ባደረገችው የ13 ኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ፣ በካህናትና በምእመናን በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠው የኦጋዴን አውራጃ ኤጲስ ቆጶስ ኾነው ተሾመዋል፡፡
በዚህ አውራጃ፣ በጠላት ፈርሶ የነበረውን ቤተ ክርስቲያን በማሠራትና በማሳደስ፤ በጦርነት ምክንያት የተሸበረውንና የተደናገጠውን ሕዝብ በማጽናናት ስለ ኢትዮጵያ አገሩ ፍቅር በማስተማርና በማስረዳት ሐዋርያዊ ተልእኳቸውን ፈጽመዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ በ1971 ዓ.ም. ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተዛውረዋል፡፡
ቅዱስነታቸው በጎንደር ሀገረ ስብከት የፈጸሙአቸው ሥራዎች፡-
በወቅቱ በነበረው አለመረጋጋት፣ በጭልጋና በደባርቅ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ሕዝቡን በማስተማር ሰላማዊ ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በየጊዜው በሚያሳዩት መልካም የሥራ ውጤት፣ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሊቀ ጵጵስና ማዕርግ ተቀብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷን እንድትችል ለማድረግ ቀዳሚ ተግባር የሚኾነው ምእመናንን በሰበካ ጉባኤ ማደራጀትና ማጠናከር ስለኾነ፣ በሀገረ ስብከት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሰበካ ጉባኤን በማቋቋምና በማጠናከር፣ የሰንበት ት/ቤቶችንም በማስፋፋት ቅርሳቅርሶች በክብካቤ እንዲያዙ፣ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች ለሕዝበ ክርስቲያን እንዲደርሱ፣ የቤተ ክርስቲያን መመሪያና ደንብ ቃለ ዐዋዲ በተግባር እንዲተረጎም አድርገዋል፡፡
በጎንደር ክፍለ ሀገር የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታደሱና በርከት ያሉ አዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ አድርገዋል፡፡ በተለይም በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ፡-
የአረጊት ኪዳነ ምሕረትን ቤተ ክርስቲያን በግል ገንዘባቸው ቆርቆሮ እንድትለብስ አድርገዋል፡፡
በዚሁ ወረዳ ውስጥ የምትገኘውን ደብረ ምሕረት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን፣ ከግል ገንዘባቸው ብር 9ሺሕ በማውጣት ቆርቆሮ እንድትለብስ አድርገዋል፡፡
መንፈሳዊ አዳሪ ት/ቤቶች እንዲከፈቱ፣ የካህናት ማሠልጠኛ እንዲቋቋምና ካህናት በተግባረ እድ የሚሠለጥኑበት ት/ቤት እንዲከፈት አድርገዋል፡፡
ምንም መተዳደሪያ ያልነበራቸው የአብነት መምህራንና ሊቃውንት፣ ለክህነት ከሚከፈለው ገንዘብ ደመወዝ እንዲቆረጥላቸው በማመቻቸት ሳይሰለቹና ሳይቸገሩ ሞያቸውን ለትውልድ እንዲያስተላልፉና የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞችም በትምህርት አቅማቸውን እንዲያሻሽሉበት አድርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ለአንድ የዜማ መምህር፣ ለአንድ የቅዳሴ መምህር፣ ለአንድ ዕቃ ቤት ጠባቂ በድምሩ ለሦስት ሰዎች ከራሳቸው ደመወዝ በመክፈል ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ በብፁዕነታቸው ሊቀ ጵጵስና፣ 43 አብያተ ክርስቲያናት ተተክለዋል፤185 አብያተ ክርስቲያናት ተሠርተዋል፡፡
የልማት ሥራዎች:-
ሀ/ በጋይንት አውራጃ በታች ጋይንት ወረዳ በምትገኘው በታላቋ ደብር ቤተ ልሔም ከአንድ በጎ አድራጊ ርዳታ በመጠየቅ በናፍጣ የሚሠራ አንድ የሞተር ወፍጮ አቋቁመው ለካህናቱና ድጓ ለሚያደርሱ ተማሪዎች ደመወዛቸውን እንዲችሉ ጥረዋል፡፡
ለ/ በደብረ ታቦር አውራጃ በእስቴ ወረዳ ሊጋባ ቅዱስ ሚካኤል በተባለው ቤተ ክርስቲያን አካባቢ አንድ የሞተር ወፍጮ በጎ አድራጊዎችን በመጠየቅ እንዲቋቋም አድርገዋል፡፡ አገልጋይ ካህናትም የወር ደመወዝተኛ እንዲኾኑ አድርገዋል፡፡
ሐ/ ጥንታውያን መጻሕፍት ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ ባደረጉት ጥረት፡- ጠቢበ ጠቢባን፣ ሙሉ ሲኖዶስ፣ የቅዳሴ አንድምታ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰናቸውን ውሳኔዎች በሙሉ በብራና እንዲጻፉ አድርገዋል፡፡ በጭልጋ፣ በሊቦ፣ በደብረ ታቦር፣ በጋይንት አውራጃዎችና በእስቴ ወረዳ የችግኝ ጣቢያዎች አቋቁመው በየዓመቱ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ችግኞች በየአብያተ ክርስቲያናቱ ሰበካና ለሕዝባውያን ድርጅቶች እንዲከፋፈሉ በማድረጋቸው የተራቆቱ መሬቶች በዛፎች እንዲዋቡ ጥረዋል፡፡
መ/ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በማስፈቀድ በማኅደረ ማርያም የሐዲሳት፣ የድጓና የቅዳሴ ት/ቤት አሠርተው ለመምህራኑ ከ50 እስከ 200 ብር ደመወዝ እንዲከፈላቸው፣ ለደቀ መዛሙርቱ ድጎማ እንዲሰጣቸው አድርገዋል፡፡
ሠ/ ጥንታዊውንና ታሪካዊውን የጣና ቂርቆስ ገዳም በብር 8ሺሕ835 እንዲታደስ አድርገዋል፡፡ በጣና ለሬማ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ብር 4ሺሕ ረድተዋል፡፡ የደረሞ ቅዱስ ሚካኤልን ቤተ ክርስቲያን ብር 21ሺሕ 114 በማውጣት አሳድሰዋል፡፡ እንዲሁም ጥንታዊውን የግርቢ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በብር 8ሺሕ860 ብር እንዲታደስ አድርገዋል፡፡ በአዘዞ በሰሚ ቅዱስ ሚካኤል ወደ ካህናቱ ማሠልጠኛ የሚወስደው መንገድ በምግብ ለሥራ መርሐ ግብር እንዲሠራ አድርገዋል፡፡
በጎንደር መንበረ መንግሥት ጥበበ እድና የአዳሪ ቤቱ ዙሪያ ርዳታ በመጠየቅ ከ9ሺሕ በላይ በማወጣት እንዲሠራ አድርገዋል፡፡ በጎንደር ጉባኤ ቤትና የዶክተር አየለ ዓለሙ የመቃብር ቤት የአራቱ ጉባኤያት ሥዕል እንዲሠራበት አድርገዋል፡፡ በሊቦ አውራጃ በቆላ እብናት ለአምራቾች የኅብረት ሥራ ማኅበር ብር 15 ሺሕ ረድተዋል፡፡ በጎንደር ከተማ በአዘዞ አባ ሳሙኤል በመጠለያ ለሚረዱ ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ መምሪያ ጋራ በመተባበር የኤልክትሪክ ምጣድ ርዳታ አድርገዋል፡፡ በዳባት ወረዳ የሚገኘውን የደፍቂ ቅዱስ ሚካኤልን በብር 5ሺሕ፣ ቆማ ፋሲለደስን በብር 5ሺሕ አሳድሰዋል፡፡ ለአምስትያ ገዳም ብር 4ሺሕ፣ ለጣርክ ማርያም ብር 7ሺሕ ረድተዋል፡፡
ዐደባባይ ኢየሱስም በብር 40ሺሕ እንዲታደስ አድርገዋል፤ የድምፅ ማጉያም አስገብተውለታል፡፡ በጎንደር ዙሪያ አውራጃ ለቸንከር ተክለ ሃይማኖት ርዳታ በመጠየቅ ብር 764ሺሕ አበርክተዋል፡፡ በዚያው በጎንደር ዙሪያ ከማክሰኝት እስከ አርባያ ለመንገድ ሥራ ብር 30ሺሕ ርዳታ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡ ከእብናት እስከ ጎሐላ ለመንገድ ሥራ የብር 6ሺሕ ርዳታ እንዲገኝ አድርገዋል፡፡
በስሜን አውራጃ ለሚገኙ ጥንታውያን ገዳማት፤ ለቤተ ሚናስ ዋልድባ ከብር 10ሺሕ በላይ፤ ለጣዕመ ክርስቶስ ብር 10ሺሕ፣ ለሰቋር ዋልድባ ብር 4ሺሕ ግምት ያላቸው የቁሳቁስ(የዓይነት) ርዳታ አድርገዋል፡፡
በጎርጎራ ገዳም በደሴተ ጣና ለሚገኙ ገዳማት፤ ለማን እንዳባ ገዳም ብር 1ሺሕ880፤ ለብርጊዳ ማርያም ገዳም ብር 1ሺሕ ለበሬ መግዣ እንዲሰጥ አድርገዋል፡፡
ከልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ መምሪያ ርዳታ ሰጪ ድርጀቶች በመጠየቅ አቅም በፈቀደ መጠን በተወሰኑ አብያተ ክርስቲያናት የቆዳ፣ የሽመና፣ የሹራብ ሥራ፣ የልብስ ስፌት፣ የወፍጮ ቤትና የዳቦ ቤት እንዲቋቋምና አገልግሎት እንዲሰጡ አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም ለስብከተ ወንጌል፣ ለሰንበት ት/ቤትና ለሕዝብም መሰብሰቢያ የሚያገለግሉ አዳራሾች በየአብያተ ክርስቲያናቱ አካባቢ አሠርተዋል፡፡ ሕዝቡ ንጹሕ ውኃ ማግኘት እንዲችል የውኃ ጉድጓድ በማስቆፈር ለዚሁ የሚያገለግል ሞተርና ቧምቧ እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረዋል፡፡
ለሀገረ ስብከቱ ያስገኟቸው ሽልማቶች:-
የሰበካ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ደንብ በትክክል እንዲፈጸም በማድረጋቸውና ሰበካ ጉባኤን በሚገባ በማደራጀታቸው፣በየዓመቱ በሚደረገው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ ጉባኤ ዓመታዊ ስብሰባ የሥራ ግምገማ በተደረሰበት ውጤት የጎንደር ሀገረ ስብከት ቅድሚያ ቦታ እንዲይዝ አድርገዋል፡፡
በዚህም መሠረት፡- ከ16ቱ አህጉረ ስብከት፣ ከ1975 እስከ 1977 ዓ.ም. በተከታታይ እንዲሁም በ1979 ዓ.ም. አንደኛ፤ በ1978 ዓ.ም. ኹለተኛ በመኾን በውጤታማነት እንዲሸለም አድርገዋል፡፡ ብፁዕነታቸው፣ ከዚህ በላይ ጠቅለል ባለ መልክ በተዘረዘረው ዓይነት ተልእኳቸውን በትክክል የተወጡ አባት ከመኾናቸውም በላይ በ1979 ዓ.ም. በተደረገው የብሔራዊ ሸንጎ አባላት ምርጫ በጎንደር ዙሪያ አውራጃ ምርጫ ጣቢያ ደንቢያ ከመረጠው 26ሺሕ127 ሕዝብ መካከል 17ሺሕ249 ድምፅ በማግኘት ተመርጠው ሕዝብን አገልግለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ መርቆሬዎስ፣ የበላዮቻቸውን መካሪ፣ የበታቾቻቸውን አክባሪ፣ በሥራ ታታሪ፣ መንፈሳዊ አባትነታቸውና ትሑት ሰብእናቸው አርኣያነት ያለው ቁጥብ አባት ናቸው፡፡
Filed in: Amharic